Friday, December 8, 2023

ኮቪድ-19 ሰብዓዊ ቀውስ ባላሸቃት የመን

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ሥር የሰደደ ችጋር፣ የንፁህ ውኃ ዕጦት፣ የግልና አካባቢ ንፅህና ጉድለትና የተፋለሰ የጤና ሥርዓት በብጥብጥና በእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በምትታመሰው የመን፣ ሰብዓዊ ቀውስ ከተከሰተ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ዛሬ ላይ ደግሞ ኮቪድ-19 ሌላ መከራ ይዞ መጥቷል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2014 ወዲህ በየመን የተቀሰቀሰው ግጭት በሁለቱ ጽንፍ ተዋጊዎች በኩል የተደረሰው የተኩስ አቁምና መንግሥት የመመሥረት ስምምነት ወደ ሰላም የመምጣበት ተስፋ ቢያሳይም፣ ለሰብዓዊ ቀውስ በተጋለጡና ጥቃት በሚፈጸምባቸው የየመን አካባቢዎች ከስምንት ወራት በፊት ጀምሮ በዓለም የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሌላ መከራን ይዞ መጥቷል፡፡

ኅብረተሰቡም ሆነ የጤና ባለሙያዎች ከኮቪድ-19 ራሳቸውን የሚጠብቁበት ቁሳቁስና የሕክምና ባለሙያዎች እጥረት መኖርም በሌላ ሕመም የሚሰቃዩ ሰዎች ጭምር እንዳይታከሙ ምክንያት ሆኗል፡፡

በረሃብ ውስጥ የሚገኙት የመናውያን ረሃባቸውንም ብቻ ሳይሆን ሕመማቸውንም ማስታገስ እየተሳናቸው ነው፡፡ የሕክምና ባለሙያዎችም ሥራቸውን እየለቀቁ መሆኑ ታውቋል፡፡

ኮቪድ-19 ሰብዓዊ ቀውስ ባላሸቃት የመን

 

ስታንፎርድ ዴይሊ በድረ ገፁ እንዳሰፈረው፣ 80 በመቶ የሚጠጋው የየመን ሕዝብ ጎርሶ የሚያድረው በሚሰፈርለት ሰብዓዊ ዕርዳታ ነው፡፡ ከ29 ሚሊዮን የየመን ሕዝብ መካከል አብዛኛውም በሰቆቃ የሚኖር ነው፡፡

በኢራን፣ በሳዑዲ ዓረቢያ፣ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች፣ በአሜሪካና በእንግሊዝ የሚደገፉ የየመንና ከሌላም አካባቢ የሰረጉ ተዋጊዎች ከሚፋለሙባት የመን፣ ጦርነቱን ለማቆም ድርድሮች ቢኖሩም፣ ጦርነቱ መቼ እንደሚቆም አይታወቅም፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ ተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረስም፣ ባለፉት ሁለት ወራት ጦርነቱ መፋፋሙና ባለፉት ሁለት ሳምንታት ደግሞ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የስታንፎርድ በቀውስ ውስጥ ያሉ ሕፃናት ፕሮግራም ኃላፊና የሕፃናት ሐኪም ፖል ዋይዝ (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ወራት የአየር ድብደባው ጨምሯል የሚሉት ፕሮፌሰር ዋይዝ፣ አላባራ ባለው ጦርነት በየመን የበሽታዎች ወረርሽኝ መለመዱንና የአየር ድብደባውና ጦርነቱ የውኃ መሠረተ ልማቶችን ማውደሙ በመላ አገሪቱ ኮሌራ እንዲከሰት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡  

 ሕፃናት ለኮሌራ ይበልጥ እየተጋለጡ ሲሆን፣ ቤተሰቦችም ሕክምና ለማግኘት ተቸግረዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2016 ጀምሮ 2,000,000 ሰዎች በኮሌራ ሲጠቁ፣ ችግሩን ለመቆጣጠርም እስካሁን አዳጋች ሆኗል፡፡

የየመን የጤና ሥርዓት በጦርነቱና በኮሌራ ምክንያት መፈተኑ፣ የጤና ባለሙያዎች ያለ ክፍያ መሥራታቸውና ከኮቪድ-19 ሊከላከላቸው የሚችል ራስን የመጠበቂያ ቁሳቁስ አለመኖሩ፣ የጤና ባለሙያዎች በዘርፉ እንዳይገቡ አድርጓቸዋል፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ደግሞ የየመንን ሁኔታ ለከፋ ችግር ዳርጎታል፡፡ የካንሰር፣ የስኳርና የሌላ በሽታ ሕመምተኞች የጤና ድጋፍ እያገኙም አይደለም፡፡ በመን እስከ ሐምሌ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በኮቪድ-19 የተያዙት ቁጥር 1,600 ቢሆንም፣ ኅብረተሰቡ ስላልተመረመረ ትክክለኛውን መረጃ ማወቅ አልተቻለም፡፡

በኅብረተሰቡ ዘንድ የኮቪድ-19 ሥርጭት ያለበትን ለማወቅ እንዳይቻልም በአገሪቱ ያለው ድህነት፣ የጤና ሥርዓቱ በፈተና ውስጥ መሆንና ጎርፍ ተፅዕኖ አድርገዋል፡፡

ወረርሽኙ በየመን በተለይ የእርስ በርስ ጦርነት ባለባቸው ሥፍራዎች የጎላ ሲሆን፣ አካባቢዎቹም የሰብዓዊ ዕርዳታውን አብዝተው የሚሹ ናቸው፡፡ ሆኖም በየመን ለችግር ተጋላጭ የሆኑትን ዜጎች ለመድረስ ውስብስብ ችግሮች አሉ፡፡

የወደቦች መዘጋትና የቁሳቁስ መወደድ ላይ ወረርሽኙ ተጨምሮ፣ ለነዋሪው በቂ ሰብዓዊ ዕርዳታ ማድረስም አልተቻለም፡፡ ይህም የመናውያንን ከማይወጡት መከራ ከቷቸዋል፡፡

ሰሞኑን ደግሞ ራሳቸውን ለማስተዳደር ያወጁት የደቡብ የመን ጽንፈኞች ሳውዘርን ትራንዚሽናል ካውንስል (ኤስቲሲ) በየመን ይመሠረታል ተብሎ በሚታሰበውና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ከሚሰጠው መንግሥት ለመቀላቀል ተስማምተዋል፡፡

ከሐምሌ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት በ30 ቀናት ውስጥ ይመሠረታል ተብሎ የሚታሰበው የየመን መንግሥት፣ በሳዑዲ ዓረቢያ በሚመራው ጥምረትና በደቡብ የመን በሚገኙት የሁቲ አማፅያን (ኤስቲሲ) መካከል ተኩስ አቁሙን ያረጋግጣል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

ኤስቲሲ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የሚደገፍ ሲሆን፣ ሳዑዲ ዓረቢያ መሩ ደግሞ ሐውቲዎቹን የኤስቲኤስ ተዋጊዎች የሚፃረር ነው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በየመን ያለው ቀውስ ያበቃ ዘንድ በሐውቲዎቹና በሳዑዲ ዓረቢያ መሩ ጦር መካከል በሰኔ 2012 ዓ.ም. የተደረሰው የተኩስ አቁምና መንግሥት የመመሥረት ስምምነት እንዲፀናም ጥሪ አቅርቧል፡፡

ይህም እ.ኤ.አ. ከ2014 ጀምሮ የ100,000ዎችን ሕይወት የነጠቀውንና የመንን ያፈራረሰውን ጦርነት ለማቆም ያስችላል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -