የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከ2008 እስከ 2012 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ያከናወናቸውን ሥራዎች ይፋ ባደረገበት ወቅት እንዳስታወቀው፣ በማዳበሪያ ግዥ፣ ሽያጭና ሥርጭት ላይ ባደረገው የአሠራር ማሻሻያ መሠረት አለአግባብ ይወጣ የነበረ በድምሩ 3.293 ቢሊዮን ብር ማዳኑን አስታወቀ፡፡
ለኮርፖሬሽኑ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት በቅርቡ የተሾሙት አቶ ክፍሌ ወልደ ማርያም፣ ሐምሌ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ ከተከናወነ የአሠራር ማሻሻያ በመነሳት፣ በዚያው ዓመት ከተከናወነ አጠቃላይ ግዥ ውስጥ የ2.7 ቢሊዮን ብር እንዲሁም በ2010 ዓ.ም. ከተከናወነ ግዥ የ593 ሚሊዮን ብር አለአግባብ ለደላሎች ይከፈል የነበረ ገንዘብ በማስቀረት በጠቅላላው 3.293 ቢሊዮን ብር ማዳን ችሏል፡፡
በዚህ መሠረትም አርሶ አደሩ የዋጋ ቅናሽ ተጠቃሚነት እንዲያገኝ በማገዝና የቀጥታ ግዥ በመፈጸም፣ በኩንታል የ300 ብር ቅናሽ እንዲያገኝ በማድረግ ከርፖሬሽኑ ማዳበሪያ እንዳከፋፈለ አስታውቀዋል፡፡
አቶ ክፍሌ እንደገለጹት፣ በኮርፖሬሽኑ ታቅደው ሲከናወኑ የሰነበቱት ሥራዎች ውጤታማ አፈጻጸም አሳይተዋል፡፡ ይህም ሆኖ የ30 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የእንስሳት መድኃኒቶችን ለማስመጣትና ለማሠራጨት አቅዶ ሊሸጥ የተቻለው ግን የ5.3 ሚሊዮን ብር ብቻ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ዝቅተኛ ውጤት ሊመዘገብ የቻለው ግን በውጭ ምንዛሪ እጥረት እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ከአፈር ማዳበሪያና ከሌሎችም የግብርና ግብዓቶች አቅርቦት አንፃር ለ2012/13 የሰብል ምርት ዘመን የሚውል በጠቅላላው የ14.58 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን፣ ከዚህ ውስጥም 13.55 ሚሊዮን ኩንታል አገር ውስጥ ገብቶ መሠራጨቱን፣ ቀሪው መጠንም እየገባ እንደሚገኝ በማስታወስ፣ የዕቅዱን 97 በመቶ እንዳሳካ ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል፡፡
በተሸኘው በጀት ዓመት የአግሮ ኬሚካሎች መርጫ መሣሪያዎች ለማቅረብ የ658.9 ሚሊዮን ብር ግዥ ተፈጽሞ ግብርና ሚኒስቴር በሚያወጣው ድልድል መሠረት ለክልሎች በመከፋፈል ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ በ2012 ዓ.ም. ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ፈሳሽ ማዳበሪያ ማሠራጨቱም ታውቋል፡፡ በሜካናይዜሽን የታገዘ የእርሻ ልማት ሥራዎችን ለማከናወን፣ 1066 ሔክታር መሬት ምንጣሮ፣ የ602 ሔክታር ግርድፍ ድልዳሎ እንዲሁም 157 ሔክታር የንጥር ድልዳሎ ሥራዎችን በማከናወን በድምሩ 16.7 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል፡፡
ከምርት ማሰባሰብና ማጓጓዝ ሥራዎች አራት ሚሊዮን ብር፣ ከእርሻና ከኮንስትራክሽን መሣሪያዎች ጥገና ሁለት ሚሊዮን ብር፣ ከእርሻ መሣሪያዎች መለዋወጫ አቅርቦት 129.14 ሚሊዮን ብር፣ ከተሽከርካሪዎች አስተዳደርና ጥገና ሥራ አፈጻጸም 11.45 ሚሊዮን ብር ጨምሮ ከሌሎች የገቢ ምንጮችም በርካታ ገቢ ማሰባሰብ እንደተቻለ ሥራ አስጻሚው አስታውቀዋል፡፡