Thursday, September 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ከስድስት ሚሊዮን በላይ ደንበኞች በማፍራት 1.5 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገቡን አስታወቀ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የግል ባንኮች በአትራፊነትና በሌሎች አፈጻጸሞች ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገባቸውን እያስታወቁ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ባንኮች በሦስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ  የገለጸው የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ፣ የ1.5 ቢሊዮን ብር ትርፍ ከማስመዝገቡም ባሻገር የደንበኞቹን ብዛት 6.2 ሚሊዮን በማድረስ ከግል ባንኮች ከፍተኛው ቀጥር እንዳስመዘገበ አስታውቋል፡፡

  ባንኩ የ2011 ሒሳብ ዓመት አጠቃላይ አፈጻጸሙን በማስመልከት ሰኞ ሐምሌ 19 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት እንዳመለከተው፣ በተጠናቀቀው ሒሳብ ዓመት የእርጅናና ሌሎች ወጪዎች ተቀንሰው ከታክስ በፊት 1.5 ቢሊዮን ብር አትርፏል፡፡

  የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ደርቤ አስፋው እንዳመለከቱት፣ ባንካቸው በ2012 ሒሳብ ዓመት ያገኘው ትርፍ፣ በዚሁ ዓመት የግል ባንኮች ካስመዘገቡት ትርፍ አኳያ በሦስተኛ ደረጃ የሚስቀምጠው ነው፡፡

  ባንኩ ለውጤታማነቱ ምክንያቶች ካደረጋቸው አንዱ፣ ዓመታዊ ጠቅላላ ገቢውን በ57 በመቶ ማሳደጉ ነው፡፡ በ2012 ዓ.ም. 5.74 ቢሊዮን ብር ገቢ አሰባስቧል፡፡ ይህ የገቢ መጠን ዓምና ከተመዘገበው በ2.1 ቢሊዮን ብር ወይም በ57 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው፡፡ ከዚህ ገቢ ውስጥ 80 በመቶው ከወለድ የተገኘ ገቢ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡ ባለፈው ዓመትም ባገኘው ትርፍ መጠን ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ እንደነበር አቶ ደርቤ አስታውሰው፣ በ2012 ዓ.ም. ግን የትርፍ መጠኑ በዕጥፍ ማደጉን ገልጸዋል፡፡  

  በ2012 ሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ያገኘው የትርፍ መጠን ከ2011 ዓ.ም. ካገኘው አንፃር በ102 በመቶ ጭማሪ የታየበትና በባንኩ ታሪክም ለመጀመርያው ከፍተኛ ውጤት ነው፡፡ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፍ የቻለበት የ2012 ሒሳብ ዓመት ለባንኩ ከፍተኛው መጠን ከመሆኑም ባሻገር፣ ከግል ባንኮች አኳያም በሦስተኛ ደረጃ የሚጠቀስ ትርፋማ ባንክ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

  ባንኩ በሌሎች አፈጻጸሞችም ቢሆን በ2012 የሒሳብ ዓመት ስኬታማ መሆን መቻሉን በዝርዝር ያመለከቱት ፕሬዚዳንቱ፣ ውጤታማ ሆነንበታል ብለው ከጠቀሱዋቸው አፈጻሞቻቸው መካከል አንዱ የባንክ አስቀማጮችን ቁጥር 6.2 ሚሊዮን ማድረስ መቻሉ ነው፡፡ ይህ የአስቀማጮች ቁጥር ከሌሎች የግል ባንኮች አንፃር ሲታይ በብዙ ርቀት ብልጫ በማሳየት በ2012 የሒሳብ ዓመትም የአስቀማጭ ደንበኞቹን ቁጥር 6.2 ሚሊዮን በማድረስ በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ስለመቻሉም አመልክተዋል፡፡ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በአንድ ዓመት ብቻ አንድ ሚሊዮን ደንበኞች መጨመራቸውን የገለጹት አቶ ደርቤ፣ ለሒሳብ ዓመቱ አጋማሽ ጀምሮ ኮሮና ተከስቶ እንደ ልብ ባለመንቀሳቀሳችን እንጂ ከዚህም በላይ እንደርስ ነበር ይላሉ፡፡ የዘንድሮው የአስቀማጭ ደንበኞቹ ቁጥር ዕድገት 20 በመቶ ነው፡፡

  ከአስቀማጭ ደንበኞቹ ቁጥር ዕድገት ጋር ተያይዞ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን 45.5 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በ2012 የሒሳብ ዓመት ብቻ 9.34 ቢሊዮን ብር አዲስ የተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ችሏል፡፡ ይህ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ የ26 በመቶ ዕድገት ያለው ሲሆን፣ በሒሳብ ዓመቱ ለመሰብሰብ ከታቀደው 12 በመቶ ከዕቅድ በላይ አፈጻጸም የታየበት ስለመሆኑ ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል፡፡

  በኢንዱስትሪው ፈታኝ ከሚባሉት ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ግኝት መሆኑን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ባንካቸው በሒሳብ ዓመቱ 363.4 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል፡፡ ይህም ከዓምናው ጋር ሲነፃፀር የ17 በመቶ ዕድገት አለው፡፡

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት 18.6 ቢሊዮን ብር ብድር ሰጥቷል፡፡ የሰጠውን ብድር ከማሰባሰብ አንፃርም በሒሳብ ዓመቱ ከ12.25 ቢሊዮን በላይ ማሰባሰብ መቻሉ ተገልጿል፡፡ ይህም 31 በመቶ አፈጻጸም የታየበት እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

  የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ በ2011 የሒሳብ ዓመት 41.79 ቢሊዮን ብር የነበረውን አጠቃላይ ሀብት የ11.13 ቢሊዮን ብር ጭማሪ በማሳየት፣ በ2012 የሒሳብ ዓመት 52.92 ቢሊዮን ብር አድርሷል፡፡

  በዓመቱ 31 አዳዲስ ቅርንጫፎችን የከፈተ ሲሆን፣ ከነዚህም 13ቱ ሙሉ በሙሉ በሸሪዓ ሕግጋት ላይ የተመሠረተ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡ የቅርንጫፎቹን ብዛት 420 አድርሷል፡፡ በዘንድሮ ዓመትም ተጨማሪ ከ3.73 ቢሊዮን ብር በላይ በብድር መልክ የሰጠ ሲሆን፣ አጠቃላይ የብድር መጠኑ 34.21 ቢሊዮን ብር አድርሷል፡፡ የተበላሸ ብድር መጠኑንም ስለመቀነሱ የሚያመለክተው የባንኩ መረጃ፣ በ2011 ዓ.ም. ከነበረው 2.8 በመቶ በ2011 የሒሳብ ዓመት ወደ 2.3 በመቶ ዝቅ ማድረግ ስለመቻሉ ተጠቅሷል፡፡

  እጅግ ፈታኝና ውስብስብ ውድድር የሚበዛበት የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ስኬታማ ዓመታትን መጓዝ ቀላል ያለመሆኑን እንደ ኢትዮጵያ ያለ አብዛኛው የማኅበረሰቡ ክፍል የባንክ አገልግሎት ጥቅምና የቁጠባ ምንነት በውል ያልተረዳውን የፋይናንስ ዕውቀቱን በማጎልበት ብሎም ግዛቤን በማስጨበጥ ሀብትን በማሰባሰብ መልሶ ለልማት እንዲውል መንገድ መሆን ይበልጡኑ አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ ብዙ የቤት ሥራዎች ቢኖሩም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሻሻሎች እየታዩ ይገኛሉ፡፡

  የኀብረት ሥራ ባንክም ሆነ ሌሎች ባንኮች በ2012 ሒሳብ ዓመት ጥሩ የሚባል አፈጻጸም እያሳዩ መሆኑን እየገለጹ ቢሆንም፣ አሁን እያገኙ ያለው ትርፍ ከታማሚ ብድሮች ላይ ታሳቢ በማድረግ ላይ ነው የሚለው አተያይ በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ድርቤ ይህ ትክክል አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ከባንካቸው አንፃር ከታማሚ ከሚባሉ ብድሮች ብድር ትርፍ ሳይሰላ የተገኘ ትርፍ ነው፡፡

  የባንኮች ትርፍ መለኪያ የሚሆነው የባንኮች ዋና ገቢ ከብድር ወለድ ገቢ የሚገኝ ነው፡፡ ብድሮቹ ጤናማ ካልሆኑ የታሰበው ወለድ በሙሉ እንደገቢ አይወሰድም፡፡ ያሉት ፕሬዚዳንቱ አጠቃላይ ብድር ጤናማ ለመሆን የአገሪቷ የማክሮ ኢኮኖሚ የፖለቲካ ድባቡ ይወሰናል ያሉ አቶ ደርቤ፣ ባሳለፍነው ዓመትም አጋጥሞ የነበረው የገንዘብ እጥረትና ኮቪድ-19 ፈተና ቢሆንም ውጤታማ መሆን ተችሏል ይላሉ፡፡

  ከታማሚ ብድር ላይ ትርፍ ያለመሰላቱን ለማመላከትም ባንካቸው የዘንድሮ ትርፉን ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ በታማሚ ብድር ምክንያት ወደ ትርፍ ያልመጣው የወለድ ገቢ እንዳለ ገልጸው፣ ታማሚ የሆነ ብድር ላይ ትርፍ አድርጎ መምጣት በብሔራዊ ባንክ ሕግም የማይቻል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆነው የታማሚ ብድሮች ወለድ ቢካተት ኖሮ ግን የባንኩ ትርፍ ከዚህም በላይ  ይሆን ነበር ተብሏል፡፡

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የታየው የገንዘብ እጥረትና ከኮቪድ-19 በቀጣይ ዓመታት የሚታይ ይሆናል የሚሉ አስተያየቶችን ተንተርሶ፣ ባንኮች በቀጣይ ዓመታት ልክ እንደ አሁኑ ሊያተርፉ አይችሉም የሚል አመለካከትን በተመለከተ አቶ ደርቤ ለቀረባቸው ጥያቄ፣ የተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ሁለት ትልልቅ ፈተናዎች ነበሩበት ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ባንኮቹ የገንዘብ እጥረትና የኮሮና ተግዳሮቶች ፈትኗቸው ነበር ይላሉ፡፡

  ወደፊት ኢኮኖሚው እየተፈተነ ከሄደ በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ ያለው ጫና እየከፋ የሚሄድ ከሆነ የባንኮች ትርፍ በዚሁ ላይቀጥል ይችላል በሚለው ሐሳብ ላይ የሚስማሙት አቶ ደርቤ፣ ይህ ግን እንደ ባንኮቹ ሊለያይ እንደሚችልም አመልክተዋል፡፡

  ባንኮች ኢንቨስት ያደረጉበት የቢዝነስ ዘርፍ ይለያያል፡፡ የባንካቸው የብድር አሰጣጥ በአብዛኛው አርሶ አደርና ደሃ ተኮር ስለሆነ አንዳንድ ብድሮች ቢበላሹም ያን ያህል ፈተና ላይሆን ይችላል ይላሉ፡፡

  ትልልቆቹ ኢንቨስትመንቶች ላይ ግን ችግሮቹን በቅርብ በማየትና በመፍታት ብድራቸው ጤናማ እንዲሆን ማድረግ ይገባናል፡፡ ነገር ግን እንደተባለው በኢኮኖሚው ላይ ፈታኝ ነገር ከተፈጠረ የባንክ ኢንዱስትሪው ሊፈተን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

  በተጨማሪም ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት በኮሮና ምክንያት ሊጎዱ ይችላሉ ተብለው የታሰቡትን በመለየት፣ ባንኩ እስከ አምስት በመቶ የሚደርስ የብድር ወለድ ቅነሳ አድርጓል፡፡

  በተለይ በአጠቃላይ ከኮሮና ጋር በተገናኘ ከላይ ከተዘረዘሩትና በሌሎች ተጨማሪ ድጋፎች ከ310 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋጽኦ ስለማድረጉም ተገልጿል፡፡ በ112.5 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታልና 300 ሚሊዮን ብር በተፈቀደ ካፒታል የዛሬ 15 ዓመት የተቋቋመው የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ፣ በአሁኑ ወቅት የተከፈለ ካፒታሉን በ46 በመቶ በማሳደግ ሦስት ቢሊዮን ብር አድርሷል፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች