በበላይ ወልደየስ (ፕሮፌሰር)
በመጀመርያ እኔ የልማት መሐንዲስ እንጂ የታሪክ ምሁር ስላይደለሁ በዚህ ጽሑፍ ላይ የቀረቡት አንዳንድ ታሪኮች ካነበብኳቸውና ካጠናኋቸው ስለሆነ፣ የታሪክ ግድፈትም ሆነ ትርጉም ቢገኝበት የታሪክ ምሁሩ የሚለው ተቀባይነት እንዳለው ለአንባቢያን እየገለጽሁ፣ ስለፈጠርኩት የታሪክ ስህተት በቅድሚያ ምሁራንን ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡
የናይል ወንዝ በዓለም ረዥሙ ወንዝ (6,700 ኪሎ ሜትር) ሲሆን፣ በአሥር አፍሪካ አገሮች ማለትም ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ኮንጎ፣ ታንዛኒያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳንና ግብፅን አቋርጦ ሜዲትራኒያን ባህር ይገባል፡፡ ዋነኛው ለናይል ወንዝ የውኃ ምንጩ የሆኑት በአትዮጵያ የሚገኙት ዓባይ፣ ተከዜ፣ ባሮና አኮቦ ወዘተ. ሲሆኑ እነዚህ ተደምረው 86 በመቶን የናይል ወንዝ ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ የናይል ወንዝ ለግብፅ ከፈጣሪ ለብቻዋ የተሰጣት ሥጦታ ነው የሚለው የግብፃውያን የፈጠራ ተረት ከፍተኛ ድርሻ በዓባይ ወንዟ የምትሰጠውን ኢትዮጵያ ፍዳ ሲያሳያት ኖሯል፡፡ ይኼም የመጣው ከግብፅ አመሠራረት ነው፡፡
የግብፅ ታሪክን ስናይ ግብፅ በአፍሪካ የምትገኝ አገር ብትሆንም አፍሪካውያን የነበሩት ተወላጅ ግብፃውያን (Native Egyptian) ከክርስቶስ ልደት በፊት እስከ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን ሲሆን፣ ከዚያ ወዲህ በግሪክና በሮማ (ቅድመ ክርስቶስ 332 – 641 ዓ.ም.)፤ በዓረብ (641 – 1516 D) በቱርክ ግዛት ሥር (1517 – 1867) በመገዛት እስከ ዘመናዊ ግብፅ የተሸጋገረች ሲሆን፣ ከቱርክ የመጡት ራሳቸውን ንጉሥ በማድረግና የእንግሊዝ የበላይነትን በመቀበል (1882 – 1952) ግብፅን በንግሥና ሲመሩ ሱዳንንም ጨምረው ገዝተዋል፡፡ የእንግሊዝም የበላይነት የቆየው ከ1882 እስከ 1953 ሲሆን፣ የተነሳውም በናስር የሚመሩ ወጣት መኮንኖች ንጉሡን አባረው ሪፐብሊክ ከመሠረቱ በኋላ ነው፡፡
እንግዲህ እነዚህ ግብፅን በቅኝ ግዛትነት ከክርስቶስ ልደት ጀምሮ የሚያስተዳድሯት አውሮፓውያን ግብፅ ካለ ናይል ለመኖር ስለማትችል የዓባይ ወንዝ መነሻን አንድ ላይ ጨምረን እንገዛለን በማለት ኢትዮጵያን ሲያስቸግሩ የኖሩ ሲሆን፣ የጥንት አባቶቻችን ግን የአገርን ሉዓላዊነት ባለማስደፈር ዓባይ ከኢትዮጵያ ምድር ተቆርሳ ወደ ግብፅ እንዳትሄድ ነቅተው ሲጠባበቁ ኖረዋል፡፡ ባለፉት ሁለት መቶ ዓመታት የዓባይ መነሻ የሆነውን የኢትዮጵያን ግዛት ቆርሶ ለመውሰድ ከፍተኛ ጥረት የተደረገ ሲሆን፣ ከነዚህም የሚጠቀሰው ከቱርክ የመጡ ቱርካውያን በግብፅ አፈንግጠው የንጉሥ ሥርዓት ከመሠረቱ በኋላ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ሁለት ጊዜ በአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት ጦርነት ገጥመው የተሸነፉበትን መጥቀስ ይቻላል፡፡
በኋላም እንግሊዝ በበላይነት ግብፅን በምታስዳድርበት ጊዜ በእንግሊዝ ውስጥ እያደገ የመጣውን የጥጥ ፍላጎት ለማርካት በዓባይ ወንዝ ላይ ዘመናዊ እርሻ በማደራጀት ጥጥና ፍራፍሬ አመርትበታለሁ ብላ የታችኛው ተፋሰስ አገሮችን እነ ታንዛንያን፣ ኬንያን፣ ኡጋንዳንና የላይኛው ተፋሰስ አገሮችን ግብፅንና ሱዳንን በቅኝ ግዛትነት ስትይዝ የዓባይ ወንዝ መነሻ የሆነችውን ኢትዮጵያንም ጨምሮ ለመያዝ ያልቆፈረቸው ጉድጓድ የለም፡፡ የእንግሊዝን ተንኮል የተረዱት የኢትዮጵያ ነገሥታት ሴራውን እየተከታተሉ የአገሪቷን ልዑላዊነት ሳያስደፍሩ ኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያን በጦርም ሆነ በሌላ ለመያዝ እንደማይችሉ የተረዱት እንግሊዞች በመጨረሻ ነገሥታቱን የይስሙላ ውኃ ክፍፍል እናድርግ እያሉ መጎትጎቱን ተያያዙት፡፡ ከአፄ ምኒልክ ጋርም ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ እንደማታቆም እንፈራረም ብለው ሲያስቸግሩ እ.ኤ.አ. 1902 ‹‹ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ አትደፍንም›› የሚለውን ውል ተፈራረሙ፡፡ እንደ ውጫሌው ውል እንግሊዞች በራሳቸው ቋንቋ ሲተረጉሙ ሌላ ቢያደርጉትም፣ ኢትዮጵያ የምትቀበለው በራሷ ቋንቋ በአማርኛ የተጻፈውን ነው ብላ አሰጥ አገባ አልገባም ብላ ጉዳዩን ዘጋቸው፡፡ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጋራ በተለያየ ጊዜ በዓባይ ወንዝ ላይ እንግሊዞች ውል እንሰር ቢሉም ተቀባይነት አላገኙም፡፡
ከጣሊያን ወረራ በኋላ እንግሊዝና ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በድል አድራጊነት አዲስ አበባ ሲገቡ እንግሊዝ እንደገና ኢትዮጵያ በጦር ቀጣና ውስጥ ስለምትገኝ የምትተዳደረው በምሥራቅ አፍሪካ የእንግሊዝ ጦር ሥር ነው የሚል ሐሳብ ለእነ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በማቅረብ የዓባይን ውኃ ምንጭ የሆነችውን ኢትዮጵያ በቅኝ አገዘዝ ሥር በማድረግ ከሱዳንና ከግብፅ ጋራ ለማደባለቅ ሙከራ አደረጉ፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ከታወቁት የጦር አርበኛ ራስ አበበ አረጋይና ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ ጋራ በመሆን በከፍተኛ ደረጃ በመቃወም ይኼንንም ሴራ ለማክሸፍ የኢትዮጵያ መንግሥት ፊቱን ወደ አሜሪካ አዞረ፡፡ አሜሪካም በአፍሪካ ለመስፋፋት ኢትዮጵያ ወሳኝ መሆኗን ስላመነችበት ኢትዮጵያን ለመደገፍ በተለይ በዓባይ ወንዝ ላይ የኃይል ማመንጫም ሆነ የኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ንድፍ (Design) አቀረበች፡፡ ከነዚህም ንድፎች አንደኛው ዛሬ የህዳሴው ግድብ ቦታ ይገኝበታል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ለዚህ ፕሮጀከት ገንዘብ በማፈላለግ ላይ እያለ እንግሊዞች በኋላም ግብፆች ገንዘብ የሚያበድሩትን አካላት በመቃወም ፕሮጀክቶቹ ሳይሳካ ቀረ፡፡
ይኼ በዚህ እንዳለ እንግሊዝ የኢትዮጵያ ነገሥታት በአገራቸው ጥቅም ላይ የማይበገሩ መሆናቸውን ስለተረዱት በተለይ በግብፅ ያላትን የጥጥና የፍራፍሬ እርሻ የውኃ ችግር እንዳይጎዳው የናይል ውኃ ከፍተኛውን ድረሻ ለግብፅ በመስጠት ከ85 በመቶ በላይ ውኃ ለናይል የምትሰጠውን ኢትዮጵያን ሳታካትት ግብፅና ሱዳንን እ.ኤ.አ. በ1929 እኛ በ1959 በማፈራረም እንግሊዝ ሌላ ቦታ እንዳደረገችው በዚህም አካባቢ መርዝ ቀበረች፡፡ እንግዲህ ይሄንን ሰነድ በመያዝ ነው፡፡ ዛሬ ግብፅ በየአገሩ አቤቱታ በማቅረብ ቅኝ ያልተገዛቸውን ኢትዮጵያ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በአዙሪት የቅኝ ግዛት ውል እንድትቀበል ግፊት የምታደርገው፡፡ የኢትዮጵያ መልስ ግን ግልጽ ነው፡፡ ‹‹እኔን በማግለል የተፈረመ ስለሆነ፣ አሁን እንድቀበል ሕግ አያስገድደኝም›› ነው፡፡
ላለፉት 70 ዓመታት ግብፅ ነፃ አገር ሆኛለሁ ብላ ከዓባይ ወንዝ የሚገኘውን ውኃ ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ ነኝ የሚለውን የጀመረላት ንጉሣዊ አገዛዝ ገልብጦ የመጣው ገማል አብድር ናስር ባፀደቀው ሕገ መንግሥት ላይ የዓባይን ውኃ ጥቅም ፕሬዚዳንቱ ይጠብቃል የሚል ዓይነት አንቀጽ በማስገባቱ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የመጡት ፕሬዚዳንቶች ዋነኛው ተግባራቸው በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጠውን የዓባይን ውኃ ግብፅ በብቸኛ መጠቀሟን ማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባራቸው ማድረግ ሆነ፡፡ ለዚህም እንደ ስትራቴጂ የያዙት ‹‹ኢትዮጵያ በልማት ካደገች የግብፅን ብቸኛ የዓባይ ውኃ ተጠቃሚነት ታስቀራለች ሆኖ ለዚህም በውስጥና በውጭ ፖለቲካ ኢትዮጵያን የማዳከም ሥራ ዓብይ አድርገው ቀጠሉበት፡፡
ከእነዚህም የሴራ ፖለቲካ በመጀመርያ ያደረጉት በአካባቢው ኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ እንዲያርፍ ‹‹ቀይ ባህር የዓረብ ነው›› በሚል ኢትዮጵያ የባህር ወደብ በቀይ ባህር እንዳይኖራት ተገንጣዮችን ሙሉ በሙሉ ጦር (ራሷ ግብፅ፣ ሶሪያና ኢራቅ ወዘተ.) በማዋጣት የኋላ ኋላ ኤርትራን በማስገንጠል ካለ ወደብ አገሪቱን አስቀሩ፡፡ በተጨማሪም በጎረቤት ያሉትን የዓረብ አገሮችንም ግብፅ በማሰባሰብ ማኅበር እንዲያቋቅሙ በማድረግና የማኅበሩን አመራር የራሷ ዜጎች በማድረግ የግብፅን አቋም እንዲያራምዱ ከማስደረጋቸውም በላይ በአንዳንድ የዓረብ አገሮች በዋና አጀንዳነት ‹‹የዓባይ ውኃ ለግብፅ የተሰጠ ብቸኛ ሀብት ነው፡፡ ሌላ ያገባኛል የሚል ካለ ከግብፅ ጋር በመቆም የግብፅን መብት እናስከብራለን፡፡ ኢትዮጵያም ከእስራኤል በመቀጠል የዓረብ ጠላት አገር ናት፤›› ብለው እንዲሠለፉ አደረጉ፡፡
ግብፅ ባገኘችው ዓለም አቀፍ መድረክ ላይም በኢትዮጵያ ላይ ያላትን ጠላትነት ማስቀመጧን ሁሌም የቤት ሥራ አድርጋ ቀጥላበት ኖራለች፡፡ በምሳሌነትም ግብፅ፣ እስራኤልና ፍልስጤማውያን የካምፕዴቪድ ስምምነት በአሜሪካ ሲያደርጉ ለግብፅ በመደለያነት ከተቀመጡት አንቀፆች አንዱ ‹‹ግብፅ በዓባይ ላይ ያላትን መብት አሜሪካ ትጠብቅላታለች›› የሚል እንዳለበት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ይናገራሉ፡፡ ግብፅ ኢትዮጵያ ከለማች የእኔ የምትለውን ዓባይን ትጋራብኛለች ብላ በመፍራት ለልማት አበዳሪ ድርጅቶች እንደ የዓለም ባንክ፣ የገንዘብ ተቋማትና አገሮች ወዘተ. በኢትዮጵያ በማንኛውም ሥፍራ ውኃ ላይ በተመሠረተ ፕሮጀክቶች ላይ በገንዘብ እንዳይሳተፉ በከፍተኛ ሁኔታ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያላትን የአካባቢ ፖለቲካ ተፈላጊነት በመጠቀም ጫና ስታደርግ ኖራለች፡፡
ይኼንን ሁሉ ደባ የተረዱት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ መለሰ ዜናዊ ግብፅ ባላሰበችበት ሰዓት ታላቁን የህዳሴ ግድብ ‹‹በራሳችን ገንዘብ፣ እኛው መሐንዲስ በመሆን እንሠራዋለን›› ብለው ለግብፅና ለዓለም አወጁ፡፡ ዜናው ለግብፆች ዱብ ዕዳ ቢሆንም በመጀመርያ ‹‹ኢትዮጵያ አቅም ስለሌላት ራሷ አትሠራውም›› በማለት ቢያምኑም፣ በኋላ ኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ገቢ ያለው በሙሉ ገንዘብ በማዋጣት ሥራውን ሲያስቀጥል ሲያዩ ግብፆች ግድቡን ለማስቆም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ያልቆፈሩት ጉድጓድ አልነበረም፡፡ ከነዚህም ከሚጠቀሱ መካከል ለኤርትራና በኤርትራ አማካይነት ለኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ኃይሎች የገንዘብና የጦር መሣሪያ በማቅረብ በኢትዮጵያ ሰላምን ማጥፋት፣ ውል ተዋውለው ግድቡን የሚሠሩትን የውጭ አገር ተቋራጮች በዓለም አቀፍ እንዲወገዙና ውሉን እንዲያቋርጡ ማድረግ፣ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ሰላም እንዳይኖር ሴራ መጎንጎን፣ አሜሪካና ምዕራባውያን መንግሥታትን ከጎኗ ለማሠለፍ ጥረት ማድረግ ወዘተ. ይገኙበታል፡፡
በዚሁ ጥረታቸው ላይ እያሉ በኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት ለውጥ መጣ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው ለውጥ ከኤርትራ ጋራ ሰላም መፍጠሩ ተቃዋሚ ኃይሎች በሙሉ ወደ አገር ቤት እንዲገቡ መፈቀዱና ግድቡንም በመፈተሽ ያለውን ችግር በመበጣጠስ ወደ መስመር ማስገባቱ ሥራው በዕቅድ እንዲጓዝ መደረጉ ወዘተ. ተስፋ ስላሳጣቸው ግብፆች ፊታቸውን ወደ ዓለም አቀፍ በማዞር ጫና ማድረግን ቀጠሉበት፡፡ በየአገሩ በመዘዋወር ‹‹ኢትዮጵያ የዓባይን ውኃ በመገደብ ወደ እኔ የሚመጣውን በከፍተኛ ሁኔታ ልትቀንስብኝ ነው፡፡ ይኼም ከሆነ የግብፅ ሕዝብ በረሃብ ያልቃል፡፡ ሕዝቡ ሲርበው ወደ አክራሪነት በመቀየር የአውሮፓና አሜሪካ ከተሞች በአክራሪዎች ይመታሉ፡፡ ይኼ ጉዳይ ለዓለም ደኅንነት ሥጋት ነው፡፡ ግድቡ መሞላት ያለበት በረዥም ጊዜ ነው ወዘተ›› የሚል የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት አገሮች እንዲደግፏቸው ተማፀኑ፡፡
ዓለም በሙሉ የተቀበለውን የእስራኤልና የፍልስጤም የሁለት መንግሥት መፍትሔ በመሰረዝ የትራምፕ አስተዳደር እስራኤል ለምትፈልገው የአንድ መንግሥት መፍትሔ ዕውቅና ስትሰጥ፣ ግብፅም የኢትዮጵያን ጉዳይ በአሜሪካ ዕርዳታ መፍትሔ አገኛለሁ ብላ በማሰብ ፍልስጤማውያንና ዓረቦችን ክዳ ከአሜሪካ ጋራ በመደራደር ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ያላትን ‹‹የዓባይ ወንዝ የእኔ ብቻ ነው›› ጥያቄ በድጋሚ አሜሪካ እንደምትደግፋት አረጋገጠችላት፡፡ ግብፅም የአሜሪካን ድጋፍ አግኝቻለሁ በማለት ‹‹ጌታውን የተማመነ በግ ላቱን ከቤት ውጪ ያሳድራል›› እንደሚባለው ግብፅ የጭቃ ጅራፏን ፈታቸው፡፡ በሚያሳፍር ሁኔታ የግድቡ የመጀመርያው የውኃ ሙሌት እንዳይካሄድ በኢትዮጵያ ላይ ሁለገብ የሐሰት ዘመቻ ከፈተች፡፡ ሁለት ጊዜ የዓረብ ማኅበር የውኃ ሙሌቱ እንዳይካሄድ የግብፅን አቋም ደግፎ መግለጪያ አወጣ፡፡ አሜሪካም ስምምነት ሳይደረግ የመጀመርያው የውኃ ሙሌቱ እንዳይካሄድ መግለጫ አወጣ፡፡ ግብፅም በነዚህ ድጋፎች በመነሳት የዓለምን መንግሥታት በሚሲዮኗ አማካይነት ለማደናገር ጣረች፡፡ ዘመኑ ያመጣውን የመገኛኛ ድረ ገጽ በመጠቀም ለኢትዮጵያዊ ጆሮ የሚቀፍ የሐሰት ወሬ ‹‹ኢትዮጵያ የግብፅን ሕዝብ በውኃ ጥም ልትጨርስ ነው፡፡ እሷ ብዙ ተፋሰሶችና የዝናብ ውኃ አላት፡፡ እኛ ኑሯችንን የመሠረትነው በዓባይ ላይ ነው፡፡ ዓባይ ከሌለ ግብፅ የለም፡፡ ኢትዮጵያ ለአካባቢው ሰላም ጠንቅ ናት፡፡ ኢትዮጵያን በጦርነት አንበርክከን የምንፈልገውን እናሳካለን ወዘተ›› የሚል በዓለም ሁሉ አስተጋባች፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብም ከወጣት እስከ አዛውንቱ በመንግሥቱ በመሰባሰብ ‹‹የመጀመርያውን የውኃ ሙሌት በተቀመጠለት የጊዜ ተመን እንሞላለን፡፡ ሉዓላዊነታችንን አስደፍረን የማንንም ፈቃድ አንሻም፤›› በማለት የኢትዮጵያዊነት ወኔ ያሳየው፡፡ በዚህን ጊዜ ነው እንግዲህ ግብፅ በቀቢፀ ተስፋ የምትይዘውን በማጣት አንዴ በማስፈራራት፣ በሌላው በኩል ለተባበሩት መንግሥታት፣ ለፀጥታው ምክር ቤትና ለአውሮፓ መንግሥታት ወዘተ ‹‹የመጀመርያውን የውኃ ሙሌት ሳንስማማ እንዳታደርግ ኢትዮጵያን አስቁሙልኝ›› በማለት የይድረሱልኝ ጥሪ ያደረገችው፡፡ መንግሥትም በሚያኮራ ሁኔታ በአቋሙ በመጽናት ‹‹ድርድሩ በሦስቱ አገሮች ብቻ መሆን አለበት፡፡ በሦስተኛ ወገን በኩል መወያየት ካለብን በአፍሪካ ኅብረት በኩል ነው እንጂ በሌላ ሊሆን አይችልም፤›› የሚለውን ታሪካዊ አቋም አስታወቀ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩም ጉዳዩን ለወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር የግብፅን አስቸጋሪነት በማስረዳት ጉዳዩ በአፍሪካ ኅብረት በኩል እንዲታይ ፍላጎት እንዳላቸው አስታወቁ፡፡ ግብፅ ከእነአሜሪካ በኩል ድጋፍ አገኛለሁ በማለት የአፍሪካ ጉዳይ በአፍሪካውያን መታየት የለበትም በማለት በአሜሪካ በኩል ለፀጥታው ምክር ቤት አቀረበች፡፡ የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ለፀጥታው ምክር ቤት ‹‹ጉዳዩ የአፍሪካ ስለሆነ መታየት ያለበት በአፍሪካ ኅብረት ነው፤›› በማለት አስታወቁ፡፡ በፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ ልዑክ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ንግግር በተመሳሳይ ተቋም በጄኔቭ ያደረጉትን በመጥቀስ ምክር ቤቱ የዛኔ እንዳደረገው፣ ዛሬም በኢትዮጵያ ላይ ጉዳዩን አየዋለሁ ብሎ ተመሳሳይ ስህተት እንዳይሠራ ጉዳዩ ወደ ባለቤቱ ወደ አፍሪካ ኅብረት ይመለስ በማለት ኢፍትሐዊ የሆነውን የምክር ቤቱ አሠራር በመቃወም ታሪካዊ ንግግር አደረጉ፡፡ ምክር ቤቱም ውሳኔ ላይ ሳይደረስ በመበተን ጉዳዩ ወደ አፍሪካ ኅብረት ሄደ፡፡ እዚያ ውይይቱ እየተካሄደ ሳለ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ‹‹የመጀመርያው የውኃ ሙሌት የሆነው 4.9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በግድቡ ውስጥ መሞላቱን አበሰሩ፡፡
ይኼ ዜና ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ደስታ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ከዓድዋ ድል ጋራ ያቀራርቡታል፡፡ ባይቀራረብም ለእኛ ዘመን ትልቅ ታሪክ ነው፡፡ ግብፆች አሁን የምንሠራው የኃይል ማመንጫ በዘላቂነት ምንም ጉዳት እንደማያመጣባቸው፣ እንዲያውም የተመጣጠነ ውኃ እንደሚያገኙ ያውቁታል፡፡ እነሱ በተሳሳተ ሁለት አቅጣጫ በማየት ነው የሚቃወሙት፡፡ አንደኛው ‹‹ዓባይ የግብፅ ሥጦታ ስለሆነ ኢትዮጵያ ሌላ ስላላት አትንካ፤›› ሁለተኛው ‹‹ኢትዮጵያ እያደገች ከመጣች በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን የዓባይ ገባር ወንዞችን ጭምር በማልማት የውኃውን ቁጥጥር ኢትዮጵያ በመውሰድ እኔ እንደፈለግሁ በብቸኝነት ውኃውን ለመጠቀም አያስችለኝም፤›› የሚሉ ናቸው፡፡
ግብፆች እነዚህን ጥያቄዎች በልባቸው ይዘው የሚፈልጉትን በተዘዋዋሪ መልስ ለማግኘት የዓለምን ሕዝብ አወናበዱት፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትንና ሕዝብ እነሱን በሚደግፉ አገሮች ጫና እንዲበዛበት አደረጉ፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ በአክራሪ ብሔርተኞች በምትታመስበት ጊዜ ተጨማሪ አጀንዳ በመሆን ሕዝቡን አስጨነቁት፡፡ በዚህም መንግሥት የውጭ መንግሥታት በሚያደርጉበት ግፊት የፖለቲካ ጫናውን ለማርገብ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ ይሰጥ ይሆን የሚለው ጭንቀት ባለፉት 20 ቀናት በሕዝቡ ውስጥ ነበር፡፡ መንግሥት ግን ጫናውን ተቋቁሞ የኢትዮጵያን ጥቅም ሳይሰጥ ተወጣው፡፡ ለዚህም የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግሥት ምሥጋና ይገባዋል፡፡ ደስታው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በአዝማሪ እንዳዘፈነው ‹‹እልል! እልል! አርሶ አደሩ! ገበሬው! ዳያስፖራው! እንኳን ደስ አላችሁ! እልል! እልል!›› ብሎ በቀረ የመደብ ክፍል የሚገለጥ ሳይሆን፣ አንድ የሃይማኖት አባት ሊቀ ጳጳስ፣ ‹‹ለዓባይ ግድብ በማህፀን ውስጥ ካለ ሕፃን፣ ከሞተ ሰው በስተቀር፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ይደግፋል፤›› ብለው እንደገለጹት በዚህ ግድብ ላይ ሁሉም ዜጋ ገንዘቡን ከፍሏል፣ በዕውቀቱ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ስለዚህ እኔ የምለው ‹‹የኢትዮጵያ ልጆች እንኳን ደስ አለን! እልል! እልል!›› ነው፡፡
ደስታችን ጅማሮ ነው እንጂ መጨረሻው አይደለም፡፡ ግብፅ የኢትዮጵያ ጠላት ስለሆነች አትተወንም፡፡ ገና ብዙ እልህ አስጨራሽ ድርድር ይጠብቀናል፡፡ ሁልጊዜ እነሱ የሚያመጡትን ሐሳብ ከመቀበላችን በፊት ኢትዮጵያን እንደማይጎዳ በደንብ አድርገን ማወቅ አለብን፡፡ ከግብፅና ከሱዳን ጋራ በቴክኒክ ከሚደራደሩት አንዳንዶች ኢትዮጵያውያን ጋራ በአንድ መሥሪያ ቤት አብረን እንሠራለን፡፡ ለብዙ ዓመት በዚሁ ድርድር ጉዳይ አብረን እናወራለን፡፡ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ብዙ ጊዜ ለተደራዳሪዎች የምናሳስባቸው ‹‹ምናልባት የፖለቲካ ጫና በዝቶባችሁ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ውል ተዋውላችሁ በታሪክ ተወቃሽ እንዳትሆኑ፡፡ ከአቅማችሁ በላይ ከሆነ ውይይቱን አቋርጣችሁ ውጡ ነበር የምንለው፤›› በዚህ አጋጣሚ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ በቴክኒክም በፖለቲካም ድርድር የነበረባቸውን ጫና ተቋቁመው የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፈው ባለመስጠታቸው ምሥጋናዬን አቀርባለሁ፡፡
ኢትዮጵያ እያራመደቸው ያለችው ክርክር ለአገሪቱም ሆነ ለላይኛው አገሮች ዘርፈ ብዙ ጥቅም ይሰጣል፡፡ ለዘመናት ኢትዮጵያ የተፈጥሮ መብቷን በግብፅ የተነጠቀችውን ለአንዴም ለመጨረሻ ጊዜ ያስቀርላታል፡፡ ዓባይንና ሌሎች በአገሪቱ ያሉ ወንዞችን ዓለም በድንበር ተሸጋሪ ወንዞች ያወጣውን ደንብ በመከተል ፍትሐዊ የውኃ ሀብቷን ለልማቷ ለመጠቀም ያስችላታል፡፡ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ማለትም ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ኮንጎ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳንና ኤርትራ ከግብፅና ከኬንያ ማስፈራራት ወጥተው ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍል ያገኛሉ፡፡ አካባቢው የሰላም አየር ይተነፍሳል፡፡ ሁሉም አገሮች ተባብረው ለልማትና ለደኅንነት እንዲሠሩ መንገድ ይከፍትላቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ይኼንን ትልቅ ግድብ በመሥራቷ ችግሯ በሙሉ ይቀረፋል ማለት ሳይሆን፣ ግድቡ መሠራቱ በከፊል የኤሌክትሪክ ፍላጎቷን የሚያረካ ብቻ ሳይሆን የአገሪቷን ክብር ጥንትም እንደነበረው ዛሬም መቀጠሉን የሚያረጋግጥ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በከፍተኛ ሁኔታ ከአሁኑ ጀምሮ መሥራት ያለብን ግድቡ በመሠራቱ ይዞ የሚመጣውን የሶሺዮ አኮኖሚ ልማት መጠቀም ላይ ነው፡፡ ለግድቡ ተብሎ በተፈጠረው ባህር ዙሪያ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አውታሮች፣ የመስኖ እርሻ፣ የሸንኮራ፣ የጎማ ዛፍና የዘንባባ ዛፍ ልማት፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የዓሳ ሀብት፣ የቱሪስት፣ የውኃ ትራንስፖርት ወዘተ. በማስፋፋት አሁን ያለብንን ሚሊዮኖችን የወጣት ሥራ ፈት ተጠቃሚ በማድረግ ለድህነት ቅነሳ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ልናደርግበት እንችላለን፡፡
እዚያ ለመድረስ ግን ብዙ ፈተናዎች ከግብፅና ከምዕራባውያን አገሮች በተለይ ከአሜሪካ ይጠብቀናል፡፡ በመጀመርያው ሙሌት እንኳ እስከ መስከረም ሊሄድ ይችላል የተባለው የእግዚአብሔር ውኃ መጥቶ የሞላውን አሜሪካ ከመቀበል ‹‹እኔ ውኃ እንዳትሞሉ ብዬ የተናገርኩትን ኢትዮጵያ ባለመቀበሏ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ላደርግ እችላለሁ፤›› ያለችው በማስረጃነት የሚጠቀስ ነው፡፡
ግብፅ የምታቀርበው መደራደሪያ በየጊዜው ይቀያራሉ፡፡ ከምታነሳቸውም አንዳንዶቹ ‹‹ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን፣ ግብፅን በማይጎዳ ሁኔታ በረዥም ዓመታት ትሙላ፣ የውኃው መጠን በድርቅ ጊዜ የሚደርስበትን እንወስንና የሚጎለውን ኢትዮጵያ ከህዳሴው ግድብ ማካካሻ ትስጥ በአጠቃላይ ግድቡ አልቆ ሥራ ሲጀምር የእኔ መሐንዲሶች እዚያው ሆነው ይቆጣጠሩ፣ ኢትዮጵያ የዝናብ ውኃ ስላላት ኢትዮጵያ ላይ የሚኖረውን የውኃ ሀብት መጠን መዝነን ሳንከፋፈል ከዚህ በኋላ በዓባይ ላይም ሆነ በገባሮቹ በውኃ ላይ የምትሠራውን ሥራ ከእኔ ጋራ ሳትስማማ መሥራት የለባትም ወዘተ›› የሚሉት ይገኙበታል፡፡ ከኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች እንደሚሰማው ግብፅ አስቸጋሪ ተደራዳሪ ስለሆነች ጥያቄዎቿ እነዚህ ብቻ ላይሆኑ ስለሚችሉ በየጊዜው ምን እንደምታመጣ ለመገመት አስቸጋሪ ነው፡፡
ይሄ በዚህ እንዳለ ኢትዮጵያ የግብፅን አስቸጋሪነት ተረድታ በትዕግሥት እስካሁን ድረስ እንደ ሄደቸው ካለመታከት በድርድሩ ላይ መሳተፍ አለባት፡፡ ግብፅ ባለፉት ዓመታት ነገሩን እያከረረች ‹‹ኢትዮጵያ ለመደራደር ፈቃደኛ አይደለችም›› በማለት በየቦታው ለመክሰስ ብትሞክርም ኢትዮጵያ ግን ሁሌም ለመደራደር ዝግጁ ነኝ እያለች ግንባታውን እንዳላቋረጠች አሁንም በዚያው መንፈስ መቀጠል አለባት፡፡ በድርድሩ ላይም የአፍሪካን ኅብረት ተሳትፎ እንዲጠናከር መወትወት አለባት፡፡ የፖለቲካ ዘመቻውን በተለይ በአፍሪካ ኅብረትና በላኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ የበለጠ ማስተባበር ይጠበቅበታል፡፡ አዲሱ የሱዳን መንግሥትንም በሚመለከት ያለበትን ችግር ማለትም በውስጥ የመከላከያው ሠራዊት ከጥንት ቅኝ ገዥው ከግብፅ ጋራ ያለውን ግንኙነት በውጭ ፖለቲካው አሜሪካ በአልበሽር ጊዜ የጣለውን የኢኮኖሚ ዕቀባ እንዲያነሳለት የሚያሳየውን ፍላጎት ተረድቶ በጥንቃቄ ግንኙነታችንን ሕዝብ ለሕዝብ ማጠናከር አለብን፡፡ አሜሪካ በተለይ የትራምፕ መንግሥትን መጠንቀቅ አለብን፡፡ ትራምፕ ለእስራኤል የማይሆነው የለም፡፡ የእስራኤልን አጀንዳ ለማስፈጸም የግብፅ አጋርነትን ይፈልጋል፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያን እንደ ኢራንና ሰሜን ኮሪያ በዓለም ፊት ጥግ እንዳያስይዘን ከፍተኛ የፖለቲካ ሥራ መሠራት አለበት፡፡
በአጠቃላይ ድርድሩ አስቸጋሪ ቢሆንም አሁን ኢትዮጵያ ከፍተኛ ዕውቀት ያላቸው ልጆች ስላሏት የዓባይ ሁለንተናዊ ጥቅምና ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ መሆኑን በማጤን የታችኛው አገሮች እንዴት ሊጠቀሙ እንደሚችሉ የዓለምን ተሞክሮ በመውሰድ የኢትዮጵያን ጥቅም አሟጦ ለመጠቀም ነቅቶ መደራደር ነው፡፡
በመጨረሻም አባቶቻችን ለዘመናት ዓባይ የሉዓላዊነት ክብር አድርገው ነቅተው በመጠበቅ እንዳቆዩልን በአሁኑ ዘመን ያለን መላው ኢትዮጵያውያን ተባብረን የሉዓላዊነት መገለጫ የሆነውን ዓባይን በልማት በመቀየር ብቻ ሳይሆን፣ የዶላር ምንጫችን በመሆን ዘፈናችንን ‹‹ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል›› የሚለውን የዓባይ ሰማያዊው ውኃ በዶላር ይጓዛል በሚል ቀይረን አገራችንን ከድህነት በማውጣት ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ቀበቷችንን ሸብ አድርገን ከግብፅና ከእነ አሜሪካ ጋራ መደራደራችንን ሥራችንን እየሠራን እንቀጥላለን፡፡አገራችን ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
ከአዘጋጁ፡– ጸሐፊው በላይ ወልደየስ (ዶ/ር፣ኢንጂነር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡