Friday, December 9, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ስፖርትበስፖርት ምክር ቤት ዓመታዊ ጉባዔ

  በስፖርት ምክር ቤት ዓመታዊ ጉባዔ

  ቀን:

  የስፖርት ማኅበራት ምዘናና ስታንዳርድ መመርያ ተዘጋቶ ውይይት ተደርጎበታል

  ስፖርቱ ኮታዊ አሠራር ተላቆ በብቃትና በክህሎት እንዲመራ ተጠይቋል

  አገር አቀፍ የስፖርት ምክር ቤት ሐምሌ 20 እና 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ዓመታዊ ጉባዔውን አካሒዷል፡፡ ምክር ቤቱ ባለፉት ዓመታት ሲሠራባቸው የነበሩ ደንብና መመርያዎችን መነሻ በማድረግ የአገር አቀፍ ስፖርት ማኅበራት በአዲስ መልክ ስለሚቋቋሙበት ሁኔታ ለመወሰን በሚያስችሉ ሁኔታዎች እንዲሁም ስፖርቱ ከኮታዊ አሠራር ተላቆ ብቃትና ክህሎት ባላቸው ሙያተኞች መመራት በሚቻልባቸው አሠራሮች ላይ በሰፊው ተወያይቷል፡፡ ለመመርያው ማጠናከሪያ የሚሆኑ ሐሳቦችን በምከር ቤቱ ተሰንዝሯል፡፡ ለአገራዊ ስፖርት ዕድገት ማሻሻያ (ሪፎርም) ተዘጋጅቶ ሊቀርብ በታቀደው ሪፖርትና የስፖርት ማኅበራት ምዘናና ምደባ ስታንዳርድ ላይም መክሯል፡፡

  ከወትሮ ለየት ባለ አቀራረብ በተካሔደው የስፖርት ዘርፉ ዓመታዊ ጉባዔ ለስፖርት ዕድገት የሚበጁ፣ ጠንካራና ሙያዊ የሆኑ አስተያየቶችና ሐሳቦች ተሰንዝረዋል፡፡ ከተነሱት ሐሳቦች መካከል ላለፉት በርካታ ዓመታት ውድድር ተኮር ከነበረው የአስፈጻሚው አካል የሥራ ድርሻ በውል ተለይቶ መቀመጥ እንዳለበት፣ ክልሎች ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችን እንዲያስተዳድሩ የሚያቀርቧቸው ዕጩዎች ተገቢውን መስፈርት የሚያሟሉ መሆን አለመሆናቸው በስፖርት ምክር ቤቱ ቀርቦ እንዲረጋገጥ የሚሉትና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡

  ለምክር ቤቱ ተዘጋጅቶ የቀረበው ጥናት በተለይ የስፖርት ማኅበራት ማቋቋሚያ መመርያ የነበሩ ክፍተቶችን መነሻ በማድረግ ማሻሻያ እንዲደረግበት የሚጠይቅ ከመሆኑ ባሻገር፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና አሶሴሽኖች ምንም መስፈርት ሳያሟሉ ስሙን ብቻ ይዘው ለዓመታት መቀጠላቸው ለመጨረሻ ጊዜ መጠሪያቸው ብቻ ሳይሆን የሚያንቀሳቅሱት የስፖርት ዓይነትና ይዘት በአዲሱ ደንብና መመርያ በውል ተለይቶ እንዲቀመጥ የሚያስገድድ ጭምር ነው፡፡

  ከ90ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ መንግሥት አገር አቀፍ የስፖርት ፖሊሲ ቀርፆ፣ የስፖርት አመራሩን በመንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ አስገብቶ፣ ዓመታዊ በጀት መድቦ የስፖርት ልማት ሥራዎች እንዲከናወኑ ለማድረግ የነበረው ዕቅድ ሳይሳካ የቀረው በጥናት ላይ የተመሠረተ ክትትልና ቁጥጥር ባለመኖሩ እንደሆነ ምክር ቤቱ የነበረውን አሠራር ተችቷል፡፡

  ለአንድ አገር መሠረታዊ ከሚባሉ የልማት አጀንዳዎች መካከል የስፖርት ልማት አንዱና ዋነኛው ቢሆንም፣ በዚህ ረገድ ከአስፈጻሚው አካል ጀምሮ የሥራ ድርሻና የኃላፊነት ወሰን ስለማይታወቅ ውጤት ማስመዝገብ አለመቻሉም ተነግሯል፡፡

  በስፖርት ፖሊሲው ከተካተቱ ‹‹ስፖርት›› መሠረታዊ የሰው ልጆች መብት ተደርጎ የሚታይ ቢሆንም፣ በነበረው የተደበላለቀ የአሠራር ሥርዓት ዜጎችን በስፖርት በማሳተፍ በሁሉም ስፖርት አገርን የሚወክሉ ብቁና የላቁ አትሌቶችን ማፍራት እንዳልተቻለ በምክር ቤቱ የሁለት ቀን ውሎ ተንፀባርቋል፡፡

  የብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና አሶሴሽኖች የሥራ ድርሻና የኃላፊነት ወሰን እንዲሁም ውድድር ተኮር ሆኖ የቆየው ስፖርት ኮሚሽኑን ጨምሮ የአስፈጻሚ አካላት ድርሻና የኃላፊነት ወሰን በዝርዝር የምክር ቤቱን ግብዓት አጠቃሎ በአዲሱ መመርያና ደንብ እንዲካተት ተጠይቋል፡፡ በዋናነት ስፖርቱን ለመምራት ኮታዊ የሆነው የክልሎች የዕጩ አቀራረብ ሁኔታ በዚህ ምክር ቤት ታይቶና ተገምግሞ ክልሉን ወክሎ የሚቀርበው ግለሰብ ይሁንታ እስካላገኘ ድረስ ባለፉት ዓመታት በነበረው አሠራር ለምርጫ መቅረብ እንደሌለበት ጉባዔው አጥብቆ የጠየቀው ጉዳይ ሆኖ ታይቷል፡፡

  የስፖርት ልማት ዕድገት በተሻለ የሕዝቦችንና የአገርን ጥቅምና ፍላጎት ባስጠበቀ መልኩ መምራትና ወደተሻለ ደረጃ ማሸጋገር የማኅበረሰቡ ሁለንተናዊ ዕድገት አንድ አካል ተደርጎ እንደሚወሰድ በዘርፉ የቀረቡ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ስፖርት ኮሚሽን ለምክር ቤቱ ካቀረበው ጉዳይ አገራዊ የስፖርት ማሻሻያ ጥናት ይህንኑ ያጠናክራል፡፡

  ዕድሜ ጠገብ የሆነው የአገሪቱ ስፖርት ባለበት የተለያዩ ውስብስብ ችግሮች ምክንያት በሚፈለገው ልክ ዕድገት ሊያመጣ አለመቻሉም በኮሚሽኑ የጥናት ሪፖርት ተካቷል፡፡ የስፖርት ልማት አሁን ባለው ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ግምገማና ፍተሻ ማከናወን የሚያስፈልገው ዘርፍ ስለመሆኑ ጭምር ኮሚሽኑ አመላክቷል፡፡

  በኢትዮጵያ ቀድሞ የነበረውን ደንብና መመርያ መነሻ በማድረግ 30 አገር አቀፍ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና አሶሴሽኖች ተቋቁመው እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ ሁሉም ተቋማት በአደረጃጀትና በመረጃ አያያዝ ሲለኩ ከፍተኛ የሚባል ክፍተት ያለባቸው መሆኑ በምክር ቤቱ ታምኖበታል፡፡

  አሁን ባለው ሁኔታ ብዙዎቹ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና አሶሴሽኖች ራሳቸውን ከመንግሥት ተረጅነት ነፃ ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ አለመታየታቸውም ተጠቅሷል፡፡ ተቋማቱ እንዲሻሻሉና ለውጥ እንዲያመጡ ከተፈለገ ክፍተቶቻቸውንና ደካማ ጎኖቻቸው ጎልተው ሊነገሩ እንደሚገባ በጉባዔው አባላት ሲነገር ተደምጧል፡፡ የተሟላ ቢሮ ሳይኖራቸው በየመንገዱ ቃለ ጉባዔ የሚያስፈርሙ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችን ከተቻለ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ማገዝ፣ ካልተቻለ ደግሞ ሕልውናቸው እንዲያከትም ማድረግ የሚሉ ሐሳቦች ሲንፀበረቁ ተስተውሏል፡፡ 

  ከማዘውተሪያ ጋር በተያያዘ በኮሚሽኑ አማካይነት ቀደም ሲል ከ27,000 በላይ የማዘውተሪያ ሥፍራዎች እንዳሉ ሲነገር የነበረው በተጨባጭ መሬት ላይ የሚታይ ምንም ነገር እንደሌለ በምክር ቤቱ ተነግሯል፡፡ ለዚህ ተብሎ የሚባክነው የመንግሥት ሀብት (በጀት) ማዘውተሪያውን ጨምሮ ትምህርት ቤቶችን ትኩረት ያደረገ ፕሮጀክት ላይ እንዲውልና በዚያ ልክ ማቀድ እንደሚያስፈልግ ሐሳብ ቀርቧል፡፡

  ለብሔር ብሔረሰቦች ዓመታዊ በዓል ማክበሪያና ማድመቂያ በየክልሎቹ የተጀመሩ ስታዲየሞች የካፍንና የፊፋን ስታንዳርድ ጠብቀው እንዲጠናቀቁ ካልተደረገ፣ ኢትዮጵያ እንደ አገር አኅጉራዊና ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን የማስተናገድ አቅም እያጣች ስለመሆኑ ጭምር ተጠቁሟል፡፡ ከማዘውተሪያ ጋር በተያያዘ ለዓመታት ምንም ዓይነት አድሳት ሳይደረግለት በቅርቡ በፊፋና ካፍ ዕገዳ እንዲተላለፍበት ለተደረገው ለአዲስ አበባ ስታዲየም ዕድሳት 25 ሚሊዮን ብር በጀት የተያዘ ስለመሆኑ ግን ኮሚሽኑ ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡

  ጉባዔው የብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ወጪን አስመልከቶ ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ በመነሳት ጉዳዩ ለመንግሥት ቀርቦ ውሳኔ እንደሚሰጥበት ተነግሯል፡፡ ከእግር ኳስ ተጨዋቾችና ክለቦች በጀት ጋር ተያይዞ የአገሪቱ የፋይናንስ ሥርዓት በሚጠይቀው ልክ መንግሥት ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ ተገቢውን ማስተካከያ ሊያደርግ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡ ከተጨዋቾች የደመወዝ ጣሪያ ጋር በተገናኘ ውሳኔው በውል ሰጭና ውል ተቀባይ መካከል የሚወሰን ሊሆን እንደሚገባ ኮሚሽኑ አመላክቷል፡፡ ዘገባው በኅትመት ምክንያት የምክር ቤቱን ማጠቃለያ አላካተተም፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመው ጭፍጨፋና ሥጋቱ

  ኦሮሚያ ክልል ከቀውስ አዙሪት መላቀቅ ያቃተው ይመስላል፡፡ ከ200 በላይ...

  እናት ባንክ ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰነ

  መጠባበቂያን ሳይጨምር የባንኩ የተጣራ ትረፍ 182 ሚሊዮን ብር ሆኗል እናት...

  ቡና ባንክ ዓመታዊ ትርፉን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማሻገር ቻለ

  ቡና ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔውን ለመጀመርያ...