በተመስገን ተጋፋው
ኮሮና ቫይረስን (ኮቪድ-19) ለመከላከል ያስችላል የተባለ ማኅበረሰብ መር የተፋጠነ የንፁህ ውኃ አቅርቦት፣ የግልና የአካባቢ ንፅህና አጠባበቅ ፕሮጀክት ይፋ ሆኗል፡፡
በኢትዮጵያና በፊንላንድ መንግሥት ትብብር የሚተገበረው የንፁህ ውኃ፣ የግልና አካባቢ ንፅህና ፕሮጀክት 200,000,000 ብር የሚፈጅ ሲሆን፣ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች በተመረጡ ሥፍራዎች የሚተገበር ይሆናል፡፡ ለፕሮጀክቱ የፊንላንድ መንግሥት 2.67 ሚሊዮን ዮሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ 81.4 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ይሆናል፡፡
የኮዋሽ ፕሮጀክት ኃላፊ ሚስተር አትሮ ሶሚኒን እንደገለጹት፣ ለቀጣዮቹ ስድስት ወር የሚተገበረው ፕሮጀክት፣ የንፁህ ውኃ አቅርቦትን በማረጋገጥና የአካባቢ የግል ንፅህናን በማስጠበቅ ማኅበረሰቡ ራሱንና ቤተሰቡን ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠብቅ የሚያግዝ ነው፡፡
በፕሮጀክቱ 25 ሺሕ ሰዎችን አሠልጥኖ በ76 ወረዳዎች በማሰማራት ማኅበረሰቡ ስለኮቪድ-19 አስከፊነት እንዲያውቅ ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች የሚሠሩም ይሆናል፡፡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የማኅበረሰቡን ፍላጎት መሠረት በማድረግ በትምህርት ቤቶችና በጤና ተቋማት ውስጥ 2,000 የውኃ፣ የንፅህና መጠበቂያና የመፀዳጃ ቤት ግንባታዎችን ለማከናወን ዕቅድ መያዛቸውንም ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
ወረርሽኙ ማኅበረሰቡ ዘንድ በስፋት ከመሠራጨቱ በፊት ጥንቃቄዎችን እንዲያደርግና ራሱን እንዲጠብቅ ፕሮጀክቱ ትልቅ ሚና ይጫወታል ያሉት ኃላፊው፣ ማስክ፣ ሳኒታይዘር፣ ፈሳሽ ሳሙና እንዲሁም በየወረዳው በሚገኙ ተቋማት ውስጥ በመሄድ የእጅ መታጠቢያ ውኃ የሚይዙ ታንከሮችን በማስቀመጥ ማኅበረሰቡ ከኮሮና ራሱን እንዲጠብቅ ለማስቻል ድጋፍ እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡
የውኃ ልማት ኮሚሽነር በሻህ ሞገስ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የውኃ አቅርቦት ትልቁን ድርሻ ስለሚይዝ፣ በክልሎች ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ፕሮጀክቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡
የማኅበረሰብ መር የተፋጠነ የውኃ፣ የግልና የአካባቢ ንፅህና ፕሮጀክት ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ ከ17,000 በላይ የውኃ ፕሮጀክት ግንባታዎችን አጠናቆ ማኅበረሰቡ እንዲመራቸው መስጠቱን ሚስተር ሶሚኒን ተናግረዋል፡፡
የእነዚህን ፕሮጀክቶች 70 በመቶ የገንዘብ ወጪ የሸፈነው የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሆነና በዚህም ከ4,000,000 ሰዎች በላይ መጠቀማቸውን አክለዋል፡፡