Wednesday, February 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለኮቪድ-19 የሚውሉ የኢትዮጵያ ባህል መድኃኒቶች እስከ ምን?

ለኮቪድ-19 የሚውሉ የኢትዮጵያ ባህል መድኃኒቶች እስከ ምን?

ቀን:

ዘመናዊ ሕክምና እንደ አሁኑ ከመስፋፋቱ በፊት አብዛኛው የዓለምም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለሕመማቸው ፈውስም ሆነ ማስታገሻ የሚሹት የአገር ባህል መድኃኒቶችን በመጠቀም ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ በዘመናዊው የጤና ዘርፍ ይህንንም ያህል ያላደገች በመሆኗ ሕዝቧ የአገር በቀል መድኃኒቶቿ ላይ ሙጥኝ ማለቱ እሙን ነው፡፡ በዓለም ላይ ከሚገኙ ከ8000000  በላይ እፅዋቶች 7000000 ያህሉ በሚገኙባት ኢትዮጵያ 80 በመቶ ያህል ሕዝብ የሚጠቀመውም ባህላዊ መድኃኒት እንደሆነ ይነገራል፡፡

ኢትዮጵያ የዘመናዊ ሕክምና ተቋዳሽ ከመሆኗ በፊት ሕዝቦቿ የነበራቸውን አገር በቀል ዕውቀት ተጠቅመው ቅጠል በመበጠስ፣ ሥር በመማስ፣ የተመረጡ ምግቦችን በመመገብ፣ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን በማጀልና በማሸት፣በመብጣትና በዋግምት በማከም የታመሙ ሰዎችን ሲፈውሱ እንደነበረ በማኅበረሰብ ሳይንስ ዘርፍ የተደረጉ ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡

ሰዎች ከልምዳቸው ተነስተው ከጓሮዋቸው ከሚገኙ ተክሎች ከራስ ምታት፣ ከሆድ ቁርጠት፣ ከጉንፋን፣ ከቁስልና ከሌሎች ሕመማቸው ሲታገሱና ሲፈወሱ ማየቱም የተለመደ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የኖቭል ኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ገባ እንደተባለም ሰዎች መድኃኒት ይሆናሉ የተባሉ የባህል መድኃኒቶችን ሲሞክሩ ተስተውለዋል፡፡ በርካታ የባህል መድኃኒት አዋቂዎችም መፍትሔ አለን ብለው መንግሥት ይስማን ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ከ50 በላይ የሚሆኑ የአገር ባህል መድኃኒት አዋቂዎች ኮቪድ-19 ቫይረስን ለማዳን ያስችላል ብለው ያመኑባቸውን የባህል መድኃኒቶችም አዘጋጅተው መንግሥት ያየው ዘንድ አቅርበዋል፡፡

መንግሥትም ከነዚህም መካከል አምስት አዋቂዎች ያመረቷቸውን መድኃኒቶች ደኅንነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ጥናት ለመጀመር የሚረዳ የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ ላይ ነው፡፡ የዳሰሳ ጥናቱ የሚከናወነው በባህል መድኃኒት ዙሪያ ቀደም ሲል በአገር ውስጥና በውጭ አገር የተዘጋጁ ጥናታዊ ጽሑፎችን በመንተራስ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የባህልና ዘመናዊ መድኃኒት ምርምር ዳይሬክቶሬት ተጠባባቂ ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍሬሕይወት ተካ እንደገለጹት፣ ለደኅንነት ጥናት የቀረቡት የባህል መድኃኒቶች እያንዳንዳቸው ከሦስት እስከ ሰባት በድምሩ 37 የሚጠጉ የዕፅዋት፣ የማዕድን፣ የእንስሳት ውጤቶችና የመሳሰሉ ድብልቆች አሉባቸው፡፡

እያንዳንዱ መድኃኒት በፈሳሽ፣ በዱቄት፣ በልቁጥ ወይ በሌላ መልክ ተዘጋጅቶ ነው የሚወሰደው? በተጠቀሱት በአንደኛው ወይም በሁሉም መንገድ የተዘጋጀው መድኃኒት ሥራውን የሚሠራው የመተንፈሻ አካል ላይ ነው? በቀጥታ ቫይረሱን ነው የሚገለው? ለሚሉትና ሌሎችም ጥያቄዎች ከቅድመ ጥናት ጽሑፎች ለመረዳት እንደሚቻል ጠቅሰዋል፡፡

በእያንዳንዱ መድኃኒት ውስጥ ያለውም ድብልቅ ዝርያውን ማወቅ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ተጠባባቂ ዳይሬክተሯ አመልክተው፣ ለምሳሌ ያህል ከድብልቆቹ መካከል ዳማከሴን ወስዶ ማየትና ዳማከሴ ብዙ ዝርያዎች እንዳሉት መረዳት እንደሚቻል፣ ከዚህም በመነሳት የትኛው ዝርያ ነው የሚደባለቀው የሚለው በባለሙያ ታውቆ መለየት እንዳለበት፣ በዚህ መልኩ ዕፆችንና ሌሎችንም ድብልቆች ለመለየትና ለማረጋገጥ ጥናታዊ ጽሑፎችን መዳሰስ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

አገሮች በምን መንገድ እየሠሩ ይገኛሉ? የሚለውን ማየትና ማንበብ፣ እኛስ እንደነሱ እንሠራለን ወይ?  እንችላለን ወይ? ብሎ መጠየቅ ለዚህም አዎንታዊ መልስ ከተገኘ ወደ ደኅንነቱ ጥናት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በጥናታዊ ጽሑፍ ላይ የሚካሄደው የዳሰሳ ጥናት የመድኃኒቱን ደኅንነት ለማረጋገጥ እንደ መንደርደሪያ እንደሚያገለግል ወ/ሮ ፍሬሕይወት ተናግረዋል፡፡

የዳሰሳው ጥናት መቼ ያልቃል? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ወ/ሮ ፍሬሕይወት ሲመልሱ፣ ‹‹በዚህ ቀን ያልቃል ብሎ ቁርጥ ያለውን ቀን ለመናገር ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም በየመድኃኒቱ የተካተተው የእያንዳንዱ ድብልቅ ዝርያ በሚገባ ተለይቶ መተንተንና መጠናቀቅ አለበት፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ደግሞ ጊዜ ይፈጃል፤›› ብለዋል፡፡

የዳሰሳው ጥናት እንዳበቃ እያንዳንዱ መድኃኒት በምን ያህል መጠን ቢወሰድ በሰው ልጅ ላይ ጉዳት ያስከትላል ወይም አያስከትልም? የሚለው በላቦራቶሪ እንስሳት ላይ የሙከራ ሥራ እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዓይነቱ የደኅንነት ጥናት የመድኃኒት አወሳሰድ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ በሚል ተለይቶ እንደሚቀመጥ፣ ኮሮና ቫይረስን የሚከላከል ከሆነ የአጭርና የመካከለኛውን ጊዜ ማየቱ አማራጭ እንደሆነ፣ በዚህም የተነሳ የአጭር ጊዜው ከአንድ ሳምንት እስከ 14 ቀናት ሲሆን፣ መካከለኛው ጊዜ ደግሞ 28 ቀናት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

አሁን ለተያዘው የደኅንነት ጥናት የመካከለኛ ጊዜው አማራጭ ተደርጎ እንደተወሰደ፣ በዚህም በእንስሳቱ ላይ ሙከራ ተደርጎ በሚፈለገው ቀን ውስጥ ሙከራ በተደረገት እንስሳት ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት የማያስከትል መሆኑ ከተረጋገጠ የፈዋሽነት ጥናት እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

የዳይሬክቶሬቱ ተግባር የአንድን መድኃኒት ደኅንነት፣ ጥራትና ፈዋሽነት ማረጋገጥ ቢሆንም፣ ኮቪድ-19ን በተመለከተ ደኅንነቱንና ጥራቱን የማረጋገጥ ሥራ ብቻ ይሠራል፡፡ ፈዋሽነቱን በተመለከተ ኢንስቲትዩቱ ባለው የላቦራቶሪ አቅም መሥራት እንደማይቻል፣ ይህም የሆነበት ምክንያት ኮቪድ-19 አዲስ እንደመሆኑ ቫይረሱን አምጥቶ በቲዩብ ወይም በዲሽ አሳድጎና በተዘጋጀው መድኃኒት ይሙት አይሙት የሚለውን ለማየት የኢንስቲትዩቱ የላቦራቶሪ መጠን ከፍ ያለ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም ፈዋሽነቱን የማረጋገጥ ሥራ ለማካሄድ ሰበታ ከሚገኘው ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ተቋም ጋር በቅንጅት ለማከናወን የሚያስችል ስምምነት መደረጉን፣ በዚህ መልኩ ለመሥራት ያስፈለገውም ተቋሙ የተሻለ ልምድና ብቁ የሆነ ላቦራቶሪ ስላለው መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

በዚህ ዓይነቱ ሥራ ላይም የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ አብሮ እንደሚሠራ፣ የወላይታና የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲዎችም በመድኃኒቱ ፈዋሽነት ሥራ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውም ታውቋል፡፡

አምስት የባህል መድኃኒት አዋቂዎች ያቀረቡዋቸው መድኃኒቶች ደኅንነታቸውን፣ ጥራታቸውንና ፈዋሽነታቸውን የማረጋገጡ ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ እንዲመዘገቡ ጉዳዩ ለሚመለከተው መንግሥታዊ አካል እንደሚቀርቡ በመቀጠልም፣ ጤና ሚኒስቴር የመድኃኒቶችን አጠቃቀም ወይም አወሳሰድ መመርያን እንደሚያወጣ በኢትዮጵያ ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውልና እንደ አማራጭ መድኃኒት ተደርጎ እንዲወሰድ የሚለውን ይወስናል፡፡

ከዚህ በፊት ከምርምር ወጥቶና በፋብሪካ ተመርቶ በፋርማሲ ውስጥ ለገበያ የቀረበ ምንም ዓይነት የባህል መድኃኒት እንደሌለ፣ ዳይሬክቶሬቱ በባህልና በዘመናዊ መድኃኒት ዙሪያ የተጣለበትን ኃላፊነት እየተወጣ ያለው ለራሱ በተመደበለት በጀት እንጂ ከውጭ የሚደረግለት የፋይናንስ ድጋፍ አለመኖሩን፣ በዚህም የተነሳ የባህል መድኃኒት አዋቂዎች ካመረቷቸው የባህል መድኃኒቶች መካከል የአምስት አዋቂዎችን መድኃኒት ደኅንነት ለማጥናት የተገደደው በአቅም ማነስ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የባህል መድኃኒት አዋቂዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ሐጂ ሼክ ዓሊ አደም ማኅበሩ ከ2,800 በላይ አባላት እንዳሉትና በባህል መድኃኒት ዙሪያ ተገቢውን ጥናትና ምርምር ለማካሄድ ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር ስምምነት ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

ደኅንነታቸውን፣ ጥራታቸውንና ፈዋሽነታቸውን ለማረጋገጥ ከቀረቡት 50 አዋቂዎች ያመረቷቸው የባህል መድኃኒቶች መካከል፣ 25 የሚሆኑት ወደ ሆድ የሚገቡ ሲሆን፣ የቀሩት ደግሞ የሚቀቡና የሚታጠኑ ናቸው፡፡ አሁን እየተካሄደ ያለው ጥናት ከተጠናቀቀ በኋላ ሌሎች አምስት አዋቂዎች ያመረቱት መድኃኒቶች ጥናት እንደሚቀጥልና የቀሪዎቹም ጥናት በዚህ መልኩ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል፡፡

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር  በመጋቢት 2012 ዓ.ም. የሀገር በቀል እውቀት ከዘመናዊው ሳይንስ ጋር በማቀናጀት ኮሮና ቫይረስን ለማከም የተሰራው መድሃኒት መሰረታዊ የምርምር ሂደት አልፎ ተደጋጋሚ የቤተ ሙከራ ሂደቶች ማለፉን መግለጹ ይታወሳል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ፣ የኢትዮ ቴሌኮምን የ2012 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም አስመልክተው ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ፣ በአገር ውስጥ ዕውቀት ተመስርቶ ለኮቪድ 19 የተሰራው መድሐኒት ላይ የተጀመረውን ሳይንሳዊ ምርምር እየደገፉ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በኩል የተጀመረውንና የአገር በቀል ዕውቀትን ከዘመናዊ ሳይንስ አቀናጅቶ ኮቪድ-19ኝን ለማከም የተሠራውን መድሐኒት ዕውን ለማድረግ፣ በሚኒስቴሩ በኩል የቀረበለትን የድጋፍ ጥሪ ተቀብሎ 600,000 ዶላር ለመስጠት ቃል በገባው መሰረት የመጀመሪያውን ዙር ገንዘብ መልቀቁን ወይዘሪት ፍሬሕይወት ተናግረዋል፡፡

በኢኖቪሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በኩል ምርምር እየተደረገበት የሚገኘው የኮቪዲ-19 መድሐኒት የተለያዩ ምርምሮችን ያለፈ ሲሆን፣ ተስፋ የታየበት መሆኑንም አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የካቲት አብዮት – ጥያቄዎችሽ ዛሬም እየወዘወዙን ነው!

በበቀለ ሹሜ አጭር መግቢያ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከ1960ዎች ወጣቶች ርዝራዦች አንዱ...

የሰሞኑ የ“መኖሪያ ቤቶች” የጨረታ ሽያጭ ምን ዓይነት ሕጋዊ መሠረት አለው?   

በዳዊት ዮሐንስ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አየር ላይ ከሚንሸረሸሩ ዜናዎች...

ሁለቱ ወጎች፡ ከሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! እስከ በዓሉ ቤርሙዳ

በተክለ ጻድቅ በላቸው ሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! ከሁለት ሦስት ዓመት...

ለትግራይ ክልል ድርቅ ተፈናቃዮች አፋጣኝና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ...