Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የሰሞነኞች ቁጭት!

እነሆ ጉዞ ከአራት ኪሎ ወደ ቦሌ። የሰው ልጅ ታሪኩ ከሚረግጠው መሬት ይጀምራል። ከእናቱ ማህፀን ወጥቶ መሬት ዱብ ብሎ መሬት እስኪገባ ድረስ፣ መሀሉ ሠልፍ የበዛበት ረጅም ጉዞ ነው። እጅግ አድካሚ ጉዞ፡፡ እናም ይህን እውነት ተቀብሎ የተበጀባትን መሬት ውስጠ ሚስጥሯን ፈልቅቆና ተመራምሮ ቁሳዊና አዕምሮአዊ ዕድገት ያሳያል። በዚች አዛውንት ምድር ሳይዛነፉ መጓዝ የውዴታ ግዴታ ነው ተብሏል። ሰው መባል ማለት ለመኖር ከመጓዝ ሌላ ምንም እስኪመስል ድረስ። አሁን ታክሲ ተሳፍረናል። ባለፍንባቸው ጥለናቸው በምንተዋቸው ዱካዎቻችን ታሪክ እየሠራን፣ እየተዋወቅን፣ እየተለያየን፣ እየተዋደድንና እየተኳረፍን ልንጓዝ ነው። ጉዞው አጭር ቢሆንም በልባችን ግን በርካታ ረጃጅም ጉዳዮች ይዘናል፡፡ በአጭር የሚያስቀሩን ነገሮች እየበዙ እንጂ ጉዳዮችስ ነበሩን፡፡ ከግል፣ ከማኅበራዊና ከአገራዊ ጉዳዮቻችንን ጋር የሚያነጋግሩን ብዙ ነገሮች ቢኖሩንም፣ ሰከን ማለትና ግራና ቀኝ ማማተር የግድ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የሚሄድ የሚመጣው፣ ወጪ ወራጁ የረሳውን እያስታወሰ፣ ያስታወሰውን እየረሳ፣ ተላቆ በማይላቀቀው ጥርሱን ያገጠጠ የሕይወት እውነት ታጅቦ ሲርመሰመስ ሲታይ የማን ያለህ ይባላል? ይህም በዚህኛው ጎዳና ላይ የምናየው የዛሬ ታሪክ ነው። ትናንት አልፏል። ተጠያቂነቱና አይጠገቤነቱን ባስታወሱት ቁጥር ግን ዕድሜና ጊዜ እንዴት እንደ ሮጡ ማስተዋል ይቻላል። ወደ ተነሳንበት ተመልሰን እስክንሄድ፣ በበቀልንበት እስክንሸኝ ድረስ እንዲህ እንዲህ እያለ መኖር ይቀጥላል። መንገዱን የሞላው ወጪ ወራጅ ብቻ ነው!

ሜክሲኮ አደባባዩን ዞሮ የመጣ ባዶ ታክሲ ስድስት ነፍሶችን ጠራርጎ ሲጭን፣ የሐምሌ ውርጭ የታከለበት ችኮ ዝናብ ያስመረራቸው ተሳፋሪዎች ዕፎይታ ፊታቸው ላይ ይነበብ ነበር። ታክሲው ጉዞ ጀምሯል። ‹‹ውይ አሁንስ ሆድ የሚሉት ክፉ ነገር ባይኖር ምን ነበረበት?›› ትላለች ጠየም ያለች ቀጭን ቆንጆ ሴት። ከሁኔታዋ ሁሉም ነገር ትክት ያላት ትመስላለች። ‹‹ሆድማ ባይኖር ኖሮ በዚህ አስቀያሚ ክረምት አንችን የመሰለች አጠገባችን ሆና መቼ ታሞቀን ነበር? አይደል እንዴ?›› ይላታል ከፊቷ የተቀመጠ ጎልማሳ። እያሳሳቀ ትፈቅደው እንደሆን ለመሞከር ያህል ይመስላል አስተያየቱ። በእርግጥም ፊቷን ፈገግ አድርጋ ታየው ጀመረች፡፡ ‹‹የእኛ ነገር አንዴ አበሳጭቶ ወዲያው ደግሞ ፈገግ የሚያደርገን ነገር ነው የሚገርመኝ እኮ። አሁን የትራንስፖርት ችግር ስሞታዋ ሳያልቅ ከመቼው ፈገግ ማለት ጀመረች?›› ይላሉ አንዲት አዛውንት ሦስተኛው መቀመጫ ላይ ሆነው። ቋሚ የሚባል ነገር ከጠፋ ዘመን እንደሌለው የሚነግራቸው ሰው አጥተው። ‹‹አይ እማማ! ታዲያ እንዲህ ካልሆነ የዘንድሮ ነገራችን ከትራንስፖርት ችግር ጋር ተደማምሮ አይገድለንም ነበር?›› ይላቸዋል ከፊታቸው ያለ ወጣት። አዛውንቷ ቀና ብለው ወጣቱን ለረጅም ደቂቃዎች ሲያስተውሉት ቆይተው፣ ‹‹ለመሆኑ እየተዘጋጀህ ነው አንተ?›› ብለው ጠየቁት። ወጣቱ ከዕድሜያቸው አኳያ የጤንነታቸው ነገር አጠራጥሮት ጥያቄው ግራ እንዳተጋባ፣ ‹‹ለምኑ ነው የምዘጋጀው እማማ?›› አላቸው ትህትናው የድምፁን ክሮች ክፉኛ እያርገበገባቸው። ‹‹ለምኑ? ለመኪናው ነዋ። ዘንድሮ አራት እግር የሌለው አራት እግሩን እስኪበላ ቆሞ ነው የሚቀረው ሲባል የትነው ያለኸው?›› ቢሉት የኮረኮሩትን ያህል ሳቀ። የልቡን ነው መሰል የነገሩት። ‹‹አትሳቅ ቀልዴን አይደለም። ዛሬ ከታክሲና ከአውቶቡስ ጥበቃ ኩሽኔታም ቢሆን ማለፊያ ነው፤›› ሲሉት ደግመው የታክሲው ተሳፋሪዎች በሙሉ ለሳቅ ተባበሩ። ይኼኔ ከኋላ መቀመጫ በዝናብ ተደብድቦ ብርድ የሚያንቀጠቅጠው ተሳፋሪ፣ ‹‹እማማ ዕድሜ ለፆታ እኩልነት የዘንድሮ ጥሎሽ እኮ የጋራ ሆኗል። ጥሎሹ የጋራ ባይሆን ኖሮ የአዳም ዘር በዚህ ዘመን ኑሮ መቼ ይሞላለት ብለው ነው?›› በማለት፣ ሁሉም ሞልቶት እንደሚዳር አወራ። ከትራንስፖርት ችግር አንስቶ ትዳር የመሠረተው የታክሲያችን ጭውውት፣ የማይተዋወቀውን እያስተዋወቀ በረቀቀ ጥበቡ መንገዱን ያሳጥረው ጀመር። ዕድሜም እንዲህ አይደል እንዴ የሚያጥረው!

ከአፍታ ፀጥታ በኋላ ተጉዘን ወሎ ሠፈር ስንደርስ፣ ‹‹እዚህ ጋ ወራጅ አለ!›› አለ መጨረሻ ወንበር የተቀመጠ ወጣት። ወያላው፣ ‹‹ይቅርታ እዚህ ጋ ማውረድ አይቻልም። ተሻግሮ ነው የማወርድህ፤›› አለው። ወጣቱ ተቆጣ፣ ‹‹ለምን? ምንድነው ችግሩ ድሮ እንወርድበት የነበረ ቦታ አይደል እንዴ?›› አለ ቱግ ብሎ። ወያላው፣ ‹‹እኛ ምን እናውቃለን ታዲያ?›› ካለ በኋላ ከኪሱ አንድ አራት የክስ ወረቀቶች አወጣ። ‹‹ይኼው አንዱን ሳንከፍል አንዱን እየተቀጣን ነው የምናገለግላችሁ፤›› ብሎ ራሱን ከተጠያቂነት ነፃ ሲያደርግ ጫጫታው በረታ። ‹‹ቆይ ምንድን ነው የዚህ መንገድ ሚስጥር? እንዴ አሁንም በመንገዱ እኩል መገልገል አይቻልም እንዴ?›› ሲል ቀጠን ያለ ድምፅ ያላት ፊት መቀመጫ ላይ የተቀመጠች ተሳፋሪ፣ ‹‹ማን በ‘ቪአይፒዎች’ ክልል ኑር አለህ?›› ስትል እንሰማለን። በራስ ላይ መቀለድ ይሉታል ይህን የአግቦ ሽሙጥ። ‹‹እውነቴን እኮ ነው!›› ይቀጥላል ለሽሙጡ መልስ ያው ወጣት። ‹‹ተመልከቱ! ድሮ የነበረው የታክሲ ፌርማታ አሁን የለም። ሁላችንም አውቶሞቢል የታደልን ይመስል። እዚያ ባለአውቶሞቢሎች ‘ማቆም ክልክል ነው!’ ‘መዞር ክልክል ነው!’ ‘ግራ ቀኝ ሳትል አሽከርክር!’ ይባላሉ። እዚህ ደግሞ እኛ ከኑሯችንና ከዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ጋር ፍፁም የማይዛመድ የግዴታ ጉዞ አለብን። ያውም የመንቀሳቀስ ሙሉ መብት ተጎናፀፍን በምንልበት የዴሞክራሲ ዘመን። ይኼን የመሰለ ለማማት የማይመችን ውብ አስፋልት መንገድ እንዲህ ‘አብስትራክት’ ማድረግ ምንድነው? ግራ ገባን እኮ!›› ብሎ እንደ ጨረሰ አሁንም የተለየ መልስ አልተሰጠውም። ‹‹ነገርንህ እኮ! ማን ‘ቪአይፒ’ ሠፈር ኑር አለህ?›› አለችው ያችው ልጅ ደግማ። ‹‹ምን ማለት ነው ‘ቪአይፒ?’›› ብለው ሲጠይቁ አዛውንቷ ወጣቱ በፍጥነት፣ ‹‹የማትበላ ወፍ!›› አላቸው። ይኼንን የሰሙ ሲስቁ ‘ሕልምና እንግሊዝኛ እንደ ተርጓሚው ነው’ የሚሉ ይመስሉ ነበር፡፡ የዘመኑ ፖለቲከኞች ግራ የሚያጋቡን ትርጓሜው በማይገባን አጀንዳቸው መስሎን!

 ወጣቱ ተሻግሮ ወርዶ ከተለየን በኋላ ድምፁን ያልሰማነው ጎልማሳ ከኋላ መቀመጫ በስልክ መነጋገር ጀመረ። ‹‹እየመጣሁ ነው አልኩህ እኮ! ሃሎ?! አይሰማም? አንተ ብቻ ፖሊሶች ፈልገህ አስይዝልኝ!›› ይላል። ንዴትና እልህ አወራጭቶ ስልኩን እየዘጋው። የታክሲዋ ተሳፋሪዎች በፀጥታ የሰውየውን ሁኔታ ይከታተላሉ። ‹‹ሰላም አይደለም?›› አለችው ከጎኑ የተቀመጠች የቦሌ ሽቅርቅር። ‹‹ኧረ ተይኝ! የዛሬ ልጅ በየት በኩል ሰላም ይሰጣል?›› ብሏት ሩቅ ያውጠነጥን ጀመር። ጥያቄዋን መግታት ያልቻለችው ዘናጭ፣ ‹‹እና ለራስህ ልጅ ነው እንዴ ፖሊስ?›› ብላ ብትጠይቀው፣ ‹‹አዎ! ይኼውልሽ የዘንድሮ ልጅ ገመናችንን እንኳ እንዳንደብቅ አድርጎ በየመንገዱ ሲያዋርደን ይውላል…›› አላት እንደማፈር እያለ። ‹‹በዚህ በኩል ለአገር ቁሳዊ ልማትና ሀብት ስንሮጥ በዚህ የልጆቻችን ነገር አሥጊ እየሆነ መጣ፤›› ብሎ እንደ መተከዝ አደረገው። ‹‹አሄሄ! የዘንድሮ ልጅ አስተዳደግ ራሱ መቼ ሥርዓት አለው? እኛ እንኳ በዚያ በድንቁርናው ጊዜ የአሁኑን ያህል ወልደን አልተውናቸውም። የዛሬ ወላጅ ካበላ፣ ካለበሰና ትምህርት ቤት ከላከ በኋላ መቼ ዞር ብሎ ያይና?›› ብለው አዛውንቷ ትዝብታቸውን አካፈሉን። ‹‹ኧረ እውነትዎን ነው። ከግለሰብ እስከ ኅብረተሰብ ብሎም እስከ መንግሥት፣ እውነት ለመናገር የመጪው ትውልድ አዝማሚያ ያሳሰበው ያለ አልመሰለኝም። መንግሥትም ሆነ ማኅበረሰቡ ታዳጊዎችንና ወጣቶችን በተመለከተ ማውጣትና ማጥበቅ ያለባቸውን ሕግ ከእነ ጭራሹ ረስተውታል። እኛም መቼም ሲፈጥረን ካፈሰስን በኋላ መልቀም ነው የሚቀናን፡፡ ከሆነ በኋላ ካለቀ በኋላ መጮህ እንወዳለን…›› ብሎ ሳይጨርስ አንዱ፣ ‹‹ኑሮ ቀልባችንን ገፎት እንዴት ብለን እንዲህ ያለውን ጉዳይ እናስታውሰው እባካችሁ? በዚያ በኩል የሰላምና የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በዚህ በኩል ያ አሳረኛ ኑሮ ከእን ግሳንግሱ ‘ቢዚ’ አድርጎን እኮ እንዴት ብለን ነው ለልጆቻችን የምንደርስላቸው?›› ብላ ጋቢና የተቀመጠች ወይዘሮ ብሶት አሰማች። ብሶት መፍትሔ ይሆን ይመስል። ብሶተኛ በዝቶ ሁሉም አስተዛዛኝ ፈላጊ ይመስላል፡፡ ኧረ ሩጫው ለማን ነው ጎበዝ!

 ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው። ውስብስብ የአኗኗራችን ጉዳዮች ታክሲያችንን በውይይት አድምቀዋት ተጉዘን ልናበቃ ጥቂት ሜትሮች ብቻ ቀርተውናል። ሁለት ተሳፋሪዎች እንዲህ ሲባባሉ ሰማን፡፡ ‹በታክሲ ተሳፍሮ የመሄድ ትርፋችን እኮ ሌላ ሳይሆን የጭውውት ነፃነትን መታደላችን ነው…› ይባባላሉ። ‹‹ምን ዋጋ አለው የዘመኑ ሰውና የዘመኑ ፖለቲካ ዋናውን ትቶ ጥቃቅኑን እያወራ ተቸገርን እንጂ…›› ይላል ጎልማሳው። አዛውንቷ በመገረም፣ ‹‹ኧረ እናንተ ሰዎች ተመሥገን በሉ። ይኼው ከዚያ ሁሉ ውድመትና ዕልቂት ለጊዜውም ተንፈስ ብለን እርስ በርስ እየተነጋገርን ነው። ቀስ በቀስ ዴሞክራሲውና ልማቱ እየተስፋፋና እያደገ መቀጠሉ አይቀርም…›› ሲሉ ከወጣቶቹ አንዱ ሳቅ እያለ፣ ‹‹አይ እማማ የእኛን አገር ነገር ከእርስዎ የበለጠ ማን ያውቀውና? እንደሚያዩት ሁሉም ነገር ሰሞነኛ፣ መግለጫው ሰሞነኛ፣ ዴሞክራሲው ሰሞነኛ፣ ውይይቱና ሽምግልናው ሳይቀር ሰሞነኛ መሆኑ ጠፍቶዎት ነው?›› ብሎ ይጠይቃቸዋል። ‘ወረት ምድሪቷን አልብሶ ሕዝቦቿ አይተው እንዳላዩ ሆነው መኖርን ክፉኛ ተለማምደውታል’ የሚሉን ዓይነት እንመስላለን። ‹‹እንዳልከው ሰሞነኛ ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡ ነገር ግን እኛ ካላስተካከልነው ማን እንዲያስተካክልልን መጠበቅ አለብን? ለምሳሌ ምድሪቱ ለም፣ ውኃው ብዙ፣ አየሩ በየዓይነቱ፣ ወጣቱ ከምታስበው በላይ በጣም ብዙ፣ አመላችንን ገርተን ወደ ሥራ ብንሰማራ ይርበን ነበር? ከዓባይ በተጨማሪ ቀሪዎቹን ወንዞቻችንን እየገራን እንኳንስ ለራሳችን ለዓለም አንተርፍም ነበር ወይ? በማይረቡ ጉዳዮች እየተጣላን ስንፋጅ አይቆጭም ወይ? ላለፉት ስህተቶቻችን ንስሐ ገብተን በአጭሩ ታጥቀን በኅብረት ብንነሳ ምርቱ ተትረፍርፎ የትና የት አንደርስም ወይ? ከሰሞነኛ ጉዳዮቻችንን ተላቀን ወደ ሥልጣኔ የምንገሰግሰው ለዘለቄታ ጉዳዮቻችንን ትኩረት ስንሰጥ ነው…›› ሲሉ እኛ እናት የአንድ ዝነኛ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰርን ያስንቁ ነበር፡፡ ታክሲያችን ቦሌ ደርሳ ስትቆም ወያላችን ‹‹መጨረሻ!›› ብሎ ሸኘን፡፡ ሰሞነኞች ደግሞ ቁጭት ውስጥ ሆነን ወርደን ተለያየን። መልካም ጉዞ! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት