Thursday, February 22, 2024

በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መሀል በምርጫ ጉዳይ የተቀሰቀሰው ውዝግብ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የትግራይ ክልል ምርጫ ማካሄድ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ማሳያ ነው በማለት የማንንም ፈቃድ እንደማይጠይቅ ካስታወቀ በኋላ፣ ሰሞኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከዚህ ድርጊቱ እንዲታቀብ ማስጠንቀቂያ እንደጻፈለት ይታወሳል፡፡ ከዚህም በማለፍ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ትዕዛዝ እንደሚሰጥም አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ክልሉ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የሌለው›› ማስጠንቀቂያ በማለት አጣጥሎታል፡፡ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ በኋላ፣ እሑድ ሐምሌ 26 ቀን 2012 ዓ.ም.  በመቀሌ ከተማ የትግራይ ክልል ልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት ያሳዩት ወታደራዊ ትርዒት በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ 

ዓለም አቀፍ ፈተናዎችን የደቀነው የኮሮና ወረርሽኝ በርካታ የዓለም ክንዋኔዎችን እንዳልነበሩ አድርጓል፡፡ በርካታ ዕቅድና እንቅስቃሴዎች እንዳይሆኑ ሆነው የዚህን ወረርሽኝ ማክተሚያ ይጠባበቃሉ፡፡ ምንም እንኳን በርካታ አገሮችና ተቋማት የወረርሽኙን ማክተሚያ ቢናፍቁና ድኅረ ኮቪድ-19 የሚለውን ቃል ለመጠቀም ቢቸኩሉም፣ የወረርሽኙ ሥርጭትና የጉዳት መጠን ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረና ተፅዕኖውም እየሰፋ ይገኛል፡፡ የዓለም የጤና ድርጅትም ወረርሽኙ ከመጥፋት ይልቅ፣ ከሰዎች ጋር አብሮ መኖሩን ይቀጥላል እያለ ነው፡፡

በወረርሽኙ ሳቢያ ማኅበራዊ ሕይወት ተናግቷል፣ የኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ተሽመድምደዋል፣ እንዲሁም ፖለቲካዊ ክንዋኔዎች ተሰናክለዋል፡፡ ከተሰናከሉ በርካታ የፖለቲካ ክንዋኔዎች መሀል ደግሞ በበርካታ አገሮች ለመከናወን ቀጠሮ ተይዞላቸው የነበሩ ምርጫዎች መሰረዝ ወይም ደግሞ መራዘም ይጠቀሳል፡፡

እንዲህ ያለው ክስተት ካስተናገዱ የዓለማችን አገሮች አንዷ ደግሞ ኢትዮጵያ ነች፡፡ ከመነሻው አገሪቱ በነበረው የፖለቲካ ትኩሳት ሳቢያ ዘንድሮ ይካሄዳል ወይስ ይራዘማል በሚሉ ሁለት ፅንፎች ሲናጥ ሰንብቶ፣ በመጨረሻም ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዲካሄድ ዕቅድ ወጥቶለት የነበረው መጪው አጠቃላይ ምርጫ የኮሮና ወረርሽኝ አደጋው እስኪቀንስ ድረስ እንዲራዘም ተወስኗል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የቀረበለትን የመፍትሔ ሐሳብ መሠረት አድርጎ ምርጫው እንዲራዘም መወሰኑ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህን ውሳኔ መሠረት በማድረግም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በቀረበለት የውሳኔ ሐሳብ መሠረት፣ የፌዴራልንም ሆነ የክልል ምክር ቤት የሥልጣን ዘመን ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ እንዲራዘም ወስኗል፡፡

ይህ ውሳኔ ከመነሻው በተቃርኖ የተሞላውን የፌዴራል መንግሥትና የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትን የሚያስተዳድረው የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ግንኙነትን ከድጡ ወደ ማጡ ወስዶታል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌዴራልም ሆነ የክልል ምክር ቤቶች የሥልጣን መራዘምን የተቃወመው ሕወሓት፣ መጪውን ምርጫ በክልል ደረጃ እንደሚያካሂድ ሲያስታውቅ የሰነበት ሲሆን፣ በዚህም መሠረት ክልላዊ የምርጫ ኮሚሽን አቋቁሟል፡፡

ኮሚሽኑ መቋቋሙን ተከትሎ ዝርዝር የምርጫ አፈጻጸም ሒደት ዕቅዶቹን ለአብነት ያህል የመራጮች ምዝገባ፣ የፓርቲዎች ቅስቀሳ ዝግጅትና የመሳሰሉትን ይፋ ባያደርግም ከሐምሌ 21 ቀን እስከ ሐምሌ 23 ቀን በክልሉ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ምዝገባ እንዲያካሂዱ ባደረገው ጥሪ መሠረት፣ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎችና 11 ግለሰቦች በክልል ደረጃ ለሚካሄደው ምርጫ ተመዝግበዋል፡፡

በክልል ደረጃ ይካሄዳል ለተባለው ምርጫ የተመዘገቡት አምስት ፓርቲዎች ደግሞ ክልሉን በማስተዳደር ላይ የሚገኘውን ሕወሓት ጨምሮ ባይቶና፣ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ፣ የትግራይ ነፃነት ድርጅትና ኢሲምባ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ናቸው፡፡

ሕወሓት በክልል ደረጃ ምርጫ ማድረግ የሚከለክል ምንም ዓይነት የሕግ ክልከላ የለም በማለት፣ የራሱን የምርጫ ሕግ በማውጣትና ክልላዊ  የምርጫ ኮሚሽን በማቋቋም በምክር ቤቱ ምርጫ እንዲካሄድ የተወሰነውን ውሳኔ እንደሚያስፈጽም እየገለጸ የሚገኝ ሲሆን፣ በተቃራኒው ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ክልል ምርጫ ለማካሄድ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ማቆም እንዳለበት የሚገልጽ ደብዳቤ ሐምሌ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ጽፏል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ክልል መንግሥት ምርጫ ለማካሄድ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ‹‹በአፋጣኝ ያቁም›› ከማለት ባለፈ፣ ክልሉ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ በሚጥል ድርጊቱ የሚቀጥል ከሆነ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱና በሌሎች ሕጎች የተሰጠውን ሥልጣን ለመተግበር እንደሚገደድም አስጠንቅቋል፡፡

ይህ ደብዳቤ ለክልሉ ከደረሰ በኋላ እሑድ ሐምሌ 26 ቀን 2012 ዓ.ም. በመቐለ ከተማ የተካሄደው፣ የክልሉ ልዩ ኃይልና ሚሊሻዎች ወታደራዊ ትርዒት በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ በዕለቱ በሠልፉ የተሳተፉ የክልሉ የልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላትም በክልሉ የሚካሄደውን ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ያላቸውን ዝግጁነት ሲገልጹ ተስተውሏል፡፡ ከዚህ ሁነት በኋላ ደግሞ የክልሉ ምክር ቤት ሰኞ ሐምሌ 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ደብዳቤ በመጻፍ ውሳኔን ተቃውሟል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አደን ፋራህ ማክሰኞ ምሽት ከኢቲቪ ጋር ባደረጉት የስልክ ቃለ ምልልስ፣ የትግራይ ክልል በደብዳቤ መልስ መስጠቱ ሳይሆን መፍትሔው ወደ ትክክለኛው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መመለስ ነው ብለዋል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የላከው ደብዳቤ ሕገ መንግሥታዊና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ እንዲከበር መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹በዋናነት ያልነው ክልሉ የፌዴራል መንግሥትን ሥልጣን ያክብር፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔ ያክብር፣ የፌዴራል ሥርዓቱን ከሚጎዳ ድርጊት ይቆጠብ ነው፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

‹‹አሁን አካሄዳቸውን ስናይ የመጫወቻ ሜዳ ውስጥ እያሉ የጨዋታውን ሕግና ደንብ አይመለከተንም፣ የዳኛውም ውሳኔ አይመለከተንም እንደሚሉ ነው የምንቆጥረው፤›› ብለው፣ ‹‹ሁሉንም የሚዳኘውና የሁሉም ነገር መሠረቱ ሕገ መንግሥቱ ስለሆነ፣ የሕገ መንግሥት የበላይነት በማክበር የትግራይ ክልል መንግሥት ተገቢውን ማስተካከያ እንዲያደርግ እናሳስባለን፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት በዚህ የሚቀጥል ከሆነ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደገና በጉዳዩ ላይ ይወያይበታል ብለዋል፡፡

ከዚህ አንፃር የሕገ መንግሥት ምሁራን የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 ንዑስ አንቀጽ ዘጠኝ፣ እንዲሁም ይህን የሕገ መንግሥት አንቀጽ ለማስፈጸም የወጣው አዋጅ ቁጥር 359 ሊጠቀም እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡

እንደ ዘርፉ ምሁራን ማብራሪያ መሠረት አዋጅ ቁጥር 359/1995 ማለት፣ ‹‹የፌዴራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ የወጣ አዋጅ›› ነው፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረት የአዋጁ መነሻ ሐሳቦች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 51 ንዑስ አንቀጽ አንድ መሠረት የፌዴራል መንግሥቱ ሕገ መንግሥቱን የመጠበቅና የመከላከል ሥልጣንና ኃላፊነት የተሰጠው በመሆኑ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 51 ንዑስ አንቀጽ 14 መሠረት ከክልል አቅም በላይ የሆነ የፀጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም፣ በክልሉ መስተዳድር ጥያቄ መሠረት የፌዴራል  መንግሥቱ የመከላከያ ኃይል እንደሚያሰማራ በመደንገጉ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ 16 መሠረት በማናቸውም ክልል ሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱና ክልሉ ድርጊቱን ማቆም ሳይችል ሲቀር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በራሱ አነሳሽነትና ያለ ክልሉ ፈቃድ ተገቢውን ዕርምጃ እንዲወስድ ለፌዴሬሽን ምክር ቤትና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ጥያቄ በማቅረብ በተደረሰበት፣ እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 ንዑስ አንቀጽ 9 ማናቸውም ክልል ሕገ መንግሥቱን በመጣስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ እንደሚያዝ የተደነገገ በመሆኑ የሚሉት ናቸው፡፡

በዚህም መሠረት የዘርፉ ምሁራን እንደሚያትቱት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ መነሻው ይህ መሆኑን ነው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ይጥሳል ላለው የትግራይ ክልል እንቅስቃሴ ከትግራይ ክልል የተሰጠው ምላሽ ደግሞ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱን መልሶ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የሌለው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ›› ሲል ገልጾታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተጻፈውን ደብዳቤ፣ ‹‹የሕገ መንግሥቱን መርሆዎች የሚጥስ፣ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊ ባለቤትነትን የሚፃረር በመሆኑ፣ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና ሕዝብ በፅኑ ይቃወሙታል፤›› በማለት የተቃውሞ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

በማከልም ‹‹የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሚያካሂደው ምርጫ ሕገ መንግሥታዊ ኃፊነቱን መወጣቱ እንጂ ከፍላጎት የሚመነጭ አይደለም፡፡ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ውሳኔ በክልሉ ሕገ መንግሥት የተመሠረተ ነው፡፡ ስለሆነም ምርጫ ማካሄድ ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ዋስትና መስጠትና ኃላፊነትን መወጣት ያመለክታል እንጂ፣ ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ሊሆን አይችልም፤›› በማለት ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡

ከዚህ አንፃር ሁለቱም ወገኖች የሕገ መንግሥቱን የተለያዩ አንቀጾች በመጥቀስ ሕገ መንግሥቱ እንዲከበር የሚያሳስቡና የሚያስጠነቅቁ ሲሆን፣ ጉዳዩም የትኛው ወገን ለሙግቱ የሚጠቅመውን አንቀጽ መረጠ ወደሚል ዕይታ እየተገባ ይመስላል፡፡

ለዚህም አንዱ ማሳያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በደብዳቤው በትግራይ ክልል የሚካሄደው ምርጫ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የሚጥስ ስለሆነ እንቅስቃሴውን በአስቸኳይ እንዲያቆም የሚጠይቅ መሆኑ ሲሆን፣ ከዚህ በተቃራኒው የትግራይ ክልላዊ ምክር ቤት ምላሽም በተመሳሳይ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን መክሰሱ ይስተዋላል፡፡

የክልሉ ምክር ቤት በጻፈው ደብዳቤም፣ ‹‹የትግራይ ሕዝብም ሆነ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ይቅርና ምርጫ ማካሄድ ከዚያ የበለጠና የሰፋ መብት እንዳላቸው በሕገ መንግሥቱ በግልጽ የተደነገገ መሠረታዊ መብት ነው፤›› በማለት፣ ሕገ መንግሥታዊ መብቶች እንዲከበሩ ይጠይቃል፡፡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤትም፣ ‹‹ኅብረ ብሔራዊ ሥርዓቱን የማስቀጠል ፍላጎት፣ ተነሳሽነትና እንቅስቃሴ ባይሆን መደገፍ አልያም አለማደናቀፍ›› እንዳለበት በማሳሰብ፣ ‹‹ይህ ሳይሆን ቀርቶ ሌላ ችግር ቢፈጠር ግን ኃላፊነቱን መወሰድ ያለባቸው፣ በዚህ ኢሕገ መንግሥታዊ ድርጊት የሚሳተፉ አካላት መሆናቸውን ለማሳሰብ እንወዳለን፤›› በማለት ያስጠነቅቃል፡፡

እንዲህ ያለው መካረርና ፍጥጫ ወደማይፈለግ አቅጣጫ ከመሄዱ በፊት ግን የሁለቱን ወገኖች ቁጭ ብሎ መወያየት የሚያሳስቡ በርካቶች ናቸው፡፡ በዚህ መካረር መሀል የሚገኙት ሁለቱም ወገኖች የሚጠቅሱት ሕገ መንግሥትና የሕዝቦች ሉዓላዊነትን ለማክበር በጠረጴዛ ዙሪያ የሚደረጉ ውይይቶችና ሰጥቶ መቀበሎች ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወቱ በመግለጽ፣ አሁንም ሳይረፍድ የውይይት ምዕራፍ እንዲከፈት ይወተውታሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -