Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉሕዝባዊ ለውጡን ለመታደግ ምን መደረግ አለበት? (ክፍል አምስት)

ሕዝባዊ ለውጡን ለመታደግ ምን መደረግ አለበት? (ክፍል አምስት)

ቀን:

ያዳ ኡመታ

በለውጥ ኃይሉ መንግሥትና በገዥው ፓርቲ ዙሪያ መነሳት ያለባቸው ጉዳዮች፣ የለውጥ ኃይሉ ስህተቶችና ሊያርማቸው የሚገቡ ተግባራት

በአገራችን እየተካሄደ ያለው ለውጥ አብዮት ሳይሆን ሪፎርም በመሆኑ፣ ወደ ፊት እየሄደ ወደ ኋላ የመመለስም ባህሪ ሊኖረው ስለሚችል የሚታዩ ክፍተቶች ቢኖሩም እምብዛም አያስገርምም፡፡ የለውጥ ኃይሉ ስለፈጸማቸው በስህተትነት የተፈረጁ ቀጥሎ የቀረቡትን ጉዳዮች በተመለከተ በማንኛቸውም በሥራ ሒደት ሊፈጠሩ የሚችሉ ያልተገመቱ ተግባራት እንጂ፣ ሆን ተብለው ለአገር ጉዳት የተፈጸሙ አለመሆናቸው ሊታወቅ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ይህ የለውጥ ኃይል ሌት ተቀን ሲሠራ እኛ ዳር ቆመን፣ ወደ አንዱ እንዳንፈረጅና የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቂ ላለመሆን በአድርባይነት ቆይተን፣ ጊዜውን ብቻ ሳይሆን ሕይወቱን ጭምር አስይዞ የሚሠራን ወገን ለመተቸት የሞራል ብቃት የለንም፡፡

- Advertisement -

ይሁን እንጂ አንዱ የሚያየውን ሌላው ለማየት የሚቸገር በመሆኑ፣ እንደ ሕዝብ አካልነት በሕዝቡ ውስጥ የሚንሸራሸሩ ሐሳቦችንና ቅሬታዎችን በጥቆማ መልክ ወደ መድረክ ማምጣቱ ለሁለቱም ማለት ለሕዝቡም ሆነ ለመንግሥት ይጠቅማል በሚል መሠረተ ሐሳብ ነው አቀራረቡ፡፡ የአንድ ጉዳይ ችግር መታወቅ የመፍትሔው ግማሽ ነው እንደሚባለው ሕዝቡ ችግሬ ታውቆልኛል፣ በይፋ ተነግሮኛል በማለት ዕርካታ የሚሰማው ሲሆን፣ የለውጥ ኃይሉ ወይም መንግሥት ደግሞ የሕዝቡን ጥያቄና ፍላጎት በተብራራና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ሲቀርብለት ምላሽ ለመስጠት ያመቸዋል፡፡ ሁኔታውም የለውጡን ሒደት የበለጠ ወደ ፊት በመግፋት ሁሉንም ይጠቅማል፡፡                                                                                                                              ስለሆነም በለውጡ ሒደት የታዩ ክፍተቶችን በመጠቆም እርማት እንዲደረግባቸው ግፊት መፍጠር ከዜጎች የሚጠበቅ በመሆኑ፣ ይህ ጸሐፊ ቀጥለው የቀረቡትን የተገነዘባቸውን ስህተቶች ለመማሪያነት እንዲያገለግሉ አቅርቧል፡፡

  1. በአቶ ዳዊድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ ሸኔ በአገር ውስጥ የነበረውን ጦር ወዲያው ትጥቅ አስፈትቶ ወደ ሕዝብ እንዲቀላቀል አለማስደረግ፣
  2. ጦሩ ትጥቅ ለመፍታት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቶ ይዞታውን እያስፋፋና ወጣቱን እየመለመለ ሲያሠለጥን ሕዝቡ ዓይቶ ይተፋዋል በሚል በቅርብ መከታተልና መቆጣጠር ሲገባ፣ በቸልተኝነት በመመልከት ችግሩ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ መድረሱና ተጎጂውን ሕዝብም በሚፈለገው መጠን መታደግ ያለመቻል፣
  3. በኦሮሚያ ኦነግ ሸኔ በኦሮሞ ሕዝብ እንዲሁም በአማራ ክልል አብን በአማራ ሕዝብ ተደጋፊነታቸውን በመፍራት ወይም በመጠራጠር ይመስላል፣ ሕዝቡን ነፃ አድርጎ ሐሳቦች በነፃነት እንዲንሸራሸሩ በማስደረግ በሕዝቡ መካከል የሚገኙትን የለውጥ ኃይል ደጋፊዎችን በአጋዥነት በብቃት መጠቀም ያለመቻል፣
  4. በሕወሓት ላይ በሚደረጉ ውንጀላዎች የትግራይ ሕዝብ የመገለልና የመጠቃት ስሜት እንዲሰማው በሚደረጉት ቅስቀሳዎች የጥንቃቄ ጉድለቶች መኖራቸውና ይህንን ለማረም የለውጥ ኃይሉ በቂ ሥራ አለመሥራቱ፡፡ ያልተፈለገ ትርጓሜ የሚያሰጡት ጉዳዮች ላይ በቂ የማስተካከያ ማብራሪያ ያለመስጠት፡፡ በአማራና በትግራይ መንገድ ክፍት አለማድረግን በተመለከተም በቂ ሥራ አለመሠራቱ፣
  5. በታችኛዎቹ መንግሥታዊ እርከን ሙስናን በማስቆምና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታትየሕዝብን ብሶትና እሮሮ ለማስወገድ ብርቱ ጥረት አለመደረጉ፣
  6. ለሚቀርቡት ጥያቄዎችና የሕዝብ ቅሬታ አፋጣኝ ምላሽ ያለመስጠትና የዕርምጃ አወሳሰድ መዘግየት፣
  7. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተፎካካሪዎችን ለማዳከምና ራሱን ለማጠናከር እየተጠቀመበት ነው የሚል ቅሬታ መፈጠር፣ ለምሳሌ ለራሱ የፓርቲ ሥራ ስብሰባዎችን ሲያካሂድ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ይከለከላል የሚባለውና የኢዜማን ጨምሮ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላት ይታሰራሉ የሚሉ እሮሮዎች በሰፊው ይሰሙ ነበር፣

8. ባለፈው ጥቅምት የአቶ ጀዋር መሐመድ ጠባቂዎችን በሌሊት ለማንሳት ሙከራ ተደርጓል፣ ተከብቤያለው በሚሉት ጉዳዩ በቂ ማብራሪያ ለኅብረተሰቡ አለመስጠቱ፡፡

9. የግልጽነት ማነስ፣ መደበቅና ሚስጥር መሆን የማይገባቸው ማብራሪያና ትንተና የሚፈልጉ በርካታ ጉዳዮች እየተሸፋፈኑና ሕዝቡን በጥራጥሬ ውስጥ የሚያስገቡ፣ እንደቀድሞ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ሸውዶ ማለፍ የሚመስሉ ሁኔታዎች መታየታቸው፣ በሕዝብ መሀል የሚመላለሱ አሉባልታዎችና ጥያቄዎችን በተመለከተ ለሕዝቡ ትክክለኛ መረጃ መስጠት አለመቻል፡፡

10. ሕግን የጣሱና መረን የተለቀቁ የመገናኛ ብዙኃን በጊዜ ፈር ማስያዝ ባለመቻል በሕዝቡ በተለይ  በወጣቱ ትውልድ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዲፈጠር መደረጉ፣

11. የመገናኛ ብዙኃን በነፃነትና በገለልተኝነት የተለያዩ ሐሳቦችንና አመለካከቶችን ወደ መድረክ በማምጣት ላይ የተሞከሩ ሥራዎች ቢኖሩም በቂ ክርክርና ውይይቶች እየተካሄዱ የሐሳብ መሸናነፎች ላይ የተፈለገውን አለመሥራቱ፣ የመርማሪ ጋዜጠኝነት ሥራ በጣም ደካማ መሆኑ፣ በመንግሥት የተያዙ የመገናኛ ብዙኃን ከመንግሥት ከደጋፊነት ፕሮፓጋንዳ ውጪ የተለያዩ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ሐሳቦችን ጭምር ወደ መድረክ በማምጣት የሐሳቦች ትግል እንዲደረግ በቂ ሥራ እንዲሠሩ አለመደረጋቸው

ስለብልፅግና ፓርቲ ፕሮግራምና አቋም ለሕዝቡ በቂ ማብራሪያ ያለመሰጠቱና በተለይ የኦሮሞ ወጣቶችን አስፈላጊ ላልሆኑ ትርጉሞች ማጋለጣቸው፡፡

የለውጥ ኃይሉ፣ መንግሥትና ገዥው ፓርቲ የበለጠ ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ ተግባራት

ተደጋግሞ እንደተገለጸውና ማንኛውም ሰው እንደሚገነዘበው በለውጥ አመራሩ እየተመራ የሚገኘው ለውጥ በሕዝብ ትግል የመጣ፣ ሕዝባዊና በሕዝብ የሚደገፍ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ የለውጥ አመራሩ ይህን ሕዝባዊ የሆነውን ለውጥ ወደ ሕዝብ በማውረድ ሕዝባዊ አጋርነቱን የበለጠ መጎናፀፍ ይኖርበታል የሚለው ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ስለሆነም ለኅብረተሰቡ መድረኮችን በማመቻቸት ከጎኑ እንዲሠለፍ፣ መንግሥት የበለጠ ኅብረተሰቡን ማሳተፍና ማንቀሳቀስ ይጠበቅበታል፡፡ ብልፅግና ፓርቲም እንደ ኢሕአዴግ ግልጽነት ይጎድለዋል የሚል ሐሜት አለ፡፡ ከሕዝብ መደበቅ የሌለባቸውም ጉዳዮች ሚስጥር ሲደረጉ ይታያሉ፡፡ ለሕዝብ በሚፈለገው መጠን ግልጽ ያለ መሆን፣ የመንግሥት አካላት ቸልተኝነቶች፣ ድብቅነት፣ አገርንና ሕዝቦችን ዋጋ እንዳያስከፍሉ ማስተካከያዎች ሊደረጉባቸው ይገባል፡፡ የኦሮሞ ተወላጆች ከሶማሌ ክልል መፈናቀል ጀምሮ እስከ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የዶ/ር ዓብይ የመግደል ሙከራ፣ ከዚያም ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. የአማራ ክልል መሪዎችና ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንንና በወቅቱ አብረዋቸው የነበሩት ሜጀር ጄኔራል መገደል፣ እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት ካደረሱት የሕዝብ መፈናቀል ጋር የተገናኙ ስላጋጠሙ ችግሮች፣ ከሕዝቡ በስተጀርባ ይህንን ስለሚሠሩትና ስለጉዳዩ ትክክለኛ መረጃና የመንግሥት ሕጋዊ ዕርምጃ አወሳሰድን ይጠብቃል፡፡ ሰዎች ተይዘው ለፍትሕ ቀርበዋል፣ ተጣርቶ ለሕዝብ ይገለጻል፣ ወዘተ. ይባልና በዚያው ጉዳዩ የውኃ ሽታ ሆኖ ይቀራል፣ ይረሳል፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ጉዳዮች ሊስተካከሉ ይገባል፡፡

 በዕርምጃ አወሳሰድ ማመንታትና ቸልተኝነት ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ይህ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ያለውን አመኔታ ይቀንሳል፣ ተስፋም ያስቆርጥና የራሱ በሆነው ለውጡ ላይ ከተቃራኒ ወገኖች ጋር እንዲቆም ይገፋፋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአንዳንዶች እየሆነ ያለው ይኸው ነው፡፡ ዶ/ር ዓብይ የሚሞግቱን ይኸው እየሠራን ያለነውን ሕዝቡ ያየዋል፣ ይገነዘባል፣ ለእያንዳንዱ ምላሽ ለመስጠት የምንሄድ ከሆነ ሌላውን ሥራ መቼ እንሠራዋለን? በዚሁ ተጠምደን ልንቀር ነው የሚሉት ሐሳቦች እውነታነት ቢኖራቸውም ተግባራዊ ሥራውንም ከሌሎች የለውጡ ተቃዋሚዎች የሚቀርቡትን የሐሰት መረጃዎችንና ፕሮፓጋንዳዎችን መመከትና ሁሉንም ባመጣጠነ መንገድ መሥራት ካልተቻለ፣ የከፋ ጉዳትና ውድቀት ስለሚያስከትል ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ለማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል የብልፅግና ፓርቲ አቋም የሁለቱ ተፃራሪ አቋሞች ማለት በዜግነት ፖለቲካና በብሔርና ብሔረሰብ ላይ በተመሠረተ ፌዴሬሽን መካከል የነበሩትን ልዩነቶች ወደ መሀል በመጣ አካሄድ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ በተለይ የብሔርተኛ ፖለቲከኞች ደጋፊዎች የሆኑት ጥርጣሬ ላይ እንዲወድቁ ያደረጋቸው ይመስላል፡፡ በዚህ ተደጋግሞ የሚገለጸው ብልፅግና አሀዳዊ ሥርዓትን ለመመለስ ነው የሚሠራው የሚሉት አሉባልታዎች ጎልተው የሚቀርቡ በመሆኑ፣ ይህ አለመሆኑን በግልጽነት በተብራራ መንገድ ለኅብረተሰቡ በተደጋጋሚ ማቅረብ አስፈላጊ ነው፡፡  

ዶ/ር ዓብይ በቅርቡ በኦሮሚፋ  ለኦብኤን የሰጡት ዓይነት ቃለ ምልልስ ከስምንት ወራት በፊት ቢሰጥ ኖሮ፣ ብዙዎቹን የኦሮሞ ወጣቶች በሌሎች አሉባልታዎችና ቅስቀሳዎች ወደ ጭንግፍ አስተሳሰቦች ከመግባት ያድን ነበር፡፡ በቃለ ምልልሱ የቀረቡት ማብራሪያዎች ተደማጭነቱ በአሁኑ ጊዜ በእነዚህ በስሜት በሰከሩ በወጣቶቹ ምን ያህል እንደሆነ ባይታወቅም፣ ብዙ ውዥንብሮችን ለማጥራት ይረዳ ነበር፡፡ እንዲያውም ይህ በቪዲዮ መልክ ተዘጋጅቶ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚካሄዱት ሕዝባዊ ስብሰባዎች ለኅብረተሰቡ ቢቀርብ ጥሩ ውጤት ያስገኛል፡፡ የትግራይ ሕዝብ የሕወሓት መደበቂያ ዋሻ ለመሆኑ፣ ይህ ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል ፕሮፓጋንዳ ሚና የነበረው መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ለእነዚያ ማስተካከያና የአፀፋ ፕሮፓጋንዳ ባለመሠራቱ ማለት ነው፡፡ ይህ በኦሮሚያ ኦኤምኤን ቴሌቪዥን ቀደም ሲል ኦኤን ቴሌቪዥን፣ እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ኩሽ፣ ገዳ፣ ወዘተ. የሚባሉት ድረ ገጾች  ያለ ምንም ተከላካይ ሕዝቡን ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ሲመሩ የቆዩትን ለመከላከል በግል አቶ ታዬ ደንደአ ከሚያደርጉት ትግል ውጪ፣ መንግሥታዊ ኃይሉ በንቀትና በቸልተኝነት ዝም ብሎ ሲያይ ነው የከረመው፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያና በአንዳንድ መደበኛ የመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ አገርንና ሕዝብን የሚጎዱ መልዕክቶች በየክንዋኔውም ባይሆን ቢያንስ በሳምንት አንድ ቀን ማብራሪያ በሌሎች ኃላፊዎች፣ በወር ካልተቻለ በሦስት ወራት አንድ ጊዜ በዶር ዓብይ ማስተባበያና ማስተካከያ ቢሰጡ የተሻለ ነበር፡፡ ይህ ሳይሆን በንቀት ዝም ብሎ መመልከት ‹‹ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል›› ዓይነት ሆኖ ችግሮችን እያስከተለ ያለ በመሆኑና አሁንም  የሚቀጥል ስለሚሆን በበርቱ ሊታሰብበት የሚገባ ተግባር ነው፡፡

በሕወሓት በአገር ላይ የተሠሩና ሲሠሩ የቆዩትንና ተሞክረው የከሸፉ ሴራዎችን፣ በተለይ የትግራይ ሕዝብ እንዲገናዘባቸው አለመደረጉ፣ ከትግራይ በሚተላለፉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሚቀርቡ አገርን የሚያተራምሱ ዓይነት ቅስቀሳዎች ሁሉ ዴሞክራሲያዊ መብት ነው በሚል በዝምታ መታየታቸው በስህተትነት የሚፈረጁ ናቸው፡፡ በእርግጥ ስለሕወሓት ብዙ ሚስጥር ማውጣት የበለጠ ያስበረግጋል፣ ወይም በትግራይ ተወላጆች ላይ የመሀል አገር ኅብረተሰቡ ቂም በቀል ይይዛል ተብሎ ሊሆን ይችል ይሆናል፡፡ ግን ይህን ጉዳት ሊያስከትል በማይችል በጥንቃቄ ጉዳዮቹ ለሕዝቡ ይፋ ተደርገው የሕዝቡን የዕይታ አድማስ ማስፋት ያስፈልግ ነበር፡፡ ይህ ቢደረግ መንግሥት በሕዝቡ የበለጠ ይታመናል፡፡ ከህዳሴ ግድብና ከዓባይ ጋር በተያያዘ ግብፆች ለዓረቡና ለዓለም ሕዝብ ሐሰትን ደጋግመው በማቅረብ እውነት አስመስለው፣ እኛ ግን እውነታን ይዘን ለማሳመን የተቸገርነው ይኸው የፕሮፓጋንዳ ክፍተታችን መሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ በእርግጥ በቅርቡ በመንግሥት እየወጡ ያሉት መረጃዎች ለውጥ የሚታይባቸው በመሆኑ ይኸው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ተመሪው ሕዝብ ስለመሪው አቅጣጫና ግብ  በበቂ ሁኔታ ካልተረዳ ትክክለኛ ተመሪ ሊሆን አይችልም፡፡ በትክክል ካልተመራ ደግሞ መበተኑ አይቀርም፡፡ ስለዚህ በተለይ መረጃን ለሕዝብ በአግባቡ ለማድረስ የሚሠራ አንድ ጠንካራ ቡድን ወይም ተቋም ሊኖር ይገባል፡፡ ባለፈው ጥቅምት 2012 ዓ.ም. የአቶ ጀዋር መሐመድ ጠባቂዎችን በሌሊት ለማንሳት ተሞክሯል በሚል የተፈጠሩ ሁኔታዎች አሳዛኝ ቢሆኑም፣ ትልቅ አቧራ አስነስተውና በለውጥ ሒደቱ አሠላለፍ የጎራ ለውጥ አስከትለው አልፈዋል፡፡

በብልፅግና ፓርቲ ምሥረታ ወቅት የፓርቲውን ምሥረታ አቶ ጀዋር ግንባር ቀደም ተቃዋሚ ነበሩ፡፡ በአንድ ፓርቲ ጥላ ሥር ኦሮሚያን ጨምሮ አገር በሙሉ እንዲመራ አቶ ጀዋርና ሌሎች ብሔርተኛ የኦሮሞ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አይቀበሉም፡፡ ይህ ኦሮሚያ ትቅደም (Oromia First) ከሚለው ፍልስፍና ጋርም ስለማይሄድም ነው፡፡ ይህ ሒደት ብሔርተኞችን ከዶ/ር ዓብይ ጋር ያፋታቸውና ይበልጥ ከሕወሓት ጋር ያቀራረባቸው፣ በፖለቲካው መስክ የመጀመሪያው የአቅጣጫ ለውጥ (Turning Point) ነበር፡፡ ከዚህ ጋር በተገናኘ አቶ ጀዋር “ኦዴፓን” ለመከፋፈልም ሞክረው ስላልተሳካላቸው፣ ዶ/ር ዓብይን በአደባባይ መዝለፍ የጀመሩበት ወቅትም ነበር፡፡ በዚያኑ ሰሞን በነበረው የፓርላማ ስብሰባ ላይ የውጭ አገር ፓስፖርት ያላቸው ፖለቲከኞችን የሚያስጠነቅቅ ንግግር ዓይነት ዶ/ር ዓብይ በመናገራቸው፣ በዕለቱ ሌሊት ይቀየራሉ  በሚል ጠባቂዎች እንዲነሱ ተደርጓል በሚል አቶ ጀዋር “ተከብቤያለሁ” ብለው ለደጋፊዎቻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ በማግሥቱና በቀጣዮቹ ቀናት በተደረገው ሰላማዊ ሠልፍና መንገድ መዝጋት በመሳሰሉት በኦሮሚያ ከ86 ሰው በላይ ሕይወት ማለፉ፣ የመቁሰልና የአካል ጉዳት ከመድረሱም በላይ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ንብረት መጎዳቱ ይታወሳል፡፡

የተደረገው ድርጊት አግባብ አልነበረም በሚል አቶ ጀዋር በተለይ በኦሮሞ ወጣቶች ባላቸው ድጋፍ  ከፍትሐዊነትም አንፃር፣ ሌሎች የኦሮሞ ኅብረተሰብ አካላትም ቅሬታ እንዲሰማቸው ተደርጓል፡፡ ከድርጊቱ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ አቶ ጀዋር በአሜሪካ በተለያዩ ግዛቶችና በአውሮፓ ባደረጉት ጉብኝትና ሕዝባዊ ስብሰባዎች፣ የበለጠ ደጋፊዎችን በውጭ ከሚኖሩ የኦሮሞ ማኅበረሰብ እንዲያገኙ አስችለዋቸዋል፡፡ በተለይ የአቶ እስክንድር በዚያኑ ጊዜ የአሜሪካ ጉብኝትና ፉክክር በሚመስል አቶ ጀዋርንና ቄሮን የሚቃወም ሰላማዊ ሠልፍ በአሜሪካ የአማራ ብሔር ተወላጆች እንዲያካሂዱና ቄሮ አሸባሪ ነው የሚል ክስም ዓይነት ማቅረባቸው፣ በሁለቱ ብሔሮች መካከል ቅራኔን የሚፈጥር ሁኔታ እንዲታይም አድርጓል፡፡ ይህ ክስተት የበለጠ ለአቶ ጀዋር ከኦሮሞ ማኅበረሰብ ተቀባይነት እንዲያገኙ አድርጎም ነበር፡፡ በዚህ የጽሑፍ አዘጋጅ ምልከታ ይህ ክስተት በርካታ የኦሮሞ ወጣቶች የተማሩትን ጨምሮ፣ ለብልፅግና ፓርቲና ለዶ/ር ዓብይ የነበራቸውን ድጋፍ እንዲቀንሱ አድርጓል፡፡ በጉዳዩም ላይ ማብራሪያና ማስተባበያ ሳይሰጥ በዝምታ መታለፉ ደግሞ የበለጠ ጥርጣሬን አስከትሏል፡፡ በኦሮሞ ኅብረተሰብ ውስጥ የሐሳብ ክፍፍል እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ምናልባት ለክቡር አቶ ለማ መገርሳ ከመድረክ መሰወር እነዚያ ሁኔታዎችም አስተዋጽኦ ሳይኖራቸው አልቀረም፡፡ በአሁኑ ጊዜ የታየው ክስተት የዚያን ጊዜ ድምር ውጤት ይመስላል፡፡ በዚያን ወቅት ከሌሎች በተለይ የአማራ ልሂቃን ሲቀርብ የነበረው  ፍትሕ አልተከበረም፣ ጥፋተኞች ለፍርድ አልቀረቡም፣ በተለይ እነ አቶ ጀዋር ለፍርድ መቅረብ ነበረባቸው በሚል በለውጥ ኃይሉ ላይ ቅሬታ እንዲፈጠርም ሆኗል፡፡ በእነዚህ ሁኔታዎች በዚያን ጊዜ የተፈጠረው ስህተት የለውጥ ኃይሉንና የለውጥ ሒደቱን ብዙ ዋጋ አስከፍሏል፡፡ በርካታ የኦሮሞ ወጣቶች ምክንያታዊ በመሆን ፋንታ ዓይናቸውን ጨፍነውና ጆሯቸውን ደፍነው እንደ ሃይማኖት እምነት የሚከተሏቸው አክራሪ ብሔርተኞች ትልቅ መስዋዕትነት በመክፈል፣ ወደ መቀሌ ያስገቡዋቸው የሕወሓት መሪዎች ዳግመኛ ከእነዚህ ብሔርተኞች ጋር “የጠላቴ ጠላት ወዳጅ” ነው በሚል መርህ የሴራ ጥምረት በመፍጠር፣ አገር በማፈራረስ የለውጥ ኃይሉን ከሥልጣን እናስወግዳለን ለሚሉት መሣሪያ እንዲሆኑ አስተዋጽኦው ቀላል አልነበረም፡፡

ይህ እንዲነሳ የተፈለገው ወደኋላ በመሄድ ለቁጭት ሳይሆን፣ የበለጠ ወደፊት ለመዝለል የተወሰኑ ዕርምጃዎችን ወደኋላ መሄድ ስለሚጠቅም ነው፡፡ ዶ/ር ዓብይና በአጠቃላይ የለውጥ ኃይሉ በጣም በርካታ ለአገራችን ኢትዮጵያ ጠቃሚ የሆኑ ትልልቅ ሥራዎችን እያከናወኑ በሚገኙበት፣ ምናልባት ከአቶ ጀዋር ጋር የተገናኘው ጉዳይ የእነርሱ እጅ ያለበት ለመሆኑ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም እነርሱ አደረጉ እንኳን ቢባል፣ ዓላማውና ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል እርግጠኛ በማይሆንበት ለአገር ደኅንነትና አንድነት ታሳቢ በማድረግ የፈጸሙት ተግባርም ሊሆን ይችላል በሚል በመቀበል፣ በይቅርታ ማለፍ ነው ከኦሮሞ ወጣትና ኅብረተሰቡ የሚጠበቀው፡፡ ካልሆነ በጭፍን የሚደረገው ጉዞ በኦሮሞ ሕዝብም ሆነ በአገሪቱ ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ቀላል አይሆንም፡፡ ከሰሞኑ የሚታየው ድርጊት በሃይማኖት ጭምር ወደሚከፋፈል አዘቅት ውስጥ የሚያስገባን በመሆኑ፣ ሁሉም ወደ ልቦናው ተመልሶ ሁኔታዎችን በማገናዘብ ጥቅምና ጉዳቶቹን በማመዛዘን ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎች ላይ መድረስ ጠቃሚ ነው፡፡ ተደጋግሞ እንደተገለጸው በዚህ ዓይነት አመፅ ሁልጊዜ መንግሥትን መቀየር አይቻልም፡፡ ይህ ሊፈጸም የሚቻለው ጊዜ፣ ወቅትና ሁኔታዎች ሲሟሉ ነው፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ግን ለዚያ የተመቻቸ ጊዜ ባለመሆኑ ሙከራው የማይሳካ ቢሆንም፣ ውጤቱ ግን አገሪቱን ለአደጋና ለውድቀት ሕዝቡንም ለሥቃይና ለውርደት ይዳርጋል፡፡

በሌላ በኩል ይህ የለውጥ ኃይል ይዞት የተነሳው ዓላማና ግብ ሕዝባዊ በመሆኑና መሪዎቹ በሙስና ውስጥ የተዘፈቁ ባለመሆናቸው ምንም የሚያስፈራቸው ከሌለ፣ ለምን ሙሉ በሙሉ ለሕዝብ ግልጽ ሆነው ታች ባሉት መዋቅሮች የሚታዩትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች በሕዝበ ተሳትፎ እንዲሻሻል አይደረግም? የሚለው ጥያቄ ተደጋግሞ የሚነሳ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ሕዝብን አሳምኖ በተወካዮቹ አማካይነት ሐሳቡን በነፃነት እንዲያንሸራሽርና መንግሥታዊ መዋቅሮችን እንዲቆጣጠር፣ የየወረዳውንም ሆነ የቀበሌ በጀት ዕቅድና አፈጻጸምን እስከ መከታተልና መቆጣጠር የሚያስኬድ ተሳትፎ በመፍጠር ተቆርቋሪነት ያለውና ኅብረተሰቡ የእሱነት ስሜት እንዲሰማው ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው፡፡ በዚህ ሒደት በሕዝቡ እምነትን ማሳደር፣ ግልጽነትና አሳታፊነቱ በጎላ መንገድ በእየ እርከኑ የሚገኙ መሪዎች በራሳቸው በመተማመን ከኅብረተሰቡ ጋር በቅርበት መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በራሱ የማይተማመንና ከኅብረተሰቡ ጋር ለመሥራት የሚቸገር የመንግሥት ኃላፊ ካለ፣ አቅሙና ፍላጎቱ ባላቸው ሌሎች ኢትዮጵያውያን መተካት እንጂ ማስታመም የለውጥ ሒደቱን ይጎዳዋል፡፡

የኅብረተሰቡ ተሳትፎን በተመለከተ ኢንቨስተሮች፣ ኢንተርፕረነሮች፣ እንዲሁም በጠቅላላው የንግዱን ማኅበረሰቦቹ ወይም ባለሀብቶች የመንግሥት ኃላፊዎች የሚፈልጓቸው የገንዘብ መዋጮ ሲያስፈልግ ገንዘብ እንዲያዋጡ ብቻ ነው ተብሎ ይታማል፡፡ በዚህ የኅብረተሰብ ክፍል ያለው ከደርግ ሥርዓት ጀምሮ የቆየው የመንግሥት አመለካከት፣ እንዲያውም ወደ ኅብረተሰቡ የዘለቀው ሸውራራነት በዚህ አጋጣሚ ሊነሳ ይገባል፡፡ ይህ የኅብረተሰብ ክፍል ከሌላው የኅብረተሰብ ክፍል በአንፃራዊነቱ ከምሁሩ ቀጥሎ የነቃ፣ በኢኮኖሚ አቅሙ ራሱን የቻለና በኅብረተሰብ ውስጥ ተቀባይነትና ተደማጭነት ያለው ነው፡፡ ይህ የኅብረተሰብ ክፍል የአገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያንቀሳቅስ፣ ራዕይ ያለው፣ በአዎንታዊ አስተሳሰብ የተጠመደ፣ በአግባቡ ቢያዝና ቢሠራበት ሌላውን የኅብረተሰብ አካላት ይዞ ወደፊት የሚያስመነድግ ኃይል በመንግሥት ኃይል ጭምር በጥርጣሬ የሚታይ በመሆኑ፣ ይህ አስተሳሰብ ሊስተካከልና ሊቀየር ይገባል፡፡

ለዚህ የንግድ ማኅበረሰብ የአመለካከቱ መዛነፍ መንስዔዎቹ ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው ኅብረተሰቡን ያጭበረብራል፣ ሀብቱን የሚያገኘው በማጭበርበር ብቻ ነው ተብሎ መወሰዱ ሲሆን፣ ሁለተኛው በኅብረተሰቡ ሥር ሰዶ የመንግሥት ኃላፊዎችንም የሚያካትተው ለምን በኢኮኖሚ በለጠን የሚለው የምቀኝነት አስተሳሰብ ነው፡፡ በተለይ የለውጥ ኃይሉ አሁን በቅርቡ እያሻሻለ መጣ እንጂ ይህ የኅብረተሰብ ክፍል ከቀድሞ የሕወሓት/ኢሕአዴግ መሪዎች ጋር ተመሳጥሮ ሀብት ያፈራ፣ በዚህ ምክንያት ለውጡ የመጣበትና የለውጡ ተቃዋሚ እንደሆነም የሚጠረጠር ይመስላል፡፡ በእርግጥ በቁጥር በጣም አነስተኛ የሆኑ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ባለፈው ከነበረው የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር፣ በኮንትሮባንድ ንግድና የመንግሥት ታክስና ገቢን  በመሰወር የተሳተፉና በዚያ የሚታሙ ይኖራሉ፡፡ በማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ማለትም በመንግሥት አካላትም ሆነ በሌላው የኅብረተሰብ ክፍል እንደሚኖሩት ሌቦችና አጭበርባሪዎች ጥቂቶች፣ በዚህም የኅብረተሰቡ አካል ቢኖሩ የሚደንቅም አይሆንም፡፡ በሌላ በኩል በመንግሥት ኃላፊዎች የሚወጡ፣ ያሉትን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት ውስጥ የማያስገቡና የማያሠሩ አዋጆች፣ ደንቦችና መመርያዎች ሲኖሩ ይህን ለማስተካከል ሲያስቸግር ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ መሰናክሉን የማለፍ ድርጊቶች ሊኖሩ ቢችሉ ይህም የማያስገርም ላይሆን ይችላል፡፡ እንደዚህ ካልሆነና ሁኔታዎች ከተስተካከሉ በአብዛኛው የንግዱ ማኅበረሰብ አገር ወዳድና ሰላማዊ የኅብረተሰብ አካል ነው፡፡

በመሆኑም የንግዱ ማኅበረሰብ ለኢኮኖሚ ዕድገትና ገቢ ማስገባት ብቻ ሳይሆን፣ ለሰላምና ለአገራዊ አንድነት እንደ አንድ ትልቅ ሪሶርስ መወሰድ ያለበት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ሰላም ቢታወክ በመጀመርያ ሀብቱ የሚቃጠለውና የሚወድመው እንዲሁም ለሀብቱ ሲባል ሕይወቱም አደጋ ላይ የሚወድቀው ይህ የኅብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ በሌላ በኩል የንግድ ሥራ በወሰንና በድንበር የማይገደብ በመሆኑ ይህን በብሔርና ብሔረሰብ የተከለለን ወሰን በመሰባበር የአገር አንድነትን ለማጠናከር ይህ ኃይል የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው፡፡ በኅብረተሰባችን ውስጥ የሚንፀባረቀውን የጨለምተኝነት አስተሳሰቦች ሊሰበሩና በሥራ ፈጠራ ድህነትን ታሪክ ማድረግ የሚቻለው፣ የዚህን ኃይል በመጠን በመጨመርና አመቺ ሁኔታዎችን በመፍጠር ማሳደግ ሲቻል ነው፡፡ ስለሆነም ይህን የኅብረተሰብ ክፍል መንግሥት መፈለግ ያለበት ለገንዘብ መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን፣ ለሐሳብ በተለይ የልማት፣ የሰላምና የፀጥታ ጉዳዮች ጭምር መሆን ይኖርበታል፡፡

የንግድ ማኅበረሰቡን በመንግሥት የሚፈለግበትን ግብር በአግባቡ መክፈል ተገቢና አስፈላጊ መሆኑ ቢታመንበትም፣ በተለያየ መንገድ በዕርዳታ መልክ የሚጠየቀው ገንዘብ የሚጠፋና ባለሀብቱ ከሚንደላቀቅበት ውስጥ እንደሆነ የሚታሰበውም ትክክል አለመሆኑ፣ ኢንቨስት ተደርጎ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ለአገሪቱ ተጨማሪ ሀብት የሚሆነው እንደሆነ ግንዛቤ ሊያገኝ ይገባል፡፡ በእርግጥ ይህም ሆኖ ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት የንግዱ ማኅበረሰቡ እንደ አንዱ ተግባርና የየአካባቢው ኅብረተሰብን ተጠቃሚ በማድረግ፣ ጤናማ ግንኙነት መፍጠር አስፈላጊም ይሆናል፡፡ ስለሆነም ይህ ሚዛናዊነቱ ተጠብቆ ሊካሄድ ይገባል፡፡ በአጠቃላይ ለማስተላለፍ የተሞከረው ሐሳብ ይህን በተግባር የተፈተነ፣ ብዙ የዕውቀት ልምድ የውጭ አገሮች ተሞክሮን ጭምር ያካበተ በመላ ማፈላለግ  መንግሥት በአግባቡ ቢጠቀም ለብዙ ጉዳዮች ማለትም ለማኅበራዊ፣ ለኢኮኖሚና ለፖለቲካው ጭምር ብዙ ዕገዛ የሚያደርግ ኃይል  ነው ለማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረተ ሐሳብ ገለልተኛ ወይም የለውጡ ደጋፊ የሆኑ ምሁራንና ታዋቂ የንግድ ሰዎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በቀበሌ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት፣ ለሕዝቡ ስለለውጡ ገለጻ ቢያደርጉና ቢያስተምሩ ዘወትር ከሚያገኙዋቸው ካድሬዎች የበለጠ ተቀባይነት ስለሚኖራቸው የለውጥ ኃይሉ እነዚህን በአግባቡ ሊጠቀምባቸው ይገባል፡፡

 ሌላው መፈታት ያለበት ኅብረተሰቡ የመንግሥት ኃላፊዎችን ውሳኔ በወቅቱ ማግኘት ያለመቻል ጉዳይ ነው፡፡ ውሳኔዎች ይዘገያሉ፡፡ የውሳኔ አሰጣጥ ከሚገባው በላይ ማዕከላዊነት የጠበቀ ነው፡፡ በየቦታው ያሉ ኃላፊዎች በተናጠል ደፍረው አይወስኑም፣ ይፈራራሉ፣ ለመወሰን በራስ ያለመተማመንም አልፎ አልፎ ይታያል፡፡ ኃላፊዎችን አግኝቶ ችግሮችን ማስረዳትም ከባድ ነው፡፡ ትልቁም ትንሹም ውሳኔ ወደ ላይ ብሎም ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይገፋል፡፡ በዚህ ረገድ በየእርከኑ ያሉት ኃላፊዎች መወሰን እንዲችሉ መሥራትና ማበረታታት፣ እንዲሁም ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ይህም ጉዳይ በብርቱ ሊታሰብበት የሚገባው ነው፡፡ ሕዝቡ ሰላም፣ ልማትና መልካም አስተዳደር ይፈልጋል፡፡ በየአካባቢው በራሱ ጉዳይ ላይ በመወሰን ለውጡን የራሱ አድርጎ መንከባከብና መጠበቅ ይሻል፡፡ ገዥው ፓርቲና መንግሥትም በሕዝቡ እምነቱን ጥሎ ለዚህ ኃላፊነቱን ለሕዝቡ ላይ በመስጠት፣ የአቅም ማሳደጊያ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይኖርበታል፡፡ ሕዝቡ በሙሉ አቅሙ ከጎኑ እንዲሠለፍ የለውጥ ኃይሉ የበለጠ መሥራት ይኖርበታል፡፡

ሰላሙን፣ ልማቱን፣ ሙስናን፣ የሕግ የበላይነት ማስጠበቅን፣ ተስማሚ ያልሆኑ አሠራሮችን የማስለወጥ፣ ኃላፊዎችን የማስነሳትና የማሾም መብት ሕዝቡ እንዲጨብጥ ከተደረገ የአገሪቱ ችግር ይፈታል፡፡ ይህ ለውጥ ሕዝባዊ ነው ሲባል አብዛኛው ሰው የለውጡ ደጋፊ ነው ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል አብዛኛው የተማረውና የከተማ ነዋሪው፣ ነጋዴውና የመንግሥት ሠራተኛው ለውጡን ይደግፋል፡፡ ይህ መንግሥት እስካሁን በኢትዮጵያ ከመጡት መንግሥታት በላይ በተማረው የሰው ኃይል ተቀባይነትና ድጋፍ ያለው ነው፡፡ ሌላው በትምህርት ያልገፋው በተለይ የገጠሩ ሕዝብ የሚያዳምጠውና የሚመራው በዚህ ኃይል ስለሆነ፣ ለምርጫውም ይህ የለውጥ ኃይል ይህን ያህል ሊሠጋ አይገባም፡፡ ኢሕአዴግ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ የተሸነፈው 85 በመቶ የገጠሩ ሕዝብ ይደግፈኛል፣ 15 በመቶ የከተማው ነዋሪ ምንም አያመጣም የሚል ትዕቢት ውስጥ ገብቶ ነው፡፡ ስለሆነም ማንኛቸውም የሕዝብንም ድምፅ እንደ ሌሎች የጎረቤት አገሮች በገንዘብ ለመግዛት መሞከርም አያስፈልግም፡፡ በገንዘብ ወደ መግዛት ከተሄደ ወደ ሥልጣን የሚመጣው በሙሰኝነት በመሆኑና የኢትዮጵያ ሕዝብ እውነትን በጉቦ የማይለውጥ ስለሆነ ተዓማኒነትን ከማጣት ውጪ ትርፍ አይኖረውም፡፡ ይህ የዴሞክራሲ ሒደቱንም የሚያጨናግፍ በመሆኑ ፈፅሞ ሊሞከር አይገባም፡፡ ለወደፊትም መራጩን ሕዝብ በገንዘብ መግዛት እንደማይቻል በግልጽ በሕግ ሊደነገግ ይገባል፡፡ ከብልፅግና ፓርቲ ወይም ከዶ/ር ዓብይ  ስለምርጫ ማሸነፍና መሸነፍ ሊጠበብና ሊጨነቅ ወይም ተፎካካሪዎችን ለማሸነፍ ሸርና ተንኮል መሥራት አይገባም፡፡ ከሥጋት ነፃ ሆኖ የለውጥ ሒደቱን በአግባቡ መምራት ብቻ ነው የሚጠበቅበት፡፡

 ዶ/ር ዓብይና የብልፅግና ፓርቲው ሕዝቡን አምኖ ራሱን ለሕዝብ በመስጠት፣ የሕዝብን ውሳኔ በፀጋ የሚቀበል ከሆነ በምርጫ ያለምንም ሥጋት አሸናፊ ይሆናል፡፡ ሆኖም በአጋጣሚ ቢሸነፍ እንኳ የአገሪቱን ታሪክ በመለወጡ አሸናፊ ያደርገዋል፡፡ በተፎካካሪነት በመሥራትና ተፅዕኖ ፈጣሪ በመሆን በሚቀጥለው ምርጫ አሸናፊ መሆን የሚችል፣ የዴሞክራሲ መሠረትን በመጣሉና ታሪክ በመሥራቱ ደስተኛ  መሆን ነው የሚኖርበት፡፡ ዶ/ር ዓብይና ብልፅግና ፓርቲ እዚህ ደረጃ ድረስ የሚዘልቅ በራስ በመተማመን ከሠሩ፣ በሕዝብ  ከበሬታና  ተቀባነት ባተረፉ ሰዎች የሚከበቡ ስለሚሆኑ  ብዙ ደጋፊና አባላት ማፍራት ያስችላቸዋል፡፡ እስካሁንም ትልቅ ታሪክ የሠሩና እየሠሩ የሚገኙ ቢሆንም፣ በዚህ ተግባራቸው ለወደፊቱም የበለጠ በመሥራት ለአገር፣ ለራሳቸውም ሆነ ለልጆቻቸው ትልቅ ኩራት ሊሆኑ ይገባል፡፡ በዚህ መንፈስ ከሄዱ በምንም ተዓምር በምርጫ አይሸነፉም፡፡ ብልፅግና ፓርቲም እንደ ጃፓን ወይም ሲንጋፖር ገዥ ፓርቲዎች አውራ ፓርቲ ሆኖ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ያለፈው የሕወሓት/ኢሕአዴግ የሚወቀስበት ከሕዝቡም ከምሁራንም የሚቀርቡ ሐሳቦችን ወስዶ መጠቀም ኃፍረት የሚሰማው መሆኑ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ብዙዎቹ የኢሕአዴግ መሪዎች በትምህርት አልገፉም ስለሚባል ይህንን ለማሸነፍ ከተፀናወተው የበታችነት ስሜት ለመላቀቅ፣ ራሱን ብቁና አዋቂ ለማሰኘት ሲባል ኢሕአዴግ የሌሎች ዜጎችን ሐሳቦች ደብቆ ካልሆነ በግልጽ አመሥግኖ አይቀበልም ነበር፡፡ አሁንም በዚህ ረገድ ለውጥ ስለመኖሩ በግልጽ አይታም፡፡ ከሕዝብ የሚቀርቡ ሐሳቦች የአገሪቱና የሕዝቦቿ ሀብቶች ናቸው፡፡ የመንግሥት ሥራ መሆን ያለበት እነዚህንና ሌሎች ቁሳዊ ሀብቶችን እንዲሰባሰቡና እንዲቀናጁ በማድረግ ሀብት ለማፍራት መሥራት ነው፡፡ መንግሥታችን ይህን ማድረግ የሚያስከብረውና የሚያስመሠግነው እንጂ፣ የሚያስንቅ ፈፅሞ ሊሆን አይችልም፡፡ የመንግሥት መሪዎች ሁሉንም እንዲያውቁ አይጠበቅባቸውምና፡፡

 ስለሆነም ገንቢ ሐሳቦችን ዕውቅና በመስጠት ሐሳቡን የሚያቀርቡትን ዜጎች አስፈላጊ ከሆነ፣ በማመሥገን ጭምር ነው ሐሳቦቻቸውን መቀበል ያለበት፡፡ ሐሳብ አቅራቢዎቹ ሐሳቡን ለማመንጨትም ሆነ አቀነባብሮ ለማቅረብ የአዕምሮ ሀብት ያፈሱበታል፡፡ ይህ ደግሞ የአገር ሀብት ከሆኑት አንዱ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በህዳሴ ግድቡ ምሁራንን በማሳተፍ አጀንዳው ሕዝባዊ እንዲሆን እንደተደረገው ሁሉ በዚህ መልካም ጅማሮው፣ በሌሎች ልማቶችም፣ በሥራ ፈጠራውም ልምድና ዕውቀት ያካበቱ፣ ሙያቸውን ለአገራቸው ዕድገት ለማበርከት ዝግጁ የሆኑ በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚኖሩ ምሁራን አሉ፡፡ እነዚህ ምሁራን በተለያዩ ዘርፎች ማለት በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በንግድ፣ በአይቲ፣ በትምህርት፣ በኢኮኖሚ፣ በፋይናንስ፣ በቱሪዝም፣ ወዘተ. በቡድን ቡድን ተደራጅተው በበጎ ፈቃደኝነት ለአገራቸው አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ መድረኮችን በስፋት በማመቻቸት የተያዘውን በዕውቀትና በእውነት ብቻ መምራትን የበለጠ ተግባራዊ እንዲደረግ ነው የሚጠበቀው፡፡ በግብርና ዘርፍ ይህ ሥራ መጀመሩም ይነገራል፡፡ ስለዚህ ይሆን በቅርቡ በግብርና ዘርፍ የሚታዩት ማሻሻያዎች በዚህ ምክንያት ይሆን? ይህ መልካም ተግባር በሌሎችም ሊቀጥል ይገባል፡፡ ሌላው የተለያዩና በርካታ የተዳከሙ የሙያ ማኅበራትን በልዩ ልዩ ድጋፍ በማጠናከር፣ በሙያ ላይ የተመሠረቱ የአገራችንን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ የምርምር ውጤቶች የሆኑ ሐሳቦች እንዲንሸራሸሩ ቢደረግ መልካም ነው፡፡ ይህ የምሁራን አንድነትንና የአገር ወዳድነት መንፈስንም ያጠናክራል፡፡ ለመንግሥትም ሙያዊ ምክር ለመለገስ ይጠቅማል፡፡ በሚቀጥለው ጽሑፌ ምን መደረግ አለበት በሚሉ ጉዳዮች ላይ ሐሳቦችን አቀርባለሁ፡፡ በክፍል አራት ይህ ጽሑፍ የመጨረሻ ይሆናል ብዬ ነበር፡፡ ግን ስላልሆነ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡

ቸር ይግጠመን!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]ግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...