Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትለዓባይ ውኃ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለምናደርገው ተጋድሎ አንድ ሁለት ነገሮች

ለዓባይ ውኃ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለምናደርገው ተጋድሎ አንድ ሁለት ነገሮች

ቀን:

በታደሰ ሻንቆ

በጥቅሉ ስለድንበር ተሻጋሪ ወንዞቻችን (በተለይም ስለዓባይ) የጋራ ፍትሐዊ ጥቅሞቻችን፣ በውስጥና በደጅ ያሉ ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ ተወላጆች ጋር ተያይዘው የሚሠሩበት የጥናት/የመረጃ ማደራጃና ማፍለቂያ ማዕከል ተቋቁሞ፣ በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች (ቢያንስ አረብኛንና እንግሊዝኛን በደንብ በሚያፈሱ አንደበቶችና ብዕሮች) እቅጮችን፣ ቅጥፈቶችንና እውነቶችን በረቺ መከራከሪያ እየፈለቀቁ ለመላው ዓለም (ለአፍሪካ፣ ለግብፅና ለመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ፣ ለአውሮፓና ለአሜሪካ፣ እንዲሁም ለዋናዎቹ ዓለም ገብ መድረኮች) ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሳወቅ የማንዘናጋበት ግዴታችን መሆኑ ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡ በዚህ ረገድ ከብዙ አቅጣጫ ምክረ ሐሳቦች፣ መረጃዎችና የመከራከሪያ ቢጋሮች፣ ወዘተ. መፍሰሳቸው እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በማመን የታዩኝን ጥቂት ነጥቦች ልወራውር፡፡

  1. ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር የምትጋራቸውን ውኃዎች በሰላምና በፍትሐዊነት ለመጠቀም የምታደርገው ትግል ለመግባቢያነት በቅቶ በተግባር እንዲዘልቅ፣ እንቅስቃሴዋና ገጽታዋ በየትኛውም ደረጃ ላይ ቀዳዳ የሌለውና በቀላሉ የማይበገር የጥቃት መከላከያ (ኢንሱሌሽን) ማበጀቱ መሠረታዊ ነው፡፡ ለመጠቃቀስ ያህል በአዋሳኝ ጎረቤቶቿ ዘንድ ከአንዳቸውም ጋር ቢሆን በወዳጅነት ረገድ አለመራቆቷ፣ የመከላከያና የመረጃ ኃይሏን ከማዘመንና ሸርን አነፍንፎ ከማምከን ባሻገር ሸርን በሸር አለመመለሷ፣ የራሷን ልማት ስታይ የሌላውን ጥቅም ላለመጉዳት መጠንቀቋ፣ ከዓባይ ውኃና ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ለፍትሐዊ የጋራ ጥቅም ያላትን ራስ ወዳድ ያልሆነ አቋም፣ ከሌሎች ጎረቤቶቿም ጋር የምትተቃቀፍበት መርህ መሆኑን ማሳወቋና በዚሁ መሠረት የማይዋዥቅ ትስስር መፍጠሯ፣ ከሁሉም በላይ የአገር ውስጥ ጠንካራ ሰላም ማበጀቷና ግስጋሴዋ መቀጠሉ አንድ ላይ ውጤታቸው ከፍተኛ ነው፡፡
  2. የልዕለ ኃያላንና የኃያላን አድሏዊ ጣልቃ ገብነት በዓለማችን ውስጥ በተለያዩ ቀጣናዎች ሰላምንና ፍትሐዊ ጥቅምን ሲጎዳ፣ ጠንቅ ሲተክልና ሲያባላ ኖሯል፣ በተለይ ከቅኝ ግዛት መስፋፋት አንስቶ፡፡ በዓባይ ተፋሰስ አካባቢም እንዲሁ ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያና የሌሎች የናይል/የዓባይ ተፋሰስ አገሮች የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ትግል መምጣትና ዛሬ የደረሰበት ደረጃ መድረስ፣ የተተከለ ጠንቅንና አድሏዊነትን የማስተካከል ነው፡፡ እናም አሮጌ አድሎኛ “ባለድርሻነትን” ታሪካዊ መብት አድርጎ በኃይል፣ በልዕለ ኃያላዊ ጫናና በቀጣፊ መከራከሪያ ለማስቀጠል መሞከር ከንቱ ድካም ነው፡፡ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ያነሱት የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ በምንም መንገድ ወደ ኋላ  ሊመለስና ሊታነቅ የማይችል፣ መቀበልን ግድ የሚል ነው ዛሬ፡፡ ምክንያቱም በፍትሐዊነት ተሳስቦና ተባብሮ በሰላም ለማደግ መታገል፣ የምሥራቅ አፍሪካና የመላ አፍሪካ የዘመኑ ጥያቄ ስለሆነ፡፡ ይህ ሁላችንን አቀፍ ጥያቄ ፈክቶ መውጣቱ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
  3. የኢትዮጵያን ከድህነት የመውጣት (የመልማት) ጥረት ለማፈን መሞከር፣ የኢትዮጵያን የውስጥ ሰላም መበጥበጥና ጦርነት መክፈት፣ (ኢትዮጵያ የዓባይን ውኃ የመቀነስ አንዳችም ተንኮል ውስጥ ሳትገባ)፣ የግርጌ አገሮችን በዓባይ ውኃ የመጠቀም ዕድል ላይ ክፉኛ ጉዳት ያደርሳል፡፡ በየትኞቹም የደባና የኃይል ሥልቶች የኢትዮጵያን ድህነት የማስቀጠል ተግባር፣ በራሱ በረሃማነትንና የዓባይ ውኃ መበከልን በማስፋፋት የውኃውን መመናመን ማስከተሉ ያፈጠጠ ሀቅ ነው፡፡ በረሃማነትን ያለአረንጓዴ ልማት መታገል እንደማይቻል እኛ ለጎረቤቶቻችንም ሆነ ለዓለም አስታዋሽ መሆን አይጠበቅብንም፡፡ የዓባይን ወንዝ መበከል በተመለከተ የዓባይ ተፋሰስ አገሮችም ሆኑ ዓለም ሊያውቀው የሚገባ እውነት አለ፡፡ ዛሬ የዓባይ ውኃ ከጣና ሐይቅ አንስቶ እንቦጭ በሚባል አደገኛ አርም እየተወረረና በመድረቅ አደጋ ውስጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን አረም ለማጥፋትና ጣናንና ዓባይን ከመድረቅ ለማትረፍ ብቻዋን እየተፍጨረጨረች ነው፡፡ ይህ ትግል ኢትዮጵያ ለራሷ ህልውናና ልማት የምታካሂደው ቢሆንም፣ በተዘዋዋሪ አይደለም በቀጥታ የዓባይ ውኃ ለሱዳንና ለግብፅ ያለው አለኝታነት እንዳይቀንስ የመዋደቅም ትግል ነው፡፡

በአጭሩ ኢትዮጵያ የሱዳንንና የግብፅን የጥቅም ቀንበር ብቻዋን ተሸክማለች፡፡ እናም የኢትዮጵያና የተፋሰሱ አገሮች አረንጓዴ ልማት፣ ለሱዳንና ለግብፅ የዓባይ ጥቅም ዋስትና እንጂ ጉዳት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን ሰላምና የልማት ተፍጨርጫሪነት በማገዝ ፈንታ ለማሰናከል መሥራት፣ የዓባይን ውኃ ከምንጩ ለማድረቅ ከሚተጋው ከእንቦጭ አረም ጎን መቆም ነው፡፡ በቀላል ቋንቋ ዓባይ እንዲደርቅ የሱዳንና የግብፅ ግድቦች ላንቃቸው ተራቁቶ ሲነሰጣጠቅ ለማየት ከመሥራት አይለይም፡፡ ይህንን ዓብይ ሀቅ የሱዳንና የግብፅ ሕዝቦችና ዓለም ሊያውቁት ይገባል፡፡

  1. የህዳሴ ግድብ ባመጣው የፊት ለፊት ጥቅም ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ ላይ አንዳችም ቅናሽ ሳታስከትል፣ ውኃው የኤሌክትሪክ ማመንጫ ውልብልቢቶችን እየመታ እንዲያልፍ በማድረግ የኤሌክትሪክ ኃይል ታገኛለች፡፡ አዲሱ ነገር ውኃው በግድብ ውስጥ በረዥም የጊዜ ሒደት ተጠራቅሞ ኤሌክትሪክ እያመነጨ ማለፉ ነው፡፡ ተደጋግሞ እንደተነገረውም፣ ውኃው በመገደቡ የግብፅንም ሆነ የሱዳንን ፍትሐዊ የውኃ ድርሻ ይጎዳል የሚል ክርክር ፈጽሞ ሐሰት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ፊት ያልነበረ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ጥቅም እንዳገኘች ሁሉ፣ እነ ግብፅም በግድቡ ምክንያት በፊት ያልነበረ (አዲስ) ጥቅም ያገኛሉ፡፡ ሲባል እንደነበረው ከጎርፍ ጥቃት ይጠበቃሉ፡፡ ግድቦቻቸው በደለል ከመሞላትና ከብክለት ይጠበቃሉ (በህዳሴ ግድብ ሲጠራቀም ያየነው ውኃ አፈርማ እንደ መሆኑ፣ ኢትዮጵያ የአፈር መታጠብና የጎርፍ ጭቃ ጣጣን መቆጣጣር ካልቻለች የግርጌ አገሮች ግድቦች በጭቃ እንዳይሞሉ ከማገልገል እጅግም ያለፈ ጥቅም አይኖራትም)፡፡ በሌላ በኩል የህዳሴ ግድብ ከሞላ ጎደል ፈረሰኛ ውኃና ድርቅ የሚፈጥሩትን ዝባት ስለሚያቻችል ሱዳንና ግብፅ ከዓመት ዓመት የተቀራረበ የውኃ መጠን የማግኘት ዕድላቸውን ያሰፋል፡፡ ይህንን ስናስተውል ነው በኢትዮጵያ ድርቅ በተከሰተ ጊዜ ስለውኃ አለቃቀቅ “ዋስትና ያለው” ስምምነት ለመፍጠር የሚደረግ ዓይን ያወጣ ጮካነት የሚጋለጠው፡፡

የህዳሴ ግድብ ተቀዳሚ ተልዕኮ የሆነው የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጪነት ከሞላ ጎደል ሙሉ ዓመት (በድርቅ ጊዜም) የሚካሄድ መሆኑ ዕውቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የዝናብ እጥረት በደረሰ ጊዜ ግድብ ከመኖሩ በፊት፣ ዓባይ ከኢትዮጵያ ድንበር ይዞት ከሚያልፈው የበለጠ ውኃ ግድቡ የሚያስገኝ መሆኑም አያከራክርም፡፡ ስለዚህ አንድ ከግድቡ በታች ያለ የዓባይ ውኃ ተጠቃሚ፣ ኢትዮጵያ በድርቅ በተመቻች ጊዜ ዓባይ የሚኖረው የውኃ መጠን ሳይነካ ይምጣልኝ እንጂ፣ ከዚያ ያለፈ ውኃ አይምጣልኝ ቢል ጥቅሜ አልገባኝም የማለት አላዋቂነት ይሆንበታል፡፡ በተቃራኒው ድርቅን ምርኩዝ አድርጎ ኢትዮጵያ ፍትሐዊ የውኃ ድርሻዋን ሳትጠቀም ለእኔ ልትለቅ ቃል ትሰርልኝ ከሆነ ደግሞ፣ አንቺ በድርቅ ተንጨፍረሪ እኔ ግን ልጠቀም ባይነት ነው፡፡

ኢትዮጵያ በድርቅ በተመታች ወቅት፣ ድርቅ ዓባይ ውኃ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ሁሉም የዓባይ ተጋሪ አገሮች የሚጋሩት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የህዳሴ ግድብ መኖር በዓባይ ውኃ ተጋሪዎች ላይ ድርቅ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ የሚያለዝብ ትሩፋት እንዳለው አጉልቶ ማውጣት አስፈላጊ ነው፡፡ እኔ እስከምረዳው ድረስ፣ ኢትዮጵያ በሚኖራት ፍትሐዊ የውኃ ድርሻ መሠረት ኤሌክትሪክ አመንጭቶ ውኃ ከማሳለፍ የዘለለ ግብርና ነክ ልማት ብታካሄድ እንኳ፣ በግብርና ልማት መጠቀምን እንደምትሻ ሁሉ፣ የኑሮና የልማቷ ሞተር የሆነው የኃይል ምንጭ የጎላ ቀውስ በማይደርስበት አኳኋን ውኃ የሚቀንስ ልማቷን የውኃ ስንቅ ከሚሻው የኤሌክትሪክ አመንጭነት ጋር ማቻቻል አይቀርላትም፡፡ እናም የህዳሴ ግድብ ለግርጌ ትሩፋት የማስገኘት ባህርይው ኢትዮጵያ ፍትሐዊ የውኃ ድርሻዋን በምትጠቀምበት ጊዜም ቢሆን፣ ከፋም ለማም ይቀጥላል እንጂ አይመክንም፡፡ ይህም በአግባቡ ሊጤን ይገባል፡፡

  1. የህዳሴ ግድብን በጋራ ሱዳን፣ ግብፅና ኢትዮጵያ በሦስትዮሽ እናስተዳድር የሚል ሐሳብን ኢትዮጵያ የምትቃወመው ድብቅ ዓላማ ስላላት ሳይሆን፣ ሉዓላዊ የውስጥ መብቷን እንደ ማንኛውም ሉዓላዊ አገር ከማስከበር አኳያ መሆኑን አጠንክሮ ለአፍሪካም ለዓለም ከማሳወቅ ባሻገር፣ ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ውኃዎችን ተጋሪ የሆኑ አገሮች ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍል ስምምነት ፈጥረው በስምምነቱ መሠረት ፍትሐዊ ድርሻቸውን አክብረው መኖራቸውን፣ በጋራ ያስተዳድሩ የሚል ፖሊሲና ድንጋጌ የአፍሪካ ኅብረት ካበጀና ሥራ ላይ ካዋለ፣ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር የጋራ ጥቅምን ለማስተዳደር የቅን ፍላጎት ችግር እንደማይኖርባት መግለጥም የሚጠቅም ነጥብ ይመስለኛል፡፡
  2. ከዚህ ቀደም ፍትሐዊ የዓባይ ውኃ ክፍፍል ሲነሳ ግብፆች ይህንን ለማምለጥና የኛን የመብት ጥያቄ ሰይጣናዊና ግፈኛ አድርጎ ለማቅረብ የሚጠቀሙበት መከራከሪያ፣ ኢትዮጵያ ብዙ ውኃዎች እያሏት ዓባይን ልትገደብ የተነሳችው ለአንድ ናይል ሌላ አማራጭ የሌላትን ግብፅ ለማስጠማትና ለማስራብ ነው በሚል አቅጣጫ ማጭበርበር ነበር፡፡ ዛሬም ይኸው ዘዴ ቀጥሏል፡፡ ፍትሐዊ የውኃ ድርሻን የማስከበር ትግል የግብፅን ህልውና ከማሳጣት ጥቃት ጋር ተዛምዶ እንዲታይ የማድረግ ብልጣብጥነትን ለማክሸፍ፣ ግብፆች በዓባይ ውኃ አጠቃቀማቸው የሚታየውን አድፋፊነት፣ ከመጠቀም አልፈው ግዙፍ የከርስ ምድር ውኃ ማጠራቀማቸውን፣ ለሌላም የሚሸጡ መሆናቸውን፣ ወዘተ በደንብ በተጠናቀረ መረጃ መግለጽ (አሁን እንደተያዘው) አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ግን የኢትዮጵያን የህዳሴ ግድብ ያመጣው ግብፅን የመሻማት ስስትና የማጥቃት ፍላጎት ሳይሆን፣ በአጠቃላይ ከድርቅ ጋር በሚያያዝ የመጠቃት ረዥም ታሪካችንን ከሰሜን እስከ ምሥራቅ ደቡብ ድረስ ለመቀየር የተነሳሳ ትግል መሆኑን፣ ከኩራዝና ወደ ሰማይ አንጋጦ ውኃ ከመጠበቅ ጋር የተቆራኘ ሰፊ የድህነት ገጽታችንን ከረዥም የድርቅና የረሃብ ታሪካችን ጋር ሰድሮ ማሳየት ያዋጣል፡፡
  3. እነዚህ የመሳሰሉ ነጥቦች ከምሁራኑና ከሊቃውንቱ ተዋጥተው የአዋጭነታቸው ጥንካሬ ተገምግሞና በመረጃና በትንታኔ ጉልበት አግኝተው በኢትዮጵያ  የዓባይ ፍትሐዊ የውኃ ተጠቃሚነት ጥያቄ ላይ የሚነዙ አሉታዊ ሥዕሎችን ለማስተካከል መሥራት አንድ ነገር ነው፡፡ በጉዳዩ የበሰሉ፣ ሐሳብን በማስረዳትና በቋንቋ አቅማቸው የተቡ መልዕክተኞችን ልኮ ለአፍሪካ ለዓረቡና ለምዕራቡ ዓለም ማስረዳት ደግሞ ሌላ ነገር ነው፡፡ አፄ ምኒሊክ በዓድዋ ጦርነት ዋዜማ የአውሮፓ አቋም ኢትዮጵያንም የሚያይ አንጀት እንዲኖረው አውሮፓዊውን አልፍሬድ ኢልግ የተባለ መልዕክተኛ ልከው ሠርቶ ነበር፡፡ ከዚህ መማር ይገባናል፡፡

 ኢትዮጵያ ታሪካዊ ጉዳቷንና ፍላጎቷ በፍትሐዊ የጋራ ተጠቃሚነት የተለካ መሆኑን ለዓለም ማስረዳት ከቻለች፣ ተሳስቦ ከመኖርና ከማደግ ፍላጎታችን ጎን የሚቆሙ ለዚህም የሚናገሩ የቅርብና የሩቅ መልዕክተኞች/ ወዳጆች ከዓረቡም ከምዕራቡም ዓለም ማፍራታችን ጥርጥር የለውም፡፡ ኢትዮጵያ ለዚህ ፍሬያማ ውጤት አልማ መሥራት አለባት፡፡ ስኬቷንም ብዙ “ባዕድ” ደጋፊ በማግኘት ፍሬ መመዘን ይገባታል፡፡ ይህ ፍሬ ግን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን በውስጥና በውጭ ላለነው ዜጎች በሚያጠጡን ዝተት የፕሮፓጋንዳ ዘይቤ የመገኘቱ ነገር ሱሚ ነው፡፡

  1. ይህም ሁሉ ተደርጎ በህዳሴ ግድብ ላይ የተያዘው ድርድር ቢጠናቀቅም፣ ከዓባይ ውኃ ጋር የተያያዙ ጣጣዎች ይዘጋሉ ማለት አደለም፡፡ ዓባይን በተመለከተ የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን ግንኙነቶች ጠንቃቃ እንክብካቤ መፈለጋቸው የሚቀጥል ነው፡፡ ይህ ራሱን የቻለ ሥራ ነው፡፡ ይህን ሥራ ለመወጣት የማይዋዥቅ የውስጥ ሰላም በኢትዮጵያ መገንባቱ ወሳኝ ነው፡፡ የውስጥ ሰላምን ይዞ ከተዋሳኝ ጎረቤቶቻችን ጋር ሁሉም የሚሳሳለት የጋራ ልማት ውስጥ መግባት ደግሞ ዋና መተማመኛችን ነው፡፡

በመጨረሻም ሁሌም የሚከነክነኝንና ሲያጋጥመኝ የማነሳውን አንድ ነጥብ ላንሳ፡፡ ኢትዮጵያ ከውጭ ወረራ ጋር ባደረገችው ነፃነትን ያለ ማስደፈር ተጋድሎ የብዙ ተቆርቋሪ ወገኖች ባለውለታ ነች፡፡ በዚህ ውስጥ አፍሪካውያን፣ ከአፍሪካ ውጪ ያሉ የካሪቢያንና የአሜሪካ ጥቁሮች እንዲሁም ፈረንጆች ነበሩበት፡፡ ዛሬም እንዲህ ያለ ተቆርቋሪነት እየታየ ነው፡፡ የአዛውንቱ ቄስ ጄሲ ጃክሰን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ለአሜሪካ በአምባሳደርነት የሠሩ ወዳጆችና የአሜሪካ ኮንግረስ ውስን አባላት ያሳዩት፣ የአሜሪካን ለሰላም የማይበጅ አድሏዊነት የተቃወመና ለኢትዮጵያ የፍትሕ ድምፅ ጀርባ ያልሰጠ ድጋፍም ሌላ ውለታ ነው፡፡

በዓረቡም ዓለም የኢትዮጵያ ትውልድ ካላቸው ተቆርቋሪዎች ውጪ ለእውነት የቆሙ ባይተዋሮች አይታጡም፡፡ ኢትዮጵያ ትናንትም ዛሬም ከሃቋ ጎን የቆሙላትን ባለውለታዎች በአግባቡ ማመሥገን ይጠበቅባታል፡፡ ይህ ምሥጋና በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ የምሥጋና መድረክ ከማዘጋጀት ማለፍ አለበት፡፡ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የታሪክ ዘመዶቻችንና የውጭ ጎብኚዎችን የሚያዩት የታሪክ ባለውለታነታችንን ከእነ ምሥጋናችን በአገራዊና በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ያሰፈረ ቋሚ መታሰቢያ፣ ይህ ቢዘገይ መታወሻ ዕለተ ቀን መሰየም  ተገቢ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...