በንጉሥ ወዳጅነው
የኢትዮጵያ መጪው አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ የሚካሄደው በሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ አካባቢ እንደሚሆን ተገምቷል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኮሮና የተባለው ተላላፊ ወረርሽኝ በመቀስቀሱ ምክንያት ነው፡፡ በዚህም መዘዝ ሰዎች የማይገናኙበትና የማይነካኩበትን ዓውድ ለመፍጠር በመታሰቡ፣ አገራችንን ጨምሮ በርካታ አገሮች ምርጫ አራዝመዋል፡፡ አሁን በትግራይ ክልል ምርጫ አካሂዳለሁ ብሎ ከሕግ ውጪ እየተንቀሳቀሰ ያለው ሕወሓት (የክልሎ ገዥ ፓርቲ) አካሄድ ቅቡልነት እንደሌለው ልብ ይሏል፡፡
በእርግጥ በእኛ አገር ሁኔታ ሲመዘን ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በተከሰተው አዲስ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ሽግግር፣ ብሎም አምባገነናዊነትን የተላበሰውን ኢሕአዴግ የመቀየር ጥረት ውስጥ የተፈጠሩ አዳዲስ ክስተቶች፣ ምርጫውን በሰከነ መንገድ ማካሄድን ግድ የሚሉ ነበሩ፡፡ በተለይ በአንድ በኩል ተገፍተው በትጥቅና በስደት የኖሩ የነበሩ ፖለቲከኞች ወደ አገር ውስጥ የገቡበት፣ በሌላ በኩል በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ታስረው የነበሩ ልሂቃን ከእስር ተፈትተው ወደ መድረኩ የገቡበት ሁኔታ፣ ከዚህ ቀደም አረረም መረረም በምኅዳሩ ውስጥ ከቆዩ ፖለቲከኞች ጋር ተዳምሮ የፓርቲዎቹን ቁጥር ከመቶ በላይ አድርሶታል፡፡
ችግሩ ያለው ግን በቁጥሩ መብዛት ላይ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ፖለቲከኞቹ የሚገዙበት አንድ ወጥ መስማሚያ ሰነድ ባለመዘጋጀቱና ባለመፈረሙ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት መንግሥት ባሳየው ቀናነት ምክንያት ጽንፈኛ ሚዲያዎች፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የማኅበራዊ ድረ ገጽ ተዋናዮች፣ ወዘተ. የያዘው ኃይል ሁሉ ሰተት ብሎ ወደ አገር ገብቶ፣ እርስ በርስ ወደ መጠዛጠዝና ሕዝብን ከሕዝብ ወደሚያጋጭ ድርጊት እየገባ አገረ መንግሥቱን የማራድ ምልክት በመታየቱ ነው፡፡
ከሁሉ በላይ ለአገር ደኅንነት፣ ለምርጫ ዴሞክራሲያዊነት፣ ለአብሮነትና ለመሰል ጉዳዮች የወጡ ሕጎች እየተዘነጠሉ በመሄዳቸው እንኳንስ ምርጫ ለማካሄድ፣ የተረጋጋ አገርንም ለማቆም እንቅፋት እየሆነ በመምጣቱ፣ የምርጫው መራዘም እንደ ችግር ሳይሆን በመልካም አጋጣሚነት የሚታይ ነበር፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ በዚህች አገር ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር የማይሳካልን ይመስል፣ ከለውጡ ወዲህ ምን ያህል ጥፋት እንደ ደረሰ ማየት ብቻ ምርጫውን አራዝሞ ቅድሚያ አገርን ማረጋጋት እንደሚገባ ያሳያል፡፡ የክልል ፕሬዚዳንትና አመራሮችን ጨምሮ በርካታ ፖለቲከኞችና የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፣ የአገሪቱ ጠቅላይ ኤታ ማዥር ሹምና በየደረጃው ያሉ የመከላካያ አዛዦች፣ ከፖለቲካው ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው ንፁኃን ዜጎች፣ የውጭ አገር ዜጎች፣ ባለሀብቶች፣ ወዘተ. ስንቶች ሕይወታቸው አልፏል፡፡ እስከ ሰሞኑ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግድያ ድረስ ዜጎች እየረገፉ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
በደሃ አገር ኢኮኖሚ ውስጥ በስንት ድካም የተገነቡ የሕዝብና የግል ኢንቨስትመንቶች፣ ድርጅቶችና ኢንዱስትሪዎች በእሳት ጋይተዋል፡፡ አንዳንዶቹ ባለሀብቶችንም ተስፋ እያስቆረጡ ላይመለሱ እያሰደደ ነው፡፡ በርካታ ባንኮች ዘረፋና ቃጠሎ ሲወርድባቸው፣ ወደ ዘር ፍጅት የሚያመራ የመንጋ ፍርድ እየተመላለሰ ሲታይ፣ እንኳንስ ምርጫ ለማካሄድ በሰላም ወጥቶ መግባትም አስጨናቂ ሆኗ ነበር የቆየው፡፡
በመሠረቱ ምርጫ የዴሞክራሲ ሥርዓት መሠረት ነው ቢባልም፣ ያለሰላምና መረጋጋት ፈፅሞ ሊሳካ የማይችል መሆኑም የታወቀ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ማለት በራሱ የሕዝብ፣ ለሕዝብ፣ በሕዝብ የሚቆም ሥርዓት መመሥረት እንደ መሆኑ፣ ባልተረጋጋ አገረ መንግሥት ውስጥ የሕዝቦችን ጥቅምና ደኅንነት ማፅናት የሚሆን አይደለም፡፡ ዴሞክራሲ የአማራጭ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው ሲባልም፣ ዜጎችና ፖለቲከኞች በአግባቡ የሚዳኙበት፣ አንዱ ከሌላው የሚወዳደሩበት ሥርዓት አበጅቶ በመደማመጥና በሠለጠነ መንገድ መንቀሳቀስ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የዋና ዋና ተዋናዮች ሚና ምን መምሰል እንዳለበት ልጠቃቅስ፡፡
የፓርቲዎች የምርጫ ሚና!
ምርጫ የሚካሄደው በአብዛኛው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል እንደ መሆኑ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች (ገዥና ተቃዋሚ ሳይባል) ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዋነኛ መሠረቶች መሆናቸው የታመነ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሌሉበት ሁኔታ የሚደረግ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊያስገኝ እንደማይችል ሁሉ፣ ፓርቲዎች በኃላፊነት ስሜትና በሥርዓት መመራት ካልቻሉም አገርን ይጎዳል እንጂ አይጠቅምም፡፡ በቂም በቀልና በእልህ ፖለቲካ ደሃ አገር ማውደም የለየለት ጥፋት ነው፡፡
በምርጫ የሚመሠረት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲኖረን ከፈለግን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አስፈላጊነት ማመንና መቀበል ግዴታችን ነው፡፡ ፓርቲዎች ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸው ሚና ኃያል ነው፡፡ ፓርቲዎቹ ‹‹ቆመንለታል›› የሚሉትን ሕዝብ መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችል አማራጭ ሐሳቦችን ያመነጫሉ፡፡ ሐሳቦቻቸው ለቆሙለት ኅብረተሰብና በጠቅላላው ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ይታገላሉ፡፡ ከዚህ አልፎ ግን በአንድ በኩል ሰላማዊ ፓርቲ፣ በሌላ በኩል ጦር ያለው ሸማቂ ሆኖ በአንድ እግር ሁለት ዛፍ ላይ ለመውጣት መሞከር በየትም አገር ሕጋዊነትን አያስገኝም፡፡
በማንኛውም ነፃ አዕምሮ ባለው ሰው እምነት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማጠናከር ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እጅግ በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ መሆኑ ግልጽ የሚሆነው፣ የእነሱ መኖር በርካታ አዳዲስና ተጨማሪ የአገር ዕድገት ግብዓቶችን ይዞ ስለሚመጣ ነው፡፡ የተተነተነና በሥርዓት የተደራጀ ሐሳብ ይዘው ይመጣሉ ተብሎም ይታመናል፡፡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችሉ አማራጭ ሐሳቦችን በማመንጨት ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህ ሐሳቦች በኅብረተሰቡም ሆነ በአጠቃላይ ሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ ይሠራሉ፡፡ ከዚህ ውጪ በሚደረግ ሁከትና ትርምስ የሚገኝ ትርፍ እንደሌለ ማጤን ይገባል፡፡
እንደ ፖለቲከኛ ነገሮችን በዘዴና በብልኃት፣ በመቻቻልና በመግባባት፣ በዴሞክራሲ አግባብና በሰላም የመተግበሩ ኃላፊነታቸውም የገዘፈ ነው፡፡ የአገሪቱን አጠቃላይ ዕድገትና ልማት ለማፋጠንና ለማስቀጠል በሚያስችል አግባብ ችግሮችን በሠለጠነ አካሄድ እየፈቱ ካልሆነ፣ አገር ለመምራት መሞከር ለማንም የሚበጅ አይሆንም፡፡ ስለዚህ በዚች አገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የብሔርም ይሁኑ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች ይህን እውነታ ለሰከንድ መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ከዚያ ውጪ አሁን ሕወሓት ለፖለቲካ ትርፍም ቢሆን እንደሚለው፣ ያለ ምርጫ ቦርድ ይሁንታ ምርጫ በአንድ ክልል አካሂዳለሁ ብሎ መንፈራፈርና ሕግን መጣስ ብቻ ሳይሆን አግባብነት የሌለውና የሚወገዝ ነው፡፡
ፓርቲዎች በቅድመ ምርጫ ጊዜ ዓላማቸውንና የፖሊሲ አማራጮቻቸውን፣ ‹‹በምርጫ ቅስቀሳና በፓርቲዎች ክርክር ላይ አቅርበናል. . . ሕዝቡ እንዲመርጠን ግንዛቤ አስጨብጠናል. . .›› ካሉና ሕዝቡም፣ ‹‹ባገኘሁት ግንዛቤ ላይ ተመሥርቼ የሚበጀኝን መርጫለሁ. . .›› ብሎ ድምፁን ከሰጠ በኋላ፣ ምንም ዓይነት ግርግርና ሁከት መፍጠር ማሰብም ሆነ በቅድመና በድኅረ ምርጫ ትርምስ ፈጥሬና ያለቀው አልቆ ሥልጣን እይዛለሁ የሚሉ ወገኖችም ቆም ብለው ሊያስቡበት ይገባል፡፡
በመሠረቱ ፓርቲዎችና መንግሥት በረጋና በቀና መንፈስ በምርጫው ለመወዳደር ብቻ ነው መዘጋጀት ያለባቸው፡፡ እዚህ ላይ በርከት ያሉ የተሻለ ልምድ ያላቸው ነባር ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች አሉ፡፡ በእነዚህ ኃይሎች በኩል እስካሁን ብዙም ችግር አይስተዋልም፡፡ ‹‹አዲስ እረኛ ከብት አያስተኛ›› እንደሚባለው የምርጫውን ሰላማዊነት ለማደናቀፍ ከሚንቀሳቀሱት መካከል ዋነኞቹ፣ ከአገራችን የምርጫ ታሪክ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ኃይሎች መሆናቸው ነው፡፡
ከዚህ አንፃር ከምርጫ በፊት በተለይ ኦሮሚያን በመሰሉ ክልሎች የሕወሓት አዛውንቶች በቀመሩት ሴራ በተወጠረው ትግራይ ክልል የሚገኙ ወጣት ኃይሎችን ሁሉም ወደ ራሱ ዓላማ እየጎተተ ለሥልጣን በመራኮት ብቻ፣ ተጠያቂነት በሌለበት መንገድ፣ ያውም በውስጣቸው የጥፋት ኃይሎችንም እያሰረጉ በሕዝብና በአገር ላይ ለጥፋት ማዝመት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በሕግ መዳኘት ያለበት አደጋ ነው፡፡ መንግሥት የብዝኃኑን የአገራችንን ሰላም ወዳድ ዜጋ ፍላጎት አስከብሮ ለመገኘት መትጋት ለነገ የማይባል ኃላፊነቱ ነው፡፡
ይህ ሁሉ ዕውን የሚሆነው ግን ፓርቲዎች ሁሉ አቀፍ ኃላፊነታቸውን መወጣት ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ በእርግጥ ፓርቲዎች የምንላቸው ሁሉ የራሳቸው ርዕዮተ ዓለምና ከሌላው የሚለያቸው አቋም ያላቸው፣ ዓላማቸውን ማራመድ የሚችሉት የዴሞክራሲ ሥርዓት ሲገነባ መሆኑን በመገንዘብ የዴሞክራሲ ባህል እንዲያብብ፣ የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲፈጠሩና እንዲጠናከሩ ለማድረግ የሚሠሩትን ነው፡፡ ከሌሎች የሚለያቸው አንድም መሠረታዊ የርዕዮተ ዓለም ልዩነት የሌላቸውን፣ ለሥርዓት ግንባታና ለአገሪቱ ዕድገት፣ እንዲሁም ለሕዝቡ ተጠቃሚነት የተለየ አማራጭ ማቅረብ የማይችሉትንና የብሔር ባርኔጣ እያጠለቁ ሕዝብን የሚያፋጥጡ፣ በፓርቲ ስም የተሰባሰቡትን ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው›› ለማለት ይቸግራል፡፡ ከሁሉ በላይ በአንድ አገረ መንግሥት ሥር ተደራጅተው፣ ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንድትፈርስ የሚቋምጡትን እንደ ሕጋዊ ፓርቲ መቁጠር መቆም አለበት፡፡
የዜጎች የምርጫ ኃላፊነት
የሕዝቡ የምርጫ ተሳትፎ ለመምረጥም ሆነ ለመመረጥ ከመመዝገብ ነው የሚጀምረው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ዜጎች ለሕግ የበላይነት መከበር፣ ለሰላምና ዴሞክራሲያዊ ጉዞ መጠናከር ሚናቸው ቀላል አይደለም፡፡ ዜጎች ከፓርቲዎችና ከፖለቲከኞች በዝርዝር የተተነተኑ ሐሳቦችን ማግኘት ይፈልጋሉ፡፡ ካሉት ፓርቲዎች መካከል የግራ ቀኙን ሰምተውና መዝነው ይበጀናል የሚሉትን ፓርቲ በራሳቸው ፈቃድ በነፃ ምርጫ ድምፃቸውን ሰጥተው ለመምረጥ፣ ስክነት የተሞላበት ቅስቀሳና የደኅንነት ስሜት የሚፈጥሩላቸው ውይይቶችን ይሻሉ፡፡
በመሠረቱ እንደ አገር ሰላምና ልማት ወይም የተረጋጋ አገራዊ ደኅንነት ይፈጠር እንጂ፣ ምርጫ በቀኑ ተካሄደም ተራዘመም በዚች አገር ውስጥ የምርጫ ማጭበርበርና ኮረጆ መሰራረቅን የሚሸከም ሕዝብ ከእንግዲህ ሊኖር እንደማይችል እየታየ ነው፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ ሕዝቡ ባለፉት ሦስት አሠርት ዓመታት መስዋዕትነት እየከፈለ በገነባው አስተሳሰብ ነው፡፡ ስለሆነም ከዚህ በኋላ የፈለገው ፓርቲ የሕዝቡን ይሁንታ ለማግኘት ሲል ምንም ቢሠራ፣ መራጩን ሕዝብ ‹‹በግድ እኔን ምረጥ›› ብሎ እጁን ይዞ በምርጫ ወረቀቱ ላይ ምልክት እንዲያደርግለት ማስገደድም የሚችልበትን ዕድል ከዳር እስከ ዳር መዝጋት አለበት፡፡
የምርጫ ሳጥን ውስጥ የሚገባው የምርጫ ወረቀት የመራጩን ስምና አድራሻ የያዘ አይደለም፡፡ ማን ማንን እንደመረጠና እንዳልመረጠ ተለይቶ የሚታወቅበት ዘዴ የለም፡፡ እንዲኖርም አይፈለግም፡፡ የተሰጠው ድምፅ በታዛቢዎች ፊት ተቆጥሮ አሸናፊው ከሚለይ በስተቀር ሌላ የመቆጣጠሪያና የማስገደጃ ዘዴም የለም፣ አይኖርምም፡፡ ‹‹እነ እገሌ አልመረጡኝም›› ለማለት የሚያስችልና ለበቀል የሚዳርግ አሠራርም ድሮ ቀረ መባል ያለበት ነው፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ከኋላ ቀርነትም ሆነ ከስሜታዊነት ወጥቶ መብቶቹን መጠቀም ነው ያለበት፡፡
ከዘህ ውጪ የራስን ወገንና ሕዝብን (ብሔርን) ብሎም ሰላማዊ ዜጋን በማሰደድ፣ ሥልጣን በድንጋይ ውርወራ፣ በሁከትና በአመፅ፣ በውዥንብር ብዛት ለመንጠቅ የሚያልሙ ጥገኞችን ሕዝቡ ማውገዝ አለበት፡፡ ሕገወጥና የጥፋት ጥሪያቸውን ባለመቀበልና አደብ እንዲይዙ በማድረግ አገሩን መጠበቅም ኃላፊነት አለበት፡፡ እውነት ለመናገር አገር በጩኸት የምትፈርስበት ታሪክ ከኢያሪኮ ጋር አብሮ አክትሟል፡፡ ሥልጣን በኢኮኖሚ አሻጥርና በዋጋ ማናር አይገኝም፡፡ ያለንበት ዘመን ዓለም የሠለጠነበትና ችግሮች ሁሉ በሠለጠነ መንገድ የሚፈቱበት እንደ መሆኑ፣ ሕዝቡም ሆነ ፖለቲከኞች ይህንኑ ማክበር ነው ያለባቸው፡፡
እንደ ዜጋ በመንግሥት ላይ አስፈላጊውን ጫና ማድረግ ቢያስፈልግ እንኳን በፀጥታ አካላት ፈቃድ ያገኘ ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ ማድረግ ሲቻል ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በአደባባይ ተሰብስቦ ሌላውን ማወክ፣ አካባቢዎችን በጩኸት መረበሽ፣ ሌሎች ወጣቶችን ለሽብር ማነሳሳት፣ በመንግሥትና በግለሰብ ሀብቶች ላይ ጉዳት ማድረስ፣ ማቃጠልና መዝረፍ፣ ወዘተ. የመሳሰሉት እንቅስቃሴዎች ወደ የማንወጣው አዘቅት የሚወስዱን ናቸው፡፡ ከዚያም አልፎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደታየው በመንጋ ፍርድ ለሥራ አይሉት ለጥፋት በደቦ ተነስቶ ወገንን በዘርና በሃይማኖት እየለዩ መፍጀት፣ ማቁሰልና ማፈናቀል አገርን ከማፍረስ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፡፡ ማንንም ቢሆን ከፍተኛ ዋጋ ማስከፈሉም አይቀርም፡፡ መቆም አለበት፡፡
የሚዲያዎች የምርጫ ሚና
የፓርቲዎች ሚና የቆሙለትን ማኅበረሰብና አጠቃላዩን ሕዝብ ድምፅ ለማግኘት ሐሳባቸውንና ዓላማቸውን፣ እንዲሁም ከሌሎች ፓርቲዎች እነሱ የሚሻሉበትን፣ ቢመረጡና የመንግሥት ሥልጣን ቢይዙ ምን የተሻለ ሥራ ሊሠሩና ምን ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚችሉ ለመራጩ ሕዝብ ማሳወቅና ማሳመን ነው ብለናል፡፡ ሕዝቡም ዓይቶ፣ አድምጦና በራሱ ወስኖ ያዋጣኛል የሚለውን መምረጥ፣ ውጤቱን በፀጋ መቀበል፣ ለመቼውም ቢሆን የአገሩን ሰላምና ደኅንነት ነቅቶ መጠበቅ ነው ያለበት፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ደግሞ ገለልተኛና ሚዛናዊ ወይም በሕግና በሥርዓት የሚመሩ ሚዲያዎች ሲበረክቱ እንጂ፣ የዘር ጥላቻና የግጭት ቅስቀሳ የሚነዙ መገናኛ ብዙኃን ተብዬዎችና አክቲቪስቶች ስለሞሉ አይደለም፡፡
ይህ ምርጫ ሲካሄድ የሚታሰብበት ሆኖ አሁን በሒደቱ የሚያስፈልገውም ስለሕጋዊው ጉዞ የሚያነቁ ሚዲያዎች፣ የአካሄድ ስህተቶችንና ጥንካሬዎችን የሚመለከቱ ገለልተኛ ቀስቃሶች መሆንም አለባቸው፡፡ በተለይም ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም፣ ዓላማና ግብ ያላቸው ፓርቲዎች ምርጫውን በብቃት ለመወዳደር በመካከላቸው ያሉትን አነስተኛና መለስተኛ ልዩነቶች በውይይት በማጥበብና በመቻቻል፣ ወደ አንድ ወይም ወደ ሁለትና ሦስት ፓርቲ ተሰባስበው ድምፃቸው ሰሚ እንዲያገኝ እንዲነሳሱ፣ ከራሳቸው ጥረት በላይ ሚዲያዎች መድረክ ሊፈጥሩላቸውና ሊያቀራርቧቸው ይገባል፡፡
ይህን በጎ አተያይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ደጋግመው ሲያሳስቡ መቆየታቸው ብቻ ሳይሆን፣ በርካታ የብሔር ፓርቲዎችን አዋህደው አንድ ብልፅግና ፓርቲ እንዲመሠረት በማድረጋቸው ታሪክ ሲስታወሳቸው ነው የሚኖሩት፡፡ ሚዲያዎችና ሕዝቡም ይህ ዓይነቱን ፈለግ በመከተል የተንሸዋረረውን የፖለቲከኞች አካሄድ ለማስተካከል መትጋት አለባቸው፡፡
ምርጫ እየተቃረበ በመጣ ቁጥር ፓርቲዎች ሽንፈታቸውን ከወዲሁ የተነበዩ በሚመስል ሁኔታ የሚያቀርቧቸው ሰበቦችንም ቢሆን፣ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሚዲያውና አንቂዎችም ተው ማለት አለባቸው፡፡ ቀዳሚው መንግሥት የሕዝብ ሚዲያዎችን ይጠቀማል፣ በመንግሥት አቅም የሚሠራቸውን ተግባራትም እንደ ምርጫ ቅስቀሳ ይጠቀምባቸዋል፣ የሚሉትን ወቀሳዎች ማስቀረት የሚችለው ራሱ መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ብቻ ሳይሆኑ፣ መገናኛ ብዙኃኑም በሕገ መንግሥቱና በአዋጁ መሠረት ብቻ ሳይሆን፣ በትክክለኛ የሙያ ሥነ ምግባርና የጋዜጠኝነት መርሆዎች ሥራቸውን መሥራት ሲችሉ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ምንም እንኳን በውስጥ አለመረጋጋቱም ቢኖር፣ ዓለም አቀፍ በሆነ ምክንያት የተራዘመን ምርጫ ወቅቱን ጠብቆ መወዳደር ሲገባው፣ ሕጋዊና ሕገ መንግሥታዊ የሆነው የምርጫ ወቅት እየመጣ እያለ ‹‹ምረጡኝ ›› እንደ ማለት ፋንታ፣ አመፅ ለማነሳሳት ወይም ሁከት ለመፍጠር ማሰብ ነውር ስለሆነ ሐሳቡን በማውገዝም ሆነ በሚዲያ ባለማስተናገድ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ለውጡ የመጣበት ዋነኛ ምክንያት የዴሞክራሲ ምኅዳሩን በማስፋት ዜጎች በመረጡት መሪ ያለ ምንም ተፅዕኖ እንዲተዳደሩ ለማድረግ መሆኑ እየታወቀ፣ በውንብድናና በጥፋት የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት ማሰብ ተያይዞ መጠፋፋትን እንደሚያስከትል ማንቃት ያለበት ሚዲያውና ኃላፊነት የሚሰማው አንቂ ሁሉ መሆን አለበት፡፡
በመንግሥት በኩልም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕጋዊ አካሄድን እስከ ተከተሉ ድረስ በምርጫው ወቅት አንዳችም ዓይነት ወከባ፣ ወይም አፈና ወይም ወደ ገጠር አካባቢዎች ለቅስቀሳ እንዳይወጡ የሚያደርግ ማዕቀብ እንዳይካሄድ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡ በሆነ አጋጣሚ ቢያንስ በታችኛው ደረጃ ከተፈጸመም ሊያጋልጠው የሚገባው ሚዲያውና ጋዜጠኞች መሆንም አለባቸው፡፡ ጉዳዩ በአገራችን የዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሙከራ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ ከምርጫ በፊትም ሆነ በኋላ በፓርቲዎች የሚቀርብ ስሞታ እንደ መሆኑ የለውጥ ኃይሉና ሕዝቡም አጥብቀው ሊያስተካክሉት የግድ ነው፡፡
በምርጫ ሒደት ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸው ሚዲያዎች ያለባቸውን ሕጋዊና ታሪካዊ ኃላፊነት ሳያጎድሉ ነው መወጣት የሚጠበቅባቸው፡፡ በተለይ የመንግሥት ሚዲያዎች የፓርቲዎችን የክርክር ነጥብና አቋምን ሚዛናዊ በሆነ ሙያዊ አሠራር መረጃዎችን ለሕዝቡ ማድረስ አለባቸው፡፡ የአንዱን ፓርቲ ቃል ሙሉውን አስተላልፎ የሌላውን ፓርቲ መልዕክት ቆራርጦ ማቅረብ ሙያዊም ፍትሐዊም አለመሆኑን ከግምት ማስገባት ግድ ይላቸዋል፡፡ አንዱን እያብጠለጠሉ፣ ሌላውን ማሞካሸትም ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ገዳዳ አተያይ ጋር መቀበር ነው ያለበት፡፡
የፓርቲዎች ሐሳብና መልዕክት በመሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን የሚፈጥር፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የሚያስከብር፣ በፌዴራል መርሆዎች ላይ የተመሠረተ፣ በነፃ ምርጫና ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር፣ በእምነትና በፆታ እኩልነት የሚሠራ የሕግ የበላይነት፣ ወዘተ ለመሳሰሉት እሴቶች ዕውቅና እየሰጠ፣ ‹‹አለኝ›› የሚላቸውን የተሻለ አማራጭ የሚያቀርብ እስከሆነ ድረስ መቆራረጥም ሆነ በኤዲቲንግ ማበላሸትም አያስፈልግም፡፡ ከሁሉ በላይ የአገራዊ አንድነትን የሚጎዱና የሕዝቦችን የዘመናት አብሮነት ጠብቆ መሄድም፣ ለፓርቲዎችም ሆነ ለሚዲያዎች የተሰመረ ቀይ መስመር መሆን አለበት፡፡
እንግዲህ ካየናቸው መንደርደሪያዎች ላይ ተነስተን ሐሳባችንን የምናጠቃልለው በዚህ የወፍ በረር ዕይታ የተዳሰሱም ሆኑ፣ ያልተወሱት የምርጫ ተዋናዮች (እንደ ምርጫ ቦርድ፣ ታዛቢዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት. . .) ሁሉ የድርሻውን መወጣት እንዳለባቸው በማስታወስ ነው፡፡ አዲስ ሥርዓት በአዲስ አስተሳሰብ በመገንባት፣ በአገራችን የተጀመረውን ለውጥ በሕዝብ ይሁንታ መሠረት ለማስያዝ ጠቃሚው መድረክ ምርጫ እንደሆነ ከወዲሁ ማሳሰቢያ ለመስጠትም ነው፡፡ መጪው ምርጫ ከቅድመ እስከ ድኅረ ጉዞው የተሳካ እንዲሆን ማድረግ ለዴሞክራሲ ማበብ ሲባል ብቻ ሳይሆን፣ ከብተና ሥጋት ወደ ለውጥ አብነት የተሸጋገረች አገር ዕውን ለማድረግም የሚበጅ በመሆኑ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡