Thursday, December 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የንብ ባንክ ትርፍ ወደ 1.4 ቢሊዮን ብር አሻቀበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ከ20 ዓመታት በላይ የዘለቀው ንብ ባንክ፣ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከታክስና ከሌሎች ተቀናሽ ወጪዎች በፊት 1.4 ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ፡፡ የትርፍ ዕድገቱ የ37 በመቶ ጭማሪ ተመዝግቦበታል፡፡

ባንኩ የ2012 ዓ.ም. አፈጻጸሙን ይፋ ባደረገበት መግለጫው እንዳስቀመጠው፣ በሒሳብ ዓመቱ ያስመዘገበው የትርፍ መጠን፣ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ትርፍ ካስዘመገቡ ባንኮች ተርታ እንዲሠለፍ አስችሎታል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ ተቋቁሞ ሒሳብ ዓመቱን ያጠቀናቀቀው ንብ ባንክ፣ ካለፈው ዓመት ከ378.3 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ የተመዘገበበት ትርፍ ማስመዝገቡን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ገነነ ሩጋ አመልክተዋል፡፡

ባንኩ ካስመዘገበው ትርፍ ባሻገር በሌሎች እንቅስቃሴዎቹም ላይ ውጤታማ ዓመት ያሳለፈበት እንደሆነ ያስታወቁት ፕሬዚዳንቱ፣ በተለይም ጠቅላላ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ወደ 33.2 ቢሊዮን ብር ከፍ ማድረግ መቻሉ አንደኛው ውጤታማነቱ ነው፡፡ ይህ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ባለፈው ዓመት ከነበረው 27.6 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ21.5 በመቶ ዕድገት እንዳሳየ ጠቅሰዋል፡፡

የባንኩ አጠቃላይ ሀብት መጠን 42 ቢሊዮን ብር መድረሱን የባንኩ መግለጫ አመላክቷል፡፡ ባለፈው ዓመት ከነበረው 33.5 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ25.1 በመቶ ብልጫ አስመዝግቧል፡፡ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ከ2.6 ቢሊዮን ብር ወደ 3.4 ቢሊዮን ብር ሲያድግ፣ አጠቃላይ ካፒታልና መጠባበቂያውም ከ4.4 ቢሊዮን ብር ወደ 5.8 ቢሊዮን ብር ከፍ በማለቱ፣ በዘርፉ በዋናነት ቀዳሚነት ከሚጠቀሱት የግል ባንኮች አንዱ የመሆን ዕቅዱን ለማሳካት የሚችልበትን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እየሠራ ለመሆኑ ማሳያ እንደሆነ ባንኩ ይገልጻል፡፡         

ንብ ባንክ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተደራሽነቱን በማስፋትና የቅርንጫፎቹን ብዛት ከ300 በላይ ሲያደርስ፣ የደንበኞቹን ቁጥርም ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ማድረስ እንደቻለ አስታውቋል፡፡ የፋይናንስ እጥረት ያጋጠማቸውን ድርጅቶች ችግራቸውን በመቅረፍ በአገሪቱ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ላይ የሚናውን በመጫወት ለዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ እንደሚገኝ የሚገልጸው ንብ ባንክ፣ በአገሪቱ የባንክ መስክ የተለያዩ የቁጠባ ዘዴዎችን በማስተዋወቅ በርካታ ደንበኞችን በማፍራት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሷል፡፡

በዓመቱ በርካታ ችግሮች ቢስተናገዱም፣ ንብ ባንክ ግን በተለያዩ መለኪያዎች ውጤታማ ስለመሆኑ የሚያመለክተው የባንኩ መረጃ፣ ወደፊትም በተሻለ አትራፊነት ለመንቀሳቀስ እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

 የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በአገር ደረጃና በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በኩል ለሚደረገው ጥረት እንዲያግዝ ከ5.1 ሚሊዮን ብር በላይ የለገሰ ሲሆን፣ ለባንኩ ተበዳሪዎችና ሌሎች ደንበኞች የወለድ ምጣኔን፣ እንዲሁም የተለያዩ ክፍያዎችን በመቀነስና አንዳንዶቹንም በመሰረዝ ከእነዚህ በአጠቃላይ ሊያገኝ ይችል የነበረውን ከ113 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ በመተውና ይህንንም አገራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ረገድ አጋርነቱን ስለማሳየቱም አመልክቷል፡፡

አካላዊ መቀራረብ እንዳይኖር ደንበኞች በባንኩ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች በኤቲኤም፣ ፖስ፣ ሞባይልና ኢንተርኔት ባንኪንግ እንዲጠቀሙ የተመቻቸ ሲሆን፣ ይህንንም ለማበረታታት የኤቲኤም የአገልግሎት ክፍያ ነፃ እንዲሆን ከማድረጉም ባሻገር በዚሁ ቴክኖሎጂ በመጠቀም እስከ 10,000 ብር ማውጣት፣ እንዲሁም በሞባይል ስልክ እስከ 30,000 ብር፣ በኢንተርኔት አማካይነት ለመደበኛ ደንበኞች የ100,000 ብር እንዲሁም ለኮርፖሬት ደንበኞች እስከ 500,000 ብር ማስተላለፍ እንዲችሉ ስለመደረጉ ጠቅሷል፡፡

በሌሎች ማኅበራዊ ኃላፊነቶችን ከመወጣት አንፃር ለሸገር ማስዋቢያ ፕሮጀክት  አሥር ሚሊዮን ብር፣ ለአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የትምህርት መሣሪያ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን በዚሁ መግለጫው ላይ አስታውሷል፡፡

ባንኩ ‹‹ይሠሯል ከልብ፣ እንደ ንብ›› የሚለውን መሪ ቃል ያነገበ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን አዘጋጅቶ በትግበራ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በዚህም የኮር ባንኪንግ ሥርዓቱን እጅግ ዘመናዊ በሆነው የT24 Version 2020 ቴክኖሎጂ፣ Tier 3 Data Center እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችንም በመጠቀም ለደንበኞች የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅቴን አጠናቅቄያለሁ ብሏል፡፡

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ አዲስ አበባ ውስጥ እያስገነባ ስላለው 4B+G+M+32 የሆነው የዋናው መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ አመልክቷል፡፡ ለአራት ኪሎ አካባቢ ውበት ያጎናፀፈው ባለ 2B+G+7 የሆነው የአራት ኪሎ ሕንፃውን በማጠናቀቅና በዚሁ ሕንፃ ላይ የፕሪሚየም ቅርንጫፉን በመክፈት ደንበኞቹን በላቀ ደረጃና ክብር እያገለገልኩ ነው ብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች