‹‹ኢትዮጵያ በዓለም ከምትታወቅባቸው በጎ ጉዳዮች መካከል ትልቁን ቦታ የሚይዙት ረዥም ዕድሜ ያስቆጠሩት የሕዝቦች ባህልና የእነዚህ ባህል ውጤቶች የሆኑት ቅርሶች ናቸው፡፡ በዘመናት ውስጥ የተለያዩ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን አልፈው ለዛሬ ትውልድ የደረሱትን እነዚህ ቅርሶች ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በሚደረገው ዘርፈ ብዙ ጥረት ውስጥ ጉልህ ድርሻ ካላቸው ባለሙያዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
‹‹የኢትዮጵያን ቅርሶች ለመጠበቅና ለመንከባከብ ብሎም ለአገራችን ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅም እንዲውሉ ለማስቻል መንግሥት በመደበኛነት ከሚመድበው በጀት ባሻገር ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ፕሮጀክቶችን በማዘጋጀት የገንዘብና የሙያ ድጋፎችን በማሰባሰብ ከፍተኛ ሥራዎችን የሠሩ ከፍተኛ ባለሙያም ነበሩ፡፡”
ይህ ዓይነት ምስክርነት የተሰጣቸው ሁነኛ ባለሙያ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክተሩ አቶ ኃይሉ ዘለቀ ናቸው፡፡ ትናንት ነበሩ፡፡ ዛሬ ግን ከአፀደ ሥጋ ተለይተዋል፡፡ ዜና ዕረፍታቸውን ተከትሎ ይህን ህያው ምስክርነት የሰጡት ደግሞ የቀድሞው የባለሥልጣኑ የአርኪዮሎጂ ባለሙያና በዩኔስኮም የሠሩት አቶ ካሳሁን አባተ ናቸው፡፡
አቶ ኃይሉ በተለይም በኢትዮጵያ ባሉና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ባገኙ ቅርሶች ላይ የሚከናወኑ የጥበቃና እንክብካቤ ፕሮጀክቶችን በበላይነት በመምራትና በማስፈፀም ከፍተኛ ምስጋናን ያገኙ ትጉህ ሰው እንደነበሩ ከመሥርያ ቤታቸው የተገኘው ገጸ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
ከዓለም አቀፉ የባህል ተቋም ዩኔስኮ ጋር በመተባበር ቅርሶች ለመጠበቅና ለመንከባከብ በተደረጉ ጥረቶች ውስጥ የአቶ ኃይሉ ድርሻ ፕሮጀክቶችን በማዘጋጀት፣ በመተግበርና ውጤታማነታቸውን በማረጋገጥ ረገድ የፈጸሙት ተግባር ተጠቃሽ ያደርጋቸዋል፡፡ ከፕሮጀክታዊ ሥራዎቻቸው መካከል `Lalibela: Bete Gebrael- Rufael Church Conservation and Consolidation Project` አንዱ ነው፡፡ በአኅጉራዊው ተቋም ‘አፍሪካን ወርልድ ሄሪቴጅ ፈንድ‘ የነበራቸው ተሳትፎም ይበልታን የተጎናፀፈ ነው።
በኢትዮጵያ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ዙርያ በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች በተዘጋጁ መድረኮች በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎችን ከማቅረብ ባለፈ፣ በታዋቂው የፈረንሳይ ኢትዮጵያ ጥናት ማዕከል ጆርናል ‘Annales D’Ethiopie’ ከታተሙት ሥራዎቻቸው መካከል ‘Some Notes on the Great Walls of Wolayta and Dawro’ ይገኝበታል።
አቶ ኃይሉ ለአዲስ አበባ ቅርሶች በተለይም ለግብረ ሕንፃዎች ከሚቆረቆሩት፣ በ“ልማት ስም” ነባርና ታሪካዊ ሕንፃዎች እንዳይፈርሱ ለመታደግ በቁርጠኝነት ከተንቀሳቀሱት አንዱ ነበሩ። እየተከናወኑ የሚገኙት የልማት ሥራዎች በታሪካዊው ቅርስ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያስከትሉ “የቅርስ ተፅዕኖ ግምገማ” በማከናወን የልማት ሥራዎቹ ከቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ጋር ተጣጥመው መተግበራቸውን ማረጋገጥ ይገባል ሲሉም በየጊዜው ድምፃቸውን ከማስተጋባት ቸል እንዳላሉ የሚያውቋቸው ሁሉ የሚያንፀባርቁት ሐሳብ ነው፡፡
ከእናታቸው ከወ/ሮ ከበቡሽ ተሾመና ከአባታቸው ከአቶ ዘለቀ ወልደፃድቅ በ1970 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ፣ ሰባ ደረጃ በሚባለው አካባቢ የተወለዱት አቶ ኃይሉ፣ የመጀመርያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን በደጃዝማች በላይ ዘለቀና በእንጦጦ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት ካጠናቀቁ በኋላ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በአርኪዮሎጂ ትምህርት ዘርፍ በ1991 ዓ.ም. የመጀመርያ ዲግሪን፣ በመቀጠልም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በ1997 ዓ.ም. ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡
የቅድመ ምረቃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንን በመቀላቀል በአርኪዎሎጂ ዘርፍ በሙያቸው አገልግለዋል፡፡ በተለይ ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ በባለሥልጣኑ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመሆን ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
አቶ ኃይሉ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ42 ዓመታቸው ሐምሌ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. አርፈው፣ በማግስቱ ሥርዓተ ቀብራቸው ቃሊቲ በሚገኘው ሳሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡ አቶ ኃይሉ ባለትዳርና የሁለት ልጆች (ሴት እና ወንድ) አባት ነበሩ፡፡
ዘንድሮ አዲስ አበባን በተለያዩ ፕሮጀክቶች የማስዋብ ተግባርን የተመለከቱት አቶ ኃይሉ፣ በተለይ ከአራት ኪሎ ሚያዝያ 27 አደባባይ ወደ ፒያሳ በሚወስደው ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንገድ እስከ ደጎል አደባባይና አራዳ ታሪካዊና ጥንታዊ ግብረ ሕንፃዎች ያሉበት አካባቢ ለተሽከርካሪዎች ዝግ እንደሚደረግ የከተማው አስተዳደር ይፋ ማድረጉን ተከትሎ በማኅበራዊ ገጻቸው “ታላቅ ምስጋና” በማለት ያስተላለፉት መልዕክት፣ ቅርስ ለርሳቸው ነፍስና ሥጋ መሆኑን ያመላከቱበት ነው።
“ከአዲስ አበባ የፖለቲካ ማዕከል አራት ኪሎ ወደ ታሪካዊው የኢኮኖሚ ማዕከል አራዳ የሚወስደው ታሪካዊ ጎዳና ለተሽከርካሪ ዝግ ተደርጎ ለእግረኞችና ሌሎች ባህላዊ ተሽከርካሪዎች ብቻ ክፍት እንደሚደረግ መወሰኑ ከቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ አንጻር ትርጉሙ ታላቅ ነው። ከንቲባውንና አስተዳደሩን የሚያስመሰግን ተግባር ነው።
“ይሄ ለጥንታዊው የከተማ ክፍል ክብር መስጠት ነው፣ ዕውቅና መስጠት ነው። መንገዱን ተከትለው ለሚገኙት ቅርሶች ዘላቂ ጥበቃና ልማት ፋይዳው ከፍተኛ ነው። የአዲስ አበባን ቅርሶች ለመጠበቅና ለማልማት የተወሰደ ታላቅ እርምጃና ቁርጠኝነት ነው ማለት ይቻላል። ከሌሎች ታሪካዊ የዓለም ከተሞች ተርታ መዲናችንን የሚያስቀምጥ ዕርምጃ ነው። ለክልል ከተሞቻችንም ተሞክሮ የሚሆን ተግባር ነው።
“ከሰባ ደረጃ ወደ አፍንጮ በር በሚወስደው– “አርመን ሰፈር” ተብሎ በሚታወቀው ሰፈር አካባቢ ተወልዶ እንዳደገ አዲስ አበባዊ ትርጉሙ የትዬለሌ ነው። የወጣትነት ራዕይ እውን ሆኖ ማየት እንደማለት ነው?
የአቶ ኃይሉ ዘለቀን ዜና ዕረፍት ተከትሎ፣ ወርልድ ሄሪቴጅ ፈንድ በቲዊተር ገጹ ለቤተሰባቸውና ለእናት መሥሪያ ቤታቸው ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ባስተላለፈው የሐዘን መግለጫ፣ አቶ ኃይሉ ለዓለም አቀፍ የአፍሪካ ቅርሶች ፈንድ ተልዕኮ ስኬት ዓይነተኛ ተግባር መፈጸማቸውን አስታውሷል። መላው የቅርስ ቤተሰብ ሁነኛውን ሰው አጥቷልም ብሏል።