የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ ሰላምና መረጋጋት ለኢንቨስትመንት ማደግና መስፋት የሚጫወተውን ወሳኝ ሚና በማጉላት፣ ይህንን የሚቃረኑ ግጭቶች የአገሪቱን መልካም ገጽታ በማበላሸት ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን እንደሚያበላሹ አስታውቋል፡፡
ምክር ቤቱ ባለፈው ሳምንት ለመንግሥት ያቀረበውን የፖሊሲ ምክረ ሐሳብ ይፋ ባደረገበትና መግለጫ በሰጠበት ስለ ሰላምና መረጋጋት አስፈላጊነትና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አስታውቆ ነበር፡፡ በሰላም ዕጦት ሳቢያ ከሰሞኑ በንግድ ምክር ቤቱ አባላት የሚንቀሳቀሱ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ ስለደረሱ ጥፋቶች የገለጹት የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጥ፣ በርካታ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ከደረሰው መስተጓጎል ባሻገር፣ ሕዝብ፣ ባለሀብቱና መንግሥት ላይ የደረሰው ጥፋት ከፍተኛ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ በኢንቨስትመንትና በንግድ ሥራዎች ላይ የሚደርሰው ጥፋት፣ ሀብታቸውን አፍስሰው የሚሠሩ ሌሎች ባለሀብቶች ፍላጎቱና መተማመኑ እንዳይኖራቸው ያደርጋል ብለዋል፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ ክስተት የሚደናገጡ ባለሀብቶች መልሰው ለመምጣትና ዳግም ወደ ሥራ ለመግባት ረዥም ጊዜ እንደሚወስድባቸውም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡
ሰላም በማስፈን የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ ለሁሉም ህልውና ወሳኝ የመሆኑን ያህል፣ በተለይ የውጭ ባለሀብቱን ፍሰት ለማስፋፋት ያግዛል ያሉት ፕሬዚዳንቷ፣ በሰላምና መረጋጋት ላይ ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግ፣ አገር ያለ ኢንቨስትመንት ማደግ ስለማይቻል፣ ወጣቶች በተለይ ለሰላም በመቆም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማስጠበቅ እንዳለባቸው ወ/ሮ መሰንበት ተናግረዋል፡፡
በአገሪቱ ዜጎች ሕይወትና አካል ላይ፣ ሀብትና ንብረታቸው ላይ የደረሰው ጥፋት ብሎም፣ በንግድ ምክር ቤቱ አባላት በሚንቀሳቀሱ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ በደረሰው ጥፋት ማዘናቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቷ፣ ባለሀብቶቹ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ መንግሥትና የንግዱ ኅብረተሰብ ድጋፍ በመስጠት የሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን በአሁኑ ወቅት የኮሮና ወረርሽኝ እያደረሰ ያለውን ዓለም አቀፍ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በማስታወስ፣ የወረርሽኙ መስፋፋት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚም ክፉኛ እንዳቀዛቀዘው ምክር ቤታቸው እንደሚገነዘብ የጠቀሱ ሲሆን፣ በበሽታው ሳቢያ በተለይ በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችም ሆኑ የንግድ ምክር ቤቱ አባላት ክፉኛ እንዳይጎዱ ብሎም ተጋላጭ እንዳይሆኑ መንግሥት እየወሰደ ያለው ዕርምጃ የንግዱ ማኅበረሰብም የሚያደርገው ተሳትፎ እየተደረገ ካለውም በላይ እንዲጠናከር ጠይቀዋል፡፡ በአንድ በኩል የሕዝብን ጤንነት፣ በሌላ በኩል የአገርን ኢኮኖሚ ከጉዳት መጠበቅ የወቅቱ ወሳኝ ሥራ እንደሆነ የተናገሩት ወ/ሮ መሰንበት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለዓመታት ከተጓዘበት የዕድገት መንገድ አኳያ፣ ምጣኔ ሀብቱ በማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች ሲመዘን በአሁኑ ወቅት ተግዳሮት እንዳጋጠመው ጠቅሰዋል፡፡
‹‹የንግድ ሚዛን ጉድለት፣ የዋጋ ንረት፣ ከፍተኛ የዕዳ ጫናና የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ኢፍትሐዊ የንግድ ውድድር፣ ደካማ የኢንቨስትመንት መሬት አቅርቦት፣ የምርታማነት ችግር፣ በዓለም መድረክ የተወዳዳሪነት ፈተና፣ የቴክኖሎጂ ኋላቀርነትና የሰው ኃይል እጥረት የምጣኔ ሀብት ዕድገቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደሩ ማየት ይቻላል፤›› በማለት በከረሙ ችግሮች ላይ አዳዲስ ችግሮች ያሳደሩትን ጫና አመላክተዋል፡፡
እንዲህ ያሉ ችግሮች የኢኮኖሚውን ግስጋሴ በተለይም የግሉን ዘርፍ ዕድገት በአሉታዊ መንገድ እንደሚገዳደሩት፣ ይህንን ተደራራቢ ችግር ንግድ ምክር ቤቱ እንደሚገነዘብ፣ የግሉ ዘርፍ በአገሪቱ የተደቀነውን ድህነትና ኋላቀርነት በማስወገድ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲሰፍን የድርሻውን እንዲወጣ የሚያስችሉ በጥናትና በዕውቀት ላይ የተመሠረቱ መፍትሔዎች ሊዘረጉለት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በግሉ ዘርፍና በመንግሥት መካከል እንደ ድልድይ በመሆን ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል የግሉን ዘርፍ ዓበይት ማነቆዎች ለመንግሥት በማቅረብ የፖሊሲ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ በጥናትና በመረጃ የተደገፈ የፖሊሲ ምክረ ሐሳብ ያቀርባል ያሉት ወ/ሮ መሰንበት፣ ምክር ቤቱ ስላቀረባቸው አዳዲስ ምክረ ሐሳቦችም ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡
በዚሁ መሠረት የአገሪቱን ኢኮኖሚና ተያያዥ ችግሮች ለመቅረፍ መንግሥት በግብዓትነት ቢወስደው እንደሚጠቅመው የገለጹትን የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ ተገቢውን ድርሻ እንዲይዝ ለማድረግ የሚያስችል የአምስት ዓመት የፖሊሲ ምክረ ሐሳብ በንግድ ምክር ቤቱ መቅረቡን አስታውቀዋል፡፡
የፖሊሲ ሰነዱ የኢኮኖሚውን ዕድገት ለማስጠበቅና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማጎልበት እንዲረዳ በማሰብ የተሰናዳ ስለመሆኑ ተገልጾ በፖሊሲ ግብዓትነት የቀበረው ሰነድ፣ በስምንት ዋና ዋና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ መፍትሔ ጠቋሚ ምክረ ሐሳቦች መያዙ ተብራርቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የግሉ ዘርፍ የልማት አጋርነት በምን አግባብ መቃኘት እንዳለበት ያሳያል ተብሏል፡፡
ፖሊሲው ከዳሰሳቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል የፋይናንስ አቅራቦትና ተደራሽነት፣ የዕዳና የበጀት ጉድለት ቅነሳ፣ የመሬት አቅርቦት፣ የንግድ ተወዳዳሪነትና ንግድን ለማንቀሳቀስ የማያመቹ ከባቢ ሁኔታዎችን ስለማሻሻል፣ ዲጂታል ኢኮኖሚና የሰው ኃይል አቅርቦት የሚሉትን ይኙበታል፡፡
ተወዳዳሪ የግል ዘርፍ ለመፍጠርና የመንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ውጤታማ እንዲሆን፣ ንግድ ምክር ቤቱ የሚያቀርበው ምክረ ሐሳብ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የጠቀሱት የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንትና አጋሮቻቸው፣ በምክር ቤቱ ሰፊ ይዘት ያለው ምክረ ሐሳብ ለመንግሥት ሲቀርብ የመጀመርያው እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
‹‹እንዲህ ዓይነት አገራዊ አስተዋጽኦ በአገራችን ብዙም ያልተለመደና ኢትዮጵያን እንወዳለን ወደ ብልጽግናም እንወስዳታለን ለምንል ወገኖችና ተቋማት ዳር ቆሞ ከመተቸት ይልቅ ቀርቦ አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚሻል የሚያመላክት በመሆኑ፣ ከሁሉ በላይ በምሳሌነቱ ትልቅ ግምት እንደሚሰጠው እናምናለን፤›› በማለት ንግድ ምክር ቤት ስለወሰደው ተነሳሽነት ተናግረዋል፡፡
በፖሊሲ ሰነዱ ውስጥ ስለቀረቡት ምክረ ሐሳቦች ከተሰጡ ማብራሪያዎች ለመረዳት እንደተቻለው ጠንካራ የግል ዘርፍ ለመፍጠር የተዘጋጀው ሰነድ፣ የንግድ ማኅበረሰቡን ችግሮች ከማመላከት ባሻገር፣ በምክር ቤቱ የተጠቆሙ የመፍትሔ ሐሳቦች ነጥረው የወጡ፣ ለፖሊሲ ዝግጅት ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ አንኳር ጉዳዮች በጊዜና በመጠን ተለክተው እንደቀረቡ ተብራርቷል፡፡
የግሉ ዘርፍ በፖሊሲ የተደገፈ ሥፍራ ሊሰጠው እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡ የወደፊቱን የአገሪቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አቅጣጫ ለማመላከት የሚያስችሉ አጋዥ የውይይት መድረኮች እንዲዘጋጁ መንገድ ይጠርጋል የተባለው የፖሊሲ ሰነድ፣ በአሁኑ ወቅት መንግሥት እየወሰዳቸው ከሚገኙ የለውጥ ዕርምጃዎች አኳያ የግሉ ዘርፍም ሚናውን እንዲወጣ የሚያግዙ ሐሳቦች የሚብላሉበትን መንገድ እንደሚፈጥር የምክር ቤቱ ኃላፊዎች አስታውቀዋል፡፡
ምክር ቤቱ ያቀረበውን የኢኮኖሚ ምክረ ሐሳቦች የተካተቱበት ሰነድ፣ ከአራት ወራት በፊት ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈትና ለሌሎችም የመንግሥት አካላት ቀርቦ እንደነበር ፕሬዚዳንቷ አስታውሰዋል፡፡ ሰነዱ የግል ዘርፉን አሳታፊ የሚያደርጉና የተቀናጀ የፖሊሲ መስተጋብር እንዲኖር ለማገዝ የተዘጋጀ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡
በንግድ ምክር ቤቱ የፖሊሲ ይዘቶች ላይ የንግድ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳና ምክትል ዋና ጸሐፊው አቶ ሺበሺ ቤተማርያም ዝርዝር ማብራሪያ አቀርበዋል፡፡ ውይይት እየተደረገበት ከሚገኘው ከአሥር ዓመቱ መሪ ዕቅድ አንፃር አኳያ፣ ንግድ ምክር ቤቱ ያቀረባቸው ሐሳቦች ተመሳሳይነትና ተዛምዶ እንዳላቸው ኃላፊዎቹ ጠቁመዋል፡፡