Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገር“ኳራንቲን ስላላስገባችሁን እናመሠግናችኋለን”

“ኳራንቲን ስላላስገባችሁን እናመሠግናችኋለን”

ቀን:

በመርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ

ወደ ዝርዝሩ ጠልቄ ከመግባቴ በፊት አንድ ጉዳይ ለአንባቢያን ግልጽ ማድረግ ፈለግኩ። ለዚህ ጽሑፍ በመሪ ርዕስነት የተጠቀምኩበት አስደማሚ የመወድስ ሐረግ ከሳምንታት በፊት፣ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና የብልፅግና ፓርቲን ሊያስታርቅ ከፍተኛ ተስፋ ሰንቆ ወደ መቀሌ የተጓዘው የአገር ሽማግሌዎች መማክርት ምክትል ሰብሳቢ ከድምፀ ወያኔ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ጋር ካካሄዱት ምጥን ቃለ ምልልስ ውስጥ በቀጥታ ቀንጭቤ የወሰድኩት ነው። አባባሉ ስላስገረመኝ የፓስተር ዳንኤል ገብረ ሥላሴን ጆሮ ገብ የመውጫ ቃለ ውዳሴ በጉልህ ላነሳውና በርዕስነት ልገለገልበት መርጫለሁ።

ሞገደኛው ጋዜጠኛ ሰውየውን አግኝቶ ያናዘዛቸው ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ሲዘጋጁ ስለነበር፣ ቡድናቸው ወደ መቀሌ ስለተጓዘበት ተልዕኮና በዚያ ስለተደረገለት መስተንግዶ ትንሽ ያወጉት ዘንድ መጠየቁ የማይጠበቅ አልነበረም። እርሳቸውስ ቢሆኑ ምናቸው ሞኝ ነው መሰላችሁ? የክልሉ መንግሥትም ሆነ ርዕሱን የሚመራው የፖለቲካ ቡድን ለታዋቂ የአገር ሽማግሌዎችና ለብፁአን የሃይማኖት አባቶች በጊዜው ያደረገላቸው ሞቅ ያለ አቀባበል የተዋጣለት እንደነበር አስታውሰው፣ የአንድ ቀን ቆይታቸው ፍሬያማ እንደነበር አውሸልሽለውም ቢሆን ሲነግሩት ተከታትለናል፡፡ በኮቪድ 19 ምክንያት ኳራንታይን ይገቡ ዘንድ እንግዶቹን ስላላስገደዷቸው በመሽኮርመም ከተሰነዘረ ተደራቢ ምሥጋና ጋር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይልቁንም ‘ምነው ዘገያችሁ’ ተብለው በአስተናጋጆቻቸው በኩል መወረፋቸውንና መገሰጻቸውን ሳይደብቁ፣ በዚህ አገር የተፈጠረው ችግር ሕወሓትንና ብልፅግና ፓርቲን ብቻ የሚመለከት እንዳልሆነ በምፀት እንደተነገራቸው በይፋ ሲገልጹለት አዳምጠናል፡፡ እንግዲህ ሕወሓት ያን ያህል ትዕቢተኛና ዕብሪቱ ጠርዝ የነካ ቡድን ነው፡፡ ይህ በሚገባ እየታወቀ ለምን እስከዚያ ደረጃ ድረስ እየወረድን ዘወትር እንደምናጎበድድለትና እንደምናባብለው ግራ ያጋባል፡፡

ያም ሆኖ ወደ መቀሌ ተጉዞ የነበረው የዚያ የሽምግልና ቡድን የሥራ ውጤት ምን እንደሆነ እስካሁን የረባና የተጨበጠ መረጃ የለንም፡፡ በእርግጥ ወደ አዲስ አበባ እንደተመለሰ ‘ጩኸቴን ቀሙኝ’ በሚል ድምፀት ሕወሓት በፌዴራል መንግሥቱ ላይ የሚያቀርባቸውን ደረቅ ስሞታዎች አንስተው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ባይጨምርም፣ ከብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ስለመወያየታቸው ፍንጭ አግኝተናል፡፡

‹ሲለምኗት እምቢ ብላ ሲጎትቷት. . .›

እነሆ ዛሬ ደግሞ ሕወሓት በተራው ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር እንዲያስታርቀው የራሱን የሽምግልና ልዑክ ወደ አዱ ገነት በህቡዕ ላከ መባልን ሰማን፡፡ ይሁን እንጂ ጉዳዩ በሚስጥር እንዲያዝ የተፈለገ ይመስላል፡፡ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ይህንኑ ለማረጋገጥ አልደፈሩም፡፡ ነገሩን መሸማገል ሳይሆን መሸነጋገል የሚያስመስለውም ይህ ዓይነቱ የሹሉክሉክታ አካሄድ ነው፡፡ ሕወሓት እንደሆነ መምጫው የማይታወቅ አካይስት ቡድን ነው፡፡ በራሳቸው አነሳሽነትም ይሁን አንዳንዶች እንደሚጠረጥሩት የሌላ ወገን ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ቀድመው ወደ እርሱ የተጓዙትን የተከበሩ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ገላምጦና አሳፍሮ የመለሰው ቡድን፣ አሁን ደርሶ ‘እባካችሁ ሸምግሉኝ’ ማለቱ የጤና ሊሆን ከቶ አይችልም፡፡ ይልቁንም በህቡዕ የሚንደፋደፍበትን የቤት ሥራ ያለ ሥጋት ለማከናወን ያመቸው ዘንድ ጊዜ ለመግዛት መሆን አለበት፡፡

ወጣቱን ከያኒ የሃጫሉ ሁንዴሳን አሰቃቂ ግድያ በኋላ በጽንፈኛ ኃይሎች እየተመራ በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ ከተማ አንዳንድ አካባቢዎች በጭካኔ የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ሁከትና አገር አውዳሚ ጥፋት ተከትሎ፣ ሐምሌ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎችና ተወካዮቻቸው ጋር አንድ የውይይት መድረክ አካሂደው ነበር፡፡ በዚያ የውይይት መድረክ አሁንም አንዳንድ ወገኖች በከባድ ወንጀል ተጠርጥረው የተያዙትን ሰዎች ይፈቱ ዘንድ ሽማግሌ እንደሚልኩባቸው በአግራሞት ይፋ አድርገዋል፡፡

ሆኖም እርሳቸው ተገቢ ባልሆነ መንገድ እጃቸውን በማስረዘም “እገሌ ይታሰር፣ እገሌ ደግሞ ይፈታ” እያሉ የትኛውንም አካል የማዘዝ ሕጋዊ መብት እንደሌላቸው ገልጸው፣ ይህ ይደረግ ቢባል እንኳ ዝንባሌው አደገኛ በመሆኑ የአገሪቱን የፍትሕ ሥርዓት የማዛባት አሉታዊ ውጤት እንደሚኖረው በውል ይረዱት ዘንድ እንቅጩን ነግረዋቸዋል፡፡ መቼም እንዲህ ያለው ቁርጥ ያለና አንጀት አርስ ማስገንዘቢያ የአንድ በሳልና አስተዋይ መሪ አስተያየት በመሆኑ፣ በኃይለኛው ሊበረታታና ሊደገፍ ይገባዋል እላለሁ፡፡ ምንጊዜም ቢሆን ከባለሥልጣናት የተናጠል ውሳኔና የዘፈቀደ ዕርምጃ ይልቅ፣ የሕግ የበላይነት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ አንድና ሁለት የለውም፡፡

እርሳቸው (ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማለቴ ነው) የሕግ አስከባሪው የመንግሥት አካል የበላይ ቁንጮ እንጂ፣ ቀድሞ ነገር ሸምጋይም አሸማጋይም እንዳልሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሠረቱ እነርሱ ብቻ ናቸው ባይባልም በመላው ዓለም የሚሠራባቸው አንጋፋዎቹ የሕግ ሥርዓቶች ሁለት ናቸው፡፡ የኮንቲነንታል (Continental) እና የኮመን (Common ሎው (Law) ሥርዓቶች፡፡

የኮንቲነንታል የሕግ ሥርዓት በታወቁ የሕግ መርሆዎች ላይ ተመሥርተው የሚጻፉ ዝርዝር የሕግ ድንጋጌዎችን በጥብቅ ተከትሎ በመፈጸምና በማስፈጸም ላይ የበለጠውን ሲያተኩር፣ የኮመን ሕግ ሥርዓት ግን በተቃራኒው አስቀድመው በተጻፉ የሕግ ድንጋጌዎች ሳይወሰን ወይም እነርሱን ብቻ ሳያመልክ ሕግጋቱ ከወጡ በኋላ በመሬት ላይ ለሚያጋጥሙ ተጨባጭ ችግሮች ተግባራዊ (Pragmatic) መፍትሔ የመስጠትን ተጨማሪ አቅም ያጎናፅፋል፡፡ በተመረጡ የወንጀል ጉዳዮችም ድርድርን ሳይቀር ይፈቅዳል፡፡ ለመጀመርያው ሥርዓት ፈረንሣይን፣ ለሁለተኛው ሥርዓት ደግሞ ታላቋ ብሪታንያን በወፍራም ምሳሌነት ይጠቅሷል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ በዋነኝነት የምትከተለው የኮንቲነንታል ሕግ ሥርዓትን ነው፡፡ ይህ ሥርዓት ግን ለፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ካልሆነ በስተቀር፣ በተለይ የጠቅላላውን ሕዝብ ደኅንነት ለማረጋገጥና የመንግሥትን ፀጥታ ለማስከበር በሚወጡ የወንጀል ሕግጋት ተፈጻሚነት ረገድ የሽምግልናን ጣልቃ ገብነት አይፈቅድም፣ አያበረታታምም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐምሌ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ለተጠራው መድረክ የሰጡት ምላሽም ይህንኑ በሚገባ ያገናዘበ ስለሚመስል በአቋማቸው እንዲገፉበት ያስፈልጋል፡፡ ብራቮ ጠቅላያችን!!!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በሕግ ሙያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በ1981 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው የሕግ ፋኩልቲ ያገኙ ሲሆን፣ በሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተመድ የሰላም ዩኒቨርሲቲ ጣምራ ትብብር ይካሄድ ከነበረው የአፍሪካ ፕሮግራም በሰላምና በደኅንነት ጥናት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ ዋና የሕግ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...