Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርለአፍሪካ ቀንድ መፍትሔ አመንጪ እንጂ ችግር እንዳንሆን!

ለአፍሪካ ቀንድ መፍትሔ አመንጪ እንጂ ችግር እንዳንሆን!

ቀን:

በገለታ ገብረ ወልድ

ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካም ምሰሶ ከሚባሉት አገሮች ተርታ የምትመደብ ነች ማለት ግነት የለውም፡፡ የሰው ዘር  መገኛ፣ የቀደምት ሥልጣኔ ባለቤት፣ የነፃነት ዓርማ፣ በተለይም የቅኝ ገዥዎቸን ቀንበር በመስበር ለጥቁሮች ነፃነት በር ከፋች፣ የራሷ ቋንቋዎች ባለቤት፣ የእምነት፣ የፊደላት፣ የዜማና የፍልስፍና መሶብ መሆኗም ለአባባሉ ማሳያ ናቸው፡፡ በዘመናዊው ዓለም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ አፍሪካ ኅብረት) መሥራችና የሰላም አስከባሪ ኃይል ብርቱ አሰማሪ መሆኗም በአፍሪካ  ወሳኝነቷን አመላካች ናቸው፡፡

ከእነዚህ ፀጋዎች በተቃራኒው በድርቅና በድህነት ውስጥ የቆየች፣ ለዘመናት በፀረ ዴሞክራስያዊ የፖለቲካ ሥነ ምኅዳር ውስጥ የኖረች፣ በእርስ በርስ ጦርነትና በተለያዩ የውጭ ኃይሎች ጥቃት ስትወጋ መኖሯ ሊካዱ አይችሉም፡፡ ከዚህ ባሻገር የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ በተለያዩ የእርስ በርስና የውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ ውስጥ የወደቀ እንደ መሆኑ፣ ትናንትም ሆነ ዛሬ ለአደጋ ተጋላጭ እንድትሆን አስተዋጽኦ የሚያደርግላት ነው፡፡ የኢትዮጵያ የውስጥ መረጋጋትና ዴሞክራሲያዊ መሆን ከሕዝቦቿ አልፎ፣ ለቀጣናው መረጋጋትና ዕድገትም ወሳኝ መሆኑ አይቀርም፡፡ በዚህ ጽሑፍም የቀጣናውን ሁኔታና የእኛን አገር ነባራዊ ሁኔታ ለመመልከት ይሞከራል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ጥንታዊው የአፍሪካ ቀንድ ብዙ ውጣ ውረድ፣ ውጥረትና ሥቃይ በታሪክ ያልተለየውና አሁንም የማያጣው አካባቢ ሆኖ ዘመናትን መዝለቁ ይታወቃል፡፡ ቅኝ ገዥዎችም ለምዝበራ እንዲመቻቻው እየነጣጣሉ ሲያባሉት የኖረና ዛሬም ጠባሳው ያለተወገደለት የምድረ አፍሪካ  አካልም  ነው፡፡ የአፍሪካ ቀንድ በዋናነት ስድስት ገደማ አገሮችን (ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ጂቡቲ፣ ኬንያና ሶማሊያ)  የያዘ  ነው፡፡  በቀይ ባህር፣ በኤደን ባህረ ሰላጤና በህንድ  ውቅያኖስ ዳርቻ የሚዘረጋ ድንበር ያለው ይህ ቀጣና የብዙ ኃያላን አገሮችን ትኩረት የሚስብ በመሆኑ ተፈጥሯዊ ወሳኝነቱን ያጎላዋል፡፡

እንዲሁም ከዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮችና ከዚያም ባሻገር ከሚገኙ ሕዝቦች ጋር ለሺሕ ዓመታት የዘለቀ ጠንካራ የንግድ ትስስር መሥርቶ ሲራራ ነጋዴዎች ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ በተዘረጋው የንግድ መስመር እየተመላለሱ ሲነግዱ የኖሩበት አካባቢ ነው፡፡ ቀጣናው ሁለቱንም ታላላቆቹን እምነቶች ክርስትናና እስልምና በማለዳ የተቀበሉ ሕዝቦች መገኛም ነው፡፡ እነዚህ እሴቶችን ለጥፋት ለማዋል ግን በየአገሮቹ በተለያዩ ጊዜዎች የሚነሱ ፖለቲከኞች በፈጸሟቸው ሴራዎች ግጭት፣ ሽብርተኝነትና ድንበር ዘለል ውጊያዎች ሲፈጸሙ ነበር የቆዩት፡፡ አሁንም የእኛን አገር ጨምሮ በየአካባቢው አለመረጋጋት እንዲኖር የማይተኙ ኃይሎች  አሉ፡፡

አካባቢው በርዝማኔው ከዓለም ወንዞች ቀዳሚ የሆነውና ከስድስት ሺሕ ኪሎ ሜትር  በላይ በመጓዝ ግብፅ የሚደርሰው የዓባይ ወንዝ የሚነሳበት ሲሆን፣  የክፍለ ምድሩ ማዕከል የሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ የውኃ ጋን እስከ መባል የደረሰች ከሞላ ጎደል ወደ ሁሉም አካባቢዎች (ከኤርትራና ጂቡቲ በስተቀር) የሚፈሱ ድንበር ዘለል ወንዞችና ሐይቆችን ያቀፈች ነች፡፡ ያም ሆኖ ዛሬም ድረስ ቀጣናው ድርቅ፣ ድህነት፣ ግቀጭትና የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ስደትና የዜጎች መንገላታት ያልተለየው  ሆኖ እንደ ቀጠለ መሆኑ አሳዛኝ እውነታ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ላለ አካባቢ ደግሞ አሰባሳቢና ምሰሶ የምትባለው አገር የሚገጥማት የውስጥም ሆነ የውጭ መቃወስ፣ ሁሉንም አገሮች ለተጨማሪ ችግር የሚያጋልጥ መሆኑ አይቀርም፡፡

ከዚህ አንፃር በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እየታየ ያለው የሕዝብ ለሕዝብ ግጭት (ሞትና ስደት)፣ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት  ውድመት፣ እንዲሁም የፖለቲካ ስክነት ማጣት በጥንቃቄ መታየት ያለበት ነው፡፡  የዘውግ ተኮሩ  ፌዴራሊዝም ብቻ ሳይሆን በውጭ ኃይሎች ጎትጓችነት እየተስተዋለም ነው፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያውያንን ከማስለቀስ ባልተናነሰ አሜሪካና የአውሮፓ  ኅብረትን ጨምሮ የተለያዩ ወዳጅ ሕዝቦችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን የሚያሳስብ ቀውስ እየሆነ ያለው፡፡ ለኢትዮጵውያን ፖለቲከኞችም ከአገራዊ ኃላፊነታቸው በላይ ሩብ ቢሊዮን ለሚሆነው የቀጣናው ሕዝብ መጨነቅ እንዳለባቸው ማስጠንቀቂያ የሚሆነው ይኼ እውነታ ነው፡፡

በእርግጥ ምሥራቅ አፍሪካ የሚያግባባ ሥርዓት መፍጠር ተስኖት የቆየው፣  እንዲሁም የመነጣጠልና የመዘነጣጠል መጥፎ የታሪክ ጓዝ ተሸክሞ እዚህ የደረሰው በውጭ ኃይሎች ሴራና ገፋፊነት ጭምር እንደነበር የታወቀ  ነው፡፡  በተለይ ዓባይን የመሳሰሉ የተፈጥሮ ሀብቶቹን ተስማምቶ እንዳይጠቀም አንዱን በአንዱ ላይ በማስነሳት፣ ለሌሎች መጠቀሚያ ተዳርጎ ቆይቷል፡፡ ሌላው ቀርቶ የአካባቢው አገሮች ተመሳሳይ ወይም የጋራ የሆነ የቅኝ ግዛት ታሪክ እንኳን ያልነበራቸው መሆኑ፣  ከአብሮነት ይልቅ መለያየትን እንዲያውጠነጥኑ አድርጓል፡፡ አንዱ በጣሊያን፣ አንዱ በፈረንሣይና አንዱ በእንግሊዝ የቅኝ አገዛዝ ሥርዓት ውስጥ የቆዩ እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡ እንግዲህ የኢትዮጵያና የሌሎቹ የተረጋጉ አገሮች (ኬንያና ጂቡቲ) ሚና እነዚህን ነባራዊ ሁኔታዎች ለመቀየር መትጋት ሊሆን ይገባል፡፡

ከአፍሪካ ቀንድ አገሮች ውስጥ ሦስቱ (ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ) ዘመናትን ተሻግሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በቂ መፍትሔ ሊገኝለት ያልቻለ ከባድ የእርስ በርስ ጦርነት አዙሪት ውስጥ ተዘፍቀው የቆዩ ብቻ ሳይሆኑ፣ አሁንም ሙሉ በሙሉ ሰላምና የተረጋጋ ፖለቲካ ያገኙ አገሮች ሊባሉ አይችሉም፡፡ በእርግጥ በእነዚህ አገሮች ባለፉት 15 ዓመታት ገደማ  የተረጋጋ ሁኔታና  ሰላም እንዲሰፍን አገራችን የተጫወተችው ሚናና የከፈለችው መሰዋዕትነት እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም፡፡  በአንድም ሆነ በሌላ ከየአገሮቹ የሚፈናቀሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችንም ስታስጠልል ነበር የቆየችው፡፡ አሁን የምንገኝበት አገራዊ ሁኔታ ግን ለሌሎች መጠለያ እንድንሆን የሚደርግ ሳይሆን፣ ከተቃወሱት ተርታ የሚያሠልፈን ነው፡፡

አሁን በተጨባጭ በኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት እየመጣ ላለፉት 30 ዓመታት ገደማ ነግሦ የነበረውን ብሔር ተኮር የሆነ ፌዴራሊዝም ጉድለቶች እያረሙ ለመቀጠል እየታሰበ ባለበት ጊዜ ውስጥ፣ እያገጠመ ያለው መቃወስ በቀደመው ደረጃ እንኳን ቀጣናውን  ስለማገዛችን አሥጊ እየሆነ ነው፡፡ በዚህም  መዘዝ  ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛ ከሚያመርቱ ጥቂት የዓለማችን ክፍሎች ተርታ ተመድበን ራሳችንን ብቻ ሳይሆን፣ ዓለምን ተስፋ እንዳናስቆርጠው ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ፖለቲካችን ከመጠቃቃት፣ ከግጭትና ከትርምስ ወጥቶ በመነጋገርና በመደማመጥ ላይ እንዲቃኝ መሥራት የሁሉም ኃይሎች ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡ መንግሥትም ሕግ የማስከበርና የአገር ሉዓላዊነት የመጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡

በመሠረቱ የአፍሪካ ቀንድ ዥንጉርጉር ገጽታና ዘወትር በቋፍ ሆኖ የሚያስጨንቅ የደኅንነት ሁኔታ ያለው ክፍለ አኅጉር  መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በጉርብትናቸው የአንዱ አገር ሁኔታ በሌላው ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድርም ነው (ለአብነት ያህል የቅርቡን ሁኔታ ብናነሳ በኢትዮጵያ የሕወሓት/ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በሕዝብ ቁጣ መመታት፣ በሱዳንም የአል በሽርን ከ30 ዓመታት በላይ አገዛዝ ለማሽቀንጠር ገፊ ምክንያት እንደሆነ ተንታኞች መናገራቸው አልቀረም ነበር፡፡ መጠኑ ይለያይ እንጂ በኤርትራም ተመሳሳይ ንቅናቄ ተሞክሮ ነበር)፡፡ ሒደቱ ያበቃለት ባይሆንም በየአገሩ የሚስተዋለው ፀረ ዴሞክራሲን የመፀየፍ ዕርምጃ ግን ወደ ኋላ የሚመልስ ሳይሆን፣ በትውልድ ቅብብሎሽ አንድ ደረጃ እንዲያድግ ነው ሁሉም ማሰብ ያለበት፡፡

አንዳንድ ተንታኞች እንደሚሉት ይህ ትስስራዊ ተፅዕኖ የሚፈጠረው የአፍሪካ ቀንድ አገሮችና በየአገሮቹ የሚኖሩ ሕዝቦች ጥንታዊና በደም፣ በቋንቋ፣ በባህልና በታሪክም የተሳሰሩ በመሆናቸው ነው፡፡ የመልከዓ ምድር፣ የሥነ ሕዝብ፣ የፖለቲካና የባህል ልዩነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከቅኝ ገዥዎች አንስቶ፣ የውጭ ኃይሎች ተፅዕኖም ለመከፋፋልና ለግጭት ሲያጋልጣቸው መቆየቱም  አይዘነጋም፡፡ በተለይ ዛሬም ድረስ ከቀጣናው ውጪ ያሉ ኃይሎች ‹‹የውክልና ፖለቲካ›› ተዋናዮችን በቀላሉ  ለማግኘት ተኝተው እንደማያድሩ ማሰላሰል ተገቢ ሆኖ ይገኛል፡፡ ይህን መገንዘብና መጠንቀቅ የማይችል ፖለቲከኛ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልግ አይደለም፡፡

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሚጠቀሰው መረጃ 250 ሚሊዮን ከሚደርሰው የቀጣናው ሕዝብ 68 በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች ሲሆኑ፣ በየወሩ በአሥር ሺዎች ወደ አውሮፓና መካካለኛው ምሥራቅ ለመሰደድ የሚዳክሩበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በሜዲትራንያን ባህርና በየበረሃው በየጊዜው የሞት ፅዋ እየተጎነጩ እስከ ዘለዓለሙ የሚያሸልቡ ታዳጊዎች መገኛም ይኸው መከረኛ ቀጣና መሆኑ ሊዘነጋ አይችልም፡፡ ይህ አደጋ ደግሞ አንዱ አገር ከሌላው የሚሻልበት አይደለም፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ለምን ከልማትና የዕድገት ጉዞ እየተነጠቡ፣ ለትርምስና ውዝግብ በር ሊከፍቱ ይችላሉ ብሎ ውስጥን መፈተሽ ይገባል፡፡

ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ ዓይነት የለውጥ ጅምር የታየ ቢሆንም፣ የፖለቲካ መካረሩና ዘረኝነቱ ልማቱን እየጎዳ ነው፡፡ የእርስ በርስ ግጭቱ  በመባባሱ የተነሳም የነበሩ ልማቶችም እየወደሙ፣ ሕዝቡ እየተሳቀቀ መሆኑ አገረ መንግሥቱን ክፉኛ እየናጠው ነው፡፡ ይህ ዓይነቱን ወደ ኋላ የሚመልስ፣ የአገርን ህልውና የሚያናጋና ቀጣናውንም ለተጨማሪ ቀውስ የሚዳርግ አካሄድን አለማረም፣ በአገር ላይ ቀውስን ከመጋበዝ ባሻገር ለምሥራቅ አፍሪካም ሆነ ለአፍሪካ አደጋ መጋረጡ አይቀርም፡፡ እንግዲህ አሁን ያለውን የእኛ ትውልድ ሊያሳስበው የሚገባው ይህ አደጋ ነው፡፡

በመሠረቱ እስካሁን ባለው ታሪክ ከእነ ችግሯ፣ በዚህ አስከፊ የምሥራቅ አፍሪካ ገጽታ ምክንያት ኢትዮጵያ የቀጣናውን ችግሮች በተናጠልና በጋራ መድረኮች ለመፍታት ወይም ለማስታገስ ሙከራ ስታደርግ ነበር የቆየችው፡፡ በተለይ ስምንት አባላት ባሉት   ‹‹ኢጋድ›› በተሰኛው የቀጣናው መንግሥታት የጋራ የምክክር መድረክ አማካይነት የተለያዩ ጉዳዮች እንዲፈጸሙ ስታደርግ ቆይታለች፡፡ በዚህም አንዳድ ተንታኞች  የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ካስማና ማዕከል ሆና የምትታየው ኢትዮጵያ ናት እስከ ማለት ደርሰው ነበር፡፡

ይህ ታሪካዊና ቀጣናዊ መሪነት ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚችለው ግን ተወደደም  ተጠላም የአገር ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲና ፈጣን ልማት ሲረጋጋጥ ከሁሉም በላይ አገራዊ አንድነቱ የጠበቀ አገረ ሕዝብ ሲገነባ ብቻ ነው፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን  ዛሬም እንደ ትናንቱ አገራችን የራሷን ሰላም ከጎረቤቶቿ ነጥላ መለየት እንደማይቻል በውል ተገንዝባ መረባረብ ስትችልም ነው፡፡  እስካሁን አካባቢውን የማረጋጋት ሚናን በግንባር ቀደምነት እየተጫወተች የቆየችው ኢትዮጵያ ከራሷ ግዛት አልፎ ለጎረቤቶቹ የሰላም ዋስትና መሆን የቻለ የመከላከያ ሠራዊቷ፣ የአገሩን ሰላምና ደኅንነት የሕዝቦችንም የመኖርና የመንቀሳቀስ ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ሳይሸራረፍ ማረጋጋጥ ሲችል ነው፡፡

በእርግጥ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የኢትዮጵያ መንግሥት በተሃድሶ መንፈስ ወደ ሥልጣን ሲመጣ፣ የበለጠ ትኩረት የሰጠው  ለአገራችን ሕዝቦች አብሮነት ብቻ ሳይሆን፣ ለጎረቤት አገሮች ወዳጅነት መሆኑ የሚዘናጋ አልነበረም፡፡ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን በመቀየር ዜጋ ተኮርና በሰጥቶ መቀበል ላይ የተመሠረተ እንዲሆን እስከ መሥራትም ተሂዷል፡፡

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎረቤት አገሮችንና መሪዎቻቸውን በቀጥታ በመጎብኘት፣ ይበልጥ ቀጣናዊ ትስስር እንዲፈጠርም ሲተጉ እንደነበር አይዘነጋም፡፡  ጉርብትናዋ በዓባይ የውኃ አጠቃቀም ምክንያት አስፈላጊ እስከ ሆነችው ግብፅ ድረስ ጥረቱ ሲታይ ነበር፡፡ ይህን ሁሉ ጥረት በጠንካራ መሠረት ማስቀጠል የሚቻለው ግን፣ የውስጥ ሰላምና የሕዝቦች አንድነትን በአገር ላይ ማረጋጋጥ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ  መንግሥት ቅድሚያ ለውስጥ ጉዳይ ይስጥ ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝቡም ከዳር እስከ ዳር አንድነቱንና የአገር ሰላሙን አጥብቆ መጠበቅ አለበት ያስብላል፡፡ 

በመሠረቱ ለእኛ አገር ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ቢሆን የአፍሪካ ቀንድን ጉዳይ አንገብጋቢና ወሳኝ የሚያደርገው፣ አካባቢው ከራስ አልፎ የበርካታ ኃያላን አገሮችን ፍጥጫ የሚያስተናግድ፣ የብዙዎች ፍላጎት የታጨቀበት በመሆኑም ነው፡፡ ስለሆነም በአንድ በኩል የአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦችና መንግሥታት ለመገመት አስቸጋሪና ትርጉም የለሽ የሆነ የስትራቴጂካዊ አሠላለፍ ምርጫ ከሚያስከትለው ቀውስ ለመጠበቅ፣ ከፊታቸው የተዘረጋውን አደገኛ ጎዳና በጥንቃቄ መጓዝ ይኖርባቸዋል፡፡

በሌላ በኩል በአፍሪካ ቀንድ የውክልና ጦርነት ማካሄድ ቀላል ነገር መስሎ የሚታያቸው ከቀጣናው ውጭ የመጡ ኃይሎች፣ ራሳቸውን ከስህተት ለመጠበቅ የአካባቢውን ታሪክና ፖለቲካ በውል እንዲረዱ የማድረግ ጠንካራ የተባባረ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፣ ይገባልም፡፡ በጉዳዩ ላይ ጥናት የሚያካሄዱ አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ራሳቸውን ከመጥፎ ቀውስ ለመጠበቅ፣ በቀዳሚነት  ሦስት ዋና ዋና ተግዳሮቶችን መፍታት ይኖርባቸዋል፡፡

      አንደኛው የአፍሪካ ቀንድ መንግሥታት ከመጎሸማመጥና ጥርጣሬ ወጥተው የሕዝባቸውን ልብ የሚገዛ ብሔራዊ ፕሮጀክት መቅረፅ መቻል ይኖርባቸዋል (ለአብነት ያህል እንደ ዋና ዋና መንገዶች፣ የጋራ ወደብ አጠቃቀም፣ የኃይል አማራጭና መሰል  ልማቶች፣ እንዲሁም የፀረ ኮንትሮባንድ፣ ሕገወጥ የመሣሪያ ዝውውርና የዕፅ ዝውውር ዓይነት ውንብድናዎችን ተጋግዘው ለመመከት ተጠናክረው መረባረብ ያስፈልጋቸዋል)፡፡  ይህም ሕዝብን በማስገደድ ሳይሆን በማሳመን ደጋፊ የማድረግ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እሴት ግንባታንና የምክክር መድረክ የማመቻቸትን ሥራ የሚጠይቅ ፕሮጀክት ነው፡፡ የባለሀብቶችን ነፃ ዝውውርና የተቃና የገበያ ሥርዓት የመዘርጋቱ ጉዳይም ለነገ የሚባል አይደለም፡፡

ሁለተኛው ጉዳይ የውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና የመልካም አስተዳዳር ማስፈን አዲስ አብዮት ማጠናከር አለባቸው (እዚህ ላይ በአሮጌ አስተሳሳብና በሬ ለማረስ የሚንገታገቱ መንግሥታትም ፈጥነው ራሳቸውን ካልፈተሹ ውርደት ማስተናገዳቸው አይቀሬ ነው)፡፡ በመሠረቱ የምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ ዘመናዊ መንግሥታዊ አስተዳደር ያልደረሰባቸውና ከብሔራዊ ተራክቦና ተዋጽኦ የተገለሉ ድንበር ተሻጋሪ የሕይወት እንቅስቃሴ ያላቸው፣ የዳር አገር ማኅበረሰቦች በብዛት የሚገኙበት አካባቢ መሆኑ መዘንጋት ለበትም፡፡  ስለሆነም ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን ማረጋጋጥ ወሳን ጉዳይ ሆኖ መታየት ይኖርበታል፡፡

ጥንቃቄ የሚስፈልገውም የተገፉ የሚመስላቸው ማኅበረሰቦች በአካባቢው አገሮች የፖለቲካ አለመግባባት ክስተት ውስጥ፣ የውክልና ሚና ይዘው ለመንቀሳቀስ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ የመኖሩ እውነታ ነው፡፡ በመሆኑም የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ውስጣዊ የፖለቲካ ሁኔታ ከአካባቢያዊ ትስስሩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ይኖረዋል፡፡ ለአብነት ያህል የኢትዮጵያን ሁኔታ ብንወስድ ከሞላ ጎደል ከሁሉም ጎረቤት አገሮች ጋር በደም፣ በታሪክና በባህል የተሳሰሩ ሕዝቦችን የሰበሰበች ነች፡፡ ይህ ሁኔታም በውስጥ እየተባባሰ የሚሄደው የፖለቲካ መካረርና የዘረኝነት አዙሪት ካልታረመ ለቀጣናዊ ትስስሩም ዋነኛ እንቅፋት መሆኑ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ከምንም በላይ የውስጥ ጉዳይን በጠንካራ መሠረት ላይ ለማቆም ሕዝብና መንግሥት ሊረባረቡ ይገባል፡፡

ሦስተኛው የአፍሪካ ቀንድ የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ፣ ከቀንዱም ሆነ ከአፍሪካ ውጪ የሚመጡ ተዋናዮች እጃቸውን በቀላሉ ለማስገባት ቀዳዳ ማግኘት የሚችሉበት አካባቢ መሆኑን የመገንዘብ ጉዳይ ነው፡፡ የአፍሪካ ቀንድ በመልካም አስተዳደር ችግር የተጠቃ፣ አንዱ አገር የሌላውን አገር ሰላም ለማደፍረስ የመንቀሳቀስ ልምድ ያካበቱ መንግሥታት የሚገኙበት አካባቢ ነው፡፡ የራሱ የአፍሪካ ቀንድ እጥረቶችና የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ተባብረው፣ አካባቢውን የደኅንነት ሥጋት የማይለየው ቀጣና አድርገውት እንደቆዩም አይዘነጋም፡፡ በቀላሉ ተቀጣጣይ የሆኑ ነገሮች በሰፊው የሚታዩበት አካባቢ ነው መባሉም ለዚህ ነው፡፡ ስለሆነም አይደለም  ‹‹ኢጋድ››ን ይቅርና ሌላ ጠንካራ የሰላምና ፀጥታ ወይም የጋራ ትብብርና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ኅብረት እየፈጠሩ በሰጥቶ መቀበል መርህ መቀጠል ነው ያለባቸው፡፡

በአጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች በጋራ ግንኙነታቸውም ሆነ በተናጠል በየውስጣቸው ከቆዩበት የመርገም አዙሪት ወጥተው በፀጋ አዙሪት ለመሽከርከር፣ ከፊታቸው የተጋረጡ እንቅፋቶችን በተናጠልም በጋራም ታግለው ማስወገድ ይኖርባቸዋል፡፡ በመተማማንና በመተጋጋዝ መንፈስ ለአስተማማኝ ትስስርም ሊነሱ ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር የሁሉም ዋልታና ካስማ የምትባለው አገራችን ኢትዮጵያም በግንባር ቀደምነቷ እንድትቀጥል፣ የውስጥ ሰላምና ብሔራዊ አንድነቷን እንድትጠብቅ ሁሉም ኃይሎች መትጋት አለባቸው፡፡ መንግሥትም ኃላፊነቱን ጠንክሮ መወጣት አለበት፡፡

ሌሎችም ቢሆኑ በውስጣቸው አሳታፊ መንግሥት (ዴሞክራሲያዊና የአገር አንድነትን የሚያፀና) በመመሥረትና በጋራም ክፍለ አኅጉራዊ ገበያ በመፍጠር፣ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስር በመገንባት ላይ ሊያተኩሩ ይገባል፡፡ ቀድሞ ለመጣ ገዥ ፍላጎታቸውን በችርቻሮ ለመሸጥ የሚጣጣሩ ሳይሆን፣ እንደ አፍሪካ ቀንድ አንድ አካል አድርጎ የሚያሠልፍ የጋራ ፍላጎትን መሠረት በማድረግ ከውጭው ዓለም ጋር ለመደራደር የሚያስችል ቁመና የመገንባት ራዕያቸውን  ከወዲህ መጀመር ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ ርብርብ ውስጥ ደግሞ የአገራችን ሚና ጎልቶ ይወጣ ዘንድ አሁን የሚታዩ የጥፋት ዝንባሌዎች መታረም አለባቸው፡፡ የትውልድም የመንግሥትም ግዴታ መሆን ያለበትም ይኼው ነው፡፡ ለአፍሪካ ቀንድ መፍትሔ አምጪ እንጂ ችግር  አለመሆን የምንችለውም በዚህ መንገድ ከተጓዝን ብቻ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...