Wednesday, September 27, 2023

በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት የተደረሰው ስምምነትና አንድምታው

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የአፍሪካ ኅብረት ጠቅላላ ጉባዔ ልዩ ቢሮ ሐምሌ 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ፣ በግድቡ ባለቤት ኢትዮጵያና በታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች በሆኑት ግብፅና ሱዳን መካከል ያለውን አለመግባባት በቀጣይ ድርድር ለመፍታት የሚያስችል ውሳኔ ማሳለፉን፣ ሐምሌ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። 

ስብሰባው የተካሄደው የኅብረቱ ጠቅላላ ጉባዔ ልዩ ቢሮ አባል አገር መሪዎች ማለትም የወቅቱ የኅብረቱ ሊቀመንበር የሆነችው ደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ በሊቀመንበርነት፣ እንዲሁም የልዩ ቢሮው አባላት ኬንያ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ግብፅና ማሊ በመሪዎቻቸው ተሰይመው በቪዲዮ ኮንፈረንስ የተካሄደውን ውይይት እንደታደሙት ገልጿል።  

በዚሁ ውይይትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (/) እና የሱዳኑ አቻቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክም መሳተፋቸውን ገልጿል። በዚህ ስብሰባ ላይም የህዳሴ ግድቡ የውኃ ሙሌትና ዓመታዊ የግድቡ አስተዳደርን፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግሥት ወደፊት ከግድቡ በላይ ሊካሄድ የሚችለውን የዓባይ ውኃ ልማት በተመለከተ ጥልቅ ውይይት መካሄዱን፣ ይህንንም ተከትሎ በሦስቱ አገሮች መካከል የጋራ መግባባት ተደርሶ በቀጣይ ድርድር መፈታት ያለባቸው ነጥቦች ላይ በስምምነት ውሳኔ መተላለፉን መግለጫው ይጠቁማል። በስምምነት የተላለፈው ውሳኔም በህዳሴ ግድቡ የውኃ አሞላልና አስተዳደርን በተመለከተ የተጀመረውን ድርድር በመቀጠል በአስገዳጅ የሕግ ስምምነት እንዲቋጭአስገዳጅ የሕግ ስምምነቱም በጥቁር ዓባይ ወኃ ላይ ወደፊት የሚካሄዱ ልማቶችን ማካተት እንደሚገባው ስምምነት መደረሱን በመግለጫው አስታውቋል። መግለጫው አይይዞም እንደገለጸው የሦስቱ አገሮችን ልዩነት ለመፍታት አፍሪካ ኅብረት የጀመረውን ሚና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ድጋፍ አግኝቷል። 

በተጨማሪም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሦስቱ አገሮች ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ የድንበር ተሻጋሪ ወንዝ አስተዳደርንና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ፣ የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ጠቁሟል። 

በማከልም ኅብረቱ የሚመራውን ይህንን ድርድር ሊያስተጓጉል ወይም በውይይቱ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር የሚችል መግለጫ ከመስጠት ሦስቱ አገሮች እንዲቆጠቡም አሳስቧል። 

የአፍሪካ ኅብረት መግለጫ ከመውጣቱ በፊት በውይይቱ የተደረሰውን መግባባት አስመልክቶየጠቅላይ ሚኒስትር ሕፈት ቤት ያወጣው መግለጫ ይዘት ግን በአፍሪካ ኅብረት ከወጣው መግለጫ ጋር መሠረታዊ ልዩነት የያዘ ነው። 

‹‹በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት የተካሄደው ስብሰባ በሦስቱ አገሮች መካከል የጋራ መግባባት ተደርሶ ተጠናቋል። በዚህም ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የህዳሴ ግድቡ የውኃ ሙሌትን አስመልክቶ የሚያደርጉት የቴክኒክ ድርድር በአፍሪካ ኅብረት የአደራዳሪነት ሚና ሥር ሆኖ እንዲቀጥልና በቀጣይም ወደ ሁሉን አቀፍ ስምምነት እንዲሸጋገር ተስማምተዋል፤›› ይገልጻል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ የህዳሴ ግድቡንና የኢትዮጵያን የወደፊት የውኃ አጠቃቀምን በተመለከተ አስገደጅ የሕግ ስምምት እንዲደረስ ስለመወሰኑ የሚጠቁመው ነገር የለም። 

በዚህ የተነሳም በህዳሴ ግድቡ ድርድር ውስጥ የወደፊት ውኃ አጠቃቀምን የተመለከተ ነጥብ እንዳይገባ ኢትዮጵያ ላለፋት ዘጠኝ ዓመታት ስትከለከል ቆይታ፣ እንዴት አሁን ይህንን ልትቀበል ትችላለች የሚል ጥያቄ በርካታ ኢትዮጵያውያንን እያነጋገረ ይገኛል። 

የወደፊት የውኃ አጠቃቀም እንዴት ወደዚህ ድርድር መጣ?

በህዳሴ ግድቡ የውኃ ሙሌትና አስተዳደር በተመለከተው በሦስቱ አገሮች ድርድር እስካሁን ያልተፈታው ትልቁ የልዩነት ምንጭ፣ በድርቅና በተራዘመ ድርቅ ወቅት የግድቡ ሙሌትና የቀጣይ ዓመታት አስተዳደርን የተመለከተው ነጥብ ነው። 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሁሉም የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች ጉዳዩን ለማብራራት የላከውና ሪፖርተር ያገኘውን ሰነድ መሠረት በማድረግም፣ ይኼንን ነጥብ እንደሚከተለው ቀርቧል።  ከላይ የተገለጸውን የልዩነት ነጥብ ለመፍታት ሦስቱ አገሮች ላለፉት በርካታ ዓመታት ባደረጉት ድርድርድርቅና የተራዘመ ድርቅ ለሚሉት ቴክኒካዊ አገላለጾች ትርጓሜ በመስጠት ልዩነቶቻቸውን ለማጥበብ ሞክረዋል። 

በዚህም መሠረት በግድቡ የመጀመርያ ዙር ሙሌት ወቅት ወደ ግድቡ የሚመጣው ውኃ 31 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብና ከዚያ በታች ከሆነ የድርቅ አመላካች እንደሚሆንበቀጣይ ምዕራፍ ሙሌትና የረዥም ጊዜ የግድቡ አስተዳደር ወቅት ወደ ግድቡ የሚመጣው የውኃ መጠን 37 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብና ከዚያ በታች ከሆነ የድርቅ ወቅት አመላካች እንዲሆን በማለት ልዩነታቸውን አጥበው ተቀራርበዋል። 

ከላይ የተጠቀሰው የድርቅ አመላካቾች ሁኔታ ለተከታታይ ዓመታት ከቀጠለ ደግሞ የተራዘመ የድርቅ ወቅት እንዲባል ቅድመ መግባባት ደርሰዋል፡፡ ነገር ግን በተሟላ ስምምነት አልተቋጨም።

ከላይ በተገለጹት ገና ስምምነት ባልተደረሰባቸው ትርጓሜዎች መሠረትም፣ በድርቅ ወቅት ወደ ህዳሴ ግድቡ የሚመጣው የውኃ መጠን የድርቅ አመላካች አኃዝ ላይ ከደረሰ ወይም ከዚያ በታች ከሆነ፣ ኢትዮጵያ የሚመጣውን ውኃ ኃይል አመንጭታበት ወደ ታችኞቹ አገሮች እንዲፈስ ታደርጋለች እንጂ በግድቡ እንዲጠራቀም አታደርግም። 

ይህ ሁኔታ ለተከታታይ ዓመታት ከቀጠለ ደግሞ የተራዘመ የድርቅ ወቅት የሚለው ትርጓሜን የሚያሟላ ስለሚሆንበዚህ ኢትዮጵያ ወደ ግድቡ የመጣውን ውኃ ኃይል አመንጭታበት ወደ ታችኞቹ አገሮች ከማሳለፍ ግዴታ በተጨማሪ ይህ ሁኔታ ከመከሰቱ አስቀድሞ በግድቡ ከያዘችው የውኃ ክምችት ላይም የታችኞቹ አገሮች ድርቁን መቋቋም እንዲችሉ ስምምነት የሚደረስበትን የውኃ መጠን ለመልቀቅ ትገደዳለች። 

በዚህ ጉዳይ ላይ መሠረታዊ መግባባት ቢኖርም ከላይ በተገለጹት አመላካች ትርጓሜዎች የሚከሰቱበት መንስዔ ላይ እስካሁን ስምምነት ያልተደረሰ ከመሆኑ ባሻገር፣ ስምምነት ላይ የመድረስ ዕድሉም አስቸጋሪ ሆኗል።

ምክንያቱ ደግሞ ወደ ግድቡ የሚመጣው የውኃ መጠን የድርቅ ወይም የተራዘመ ድርቅ አመላካች ተብለው የተቀመጡት (አሁን ስምምነት ያልተደረሰባቸውን አኃዞችማለትም 31 እና 37 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ) የውኃ መጠኖች ሊከሰቱ የቻሉበት መንስዔ ነው።

ይህም ማለት የድርቅ ወቅት አመላካች የውኃ መጠን የተፈጠረው ተፈጥሯዊ በሆነ የዝናብ እጥረት ምክንያት ነው? ወይስ ኢትዮጵያ ከግድቡ በላይ በሚገኘው የዓባይ ተፋሰስ ላይ ተጨማሪ ልማቶችን በማካሄዷ? የሚለው መሠረታዊው የሦስቱ አገሮች የልዩነት ነጥብ ነው።  የወደፊት የውኃ አጠቃቀም ጉዳይ የሚከሰተውም እዚህ ላይ ነው። 

ኢትዮጵያ ወደ ግድቡ የሚመጣው የውኃ መጠን የድርቅ ወይም የድርቅ ወቅት አመላካች መጠን ወይም ከዚያ በታች የሆነው በተፈጥሯዊ የዝናብ እጥረት የተነሳ እንደሆነ ግዴታውን ለመቀበል እንደምትችልነገር ግን የተገለጸው ሁኔታ የተከሰተው ከግድቡ በላይ በሚገኘው የዓባይ ተፋሰስ ላይ ወደፊት በምታካሂደው ልማት ምክንያት ከሆነ ለግድቡ ሙሌት ተብለው በተቀመጡት አኃዞች እንደማትገደድ ገልጻለች። 

የዚህ ምክንያቱም በላይኛው የዓባይ ተፋሰስ ላይ ወደፊት በምታካሂደው ተጨማሪ ልማት ምክንያት የግድቡ ሙሌትን የሚያደናቀፍ፣ ወይም ኃይል የማመንጨት አቅሙ ላይ አሉታዊ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ ነው። 

በተጨማሪም ግድቡ የውኃ ሙሌት ወይም ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳይቀንስ ሲባል፣ በላይኛው የዓባይ ውኃ ላይ ወደፊት ልማት እንዳታካሂድ የሚያስር ስለሚሆን ነው። 

ይህ ደግሞ በዓባይ ውኃ ላይ ለዘመናት የቆየውን የግብፅን በብቸኝነት የመጠቀም ኢፍትሐዊ አካሄድ የሚያስቀጥልና የአሁኑንም ሆነ የመጪውን የኢትዮጵያ ትውልድ በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብት የሚያሳጣ ነው የሚል አቋም በመያዝ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ፈጽሞ ልትስማማ እንደማትችልና ዓለም አቀፍ ሕጎችንና መርህን በመከተል በታችኞቹ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መንገድ መብቷን ተግባራዊ እንደምታደርግ አስረግጣ አስታውቃለች። 

በአፍሪካ ኅብረት ላይ ተደረሰ የተባለው መግባባት አንድምታ 

በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ሦስቱ አገሮች ሰሞኑን ደረሱበት የተባለውን መግባባት በተመለከተ፣ በኢትዮጵያ በኩል ያለው ግንዛቤ ልዩነት ይስተዋልበታል።  ይህንንም የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (/) ድርድሩ የደረሰበትን ደረጃ አስመልክቶ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴው ሐምሌ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ካቀረቡት ሪፖርት መረዳት ይቻላል። እንደ ሚኒስትሩ ከሆነ በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት በተደረገው የሰሞኑ ድርድር የተደረሰው መግባባት፣ የወደፊት የውኃ አጠቃቀምን የተመለከተ አጀንዳ ከግድቡ ሙሌትና አስተዳደር ድርድር ተነጥሎ ለብቻው እንዲካሄድ የሚል ነው።

በቅድሚያ የህዳሴ ግድቡ አጠቃላይ የውኃ ሙሌት ደረጃዎችንና የግድቡ አስተዳደርን የተመለከተው ጉዳይ፣ በአጭር ጊዜ ስምምነት እንዲደረስ መግባባት መደረሱን ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

በቀጣይ ደግሞ የወደፊት ውኃ አጠቃቀምን ጨምሮ በዓባይ ውኃ ላይ ሁሉን አቀፍ አጠቃላይ ስምምነት እንዲደረግ መግባባት መደረሱን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የወደፊት የውኃ አጠቃቀምን በተመለከተ ሁሉን አቀፍ ስምምነት እንዲደረስ ለረጅም ዓመታት ስታራምደው የነበረ አቋም በመሆኑበኅብረቱ ድርድር አማካይነት ግብፅ አቋሟን ቀይራ ወደ ሁሉን አቀፍ ስምምነት ለመምጣት መግባባቷ ጠቃሚ መሆኑን አክለዋል። 

ሁለቱ ጉዳዮች ተነጣጥለው ድርድር የሚደረግባቸው መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩይህም ቢሆን የወደፊት የውኃ አጠቃቀምን የሚመለከተው ጉዳይ በጣም ፈታኝ ነጥብ እንደሚሆን ገልጸዋል። 

ግድቡን ለመሙላትና ለማስተዳደር የሚስማሙባቸው ደንቦችና መመርያዎች እንደ ሁኔታው በየጊዜው የሚሻሻሉ ሊሆን እንደሚገባ ኢትዮጵያ አቋም መያዟን የገለጹት ሚኒስትሩበአንድ ግድብ ላይ የሚደረግ ስምምነት በቀጣይ የዓባይ ውኃ አጠቃቀም ላይ እንደ ተሰጠ ብይን መወሰድ የለበትም የሚል የማያወላዳ አቋም በኢትዮጵያ በኩል መያዙን አስታውቀዋል። 

የወደፊት የውኃ አጠቃቀምን በተመለከተ ሉዓላዊ መብትንና ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ ዓለም አቀፍ መርህን መሠረት አድርጎ ሊታይ እንደሚገባውም፣ ኢትዮጵያ የምታራምደው ጠንካራ አቋም መሆኑን አመልክተዋል። 

ሱዳን የኢትዮጵያን የወደፊት የመጠቀም መብት የምታከብር ሲሆን፣ ‹‹በግብፅ በኩል ግን ኢትዮጵያ ወደፊት በዓባይ ውኃ ላይ የምታካሂዳቸውን ልማቶች በጋራ መወሰን አለብን የሚል አቋም ይዘዋል፤›› ብለዋል። 

የወደፊት የዓባይን ውኃ የመጠቀም ጉዳይ በማንም መልካም ፈቃድ የሚወሰን ሳይሆን በኢትዮጵያ የመጠቀም መብት ላይ የሚመሠረት እንደሆነ የጠቆሙት ሚኒስትሩበዚህ ማዕቀፍ መሠረት በሚደረግ ድርድር ላይ ቅራኔዎች ከተፈጠሩ ሁሉን አቀፍ ወደ ሆነ የውኃ ክፍፍል ድርድር እንደሚገባ አስታውቀዋል። 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -