ብሔራዊ አትሌቶች ዝግጅት መጀመራቸው ተገለጸ
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በክልልና በከተማ አስተደዳደር ሥር ለሚገኙና ልዩ ድጋፍ ለሚሹ አትሌቶችና አሠልጣኞች የገንዘብ ድጋፍ አደረገ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በኮቪድ 19 ምክንያት ተቋርጠው በቆዩ የአገር ውስጥን ጨምሮ አኅጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን አስመልክቶ ማብራርያ ሰጥቷል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ማክሰኞ ሐምሌ 28 ቀን 2012 ዓ.ም. ጉርድ ሾላ በሚገኘው ጽሕፈት ቤቱ በሰጠው መግለጫ፣ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው አትሌቶችና አሠልጣኞች የተበረከተው የገንዘብ ድጋፍ 3.4 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ የገንዘብ ርክክቡ ለክልልና ለከተማ አስተዳደር አትሌትክስ ፌዴሬሽን ኮሚሽነሮች ፌዴሬሽኑ በሚልክላቸው መሥፈርት መሠረት ተግባራዊ እንደሚደረግም አስታውቋል፡፡ ወረርሽኙ እስካለ ድረስ ዕገዛና ድጋፉ እንደሚቀጥል ተነግሯል፡፡
በወርኃ ታኅሳስ 2012 ዓ.ም. በቻይና ግዛት ሁዋን ከተማ የተከሰተውና ዓለምን በከፍተኛ ፍጥነት እያዳረሰ የሚገኘው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ በእጅጉ ከጎዳቸው ዘርፎች መካከል ስፖርቱ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ወረርሽኙ ከሐምሌ 23 እስከ ነሐሴ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በጃፓኗ ቶኪዮ ከተማ አስተናጋጅነት ሊካሄድ ታስቦ የነበረውን የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ጨምሮ በሚሊዮን ዶላሮች የሚንቀሳቀሱ ስፖርታዊ ክንውኖች እንዲሰረዙ፣ ወይም ወደ ሌላ የውድድር ዓመት ኢንዲሸጋገሩ ማስገደዱ ይታወቃል፡፡ ችግሩ ለአንዳንዶቹ ስፖርቶች እስካሁን ድረስ ቀድሞ ወደነበሩበት መቼና እንዴት ይመለሱ ለሚለው ትክክለኛ መልስ እንዳይገኝ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
በአትሌቲክስ ከታላላቆቹ የዓለም አገሮች ምሥራቅ አፍሪካውያኑ ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን አትሌቶች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ይሁንና ዓለም በአስከፊው ወረርሽኝ መጠቃት ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ ታላላቆቹ አገሮች በሚያዘጋጇቸው ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በመወንጨፍ የሚታወቁት እነዚያ እግሮች ዛሬ ለተረጂነት ተዳርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ችግሩን በመገንዘብ ቀደም ሲል ጀምሮ በወረርሽኙ ምክንያት ችግር ለገጠማቸው ለክልልና ለከተማ አስተዳደር የአትሌቲክስ ፕሮጀክቶች፣ እንዲሁም ለአትሌቶችና ለአሠልጣኞች ዕገዛ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በዚህ ሁኔታ ሲደግፍ የቆየው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ፣ ወረርሽኙ አሁንም ባለመገታቱ በተለይ በክልልና በከተማ አስተዳደሮች ሥር ሆነው ግን ደግሞ ድጋፍ የሚሹ ታዳጊና ወጣት አትሌቶች በዚህ ችግር ተስፋ እንዳይቆርጡ፣ አመራሩ ሐምሌ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በወሰነው መሠረት ድጋፍ እንዲደረግላቸው አድርጓል፡፡
ከተደረገው የገንዘብ ድጋፍ 3.1 ሚሊዮን ብር በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች ለሚገኙ አትሌቶችና አሠልጣኞች፣ ወደ 300 ሺሕ ብር የሚጠጋ ገንዘብ ደግሞ በአዲስ አበባ አካባቢ ለሚኖሩና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው 100 ለሚሆኑ አንጋፋ አትሌቶች (ከዚህ ውስጥ 150 ሺሕ ብር በአቶ አብነት ገብረ መስቀል የተሸፈነ) በድምሩ 3.4 ሚሊዮን ብር መሥፈርት በማውጣት፣ ለተጠቀሱት አትሌቶችና አሠልጣኞች እንዲሰጣቸው መወሰኑን ፌዴሬሽኑ በመግለጫው አስታውቋል፡፡
ድጋፍ የሚደረግላቸው አትሌቶችና አሠልጣኞች የገንዘብ ድጋፉ ከመደረጉ በፊት ተረጂዎቹን በሚመለከት ፌዴሬሽኑ ካስመጠው መሥፈርት መካከል፣ በክልልና በከተማ አስተዳደር ክለቦች የፈረሱባቸው ወይም በችግሩ ምክንያት ክለቡ ወርኃዊ ደመወዝ ያቋረጠባቸው አትሌቶች፣ በክልልና በከተማ አስተዳደር በተቋቋሙ የአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕካላት የሚገኙ አትሌቶች፣ በክልልና በከተማ አስተዳደር የሚገኙ የፕሮጀክት አትሌቶችና አሠልጣኞች፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማናጀሮችን በመጠጋት በግል ሥልጠና የሚያገኙና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው አትሌቶችን የሚያካትት ሲሆን፣ ቀደም ሲል በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አማካይነት ተመሳሳይ ድጋፍና ዕገዛ የተደረገላቸው የብሔራዊ ቡድንና የኦሊምፒክ አትሌቶችን አይመለከትም ተብሏል፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጠው የቆዩ አኅጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በሚመለከት፣ እየተደረገ ያለውን የዕቅድ ዝግጅት ምን እንደሚመስል ማብራራቱን አስታውቋል፡፡
የዕቅዱን አስፈላጊነት አስመልክቶ ፌዴሬሽኑ፣ ወረርሽኙ በአትሌቶችና በአትሌት ማኅበረሰቡ ላይ ያሳደረውን ሁለንተናዊ ተፅዕኖ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እየተዘጋጀ መሆኑን በመግለጫው አካቷል፡፡
የዕቅዱን ዓላማ በሚመለከት ችግሩ በአትሌቲክሱ ማኅበረሰብ ላይ ያሳደረውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት በጥናት በማስደገፍ፣ ተጎጂዎችንና የጉዳቱን ደረጃ፣ የተጎጂዎችን መጠንና የጉዳቱን ጥልቀት በመለየትና በመተንተን ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ማድረግ ታሳቢ ያደረገ ስለመሆኑ ጭምር አብራርቷል፡፡
የወረርሽኙን የጉዳት መጠን ለማወቅ በአዲስ አበባ አካባቢ ፈጣን የዳሰሳ ጥናት ተካሂዷል፡፡ በሥነ ልቦናው ረገድም የጤናና ተያያዥ ጉዳዮች ማለትም በወረርሽኙ ጊዜ አትሌቶች ማድረግ ስለሚገባቸው ክህሎት፣ የአኗኗር ዘይቤና መሰል ትምህርታዊ ሰነዶች ተዘጋጅተው ሥልጠና ስለመሰጠቱ ጭምር በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
ችግሩን ለመቋቋምና አትሌቶቹን ወደ ነበሩበት ለመመለስ ይቻል ዘንድ፣ ከመንግሥት በሚገኘው የፋይናንስ ድጋፍ መሠረት የጉዳቱ ሰለባ ለሆኑ አትሌቶችና የአትሌት ማኅበረሰብ ሊሰጥ የሚገባው የድጋፍ ዓይነትና መጠን፣ ድጋፍ የሚሰጥበት ቦታና ፕሮግራም በሚመለከት ፌዴሬሽኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በዝርዝር ስለመነጋገሩም አስታውቋል፡፡
ቀጣይ አኅጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በሚመለከት ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤፍ) የውድድር ፕሮግራሞችን አውጥቶ መላኩን አስረድቷል፡፡ በዚህ መሠረት ፌዴሬሽኑ ለዳይመንድ ሊግ ውድድር 12 ብሔራዊ አትሌቶችን በልዩ ጥንቃቄ (የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መቼና እንዴት እንደሚቆም ስለማይታወቅ) ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡