Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የድል ብስራት!

አንገት ቀና ከሚያደርጉ ዜናዎች መካከል የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመርያው ምዕራፍ የውኃ ሙሌት ሥራ መጠናቀቅን የመሰለ የብሥራት ዜና አልተደመጠም፡፡ ዜናው ኢትዮጵያውያንን አስፈንድቋል፡፡ በርካቶች በደስታ ሲቃ አንብተዋል፡፡ ደስታቸውን ሲገልጹ የተደመጡ በርካቶች ናቸው፡፡ የግድቡን የድል ብስራት የሚስተካከል ዜና አልተደመጠም፡፡

ከዘመናት በኋላ በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብታችንን ዕውን ለማድረግ የመጀመርያው ምዕራፍ ሲጀመር ለዓለም ያሳየንበት፣ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን የሥራ ውጤት በመሆኑ ልብ የሚያሞቅ ታሪካዊ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

የግድቡ የመጀመርያ ዙር የውኃ ሙሌት ሥራ መጠናቀቅ፣ የግንባታው 74 በመቶ መድረስ የብዙ እልህ አስጨራሽ ጥረቶች ውጤት ነው፡፡ ፕሮጀክት ጀምሮና ገንብቶ ለማጠናቀቅ የሚታየው ውጣውረድና ፈተና በኢትዮጵያችን ልማዳዊ ችግር ቢሆንም፣ የህዳሴው ግድብ ግን ከዚህም ያለፈ ውስብስብና ጂኦፖለቲካዊ ጫናዎችን አልፎ ቢዘገይም ብሩኅ ተስፋ የረጨበትን ምዕራፍ አሳክቶ ማለፍ መቻሉ ትልቅ ድል ነው፡፡ የተበላሹ፣ የጓጎጡና የጎበጡ ሥራዎችን አቃንቶ፣ ወደ ግብ ማድረስ መቻል ያውም ዓለም አቀፍ ጫናን ተቋቁሙ በራስ አቅምና ገንዘብ ለውጤት መብቃት መቻልን የመሰለ ትልቅ ድል ነው፡፡ ድሉ የጀመሩትን ሥራ በማሳካትና ዳር በማድረስ ብቻ አይገለጽም፡፡ ይልቁንም ሥነ ልቦናንና ተፅዕኖ ፈጣሪነትንም ለኢትዮጵያውያን ማላበስ የቻለ፣ ቀና ማለት ብቻም ሳይሆን፣ መብትን ለመጠየቅና በመብት ለመጠቀም የማንንም ፈቃድ መጠየቅና የማንንም ይሁንታ የማይሻ፣ ግንባሩን የማያጥፍ ሕዝብ መፈጠሩን ያሳየ ትንግርትም ጭምር በመሆኑ ልዩና ታሪካዊ ነው፡፡

እርግጥ ነው በአምስት ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የተጀመረው ግዙፉ የአገር ዓርማ ፕሮጀክት፣ በአሥረኛ ዓመቱ ዋዜማ ላይ የመጀመርያውን ምዕራፍ ማሳካቱ ቢቆጠቁጥም ሥራውን አስጀምረው፣ ለተረኛው ያስረከቡት፣ ሥራውን ተቀብለው ያጠናቀቁት መሪዎችና ባለሙያዎች ለሕዝቡ ተሸጋሪ ተስፋን አስርጸውበታል፡፡ ቢዘገይም ተስፋ ሳይቆረጥ የተሠራው ሥራ ውጤት አስገኝቷል፡፡ ጠላቶች ድል ተመተውበታል፡፡ የዘመናት ምኞትን ማሳካት የተቻለበት፣ ይህ ትልቅ ዓርማ ለሌሎች ወሳኝ መልዕክትም አለው፡፡ ኢትዮጵያውያን የፈረሙበት የህዳሴው ግድብ በወቅቱና በጊዜው አለመጠናቀቁ ቢያስቆጭም፣ ከሁለት ዓመታት ወዲህ እንደ አዲስ በተደረገው ጥረት፣ ከባዱን ዲፕሎማሲ በማሸነፍ ጭምር ውጤት ማስገኘቱ ለአገር የቆረቱ ዜጎች ምን ያህል መራመድ እንደሚችሉ ያሳየ የልብ ሥራ ሆኗል፡፡

የፕሮጀክቱ ውጤት ከብዙ ልፋትና እልህን ከሚያስጨርሽ ፈታኝ ጥረት በኋላ ሊሳካ የቻለ መሆኑ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ በዓባይ ውኃ ለመጠቀም የምንችበት ወሳኝ ወቅት ላይ የምንገኝበት ጊዜ ላይ እንደምንገኝ ልብ እንድንል የሚያመላክት ውጤት ተገኝቷል፡፡ በውኃችን እንዳንጠቀም ሲፈጸሙ የቆዩ ደባዎችን በማክሸፍ ከህዳሴው ግድብ በተጨማሪ ዓባይን ወንዝን በመጠቀም ሌሎች ፕሮጀክቶችን መሥራት የምንችልበትን የመብት ኮርቻ ለመፈናጠጥ ፈር የቀቀደ ወሳኝ ፕሮጀክት ነው፡፡

በርካታ የውስጥና የውጭ ጠላት የተረባረበበት፣ ግድቡ እንዳይገነባ ብዙ መሰናክሎችና ጥልፍልፎች የከበቡት የህዳሴው ግድብ፣ እየተገማሸረ የሚነጉደውን ወርቃማውን የዓባይ ውኃ ከትሮ አደብ እያስገዛ፣ እኛም ቤት ሥራ እንዳለበት፣ ጉልበቱን የሚገታ ሥራ ተበጅቶለታል፡፡ የመጀመርያው ምዕራፍ የውኃ ሙሌት በተሳካ መንገድ መጠናቀቁ፣ በቅርቡም ሁለቱ ኃይል የሚያመነጩ ተርባይኖች ሥራ እንዲጀምሩ የሚችሉበት ደረጃ ላይ መደረሱ፣ 750 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማምረቻው ጊዜ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ሊሳካ እንደሚችል መገለጹ ጮቤ ያስረግጣል፡፡ ይህ በእርግጥም ከብሥራት በላይ የሆነ ዜና ነው፡፡ ነገር ግን የፕሮጀክቱ ሥራ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ባለመድረሱ የሩብ ምዕራፍ ያህል ፈታኝ ሥራ እንደሚቀር መታወቅ አለበት፡፡

የግድቡን ሥራ ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ ብዙ ገንዘብና ጉልበት የሚጠይቁ በርካታ ሥራዎች ይቀራሉ፡፡ ደስታችንን ምሉዕ ለማድረግ፣ ለቀሪው ሥራ ጥረታችንና ጥሪታችን ወሳኝ እንደሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

አጠቃላይ የግድቡ ሥራ በ2015 ዓ.ም. የሚጠናቀቅ በመሆኑ፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ በየሰበቡ ግንባታው እንዳይጓተት ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ግድቡን ለመጨረስ ከእስካሁኑ በላይ መትጋት ይጠበቅብናል፡፡ ግድቡን ለማስጨረስ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ማዋጣትና ማሰባሰብ አንዱ ሲሆን፣ በግድቡ ላይ ዓይናቸው የቀላ ታሪካዊ ጠላቶችንም በሁሉም አቅጣጫ እንዳመጣጣቸው መመከት ያስፈልጋል፡፡

ይህ ለመንግሥት የሚተው ተግባር አይሆንም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደተመለከትነው ‹‹ዓባይ የእኔ ነው›› የሚለውን ታላቅ መፈክር እንደ ብሔራዊ ዓርማ በማንገብ በዓባይ ውኃ የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብታችንን ዓለም እንዲያውቀውና ብቻም ሳይሆን እንዲያረጋግጠውና እንዲቀበለው ለማድረግ ዓለምአቀፍ ዘመቻ ማድረግ አንዱ ወሳኝ ዕምርጃ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ባህል ለማስተዋወቅ ‹‹ሕዝብ ለሕዝብ›› ተብሎ የተደረገውን ዓይነት ንቅናቄ፣ አሁንም ዓባይ የኢትዮጵያ ምንጭ መሆኑን ለዓለም የማሳወቅ ሕዝባዊ ተልዕኮ በማካሄድ የዓለም የተንሿረረና ለአንድ ወገን ያደረ አስተሳሰብ ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡

የህዳሴው ግድብ የማንም ፖለቲካዊ አጀንዳ መሆን የለበትም፡፡ ግድቡ ከኢትዮጵያውያን በላይ ኢትዮጵያዊ በመሆነው የዓባይ ወንዝ ላይ የተገባ ማኅተም ነው፡፡ ስለዚህም በኅብረት የምንገነባው ቅርሳችን እንደሆነ ማሳወቅ የሁላችን ሥራ መሆን አለበት፡፡ ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ የአገራችን ዲፕሎማቶች ትልቁ ሥራቸው ይህ ፕሮጀክት ተገቢውን ተቀባይነትና ድጋፍ እንዲያገኝ በሚያስችሉ ተልዕኮዎች ላይ ማነጣጠር ይኖርበታል፡፡ ለግድቡ ሥራ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ ከእስካሁኑ በተለየና በተደራጀ ሁኔታ ማሰባሰብም ከሥራዎች አንዱና ወሳኙ ሥራ ነው፡፡

ዓባይ የእኔ ነው ካልን ከግድቡ የሚገኘውንም ጥቅም በጋራ ለመቋደስ ዜጎች በተለየ መንፈስ የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት አለባቸው፡፡ ከግቡ ደርሶ የሚፈለው ውጤት ሲገኝ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ትለወጣለች፡፡ ስለዚህ የውኃ ሙሌቱ መሳካት የፈጠረውን አገራዊ ስሜት በተግባር በሚገለጽ መነሳሳት ለውጦ ግድቡን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ወደ ሚያስችል ጉልበት መምራት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ማድረግ የግድ እንደሆነ መቼም የግብፅንና የአባሪዎቿን መውተርተር ማየቱ በቂ ነው፡፡ ግደቡ የኢትዮጵያን ወዳጆችና ጠላቶች አደባባይ አውጥቷል፡፡

የህዳሴው ግድብ ስኬታማ መሆን የዓባይ ውኃ ድርሻችንን በመጠቀም ሌሎች ሥራዎችን ለመሥራት የምንችልበትን ገልበትና አቅም ይሰጠናል፡፡ ኃይል ይሆነናል፡፡ እዚያ ለመድረስ ግን ቀሪውን የግድቡን ሥራ ለማጠናቀቅ የሚያግዙ ክንዶችን እናስተባብር፤ እናብር፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት