Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልሰባኛ ዓመቱ እየታሰበ ያለው ቃኘው የከተተበት የኮርያ ዘመቻ

ሰባኛ ዓመቱ እየታሰበ ያለው ቃኘው የከተተበት የኮርያ ዘመቻ

ቀን:

ከሰባት አሠርታት በፊት ደቡብ ኮርያ በሰሜን ኮርያ መወረሯን ተከትሎ በምላሹም የደቡብ ኮርያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ኢትዮጵያ ከሌሎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አባል አገሮች ጋር ተባበረች​​፡፡ ዘንድሮ የኮርያ ጦርነት የተጀመረበት 70 ዓመት መታሰቢያ ከአገሪቱ በተጨማሪ በጦርነቱ የተሳተፉት አገሮች እያከበሩት ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ያዘመተው የቃኘው ሻለቃ ጦር ደግሞ በጦርነቱ ከተሳተፈ 69 ዓመት ሆኖታል፡፡ ሁለቱ ኮርያዎች ቀኑን አክብረው ሲውሉ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በዘመቻው የተሳተፈችበትን ቀን ታስቦ እንዲውል አድርጋለች፡፡

 ደቡብ ኮርያ ባካሄደችው በዓል ላይ የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች ተወካይ ያልተገኙትና ቀኑም ታስቦ ብቻ እንዲውል የተደረገው ዓለምን እያተራመሰ ባለው ኮቪድ-19 ምክንያት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች ማኅበር ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መለሰ ተሰማ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በኮርያ ጦርነት ውስጥ የተሳታፊነት ጥሪ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደደረሳት ጦሯን በማሰማራት ረገድ ለአንድ ዓመት ያህል ዘግይታለች፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት በአገሪቱ የሠለጠነና ዘመናዊ ጦር የነበረው የክብር ዘበኛ ሠራዊት ብቻ ስለነበረና ከዚህም ሠራዊት ብቃትና ጥንካሬ ያላቸውን ወታደሮች ለመምረጥ፣ ትምህርት (ኦረንቴሽን) ለመስጠትና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ለማከናወን በቂ ጊዜ በማስፈለጉ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይሏን በመላክ ብቻ ሳትወሰን ለደቡብ ኮርያ የ400 ሺሕ ዶላር ድጋፍ እንዳደረገች፣ አከታትላም የመጀመርያውን ቃኘው ሻለቃ ጦር ሚያዝያ 6 ቀን 1943 ዓ.ም. ቀጥላም ሁለተኛውን፣ ሦስተኛውን፣ አራተኛውን ቃኘው ሻለቆችን ከ1944 እስከ 1947 ዓ.ም. ድረስ በየተራ እንዳዘመተች ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት፡፡

ከኮሎኔል መለስ ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው፣ ኢትዮጵያ ጥሪውን የተቀበለችው በሦስት ዋና ዋና ምክንያቶት ነው፡፡ ከምክንያቶቹም መካከል አንደኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገሮች ድጋፍ ሲጠይቁ በቻርተሩ መሠረት ድጋፉን ማግኘት መብታቸው በመሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በሊግ ኦፍ ኔሽን በደረሰበት ድጋፍ ማጣት የተነሳ ቂም አለመያዟን ለማሳየት ሲሆን፣ ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች መካከል ጥሪው የደረሳት ብቸኛዋ አገር በመሆኗ ነው፡፡ ይህም ሁኔታ ኢትዮጵያ ለ”ሴኩሪቲ ኮሌክቲቭ” ያላትን ቁርጠኛ አቋም እንደሚያሳይና ለገፅታም ግንባታ አመቺ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡

ቃኘው ሻለቃ ጦር ዓለም አቀፍ ግዳጁን ለመፈጸም በተንቀሳቀሰበት ወቅት የተለያዩ ተግዳሮቶች ገጥመውት እንደነበር ፕሬዚዳንቱ አስታውሰው፣ ከገጠሙትም ተግዳሮቶች መካከል የትራንስፖርት ቅብብሎሹና የመግባቢያ ቋንቋ ችግሮች ተጠቃሾች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የትራንስፖርቱን ቅብብሎሽ በተመለከተ ከጃንሜዳ ለገሃር ድረስ አሜሪካ ሠራሽ በሆነው ‹‹ማክ›› መኪና ላይ ተሳፍሮ መጓጓዝ፣ ከዛም እስከ ጂቡቲ ድረስ በባቡር፣ ከጂቡቲ የደቡብ ኮርያ የወደብ ከተማ ከሆነችው ‹‹ፑዛን›› ድረስ በመርከብ የ22 ቀን ጉዞ፣ እዛም እንደደረሱ ስድስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው ማሠልጠኛ ካምፕ በተሽከርካሪ፣ እንዲሁም ውጊያው በሚካሄድበት አካባቢ ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ በእግርና በመኪና ያደረገው ጉዞ ድካም እንዳስከተለበት ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ለሦስት ወራት ያህል በተካሄደውም ሥልጠና በልዩ ልዩ ዓይነት ዘመናዊ የጦር መሣሪያ አጠቃቀም ጠቃሚ ዕውቀት ለመቅሰም ችሏል፡፡ ከዚህም ሌላ ከአካባቢው ኅብረተሰብ፣ ከአካባቢያዊ አየር ሁኔታ እንዲሁም ኮረብታማ፣ ሰበርባራማና ዳገታማ ከሆነው የደቡብ ኮርያ መሬት አቀማመጥ ጋር ለመለማመድና ለመዛመድ አስችሎታል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ወዲያ የሻለቃው አባላቱ መቅጠንና ከሲታ የሆነ የሰውነት ቅርጽ መኖር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አባል አገሮቹ መከላከያ ኃይሎች አመራሮች ዘንድ ንቀት እንዳሳደረባቸው፣ ይህን መሰል ከሲታ ጦር ውጊያውን ማሸነፍ ቀርቶ መቋቋም እንኳን እንደማይችል አድርገው ገምተው እንደነበር ነው ኮሎኔል መለስ የገለጹት፡፡

የሻለቃው አባላት ግን ቋንቋውንም ለመልመድ ጊዜ እንዳልፈጀባቸው፣ በተሰማሩበት የውጊያ ቀጣና ሁሉ ድል ከማስመዝገብ በስተቀር የተማረከበት ሰው አለመኖሩ፣ ሌሎች የድርጅቱ አባል አገሮች ዘማቾች ያቃታቸውን የውጊያ እንቅስቃሴ የቃኘው ሻለቃ ጦር አባላት እየተተኩ በጠላት ላይ ከፍተኛ ድል በመቀዳጀት አካባቢውን ነፃ በማውጣት ያስመዘገቡት የድል ውጤት ሲታይ አፍሪካ እንዲህ ዓይነት ጀግና ጦር አላት ወይ? እስከሚያስብል የደረሰ አድናቆት ማትረፋቸውን ነው ያመለከቱት፡፡

    አሜሪካም የራሷን የጦር ኃይል፣ ለዕርዳታ ከመጣውና ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተመድ አባል አገሮች ጦር ጋር በማቀናጀት ወራሪውን የሰሜን ጦር መልሶ በማጥቃት ደቡብ ኮርያን ነፃ አወጣች፡፡ ጥምር ጦሩም ደቡብ ኮርያን ነፃ በማድረግ ብቻ ሳይወሰን ወራሪውን ጦር ወደ ሰሜን ኮርያ እያሳደደ የቻይናና የሰሜን ኮርያ ወሰን የሆነችውን ማንቹሪያን ለመያዝ ተቃረበ፡፡ ያን ጊዜ ቻይና ጎረቤቴ ስትወረርና ወሰኔ ሲደፈር ዝም ብዬ አልመለከትም ብላ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ጦር አስታጥቃ ጦርነት ውስጥ ገባች፡፡

ቻይና ጦርነት ውስጥ ስትገባ የውጊያው መልክ ተለወጠ፡፡ በዚህም የተባበሩት መንግሥታት ጦር ወደኋላ በማፈግፈግ ሰሜን ኮርያን ለቆ መውጣት ነበረበት፡፡ ይህም ሆኖ ከዚህ በፊትት ከነበረው ወሰን ሲደርስ የፈሰሰ ደም ይፍሰስ እንጂ ከዚህ በኋላ አናፈገፍግም በማለት በኃይል መዋጋት ጀመረ፡፡ የቻይናና ሰሜን ኮርያ ጦርም ከዚህ በኋላ ባለበት እንዲቆምና መከላከያ እንዲይዝም ተገደደ፡፡ አሁን ድረስም የሁለቱ ተከላካይ ኃይሎች ተፋጠው የሚገኙት በዚሁ ሥፍራ ነው፡፡ ይህም ሥፍራ 38ኛው መስመር (ሰርቲ ኤይት ፓራላል) በመባል ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያም ካሰማራቻቸው የጦር ኃይሎች መካከል ከፍተኛውን የጦር ገፈት የቀመሱት የመጀመርያውና ሁለተኛው ቃኘው ሻለቆች ሲሆኑ በተለይ አራተኛው ቃኘው ሻለቃ የዘመተው በሰሜንና ደቡብ ኮርያ መካከል የተኩስ አቋም ስምምነት ከተደረገ በኋላ ነው፡፡ ሲሠራ የቆየውም ሰላም የማስከበሩን እንቅስቃሴ ተግባራዊ በማድረግ ነው፡፡ ወደ አገሩም የተመለሰው፣ ከመካከሉ 150 የሰው ኃይል ያለው አምስተኛ ቃኘው የሻምበል ጦር ኮርያ ውስጥ ቆይቶ የማረጋጋቱን ሥራ እንዲያከናውን በማድረግ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድም በቀሩት የተመድ አባል አገሮች ኃይሎችም ዘንድ ተፈጻሚነት ሆኗል፡፡

እንደ ኮሎኔል  መለስ ማብራሪያ አንደኛው ሻለቃ ለመጀመርያ ጊዜ  ከጠላት ነፃ በወጣው ‹‹ቻንቹን›› ከተማ ውስጥ ለኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች መታሰቢያ ሐውልት ቆሞላቸዋል፡፡ ሐውልቱንም የመረቁት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ናቸው፡፡ ከዚህም  ሌላ በሐውልቱ አካባቢ ጣሪያቸው በሳር ክዳን የተሸፈኑና የኢትዮጵያን ባህላዊ  ገጽታ የሚያንፀባርቁ ጎጆዎች ተገንብተዋል፡፡ በጦርነቱ  ከፍተኛ ተጋድሎ  ለፈጸሙና ድል ለተቀዳጁ ኢትዮጵያውያን ጨምሮ ለአራት የተመድ አባል አገሮች መከላከያ ኃይሎች መታሰቢያ የሚሆንና በየአገሮቻቸው ስም የሚጠሩ አዳራሾችም ተሠርተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ትልቁ አዳራሽ የኢትዮጵያ አዳራሽ ነው፡፡ እነዚህም ግንባታዎች ከፍተኛ የሆነ የቱሪስት መስህብ ለመሆን በቅተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ለመጀመርያ ጊዜ በነርስነት ካሠለጠናቸው ስድስት ነርሶች መካከል ሁለቱ ማለትም፣ ሲስተር አስቴር አያናና ሲስተር ብርቅነሽ ከበደ ኮርያ በመዝመት በጦርነቱ ለቆሰሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገሮች ወታደሮች ተገቢውን የሕክምና ዕርዳታ በመስጠትና በአስተርጓሚነትም በመሰማራት ዓለም አቀፍ ግዳጃቸውን ተወጥተዋል፡፡

በዚህም አገልግሎታቸው ሁለቱም እንስቶች የሙሉ መቶ አለቅነት ማዕረግ ያገኙ ሲሆን የመቶ አለቃ ሲስተር አስቴር አያና ግን ለሁለተኛ ጊዜ ኮንጎ በመዝመት ላበረከቱ ሰብዓዊ አገልግሎትና ለፈጸሙት ጀግንነት የሻምበልነትን ማዕረግ አግኝተዋል፡፡ ግዳጃቸውን ፈጽመው ወደ አገራቸው ከተመለሱም በኋላ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘንድ ቀርበው ምስጋና ተችሮአቸዋል፡፡ ከጊዜ በኋላ በደረሰባቸው የጤንነት መታወክ ሳቢያ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ በሕይወት የሚገኙት መቶ አለቃ ሲስተር ብርቀነሽ ናቸው፡፡

በኮርያ ልሳነ ምድር ዓለም አቀፍ ግዳጃቸውን ፈጽመው ወደ አገር ከተመለሱት የቃኘው ሻለቃ አባላት መካከል በአሁኑ ጊዜ በሕይወት የሚገኙ ከ100 በላይ ሲሆኑ፣ የደቡብ ኮርያ መንግሥትም ለእነዚህ ባለውለታዎች በየወሩ በነፍስ ወከፍ 1500 ብር አበል ይከፍላቸዋል፡፡ አዲስ አበባ በሚገኘው ኮርያ ሆስፒታል ውስጥ ሙሉ የሕክምና ዕርዳታ በነፃ፣ ለሚስቶቻቸው ደግሞ 50 በመቶ በማስከፈል ተገቢውን ሕክምና ዕርዳታ ያገኛሉ፡፡ ለልጆቻቸውም ደቡብ ኮርያ ውስጥ ነፃ የትምህርት ዕድል (ስኮላርሺፕ) ሰጥቶላቸዋል፡፡

ከዚህም ሌላ አፍንጮ በር አካባቢና ናይጄሪያ ኤምባሲ አጠገብ የሚገኘውን ፓርክ የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች ብሔራዊ ፓርክ ተብሎ የተሰየመ ሲሆን፣ በፓርኩም ውስጥ ለደቡብ ኮርያ ነፃነት ከጠላት ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ሲተናነቁ ለወደቁ የቃኘው ሻለቃ ጀግኖች መታሰቢያ ሐውልት ቆሞላቸዋል፡፡ በፓርኩ ሙዚየምና የማኅበሩ ጽሕፈት ቤት ከመገንባቱ በተጨማሪ፣ ጃንሜዳና የቀድሞ ክብር ዘበኛ ካምፕ አካባቢ የሚገኘው አደባባይ በቃኘው ሻለቃ ጦር ስም መሰየሙን ኮሎኔል መለስ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...