Friday, July 19, 2024

ኢትዮጵያዊያን እንደ አንድ ቤተሰብ ከተባበሩ የሚያዳግታቸው ነገር የለም!

ኢትዮጵያውያን ከፊታቸው በርካታ ሥራዎች ይጠብቋቸዋል፡፡ ከእነዚህ ሥራዎች መካከል ዋነኞቹ ተብለው የሚጠቀሱት የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የሚከናወነው አገር አቀፍ ዘመቻ፣ በበርካታ ችግሮች የተተበተበውን ኢኮኖሚ ከውድቀት ለማዳን ርብርብ፣ ለግጭት ምክንያት የሚሆኑ ፖለቲካዊ አለመግባባቶችን ለማስወገድ የሚረዱ ምክክሮችን ማስፋፋት፣ እንዲሁም ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች በእኩልነት የሚያሳትፍ ምኅዳር ለመፍጠር በጋራ መነሳት የሚሉት ናቸው፡፡ አገር በሰላምና በእኩልነት መኖር የሚቻልባት ለመሆኗ ማረጋገጫው፣ በግልጽነትና በመተማመን መንፈስ በጋራ ለመሥራት አስቻይ ሁኔታዎች መኖራቸው ነው፡፡ ልዩነቶችን የግጭት መቀስቀሻ ለማድረግ የሚያግዙ ፀብ አጫሪ ድርጊቶችን በማስወገድ፣ ለጋራ ጉዳይ አብሮ መሥራት እንደሚቻል በአርዓያነት ማሳየት ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ፖለቲከኞች፣ የእምነት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ መሪዎች፣ መምህራን፣ የሕክምና ባለሙያዎች፣ እንዲሁም በተለያዩ የሙያ መስኮች የተሰማሩ ዜጎች በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ግዴታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የሚያዋጣት ከግጭት ፀድታ ለልማት መሰማራት ነው፡፡ በርካታ ለምና ጠፍ መሬቶች ፆማቸውን እያደሩ ብዙኃኑ ሕዝብ መራብ የለበትም፡፡ መሥራት የሚችሉ እጆች ሥራ ፈተው መሰቃየት ተገቢ አይደለም፡፡ ለአገር የሚጠቅሙ በርካታ ሐሳቦች ታፍነው በችግር መቆራመድ ያሳፍራል፡፡ ኢትዮጵያዊያን እንደ ቤተሰብ በአንድነት ተባብረው መነሳት አለባቸው፡፡ 

የአገር ሰላምና የሕዝብ ደኅንነት አስተማማኝ ሆኖ የየዕለት ተግባርን ማከናወን የሚቻለው፣ ከሸፍጥና ከሴራ በመፅዳት ለወጣቱ ትውልድ አርዓያነት የሚሆን ቅርስ በማኖር ጭምር ነው፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች ያሉባት አገር ብትሆንም፣ ሰላም በማስፈን መሥራት ከተቻለ ተዝቀው የማያልቁ የተፈጥሮ ፀጋዎች አሏት፡፡ ከ110 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ ወጣት ያላት አገር የተፈጥሮ በረከቶቿ ከተሠራባቸው፣ በአፍሪካ ግንባር ቀደም ኃያል ከመሆን የሚያግዳት የለም፡፡ ይህ ዕውን ይሆን ዘንድ ግን ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ በተዘረጋው መልክዓ ምድር ውስጥ የሚኖሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን እንደ አንድ ቤተሰብ መተያየት አለባቸው፡፡ በዚህም ምክንያት በተልካሻ ምክንያቶች ሊከፋፍሏቸውና ሊያጣሉዋቸው የሚፈልጉ የፖለቲካ ኃይሎች መገታት ይኖርባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን የሚያምርባቸው ሲተባበሩና መሰናክሎችን በአንድነት ሲያልፉ እንጂ፣ በማይረቡ ጉዳዮች ሲነታረኩና ሲበጣበጡ አይደለም፡፡ ለልማት መረባረብ ሲኖርባቸው ለሥልጣን ጥመኞች ሲባል አገር የሚያፈርስ ድርጊት ውስጥ መገኘት የለባቸውም፡፡ ሥልጣን ከድምፅ ሳጥን እንጂ ከጠመንጃ አፈሙዝ እንደማይገኝ መታወቅ አለበት፡፡ በርካታ ሥራዎች በሚጠብቃት አገር ውስጥ ለውይይትና ለድርድር ጀርባ በመስጠት፣ እሳት ለመጫር የሚደረገውን ማናቸውንም ዓይነት ጥረት ማምከን ይገባል፡፡ ኢትዮጵያውያን ለአገር ፋይዳ የሌላቸው ድርጊቶችን በመፀየፍ በኅብረት እንደ ቤተሰብ መነሳት አለባቸው፡፡

ከወቅቱ አስቸጋሪነትና ከዓለም አቀፋዊ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች አንፃር፣ ኢትዮጵያዊያን በኅብረት እንደ አንድ ቤተሰብ ለኮሮና ወረርሽኝ መከላከል ብሔራዊ ዘመቻ ድጋፍ ማድረግ አለባቸው፡፡ ሰሞኑን በተጀመረው ብሔራዊ ንቅናቄ በ200 ሺሕ የላብራቶሪ ምርመራዎች 17 ሚሊዮን ያህል ሰዎችን ለመመርመር ታስቧል፡፡ የተጀመረው የአንድ ወር ንቅናቄ ወረርሽኙ ያለበትን ሁኔታና ደረጃ በመገንዘብ ለአዲሱ ዓመት ውሳኔ የሚረዳ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያዊያን የተለመደ ትብብራቸው ይጠበቃል፡፡ በተጨማሪም አፍና አፍንጫን በሚገባ በመሸፈን፣ እጅን ያለ መታከት በማፅዳት፣ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅና ሰዎች ከሚበዙባቸው አካባቢዎች በመራቅ የጥንቃቄ መመርያዎችን ተግባራዊ ማድረግ የግድ ነው፡፡ በዚህ አገር አቀፍ እንቅስቃሴ ተላላፊ በሽታዎችና ሌሎች ሕመሞች ጭምር በሕዝብ ላይ ጉዳት እንዳያስከትሉ፣ የጤና ተቋማት በስፋት ሕክምና እንዲሰጡ ግፊት ይደረጋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሌሎች ሕመሞችና በምግብ ዕጦት የሚሞቱ ወገኖች ቁጥር እያሻቀበ መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ በተጨማሪም በመጪው የትምህርት ዘመን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ የሚያስችሉ ሁኔታዎች በንቅናቄው ይቃኛሉ፡፡ በወረርሽኙ ምክንያት ሥራቸውን አጥተው የተቸገሩና ለወረርሽኙ በቀጥታ ተጋላጭ የሆኑ ጭምር ያሉበት ሁኔታ ስለሚታይ፣ ኢትዮጵያዊያን ዕገዛቸው አስፈላጊ በመሆኑ ዝግጅት ማድረግ አለባቸው፡፡ የኮሮና ወረርሽን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ ምንጫቸው የማይታወቅ ሐሰተኛ መረጃዎችን በጥንቃቄ በመከታተል፣ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጠሩ መዘናጋቶችን በማስወገድ ኢትዮጵያ በወረርሽኙ እንዳትፈታ በትብብር መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ለሕዝብ ጤና፣ ደኅንነትና ሰላም ኃላፊነት ያለባቸው ወገኖችም ብሔራዊ ንቅናቄው ግቡን ይመታ ዘንድ ማገዝ አለባቸው፡፡ ልጆቻቸው በወረርሽኙ ምክንያት ከትምህርት የተስተጓጎሉባቸው ወላጆች፣ እንዲሁም የትምህርት ቤቶች ሥራ መሪዎችና መምህራን ብሔራዊ ጥረቱ እንዲሳካና ትምህርት በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲጀመር ለንቅናቄው ስኬት ዕገዛ ያድርጉ፡፡ በወረርሽኙ ምክንያት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጉዳት የደረሰባቸው ሁሉ፣ ለንቅናቄው ውጤታማነት የሚፈለግባቸውን ያከናውኑ፡፡ ኢትዮጵያዊያን እንደ አንድ ቤተሰብ በኅብረት ከተነሱ ምንም አያዳግታቸውም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በምግብ ዕጦት ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሕፃናት ይሞታሉ፡፡ በቀን አንዴ እጅና አፋቸውን ማገናኘት የሚቸግራቸው ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ በርካታ ሚሊዮኖች ናቸው፡፡ በከተማና በገጠር በሥራ ዕጦት በደሃ ወላጆቻቸው ላይ ጥገኛ የሆኑ በርካታ ሚሊዮን ወጣቶች ናቸው፡፡ አሁንም አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ የሚለመንላቸውና በሴፍቲኔት የታቀፉ ሚሊዮኖች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውጪ ያሉት ደግሞ በከፋ ድህነት በጎስቋላና በተፋፈጉ መንደሮች ውስጥ እየኖሩ የሚራቡ አሉ፡፡ መካከለኛ ገቢ አላቸው የሚባሉት ሳይቀሩ ደመወዛቸው ወይም ገቢያቸው ከምግብና ከቤት ኪራይ ማለፍ የሚያዳግተው ነው፡፡ ለዝንተ ዓለም ኑሮ ያደቀቃቸው ኢትዮጵያውያን ይህ አልበቃ ብሏቸው፣ በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ ችግሮች ሳቢያ የአገራቸው ኢኮኖሚ ተሽመድምዷል፡፡ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ከደረሰው የንግድና የኢንቨስትመንት መቀዛቀዝ በተጨማሪ፣ በተለያዩ ጊዜያት በሚቀሰቀሱ ግጭቶች በርካታ ንብረቶች ወድመዋል፡፡ በበርካታ አካባቢዎች ሥራዎች ቆመው ሠራተኞች ተበትነዋል፡፡ በክልሎች ተንቀሳቅሶ መሥራት አዳጋች እየሆነ ኢኮኖሚው ውርጭ መቶት ቆርፍዷል፡፡ በዚህ ሁኔታ መቀጠል ስለማይቻል በኅብረት ሰላም በማውረድና ለሥራ እጅ ለእጅ ተያይዞ በመነሳት፣ ኢኮኖሚውን ከገባበት ማጥ ውስጥ ጎትቶ ማውጣት ይገባል፡፡ ኢኮኖሚው አገግሞ እንደገና እንዲያንሰራራ ብርቱ ጥረት ካልተደረገ አደጋው ከባድ ነው፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያዊያን እንደ አንድ ቤተሰብ ሆነው አገራቸውን ከገባችበት ችግር ውስጥ የማውጣት ታሪካዊም ሆነ ሞራላዊ ግዴታ ያለባቸው፡፡ ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ ደግሞ ባለሀብቶችን ከሚያተጉ ማበረታቻዎች በተጨማሪ፣ አስተማማኝ ሰላም በመፍጠር በራስ መተማመናቸውን በተጨባጭ ማረጋገጥ  ተገቢ ነው፡፡ መንግሥትና መላው ሕዝብ በዚህ ጉዳይ ላይ የጋራ መግባባት ሊኖራቸው የግድ ይላል፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ከበፊት ጀምሮ እንደ ጉድለት የሚጠቀስባቸው፣ ለውይይትና ለድርድር ዳተኛ መሆናቸው ነው፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው እንዴት ሥልጣን ላይ መቆየት እንዳለበት ሲያሴር፣ ለሥልጣን የሚታገለው ደግሞ እንዴት ሥልጣን ላይ ያለውን እንደሚያስወግድ ዘዴ ሲቀምም ጊዜያቸውን ያባክናሉ፡፡ በመሀል የሚጎዳው ግን ሕዝብ ነው፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ ሥልጣን ላይ ላለው የሚያሸረግዱ ሲኖሩ፣ ነገ ሥልጣን ቢይዝ ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው ከሚያስቡት ኃይል ጋር የሚሞዳሞዱም አሉ፣ ነበሩ፡፡ ሁለቱም ወገኖች በአንድ በኩል ግላዊ ጥቅምን ከማሳደድ በሌላ በኩል ደግሞ በተለያዩ ችግሮቻቸው ምክንያት አገርን ከመጥላት፣ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት እየፈጸሙ አገርን ችግር ውስጥ ሲከቱ ኖረዋል፡፡ አገርን ለባዕዳን የሚሰልሉ ሰይጣኖች ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን ከማራከስ ጀምሮ ሰብዓዊ መብቶችን በመጋፋት ጭምር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሰከነ ፖለቲካዊ ውይይትና ድርድር እንዳይኖር ያሴራሉ፡፡ ኢትዮጵያዊነትን የሚፀየፉና የትውልዱን ሞራል ለማነከት ያሰፈሰፉ ድውዮች ሕግና ሥርዓት ተከብሮ ፖለቲካዊ መስተጋብሩ የሠለጠነ እንዳይሆን፣ ለሚዲያ ዘገባ ብቁ ያልሆኑ አሉባልታዎችን በመንዛት መደናገር ይፈጥራሉ፡፡ በአገርና በሕዝብ ላይ ያመፁ ድውዮችን በመወከል፣ ለግላዊ ጥቅማቸው ሲሉ ብቻ የእውነተኛ አገር ወዳዶችን ስም ያጠፋሉ፡፡ ራሳቸውን ከፖለቲካ ገለልተኛ በማስመሰል ጭንብል ውስጥ ሆነው የአሉባልታ መርዛቸውን እየረጩ ብዙዎችን ያስታሉ፡፡ እነዚህ ከፋይ እስካገኙ ድረስ የጥፋት ጥግ ድረስ ይሄዳሉ፡፡ ከፋፋይ አሉባልታ ከማሰራጨት አልፈው የአገር ሚስጥር ያስፈተልካሉ፡፡ በሳል ፖለቲካዊ ውይይቶች ተካሂደው ፖለቲከኞች እንዳይረጋጉ ያዘናጋሉ፡፡ ለዚህም ነው ለፖለቲካዊ ምክክሮችና ድርድሮች ሲባል፣ ከአሉባልተኞችና ከባዕዳን ተላላኪዎች ሴራ መጠበቅ የሚያስፈልገው፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ ፖለቲከኞች በመርህ ሲመሩ መርዝ ተሸክመው የሚዞሩትን ያመክናሉ፡፡ በዚህም መስክ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ ፖለቲካዊ ምክክሮች፣ ክርክሮችና ድርድሮች በደረጀ መንገድ እንዲከናወኑ መረባረብ የግድ ይሆናል፡፡ ለዚህም ሲባል ኢትዮጵያዊያን በቤተሰባዊነት መንፈስ ፈሩን ማስያዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡

አውሮፓና አሜሪካ ሆነው ከርቀት ኢትዮጵያ ውስጥ ሁከት በመቀስቀስ ሌላ ዙር ዕልቂት እየደገሱ ያሉ ግለሰቦችና ስብስቦች፣ አሁንም ያለ ማቋረጥ ፕሮፓጋንዳቸውን እየነዙ ነው፡፡ የእነዚህን ድርጊት በስኬት ማክሸፍ የሚቻለው ግን የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት የሚረዱ ተጨባጭ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ነው፡፡ ገዥው የብልፅግና ፓርቲም ሆነ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት፣ ለመጪው ምርጫ ዝግጅት ለማድረግ አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር፣ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በኃላፊነት ስሜት እንዲሠሩና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሚችሉበት ዓውድ ለመፍጠር መትጋት አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለመደው የፖለቲከኞች መጠላለፍና አላስፈላጊ ግብግቦች መቆም አለባቸው፡፡ የሥልጣኑ ሉዓላዊ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እየተናቀና ወደ ጎን እየተገፋ፣ የፖለቲከኞች ሽኩቻ ሰለባ መሆን የለበትም፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍንና ኢትዮጵያዊያን የሚፈልጉትን በነፃነት እንዲመርጡ የሚያስችል ምኅዳር የሚፈጠረው ፖለቲከኞች በሠለጠነ መንገድ ሲነጋገሩ ብቻ ነው፡፡ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች የሚሆንበት አምባገነናዊ አካሄድ ለማንም አይበጅም፡፡ ሥርዓት ባለው መንገድ በመነጋገርና በመደራደር የፖለቲካ ጨዋታውን ማሳመር ይገባል፡፡ በሰጥቶ መቀበል መርህ መመራት ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ይበጃል፡፡ የአመፅ ጎዳና ውስጥ ገብቶ ስለነፃነት፣ እኩልነትና ማኅበራዊ ፍትሕ መነጋገር አይቻልም፡፡ የአመፅ ጎዳናው የሚያመራው ወደ ዘር ተኮር ዕልቂትና ውድመት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከመቼውም ጊዜ በላይ ፖለቲከኞችን መጫን ያለባቸው ከአመፅ ጎዳና እንዲርቁ ነው፡፡ የመንግሥት ሥልጣን የጨበጡትም ሆኑ ለሥልጣን የሚፎካከሩት ከአደገኛ ድርጊቶች ራሳቸውን እንዲያቅቡ፣ ኢትዮጵያዊያን በተባበረ ድምፅ ማስገደድ አለባቸው፡፡ ከአሁን በኋላ የሻሸመኔን፣ የዝዋይን፣ የአሳሳን፣ የዴራን፣ የኮፈሌን፣ የአጋርፋን፣ የአርሲ ነገሌን፣ ወዘተ ዓይነት ሰቆቃዎች ለመድገም የሚታገሉትን ጭምር ተባብረው ማስቆም አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያዊያን እንደ አንድ ቤተሰብ ሆነው የጥፋቱን መንገድ ለማስቆም ፖለቲከኞችን መግራት አለባቸው፡፡ ይህንንም ማድረግ አያቅታቸውም፡፡ በዚህ መንፈስ አንድ ላይ ከተንቀሳቀሱ የሚያዳግታቸው ምንም ዓይነት ነገር አይኖርም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...

የዘንድሮ ነገር!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ካዛንቺስ፡፡ ከእንጦጦ በኩል ቁልቁል እያስገመገመ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...

ከሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ተፃራሪ ላለመሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ድብልቅልቅ ስሜት የሚፈጥሩ በርካታ ሁነቶች ማጋጠማቸው አዲስ ነገር ባይሆንም፣ በዚህ ወቅት ከተለያዩ ፍላጎቶችና ዓላማዎች ጋር የተሸራረቡ ሥጋት ፈጣሪ ችግሮች በብዛት እየተስተዋሉ ነው፡፡...