Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበህዳሴ ግድቡ ላይ የሚደረገው ድርድር ዳግም ለአንድ ሳምንት ተገፋ

በህዳሴ ግድቡ ላይ የሚደረገው ድርድር ዳግም ለአንድ ሳምንት ተገፋ

ቀን:

ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌትና አስተዳደርን አስመልክቶ የራሷን የድርድር ሰነድ ካቀረበች በኋላ፣ ግብፅና ሱዳን ጊዜ በመጠየቃቸው ድርድሩ ለአንድ ሳምንት እንዲገፋ ተደረገ።

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በህዳሴ ግድቡ ላይ የሚያደርጉት ድርድር ሐምሌ 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ከተጀመረ በኋላ ወደዚህ ሳምንት መገፋቱ የሚታወስ ሲሆን፣  ድርድሩ ሰኞ ሐምሌ 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ከተጀመረ ከአንድ ቀን በኋላ ዳግም ወደ ቀጣዩ ሳምንት እንዲሸጋገር ተደርጓል።

በዚህ ምክንያቱ ኢትዮጵያ የግድቡ የውኃ ሙሌትና አስተዳደርን የተመለከተ አዲስ ሰነድ ለድርድር ማቅረቧን ተከትሎ፣ ግብፅና ሱዳን ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ሰነድ ለመመልከት ጊዜ እንደሚፈልጉ በመጠየቃቸው እንደሆነ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ማክሰኞ ሐምሌ 28 ቀን 2012 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በዚህም መሠረት ድርድሩ ለአንድ ሳምንት ተገፍቶ በመጪው ነሐሴ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ዳግም ለመገኛኘት ቀጠሮ መያዙን በመግለጫው ተመልክቷል።
ውይይቱ ተቋርጦ ወደዚህ ሳምንት ከመተላለፉ በፊት ሱዳን በውይይቱ አካሄድ ላይ ጥያቄ አቅርባ የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ አንስታ የነበረው ጥያቄም ድርድሩ ከጭብጥ እየወጣ እንዳስቸገረና ጊዜም እያመለጠ በመሆኑ ተገቢ አይደለም የሚል እንደነበር የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል።

ይህንንም መሠረት በማድረግ ሱዳን የራሷን ውስጣዊ ውይይት ለማድረግ እንደምትፈልግ በማሳወቅ ድርድሩ ተቋርጦ ወደዚህ ሳምንት እንዲሸጋገር ጠይቃ፣ ባለፈው ሳምንት ስብሰባ መቋረጡ ይታወሳል።

የሦስቱ አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሰኞ ሐምሌ 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ዳግም በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካይነት ተገናኝተው የመከሩ ሲሆን፣ በዚሁ ዕለት በተጠናቀቀው ውይይታቸውም የግድቡ የውኃ ሙሌትና አስተዳደርን የተመለከተው ድርድር የሚካሄድበትን ሥነ ሥርዓት ተወያይተው ስምምነት ላይ እንደደረሱ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ ያመለክታል።

በዚህም መሠረት ድርድሩን ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት በማካሄድ ውሳኔ ላይ ለመድረስ መስማማታቸውን ገልጿል። በተቀመጠው ጊዜ ውስጥም በተለያዩ መድረኮች የተሰባጠሩ ድርድሮች እንደሚካሄዱ አስታውቋል።

እነዚህም የሦስቱ አገሮች የውኃ ሚኒስትሮች የሚሳተፉበት ድርድር፣ የሦስቱ አገሮች የቴክኒክና የሕግ ባለሙያዎች በተናጠል የሚያደርጉት ድርድር፣ እንዲሁም የሦስቱ አገሮች የባለሙያዎች ቡድን ታዛቢዎች በሚገኙበት የሚደረግ ድርድር መሆናቸውን አስታውቋል።

በቀዳሚነትም የሦስቱ አገሮች የባለሙያዎች ቡድን ስብሰባ ለሁለት ቀናት እንዲካሄድ የተወሰነ ሲሆን፣ የባለሙያዎቹ ቡድንም መግባባት ባልተደረሰባቸው የቴክኒክና የሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያደርገውን ድርድር እንደሆነ አመልክቷል።
አሁን ሦስቱ አገሮች መግባባት ካልደረሱባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሱት የግድቡ የውኃ ሙሌትና አስተዳደርን በተመለከተ በድርድር የሚደረስበት ስምምነት አፈጻጸም ላይ አለመግባባት ቢከሰት የሚፈታበት መንገድ አስገዳጅ ሊሆን ይገባልና አስገዳጅ ሊሆን አይገባም የሚለው አንደኛው ነው።

ሌላው ደግሞ የኢትዮጵያን የወደፊት የውኃ አጠቃቀም ከግድቡ የውኃ ሙሌት ጋር መተሳሰር አለበት የሚለውና የወደፊት የዓባይ ውኃ አጠቃቀም፣ በማንም መልካም ፈቃድ ላይ ሊመሠረት አይችልም የሚለው የኢትዮጵያ የልዩነት አቋም ነው።

በተያየዘ ዜና የአሜሪካ መንግሥት፣ ‹‹ድርድሩ የሦስቱንም አገሮች ጥቅም በማከለ ሁኔታ በስምምነት እንዲቋጭ ለማድረግ ኢትዮጵያ ያላት ጊዜ አጭር ነው፤›› ማለቱን መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ብሉምበርግ የተባለው ሚዲያ ሰኞ ዕለት ዘግቧል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ተናግሮታል የተባለው ይህ መልዕክት፣ ኢትዮጵያ ድርድሩ በስምምነት እንዳይቋጭ እያጓተተች ነው የሚል አንድምታ ያዘለ ቢሆንም ዘገባው ግን ዝርዝር መረጃ አላካተተም።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...