Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናሰሞኑን የተጀመረው የህዳሴ ግድቡ ድርድር ተቋርጦ ለመጪው ሳምንት ተላለፈ

ሰሞኑን የተጀመረው የህዳሴ ግድቡ ድርድር ተቋርጦ ለመጪው ሳምንት ተላለፈ

ቀን:

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌትና አስተዳደርን የተመለከተው ድርድር ሰኞ ሐምሌ 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ከተጀመረ በኋላ፣ ሱዳን ባቀረበችው ጥያቄ ምክንያት ተቋርጦ ወደ ቀጣዩ ሳምንት እንዲተላለፍ ተወሰነ። 

በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት የታላቁ የህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌትና አስተዳደር የተመለከተው የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን ድርድር ሰኞ ዕለት እንደገና የተጀመረ ቢሆንም፣ ሱዳን ጉዳዩን በተመለከተ ውስጣዊ ምክክር ማድረግ እንደምትፈልግ በመግለጽ ድርድሩ እንዲራዘምላት በመጠየቋ ወደ ሚቀጥለው ሳምንት እንዲተላለፍ ተወስኖ መቋረጡ ታውቋል። 

ኢትዮጵያ በግድቡ 4.9 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ ተይዞ የመጀመርያው ዓመት ሙሌት ሐምሌ 12 ቀን 2012 ዓ.ም. መጠናቀቁን ማስታወቋ ይታወሳል። 

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሰኞ ዕለት በተጀመረው ድርድር ወቅት ሱዳን የመጀመርያው ዓመት የግድቡ የውኃ ሙሌት ስምምነት ሳይደረግበት፣ በኢትዮጵያ በኩል መከናወኑ ተገቢ አይደለም የሚል ተቃውሞ ማሰማቷን የአገሪቱ የውኃና መስኖ ሚኒስትር ያሲር አባስ በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል። 

የግብፅ የውኃና መስኖ ሚኒስትር ቃል አቀባይ የመጀመርያው ዓመት የውኃ ሙሌት መከናወኑን አስመልክቶ ለአገሪቱ ሚዲያዎች በሰጡት አስተያየት፣ ሙሌቱ መከናወኑ ወደ ግብፅ በሚመጣው የውኃ መጠን ላይ ጉዳት አለማድረሱን ገልጸዋል። 

ሱዳን የህዳሴ ግድቡን ጉዳይ የሚከታተል ላዕላይ ምክር ቤት ከሳምንት በፊት ያቋቋመች ሲሆን፣ ምክር ቤቱም በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ሰብሳቢነት የሚመራና በአባልነትም የውጭ ጉዳይ፣ የፍትሕ፣ የውኃና መስኖ ሚኒስትሮችና ብሔራዊ ደኅንነት ቢሮ ኃላፊው ተወክለዋል። 

ሰኞ የተጀመረው ድርድር በተቋረጠ በማግሥቱም የሱዳን ላዕላይ ምክር ቤት የመጀመርያውን ስብሰባ ማካሄዱን፣ የሱዳን ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። 

ምክር ቤቱ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ በሚደረገው ድርድር የሱዳን አቋምና ጥቅም መከበርን እንደገመገመ የሚገልጸው የሚኒስቴሩ መግለጫ፣ ሦስቱ አገሮች ስምምነት ሳይደርሱ የግድቡን የመጀመርያ የውኃ ሙሌት ኢትዮጵያ ማከናወኗ በቀጣይ ድርድር ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖረው መገምገሙን አስታውቋል። 

ሪፖርተር ከኢትዮጵያ መንግሥት ምንጮች ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ፣ ሱዳን የግድቡ ግንባታ ላይም ሆነ በግድቡ የውኃ ሙሌት ላይ የምታራምደው አቋም ከኢትዮጵያ አቋም ጋር ያለው ቅራኔ መጠነኛና መግባባት ሊደረስበት የሚችል ነው፡፡

የግድቡ የውኃ ሙሌት መጀመርን ተከትሎ በየቀኑ ከግድቡ የሚወጣው የውኃ መጠን ልዩነት ስለሚኖረው ሱዳን የመጀመርያው ዓመት ሙሌት ከመከናወኑ አስቀድሞ፣ በዕለታዊ የውኃ መጠን ላይ ስምምነት እንዲደረስ አጥብቃ ጠይቃ እንደነበር ምንጮች ይገልጻሉ። 

ሙሌቱ የተካሄደው በሱዳን ላይም ሆነ በግብፅ ላይ ምንም ጉዳት ሳያደርስ ቢሆንም፣ ሱዳን ባነሳችው ጥያቄ ላይ ስምምነት ሳይደረግ የመጀመርያው ምዕራፍ ሙሌት መጠናቀቁ እንዳስከፋት ጠቁመዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የዓባይ ውኃ ይዞት የሚሄደውን ደለል በመጠቀም በርካታ ሱዳናዊያን በሸክላ ሥራ የሚተዳደሩ ስለሆነና የግድቡ ሙሌት ከተጀመረ በኋላ ወደ ሱዳን ተጠርጎ የሚሄደው ደለል የሚቀንስና በኋላም ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ የሚቀር በመሆኑ፣ የሱዳን መንግሥት ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የመፍትሔ ጥያቄ ማንሳቱን  ምንጮች ገልጸዋል፡፡ መፍትሔው ግን ከኢትዮጵያ በኩል የግድቡን ግንባታ ተንተርሶ ሊመጣ የሚችል አለመሆኑን አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...