Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አቢሲኒያ ባንክ ከቪዛ ኮርፖሬሽን የሚጠቀምበትን የዲጂታል ክፍያ ቴክሎኖሎጂ ለመተግበር ተስማማ

ተዛማጅ ፅሁፎች

አቢሲኒያ ባንክ በዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎቶቹ ከሚታወቀውና ቪዛ ኮርፖሬሽን ከተሰኘው የአሜሪካ ኩባንያ ጋር በኤሌክትሮኒክ ዘዴ የሚካሄዱ ክፍያዎችን ለማቀላጠፍ የሚረዳ ‹‹ቪዛ ሳይበር ሶርስ›› የተሰኘ አማራጭ የቴክኖሎጂ አጋርነት ስምምነት መፈጸሙን አስታወቀ፡፡ ባንኩ ከቪዛ ኩባንያ ጋር በአጋርነት ለመሥራት በመስማማቱ በተለይም በቪዛ ካርድ የሚከናወኑ ዓለም አቀፍ ክፍያዎችን ለማከናወን በሚያስችለው ሥርዓት ውስጥ በአባልነት ለመካተት እንዳስቻለው ገልጿል፡፡

ከቪዛ ጋር የተደረገውን ስምምነት በማስመልከት ባንኩ እንዳስታወቀው፣ ይህ ስትራቴጂካዊ አጋርነት የኤሌክትሮኒክ ንግድን መሠረት ያደረጉ የዲጂታል ክፍያዎችን በክሬዲት ካርድ አማካይነት ለመፈጸም የሚያግዝ አሠራር ይፈጥራል፡፡

በኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ላይ የተመሠረተ የንግድ እንቅስቃሴ ኋላ ቀር በሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የጠቀሰው አቢሲኒያ ባንክ፣ ሆኖም ቱሪዝም፣ ሆቴል፣ ትራንስፖርት፣ ማኑፋክቸሪንግና መሰል ዘርፎች የዲጂታል ግብይትን ለማከናወን የሚችሉበት ጠቀሜታ እንዳለ ያስገነዝባል፡፡ የኤሌክትሮኒክ ግብይትን በሚመለከት በቅርቡ የተረቀቀው ሕግና ሌሎችም አጋዥ ማዕቀፎች የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ አመቺ ሁኔታዎችን እየፈጠሩ ስለመምጣታቸው አስታውሷል፡፡

አቢሲኒያ ከቪዛ ኩባንያ ጋር የተጣመረበት አዲስ የአገልግሎት፣ ጀማሪ የንግድ ተቋማት ክፍያቸውን በኦንላይን መፈጸም እንዲችሉ በማገዝ የንግድ ሥራቸውን ለማሳደግ እንደሚረዳቸው ይነገርለታል፡፡ በአቢሲኒያ ባንክ የዲጂታል ባንኪንግ ዋና ኦፊሰር የሆኑት ወ/ሮ ሶስና መንገሻ ስለ አገልግሎቱ ሲገልጹ፣ የቪዛ የሳይበር ሶርስ የክፍያ አማራጭ ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ መተግበር መጀመሩ፣ ለኤሌክትሮኒክ ክፍያ አዲስ አማራጭና ዕድል እንደሆነ ጠቅሰው፣ ባንኩ በዘርፉ እያደረገ ያለውን ጥረትና ዘመናዊ አሠራርን ለማስረጽ ያለውን ፍላጎት ማሳያ ብለውታል፡፡

የቪዛ ሳይበር ሶርስ የክፍያ አማራጭ ለተለያዩ የንግድ ተቋማት ክፍያዎችን ያለምንም ችግር በኦንላይን ለመቀበል የሚያስችል ሲሆን፣ ሸማቾችና ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ጎብኚዎች ደኅንነቱ የተጠበቀ የክፍያ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሠራር አለው፡፡ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም አገር ቤት ለሚገኙ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው አገልግሎቱን በመጠቀም ያሻቸውን መሸመት የሚችሉበት አሠራር ያካተተ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ የቪዛ ኮርፖሬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ አበበ ግርማይ በበኩላቸው ‹‹መጪው ዘመን የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትና ከገንዘብ ንክኪ ነፃ የሆነ ማኅበረሰብ የሚፈጠርበት ነው፡፡ ቪዛም የወደፊቱን የንግድ ሥርዓት ቅርፅ ለማስያዝ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሀብቶች፣ መሠረተ ልማት እንዲሁም በዲጂታል አቅምና ክህሎት ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እያፈሰሰ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡

አቢሲኒያ ባንክ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ላለፉት 24 ዓመታት ሲንቀሳቀስ የቆየ የግል አክሲዮን ኩባንያ ሲሆን፣ በየዓመቱ ትርማነታቸውን በከፍተኛ መጠን እያሳደጉ ከመጡና በ2012 ዓ.ም. ተቀማጭ ገንዘባቸውን በከፍተኛ መጠን ካሳደጉ ባንኮች አንዱ ነው፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች