የኮሮና ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ለአምስት ወራት የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከማብቃቱ በፊት፣ አዋጁን የማራዘም አስፈላጊነት ገምግሞ ለመወሰን መንግሥት ምክክር እያደረገ መሆኑ ታወቀ።
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሐሙስ ሐምሌ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ባዘጋጀው ዝግ መድረክ፣ ከተለያዩ ምሁራን ጋር በጉዳዩ ላይ ምክክር ማድረጉን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል።
የውይይቱ ትኩረትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማራዘም ተገቢነት አለው ወይስ የለውም የሚለውን በተመለከተ፣ ባለሙያዎቹ የሚሰጡትን ሙያዊ ትንታኔ መቀበል እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል።
በሌላ በኩል የአዋጁን አፈጻጸም ለመከታተል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ፣ እንዲሁም ጤና ሚኒስቴርና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በጋራ በመሆን የአዋጁን አፈጻጸም ለመገምገም ለማክሰኞ ነሐሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ መያዛቸው ታውቋል።
አፈጻጸሙን ከመገምገም ባለፈም አዋጁ መራዘም አለበት ወይስ የለበትም በሚል ጉዳይ ላይም እንደሚመክሩ፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ወረርሽኙን ለመከላከል የተጣለውና በአሁኑ ወቅት በተግባር ላይ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ተፈጻሚ መሆን የጀመረው መጋቢት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ሲሆን፣ ፀንቶ እንዲቆይ የተወሰነውም ለአምስት ወራት ነው።
በዚህ መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈጻሚነት በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ያበቃል። ነገር ግን አዋጁን ለማራዘም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ለተጨማሪ አራት ወራት ማራዘም እንደሚቻል በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93(3) ላይ ተደንግጓል።
‹‹በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተደነገገው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ሊቆይ የሚችለው እስከ ስድስት ወራት ነው። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምፅ አንድን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በየአራት ወሩ በተደጋጋሚ እንዲታደስ ሊያደርግ ይችላል፤›› በማለት ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 93(3) ላይ ደንግጓል።
በአንቀጽ 93 (6) (ሠ) ሥር ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸምን ለመከታተል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚቋቋመው መርማሪ ቦርድ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲቀጥል ለምክር ቤቱ ጥያቄ ሲቀርብ አስተያየቱን ለምክር ቤቱ እንደሚያቀርብ ተደንግጓል።
ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች፣ አብዛኞቹ አዋጁ እንዲራዘም ምክረ ሐሳባቸውን እንደ ሰጡ ምንጮች ገልጸዋል።
በዚህ ውይይት ላይ የተሳተፉት ምሁራን አዋጁ መራዘም እንዳለበት ቢያምኑም አዋጁ የሚጥላቸው ክልከላዎች ላይ ማሻሻያ ሊደረግ እንደሚገባ መምከራቸውን፣ ለዚህም ያቀረቡት ምክንያት ወረርሽኙ ለተራዘመ ጊዜ የመቆየት ዕድሉ ሰፊ በመሆኑ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ታሳቢ ማድረግ ይኖርበታል የሚል ነው።
ወረርሽኙ በዓለም አቀፍ ደረጃ አዲስ የአኗኗር ዘዬን እየፈጠረ በመሆኑ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መቀጠል የለበትም ብለው የተከራከሩ ጥቂት ተሳታፊዎች እንደነበሩም ለማወቅ ተችሏል።
መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም አለበት ብሎ የሚወስን ከሆነ፣ በእረፍት ላይ የሚገኘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰኔ ወር ከማብቃቱ አስቀድሞ ለአስቸኳይ ስብሰባ ተጠርቶ ማፅደቅ ይኖርበታል።