Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

እንግሊዝ ለመሬት ይዞታና ለኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራሞች 105 ሚሊዮን ፓውንድ ድጋፍ ሰጠች

ተዛማጅ ፅሁፎች

እንግሊዝ በኢትዮጵያ የሚካሄዱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ታሳቢ በማድረግ፣ የመሬት አስተዳደር ሥራዎችን ጨምሮ የሥራ ዕድል ለማስፋፋት የሚያግዙ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራሞችን ለማስፈጸም የሚያግዝ 105 ሚሊዮን ፓውንድ ስተርሊንግ ወይም 4.71 ቢሊዮን ብር ዕርዳታ መስጠቷን መንግሥት አስታወቀ፡፡

ዕርዳታውን በእንግሊዝ በኩል የኮመን ዌልዝ ጽሕፈት ቤትና የዓለም አቀፍ ልማት ተቋምን እንደ አዲስ በማጣመር እንዲወክል በተደረገው የእንግሊዝ የውጭ ጉዳዮች መሥሪያ ቤት፣ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ጄምስ ዱድሪጅ ከገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ ጋር በመሆን፣ ማክሰኞ ሐምሌ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. በገንዘብ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ውስጥ ተፈራርመዋል፡፡

ገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ መሠረት፣ እንግሊዝ ለመሬት ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የሚውል 60 ሚሊዮን ፓውንድ ድጋፍ ሰጥታለች፡፡ ይህም በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይና በደቡብ ክልሎች ተግባራዊ ለሚሆኑ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫና ለገበያ ሥርዓት ማስተግበሪያ እንዲውል የተሰጠ  ድጋፍ ስለመሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በዚህ ፕሮግራም መሠረት፣ የይዞታ ማረጋገጫ ካላገኙ 36 ሚሊዮን ሽንሽን መሬቶች ውስጥ ሰባት ሚሊዮኑን ያህሉ የሁለተኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ እንዲሠራላቸው፣ እንዲሁም 103 ወረዳዎችን በዲጂታል የመሬት አስተዳደር ሥርዓት በማስተሳሰር የሚሠሩበትን ዕድል ለመፍጠር እንዲቻል 60 ሚሊዮን ፓውንድ ዕርዳታ ከእንግሊዝ መንግሥት ተበርክቷል፡፡ በሒደት 1.2 ሚሊዮን አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች እስከ 15 በመቶ  የተሻሻለ ገቢ እንዲኖራቸው ለማስቻል የታቀደ ፕሮግራም ስለመሆኑ ገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ሁለተኛው የዕርዳታው ክፍል 45 ሚሊዮን ፓውንድ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራምን ለማፋጠን የተወጠነውን ፕሮግራም ለማስፈጸም የሚውል ድጋፍ የተደረገበት ነው፡፡ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚመረቱና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ለሚያመርቱ የአገር ውስጥ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ድጋፍ የሚሰጡ ሥራዎች የሚደገፉበት ይህ ፕሮግራም፣ የአገሪቱን የኢንዱስትሪ ጉዞ ለማገዝ፣ የምርት ሒደት ላይ እሴትን በማሻሻል የሥራ ፈጠራን ለማስፋፋት የሚረዱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች የሚደገፉበት ነው፡፡

በዚህም መሠረት 40 ሺሕ አዳዲስ የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ ለማስቻል 25 ሚሊዮን ፓውንድ የተመደበ ሲሆን፣ በዚህም በአሥር የመንግሥት ተቋማትና በአራት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከሚገኙ የውጭ ኩባንያዎች ጋር የሚሠሩ 60 የአገር ውስጥ የንግድ ኩባንያዎችን ጨምሮ፣ በርካታ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን ለመደገፍ የእንግሊዝ መንግሥት ድጋፍ መስጠቱን ገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች