የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ 12ኛ መደበኛ ጉባዔውን ማክሰኞ ሐምሌ 28 ቀን 2012 ዓ.ም. ሲያካሂድ፣ የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ካደረጉት ንግግር የተወሰደ፡፡ ሚኒስትሯ አክለውም አገር ሰላም እንዳትሆን የሚፈልጉ ኃይሎች የከፋ ጉዳት ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውንና ይህንን ጥረት ማምከን እንደሚገባ፣ ካልሆነ ግን በርካታ ነገሮች ከእጅ አምልጠው የበለጠ ችግር እንደሚፈጠር አሳስበዋል፡፡ ሕግ ማስከበር የመንግሥት ዋነኛ ድርሻ መሆኑን ጠቁመው፣ ነገር ግን ሕግ ማስከበር ከቅን ልቦና ጋር አብሮ ካልሄደ ከንቱ ልፋት እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ የሃይማኖት ተቋማትና አባቶች በኅብረተሰቡ ውስጥ የዋሉና ያደሩ ችግሮችን በሠለጠነ አስተሳሰብና በቅን ልቦና ለማስተካከል ድርሻቸው ጉልህ ነው ብለዋል፡፡