Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የአዲስ አበባን የምግብ ፍጆታ 25 በመቶ ይሸፍናል ተብሎ የሚጠበቀው የከተማ ግብርና

 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ከተዋቀረ ዓመት ሆኖታል፡፡ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ እንደ አንድ የሥራ ሒደት አገልግሎት ይሰጥ የነበረ ሲሆን፣ ተመሳሳይና ተቀራራቢ የሆኑ የሥራ ሒደቶችን በአንድነት እንዲዋቀሩ በተደረገበት ሒደት የተፈጠረ ኮሚሽን ነው፡፡ ኮሚሽኑ ሁለት መሠረታዊ የሆኑ የሥራ ሒደቶችን ወደ አንድ እንዲጠቃለሉ አድርጓል፡፡ የመጀመርያው የከተማ ግብርና ሲሆን፣ ከከተማ መስፋፋትና ዕድገት ጋር ተያይዞ አርሶ አደደሮችን በዘለቄታዊነት መልሶ ማቋቋም የሚለው በአዋጅ የተሰጠው ሁለተኛ ተግባሩ ነው፡፡ ኮሚሽኑ በአንድ ዓመት ውስጥ የተለያዩ ሥራዎችን ማከናወኑን ይገልጻል፡ በተለይ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ የከተማ ግብርናን በሰፊው እያከናወነ ነው፡፡ አቶ መሐመድ ልጋኒ ሣሬሳ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ምክትል ኮሚሽነር ናቸው፡፡ የከተማ ግብርናና የተሠሩ ተግባራት በተመለከተ ሔለን ተስፋዬ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡– ኮሚሽኑ ከተዋቀረ በኋላ ምን ዓይነት ሥራዎችን አከናውኗል?

አቶ መሐመድ፡– ኮሚሽኑ በሦስት መሠረታዊ ተግባሮች ላይ በዋናነት ይሠራል፡፡ የመጀመርያው ተግባር በልማትና የከተማ መስፋፋት ተከትሎ በወቅቱ ፍትሐዊ ካሳ ባለመሰጠቱ ዛሬ ላይ ለችግር የተጋለጡትን መልሶ የማቋቋም ሥራ ይሠራል፡፡ ሁለተኛው የከተማ ግብርናን ማስፋፋት ነው፡፡ አደጉ ከተባሉ አገሮች ተሞክሮ እንዳየነው አብዛኛው የከተማ የምግብ ፍጆታ በከተማ ግብርና የሚሸፈን ነው፡፡ የኢትዮጵያ በርካታ ከተሞች ለኑሮ ብቻ ሳይሆን ለከተማ ግብርናም ምቹ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ የአየር ጠባይና ማኅበረሰቡ ለግብር ያለውን ግንዛቤ ጨምሮ ምቹ ሁኔታን ሳንጠቀም ቆይተናል፡፡ የኑሮ ውድነቱ ይብዛም ይነስም የመጣው በዘርፉ የተሠራው ሥራ በሚፈለገው ደረጃ ባለመሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም የከተማ ግብርናን በሰፊው መተግበር እንዳለብን መገንዘብ ችለናል፡፡ የከተማ ግብርና በሁለት መንገድ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ከአዲስ አበባ ዙሪያ  በልማት ያልተነሱ አርሶ አደሮች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉና ምርትና ምርታማነት ከፍተኛ እንዲሆን እገዛ ይደረግላቸዋል፡፡ ከከተማው ጋር ያላቸው ቅርበትና ቁርኝት የጠበቀ እንዲሆንና ምርታማነታቸው እንዲያድግ የተለያዩ የግብርና ድጋፍ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፡፡ አሁን ባለው መረጃ በልማት ምክንያት ያልተነሱ 4,192 አርሶ አደሮች አሉ፡፡ ሙሉ ለሙሉ በእርሻ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሲሆኑ፣ ምርታማ እንዲሆኑ በማገዝ በተመጣጣኝ ዋጋ አቅራቢ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡ ሁለተኛው የከተማ ግብርና ሲሆን፣ በአነስተኛ ቦታ ላይ የተለያዩ ምርቶችን እንዲያለሙ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በተለይም ከኑሮ ውድነት አንፃር እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመቅረፍ በጥቂት ቦታ የጓሮ አትክልት እየተመረተ መጠቀም እንዲቻል እየተሠራ ነው፡፡ ይህ ማኅበረሰቡ ጤናማና ተስማሚ የሆኑ ምርቶችን በማምረት እየተጠቀመ ጤናውን እንዲጠብቅ ያግዛል፡፡ አካባቢውን አረንጓዴና ለዓይን ማራኪ በማድረግ ንፁህ የአየር ሁኔታ እንዲፈጠርም እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡ ከተለያዩ የክልል ከተሞች የሚገቡ የግብርና ውጤቶች ለነዋሪው ከመድረሳቸው በፊት ጥራታቸውን ያረጋግጣል፣ ይቆጣጠራል፡፡ ለምሳሌ በከተማዋ የሚታረዱ ከብቶች በኮሚሽኑ አማካይነት ተመርምረው ኅብረተሰቡ ጋር እንዲደርሱ ያደርጋል፡፡

ሪፖርተር፡ ከልማት ጋር በተያያዘ የተነሱ አርሶ አደሮች መልሶ የማቋቋም ሥራ ምን ይመስላል?

አቶ መሐመድ፡– ላለፉት ዓመታት ከከተማ ዕድገት ጋር ተያይዞ የሚነሱ አርሶ አደሮች አሉ፡፡ እነዚህ አርሶ አደሮች ከመንግሥት ፍትሐዊ የሆነ የካሳ ክፍያ ባለማግኘታቸው ለኢኮኖሚ፣ ለሥነ ልቦናና ለሌሎችም ችግሮች ተጋልጠዋል፡፡ ኮሚሽኑ እንደ አንድ ግብ ብሎ ከያዘው የሥራ ሒደት ውስጥ አርሶ አደሮቹን በሥነ ልቦናም በሌሎችም ማቋቋም ነው፡፡ አርሶ አደሮቹ የሚታገዙት ላልተፈለገ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ በመዳረጋቸው ነው፡፡ በስፋት በግብርና ዘርፍ ላይ ተሰማርተው ውጤታማ የነበሩ በመሆናቸው የከተማ አስተዳደሩ ጥናት አድርጎ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አቋቁሞ ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ በዚህም መሠረት 26,000 አርሶ አደሮችን መልሶ ለማቋቋም  እየተንቀሳቀስን ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 22,000 ሚሆኑት መጠለያ  እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡– እስካሁን በከተማ ግብርና ምን ያህል ሰው ተሳትፏል?

አቶ መሐመድ፡– ከዚህ ቀደም የተሟላ ድጋፍ ባይኖርም 94,000 ነባር የግብርና ኤክስቴሽን ተጠቃሚዎች አሉ፡፡ እነዚህ በባለሙያዎች በጥቂት ቦታ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችና ፍራፍሬዎች እንዲተክሉ በኮሚሽኑ የሚደገፉ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አዳዲስ የከተማ ግብርና ላይ የሚሳተፉ ሰዎች የማስገባት ሥራ ተሠርቷል፡፡ በዚህም 50,000 አዲስ የከተማ ግብርና ለማሳተፍ ታቅዶ 54,000 አዲዲስ አባወራዎችን በከተማ ግብርና ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ በዚህ መንገድ ከሄድን በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካቶችን በከተማ ግብርና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት በሙለ በኮሚሽኑ የግብርና ኤክስቴክሽን እየተደገፉ የሠሩ ሲሆን፣ በ2012 ዓ.ም. በየቦታው በራሳቸው ተነሳሽነት የጓሮ አትክልቶችን በመትከል ተጠቃሚ የሆኑም አሉ፡፡

ሪፖርተር፡– የከተማ ግብርና የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንፃር እንዴት ይገልጹታል?

አቶ መሐመድ፡– ኮሚሽኑ በአዋጅ ከተሰጠው የሥራ ሒደት በተጨማሪ ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ማድረግ ሌላኛው ሥራው ሆኗል፡፡ ከምግብ አቅርቦት ባለፈ ለብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ በ2012 ዓ.ም. በከተማ ግብርና ላይ 50,000 ዜጎች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ይረጋል ተብሎ ታቅዶ ነበር፡፡ አሁን ላይ አፈጻጸሙ ሲገመገም ለ29,000 ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡

ሪፖርተር፡– የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ የሚደረገው እንቅስቃሴ እንዴት እየተከናወነ  ይገኛል?

አቶ መሐመድ፡– ወረርሽኙ ዓለም አቀፍ በመሆኑ የሚወጡ መረጃዎችን በመከታተልና የምግብ እጥረት በከፍተኛ መጠን ሊኖር እንደሚችል በመገመት በሰፊው ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ በመንግሥት ደረጃ በትኩረትና በስፋት ሲሠራ የነበረው የከተማ ግብርና ላይ ነው፡፡ በወረርሽኙ ምክንያት ሊከሰት ከሚችለው የምግብ እጥረት መቅረፍ የሚያስችል ሰፊ ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በመንግሥትና በግል ተቋማት የተያዙ ክፍት ቦታዎችን በከተማ ግብርና ሥራዎች እንዲሸፈኑ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ ችግሩን ለመቋቋም በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርሱ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬዎች እንዲተከሉ ተደርጓል፡፡ በ156 ትምህርት ቤቶች፣ የመንግሥትና የግል ተቋማት በአይሲቲ ፓርክ በሌሎችም 142 ተቋማት ክፍት ቦታዎች ለከተማ ግብርና እየዋሉ ይገኛሉ፡፡ ለልማት ታጥረው የተቀመጡ 1,097 ክፍት ቦታዎች ማኅበረሰቡ በወረርሽኙ ሳቢያ ለችግር እንዳይጋለጥ እንዲያግዙ ለከተማ ግብርና የታለሙ ናቸው፡፡ እነዚህ ቦታዎች በወረርሽኙ ምክንያት እንቅስቃሴዎች ስለማይደረግባቸው በጊዜያዊነት ለከተማ ግብርና እየዋሉ ሲሆን፣ በቀጣይ ወደ ነበሩበት የሚመለሱ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡– በትምህርት ቤቶች በተቋማት ውስጥ ምን ያህል ሥራዎች ተሠርተዋል?

አቶ መሐመድ፡– ከትምህርት ቤቶች 55.6 ሔክታር፣ 141.8 ሔክታር ከተቋማት የተገኘ ሲሆን፣ 569 ሔክታር ክፍት ቦታዎች ለከተማ ግብርና እንዲውሉ ተደርጓል፡፡ ከተለዩ ቦታዎች ውስጥ በ706ቱ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡ ታርሰውና ተዘርቶባቸው ምርታቸው እየደረሰ ይገኛል፡፡ ጎመን፣ ሰላጣ፣ ቆስጣ፣ ቃሪያ፣ ድንችና ሌሎችም በአጭር ጊዜ ሊደርሱ የሚችሉ አትክልቶች እንዲመረቱ እየተደረገ ነው፡፡ ከታሰበው አንፃር እስከ ዓርብ ሐምሌ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ 73 በመቶ የተለዩ ቦታዎች በመሉ በምርት እንዲሸፈኑ ተደርጓል፡፡ በመኸሩ የተሠሩ ሥራዎች ምርቶቹ ሲደርሱ 80.6 ቶን ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ቀደም በከተማ ግብርና ይገኝ የነበረው ምርት ሁለት በመቶ ሲሆን፣ በዘንድሮ የተሠራው ሥራ የአዲስ አበባ ከተማን የምግብ ፍጆታ 25 በመቶ ይሸፍናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሪፖርተር፡– ምርቶቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማኅበረሰቡ እንዲደርሱ በኮሚሽኑ ምን ዓይነት የገበያ ትስስር ይፈጠራል?

አቶ መሐመድ፡– አርሶ አደሩ በቀላሉ ለሸማቾች የሚያደርስበት መንገድ ተመቻችቷል፡፡ በመሃል ሌላ አገናኝ ስለማይኖር ማኅበረሰቡ በቀላሉና በአነስተኛ ዋጋ እንዲሸምት ዕድል ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡– በእናንተ በኩል የሥራ ዕድል ያገኙ ዜጎች ቀድሞ የከተማ ግብርና ግንዛቤ አላቸው?

አቶ መሐመድ፡– ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት የሚወስዱት ሥልጠና አለ፡፡ ከዚህ በኋላ የሚሠሩት እያንዳንዱን እንቅስቃሴያቸውን የሚከታተሉ ባለሙያዎች ተመድቦ ነው፡፡ ኮሚሽኑ ባለው የሠርቶ ማሳያ እንዲያዩና በቀላሉ እንዲረዱ ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡– የዘር አቅርቦቱ ከየት ነው የሚገኘው?

አቶ መሐመድ፡– ኮሚሽኑ የራሱ ችግኝ የሚያባዛበት ቦታ አለው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኖችን በማባዛት ለኅብረተሰቡ የማድረስ ሥራ  ይሠራል፡፡ ከ3.5 ሚሊዮን ብር በላይ ዘር ተገዝቶ ባሉበት ወረዳ ላይ ዘር እንዲወስዱ እየተደረገ ነው፡፡ ከዘር አቅርቦት በተጨማሪ በኮሚሽኑ በተገዙ ሁለት የእርሻ ትራክተሮች አማካይነት ስፋፊ ቦታዎችን በቀላሉ በማረስ እያገዘ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡– የማዳበሪያ አቅርቦትስ ምን ይመስላል?

አቶ መሐመድ፡– በአጠቃላይ 2,684 ኩንታል ማዳበሪያ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ለዚህ አገልግሎት እንዲውል ተደርጓል፡፡ 2,584 ኩንታል ዩሪያ ማዳበሪያ ግዢዎች ፈጽመን ለተጠቃሚዎች ድጋፍ አድርገናል፡፡ ይህ ኮሚሽኑ በራሱ የሚያደርገው ነው፡፡ በዚህ ብቻ ሳይሆን 10,000 የፍራፍሬ ችግኞችና 215 የውኃ መሳቢያ ፓምፖችን አርሶ አደሮች እንዲጠቀሙ ተደርጓል፡፡ አዲስ አበባ ዳርቻ ላይ ላሉ አርሶ አደሮች የጤፍና የስንዴ ዘር በመስጠት ምርታማ እንዲሆኑ እያገዝን እንገኛለን፡፡ መደረግ ያለበት የተለያዩ የሕንፃ ግንባታዎች ሲሠሩ የከተማ ግብርናን በሚያሳትፍ መንገድ ቢሆን ብለን እንመክራለን፡፡ ይህ አካባቢውን ዓይነ ግቡና ማራኪ ከማድረጉ በበለጠ፣ የእለት ጉርስ ከደጅ ማግኘት የሚያስችል ዘዴ ይሆናል፡፡ የትኛውም ግንባታ ሲካሄድ ፍራፍሬዎችና አትክልቶች የሚተከሉበት ቦታ ቢኖራቸው የተሻለ ይሆናል፡፡ ከተፈጥሮ ተነጥሎ ለውጥ ሊመጣ ስለማይችል ግለሰቦች፣ ባለሀብቶችና ሁለም የኅብረተሰብ ክፍሎች በሚያደርጉት ግንባታዎች ይኼን ታሳቢ ያደረገ ሥራ ቢሠሩ የተሻለ ይሆናል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ሠራተኛ ስቀጥር ካለመሠልጠናቸውም በላይ ስንት ይከፈለኛል ብለው ሲጠይቁ እደነግጥ ነበር›› ወ/ሮ ቅድስት ጌታቸው፣ የሶጋ ትሬዲንግና ፖላር ፕላስ ኤክሰለንስ ሀብ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ

በኢትዮጵያ የሚገኙ ቀጣሪ ድርጅቶች የሚፈልጉት የሠለጠነ የሰው ኃይልና የሥራ ፈላጊው ብቃት በብዛት አይጣጣምም፡፡ በዚህም ቀጣሪዎች ብቁ የሰው ኃይል አለማግኘታቸውን፣ ሠራተኞችም የሚፈልጉትን የሥራ ዓይነት አጥተው...

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል›› አቶ ያዕቆብ ወልደ ሥላሴ፣ የሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ተቋሞችን መደገፍ የግድ እንደሚል ይታመናል፡፡ መንግሥት ሊያደርግ ከሚችለው ድጋፍ አንዱ ደግሞ የውጭ...

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...