Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበትግራይ ክልል ምርጫ ተካሂዶ ሕወሓት ሥልጣኑን ለሌላ ፓርቲ ካስረከበ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ...

በትግራይ ክልል ምርጫ ተካሂዶ ሕወሓት ሥልጣኑን ለሌላ ፓርቲ ካስረከበ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታወቁ

ቀን:

በትግራይ ክልል ይካሄዳል የተባለው ምርጫ ተካሂዶ በአሁኑ ወቅት ሥልጣን ላይ የሚገኘው የክልሉ ገዥ ፓርቲ ሕወሓት ሥልጣኑን ለሌላ ፓርቲ ካስረከበ፣ የፌዴራል መንግሥት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ጣልቃ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስታወቁ። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ፣ ሐምሌ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጽሕፈት ቤታቸው በተወያዩበት ወቅት ነው። በተደረገው ውይይት ተሳታፊ ከነበሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ፣ የትግራይ ክልልን የሚመራው መንግሥት ‹‹ምርጫ አካሂዳለሁ በማለት ሕገ መንግሥቱ ለፌዴራል መንግሥት የሰጠውን ሥልጣን እየጣሰ ነው፣ መንግሥት ለምን ዕርምጃ አይወስድም?›› የሚለው ይገኝበታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹በትግራይ ክልል ተቀምጠው የክልሉን ሕዝብ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ለማጋጨት የሚሠሩ አካላት ቢኖሩም፣ መንግሥት ከክልሉ ሕዝብ ጋር ግጭት የመፍጠር ፍላጎት የለውም፤›› ብለዋል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ክልሉን እያስተዳደረ የሚገኘው ሕወሓት አደርጋለሁ በሚለው ምርጫ ሥልጣኑን ማራዘም እንጂ ሌላ ፍላጎት የለውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ክልሉን እንዲመራ የተቋቋመው መንግሥት እስከ ቀጣዩ ምርጫ ድረስ በሥልጣን እንዲቆይ አስቀድሞ የወሰነ በመሆኑ፣ በትግራይ ይካሄዳል የሚባለው ምርጫ ትርጉም እንደማይኖረው ተናግረዋል። 

ነገር ግን ‹‹ክልሉ አደርገዋለሁ በሚለው ምርጫ አማካይነት ከሕወሓት ውጪ ሌላ ፓርቲ ወደ ሥልጣን ቢመጣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን የሚጥስ በመሆኑ ተቀባይነት አይኖረውም፣ ወዳልተፈለገ ግጭትም ያመራል፤›› ብለዋል።

ይህ ሁኔታ ከተፈጠረ ግን ሥልጣን ላይ የሚገኘው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚወስነው መሠረት፣ የፌዴራል መንግሥት ሕግ እንደሚያስከብር አስታውቀዋል። 

ከላይ የተገለጸው ዓይነት የፖለቲካ ውዝግብ ቢከሰት የፌዴራል መንግሥት በክልል ጣልቃ ሊገባ የሚችለበትን የሕግ አግባብ አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕገ መንግሥት ምሁራን፣ የፌዴራል ሥርዓት በሚከተሉ አገሮች እንዲህ ዓይነት ግጭቶች የተለመዱ በመሆናቸው፣ አገሮቹ ግጭቶችን የሚፈቱበት የሕግ ሥርዓት እንደሚያወጡ አስረድተዋል። 

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም ይህንኑ ማዕቀፍ በአንቀጽ 62(9) ላይ በግልጽ እንደሚደነግግ፣ ድንጋጌውን መሠረት በማድረግም ‹‹የፌዴራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ የወጣ አዋጅ›› በማለት አዋጅ ቁጥር 359 በ1995 ዓ.ም. በፓርላማ ማፅደቁን ይገልጻሉ። 

በዚህ አዋጅ አንቀጽ 12 ድንጋጌ ላይ በአንድ የክልል መንግሥት ተሳትፎ ወይም ዕውቅና ሕገ መንግሥቱን ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ባለማክበር የሚደረግ ድርጊት፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል እንደሆነ ተቆጥሮ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ እንደሚወሰን መደንገጉን ባለሙያዎቹ ጠቁመዋል። 

የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ውሳኔ የሚሰጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደሆነ፣ ምክር ቤቱ ውሳኔውን ከማሳለፉ በፊት ግን ጉዳዩን መርምሮ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣሉት ምክንያቶች የሚፈቱበት ሰላማዊ መንገድ መሟጠጡን ማረጋገጥ እንዳለበት በአዋጁ መደንገጉን አስረድተዋል። 

የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሊወስን እንደሚችል በአዋጁ መደንገጉን የገለጹት ባለሙያዎች፣ እንደ ችግሩ ክብደትም አደጋውን ሊያስወግድ የሚችል የፌዴራል ፖሊስ ወይም የመከላከያ ሠራዊት፣ ወይም ሁለቱም በክልሉ እንዲሰማሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመወሰን ሥልጣን እንደሚኖረው በአዋጁ አንቀጽ 14(2) ሥር መደንገጉን አክለዋል። 

በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ሁለት (ለ) ሥር የፌዴሬሽን ምክር ቤት የችግሩን ክብደት በመመዘን፣ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብቶ የክልሉን ምክር ቤትና የክልሉን ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ አካል በማገድ፣ ለፌደራል መንግሥት ተጠሪ የሆነ ጊዜያዊ አስተዳደር ሊያቋቋም እንደሚችል መደንገጉን ባለሙያዎቹ ጠቁመዋል፡፡

በዚህ መሠረት የሚቋቋም ጊዜያዊ አስተዳደር ሕግ የማስከበር፣ ክልሉን የማረጋጋትና ምርጫ የማከናወን ኃላፊነት እንደሚኖረውና በኃላፊነት ላይ የሚቆየውም ከሁለት ዓመታት ላልበለጠ ጊዜ እንደሚሆን፣ ነገር ግን አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ከስድስት ወራት ላልበለጠ ጊዜ ሊራዘም እንደሚችል አስረድተዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ (ክፍል አንድ)

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...