ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚካሄደው ማኅበረሰብ አቀፍ ንቅናቄና ምርመራ ዘመቻ ከ17 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ሐምሌ 28 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሐምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ ያደረጉት ማኅበረሰብ አቀፍ የኮቪድ- 19 ንቅናቄና ምርመራ ዘመቻ ለአንድ ወር የሚቆይ ሲሆን፣ በእነዚህ ጊዜያት በሚከናወነው ዘመቻ 17 ሚሊዮን ሰዎችን ለማዳረስና 200 ሺሕ የላብራቶሪ ናሙና ምርመራዎችን ለማድረግ መታቀዱን ዶ/ር ሊያ ተናግረዋል፡፡
በዘመቻው ማኅበረሰቡ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ሥርጭቱን ለመግታት ዋነኛ ተዋናይ መሆን የሚጠበቅበት ሲሆን፣ በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችና በተለያዩ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች የሚሰጡና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የወጡ ክልከላዎች ላይ ቁጥጥር የሚደረግም ይሆናል፡፡
መታጠብ፣ መራራቅ፣ መሸፈንና መተሳሰብ የሚሉትን የ ‹‹መ›› ሕጎች ዘወትር በመተግበር ራስንና ማኅበረሰብን ከቫይረሱ መጠበቅ የዘመቻው ዓላማ ነው።
የላብራቶሪ ምርመራዎቹ ቫይረሱ በብዛት በታየባቸው አካባቢዎችና በከተሞች አካባቢ ትኩረት ሲያደርግ፣ ዘመቻው የተሳካ እንዲሆንም ከፌደራል እስከ ክልል መዋቅር ባሉ አደረጃጀቶች የሕዝብ ንቅናቄ እየተሠራ እንደሆነ ዶ/ር ሊያ አስታውቀዋል፡፡
በሚቀጥለው ሳምንት የላቦራቶሪ ምርመራ እንደሚጀመር፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) እና ሌሎች መከላከያ ዘዴዎችን የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሠራና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎቹ ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረው፣ ኅብረተሰቡ ለዘመቻው ስኬት እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል።