በተስፋዬ ኃይለ ሚካኤል
በጣም ለምወድሽና ለማከብርሽ ውድ እናቴ ኢትዮጵያ የጻፍሽልኝን ደብዳቤ በሙሉ ልቦናዬ ትኩረት አንብቤዋለሁ፡፡ ደብዳቤሽ ካሁን በፊት ከምትልኪልኝ ደብዳቤዎች ሁሉ ለየት ያለ በመሆኑ ሳነበው አልደነገጥኩም ብልሽ እውነት አይሆንም፡፡ ጠንከር ያለ በመሆኑም ወዲያው ሳልመልስ ተቆጥቤያለሁ፡፡ አንቺ ሁልጊዜ የምትይውን መርህ ተከትዬ አስቤ መልስ የሚሆነውን ጥቂት ቀናት ወስጄ አውጥቼ አውርጄ ለመመለስ በቅቻለሁ፡፡
ውድ እናቴ ደብዳቤሽን ሳነብ የተሰማኝን በቃላት መግለጽ ብፈልግም፣ በአጭሩ መጥቀስ አስፈራኝና በተቻለኝ መጠን ቃላትን ለመውለድ ተገደድኩ። የግብፅ ዕብሪተኝነት እንደምታውቂው ዛሬ አልተጀመረም። ከአሁን በፊት በተለያዩ ጊዜያት የአንቺን ህልውና ለማጥፋት ከሌሎች ጋር በማበር፣ አንቺን ለመውረር መሞከራቸው አይረሳም። የጥንቱን ብንረሳው እንኳን በአፄ ዮሐንስ ላይ ከቱርኮች ጋር አብረው ያደረጉትን ልንረሳው አንችልም። ከዚያም በኋላ አገራችንን በአራት ማዕዘን ፀጥታዋን ለማተራመስ አውሮፓውያን ሲሞክሩ፣ ግብፅ ከእንግሊዝ ጋር በመሆን (Anglo-Egypt) የጦር ኃይል ፈጥረው ኢትዮጵያን ለመውረር ሞክረዋል። በጣም የሚገርመው ኢትዮጵያ ጣሊያንን በዓድዋ አሸንፋ የጣሊያንን ጦር ወደ መጣበት ቀይ ባህር ስትነዳው በነበረበት ጊዜ ነው፣ የአንግሎ ግብፅ ጦር በሱዳን በኩል ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት የሞከረው። ይሁንና የአንቺ ጀግኖች ልጆችች የአንግሎ ግብፅንና የኢጣሊያንን ጦር ድል ነስተዋል፡፡ ሆኖም የግብፅና የእንግሊዝ የጦር ሙከራ የአንቺን ልጆች ብዙ መስዋዕትነት እንዲከፉሉ አድርጓል።
ይህ ሁሉ ሲሆን አንቺ ሆደ ስፊ ስለሆንሽ በግብፆች ላይ ቂምና በቀል ይዘሽባቸው አታውቂም፡፡ እኔና ወንድሞቼ ለግብፅ የምናደርጋቸውን ቱርፋቶች እንድናቆም ጠይቀሽን አታውቂም፡፡ እኛም ብንሆን ያተኮርነው የሱዳንና የግብፅን ሕዝብ ኑሮ ለማሻሻል ሌት ከቀን በመሥራት ላይ ነው እንጂ የአገራችንን ኑሮ ለማሻሻል አይደለም፡፡ ሥራችንም በጣም ስኬታማ በመሆኑ እነሆ ዛሬ ግብፅ የምታመርተው ሰብል ይህ ነው ለማለት ባይቻልም ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል ሩዝ፣ ስንዴ፣ ቲማቲምና ድንች፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ አትክልቶችችን ነው፡፡ የግብፅ 90 ሚሊዮን ሕዝብ ዛሬ ተንደላቆ ሊኖር እንዲችል ውኃውን፣ አሸዋውን፣ አፈሩን እንዲሁም ድንጋዩንና ዛፉን ሳይቀር ከአንቺ ምድር ለሰባት ሺሕ ዓመታት እያጋዝን አገሪቱን ገንብተናል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ሀብት ከአንቺ ምድር መምጣቱን የግብፅ ሕዝብ ለሰከንድ እንኳን የአንቺን ውለታ የሚዘክረው አይመስለኝም፡፡ አንቺ እኔን የምታኮሪኝ ላደረግሽው ውለታ ምሥጋና ለማግኝት አለመፈለግሽ ነው።
ያለንን ማካፈል ግዴታ ስለሆነ ከሰው ምሥጋናን መጠበቅ አያስፈልግም የምትይው ትዝ ይለኛል፡፡ ከዚያም በላይ ለሱዳንና ለግብፅ ሕዝቦች የምታሳይው ከልብ የመነጨ ፍቅር የአንቺን ማንነት ይገልጻል።
ውድ እናቴ ሆይ በደብዳቤሽ እንደገለጽሽው እኔም ሆንኩ ወንድሞቼ ተከዜ፣ ዜጋወደም፣ ዠማ፣ ጣናና ባሮ ምንም እንኳን እስካሁን ድረስ ባደረግናቸው ቱርፋቶች ኩራት ቢሰማንም፣ አንዳንድ ጊዜ ለኢትዮጵያ ሕዝባችን ይኽ ነው የሚባል ስላላደረግን ይፀፅተናል፡፡ ነገር ግን ፈረንጅ ‹‹Never too Late›› እንደሚለው አሁንም አልመሸም፣ የአንቺን ደብዳቤ በደንብ እንድናነብ አድርጎናል፡፡ እኛ ለፍተን ይኸው ዛሬ ግብፅ የዓመቱ ከ300 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንድታገኝ አድርገናል፡፡ ለየዋህዋ ኢትዮጵያ ደግሞ በዓመት 100 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ሆኖ ሕዝቦቿ ከግብፅ ያነሰ ይኖራሉ፡፡ ከአሁን ወዲያ ግን የኢትዮጵያ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ቆርጠን ተነስተናል። በመገንባት ላይ ባለው የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ የእነ ግብፅ ተቃውሞ መሠረት የሌለው ከመሆኑም ሌላ፣ በሁለቱ አገሮች መካከል የቆየውን ግንኙነት የሚያሻክር ነው፡፡ እኔንም ሆነ ወንድሞቼን አስቆጥቶናል። ቆሽታችን እንዲቃጠል አድርጎናል። ለግብፅም ሆነ ለሱዳን የምናደርጋቸውን ቱርፋቶች ጥያቄ ውስጥ እንዲገቡም አድርጎታል፡፡ ኢትዮጵያውያን በተፈጥሮአችን ሰብዓዊነትን፣ ትክክለኛ ፍርድን፣ ቱርፋትን እንደ መመርያችን አድርገን የምንቀሳቀስ ከመሆናችን በላይ፣ በደል እንኳን በራሳችን ላይ ቀርቶ በማንም ላይ እንዲደረግ አንፈልግም፡፡ የግብፅ ድርጊት ተቀባይነት የለውም፡፡ የግብፅ አማካሪዎችም የሚነዙት ፕሮፓጋንዳ በእኛ በኩል ቦታ የለውም፡፡
ውድ እናቴ ሆይ አንቺን የነካ እኛን እንደ ነካ፣ አንቺን የበደለ እኛን እንዳጠቃ፣ የአንቺ ሕዝቦች ሲራቡ፣ ሲጠሙና ሲጠቁ ማየት እንደማንችል ግብፆችም ሆኑ የእነሱ ተቀጽላዎች ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ከአሁን በኋላ የእኛ አንደኛ ዓላማ ሕዝባችንን ከኩራዝና ከማገዶ ነፃ ማውጣት ብቻ ሳይሆን ሕዝባችንን በዓመት እንደ ግብፅ ሦስት ጊዜ መኸር እንዲሰበስብ ማድረግ ነው፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ሌት ከቀን ሠርተን በግብፅ ያደረግነውን ውጤታማ ሥራ በአገራችን ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ በግብፅ በረሃ ላይ የተንጣለለ እርሻ በሰው ሠራሽ ዝናብ ማድረግ ከቻልን ለም በሆነቺው ኢትዮጵያ ማድረግ አያቅተንም፡፡ በመስኖ ሥራ አዘምነን የወንድሞቼንም ሆነ የእኔን ውኃ ተጠቅመን አገራችንን በእርሻ አዘምነን ለባላንጣዎቻችን እህል እንሸጥላቸዋለን።
ውድ እናቴ ሆይ ምንም እንኳን የአንቺን ጥንካሬ የማይፈልጉ ብዙ አገሮች ቢኖሩም፣ ገሚሱ ጥፋት የአንቺው ልጆች መሆኑን መገንዘብና አስፈላጊውን ዕርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው፡፡ የውጭ ጠላት ምን ጊዜም የሚያተኩረው በውስጣችን ልዩነት ሲያይ ነው፡፡ ስለሆነም በልጆችሽ መካከል ክፍተት እንዳይኖር ዕርምጃ መውሰድ ይኖርብሻል ስል ከይቅርታ ጋር ነው፡፡ በአገራችን ውስጥ ላሉት አንዳንድ ችግሮችም ተጠያቂነትን መቀበል ይኖርብናል፡፡ መፍትሔውን የመፈለግ ግዴታ አለብን፡፡
ውድ እናቴ ደብዳቤዬ ምናልባት እንዳንቺ እንደ እናቴ ጥልቅነት ያለው ሁኔታዎችን ሰፋ አድርጎ የማየት ትዕግሥተኝነትን የማይመጥን ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም በቅድሚያ ይቅርታሽን እጠይቃለሁ፡፡ በመጨረሻ ቃል የምገባልሽ ዕትብቴ የተቀበረበት አገሬ ስትከፋ እኔም ሆንኩ ወንድሞቸ ቁጭ ብለን እንደማናይ ነው፡፡ ከዚያም ሌላ ያለንን ሁሉ የአንቺን ህልውና ለመጠበቂያ ለመዋል እንደማንመለስ መታወቅ ይኖርበታ፡፡ አንቺ እንዳስተማርሽን ሲያከብሩን ማክበር ለተጎዱ መርዳት ለፍትሕ መቆም በሰውነታችን ላይ ያለ መደራደር የማይነቃነቅ አቋም ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የሚከተለውን ለወንድሞቼና ለእህቶቸ እንድታደርሽልኝ በትህትና እጠይቃለሁ፡፡ ውድ አባቶች፣ እናቶች፣ ወንድሞችና እህቶች ምንም እንኳን በዓለም ላይ ያንዣበበው ጨለማ አስፈሪ ቢመስልም የወረርሽኝ በሽታ የእህቶቻችንን፣ የወንድሞቻችን፣ የአባቶቻችንንና እንዲሁም የእናቶቻችንን ሕይወት በየቀኑ ቢቀጥፍም፣ ጊዜያዊ ችግር በየቤቱ ቢኖርም፣ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው የግብፅን ዛቻ በየቀኑ ብንሰማም፣ የተደቀነው አደጋ ጊዜዊ እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የእያንዳንዳችን ቁርጠኝነት ኅብረተሰቡን ለመርዳት መጨመር ይኖርበታል፡፡
አንዳንድ የአኗኗር ዘይቤዎቻችንን መለወጥ ግዴታችን መሆን አለበት፡፡ እኔ ከማለታችን እኛ፣ አብሮ ከመብላት አልፈን አብረን መሥራትን፣ ጊዜያዊ የሆኑ ነገሮችን ከመመልከት አልፈን ዘላቂ የሆነውን የሕዝብን ሕይወት ሊቀይሩ የሚችሉ ፕሮጀክቶችን ማሰብ ለልጅ ልጆች ምን ጥዬ ብሄድ የእነሱን ሕይወት ይቀይራል? ከቀዬ አስተሳሰብ ወጥተን ወደ አገራዊ፣ ከዚያም አኅጉራዊ ዕሳቤ መሸጋገር ግዴታችን ነው። በአሁኑ ጊዜ የተጋረጡትን ችግሮች እንደ ማስጠንቀቂያ ወስደን የወደፊቷን ኢትዮጵያ ከመቼውም በበለጠ ለመገንባት ሌት ከቀን እንሥራ።
ድል የሁላችን ነው!
ዓባይ ኢትዮጵያ!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡