Tuesday, July 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

በቀደም ዕለት በክረምቱ ቅዝቃዜና ጭጋግ ሰውነቴ ተኮራምቶ በጠዋት ቢሮ ስደርስ፣ የሥራ ባልደረባዬ ትክዝ ብሎ ጣራ ጣራውን ሲያይ አገኘሁት፡፡ ለወትሮው ሳቂታና ተጫዋች የነበረው ይኼው የሥራ ባልደረባዬ በመሥሪያ ቤታችን ውስጥ የሚታወቀው በጨዋታ አዋቂነቱና አዝናኝነቱ ብቻ አይደለም፡፡ በተለያዩ የትምህርት መስኮች የተለያዩ ዲግሪዎችን ያገኘና በሥራው ዓለምም የበርካታ ዓመታት ልምድ ያለው ሰው ነው፡፡ ይህ ለሌሎቻችን አርዓያና መምህር የሆነ የሥራ ባልደረባዬ እንዲህ ክፍትና ትክዝ ያደረገው ምን ይሆን? መቼም በዚህ ከበድ ያለ ጊዜ ማንም ቀን ሰው የራሱ ብቻ ሳይሆን የቤተሰብ፣ የዘመድ፣ የጎረቤትና ከዚያም አልፎ የሰብዓዊ ፍጡራን ችግርና መከራ እያስከፋው መተከዙ አይቀርም፡፡ ለማንኛውም የሥራ ባልደረባዬን የገጠመውን ማወቅ ስላለብኝ ወደ እሱ አመራሁ፡፡

የተለመደውን ሰላምታ ካቀረብኩለት በኋላ ምን እንዳስተከዘው ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ በንዴት የቀሉ ዓይኖቹን እያንከባለለ ለመናገር ሲሞክር ያ ርቱዕ አንደበቱ ተሳሰረበት፡፡ ከዚህ በፊት የሚፈልገውን መልዕክት ለማስተላለፍ ፈጣን የነበረው አንደበቱ ከመያያዙም በላይ፣ እጆቹና እግሮቹ ከቁጥጥር ውጭ ሆነው እየተንቀጠቀጡ ነበር፡፡ ያመመው ስለመሰለኝ ወደ ክሊኒክ እንደምወስደው ነገርኩት፡፡ በሚንቀጠቀጠው እጁ አለመታመሙን ከነገረኝ በኋላ በረጅሙ ተነፈሰ፡፡ አተነፋፈሱ ከበድ ያለ ጉዳይ እንደ ገጠመው ያስታውቃል፡፡

ከአፍታ ዝምታ በኋላ፣ “ይኼውልህ እስካሁን ድረስ ከዛሬ ነገ ይስተካከል ይሆናል በማለት በውስጤ አፍኜው የያዝኩት ጉዳይ ነበር፡፡ አሁን ግን ተስፋ የሚያስቆርጥ ደረጃ ላይ መድረሱን ሳውቅ እንቅልፍ ካጣሁ ሳምንት ተቆጠረ፡፡ ምግብ አልበላህ አለኝ፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ በጣም የምወዳቸውን አምስት ዘመዶቼ የደረሰባቸውን መከራ ሳስብ መታገስ አቃተኝ…” እያለ ሲብሰለሰል ደነገጥኩ፡፡ ምን ሆኖ ይሆን? በሐኪም የተነገረው አሥጊ ሕመም ደርሶባቸው ይሆን? ከዚህ በፊት ኤችአይቪና ካንሰር የያዛቸው ሰዎች አጋጥመውኝ ስለሚያውቁም ግራ ተጋባሁ፡፡

እንደ ምንም ራሴን ካረጋጋሁ በኋላ፣ “ምን አጋጠማቸው?” በማለት እየፈራሁ ጠየቅኩት፡፡ “በአምስት ዘመዶቼ ንብረት ላይ ውድመትና ዝርፊያ ከመፈጸሙም በላይ፣ ይህንን ድርጊት ከዚህ ከአዲስ አበባ ጭምር ያቀነባበሩ ሰዎች መኖራቸውን ከሰማሁ ወዲህ እንቅልፍ አጥቻለሁ፡፡ በጽንፈኛ ፖለቲከኞች ተቀስቅሰው የወጡ ወጣቶች ንፁኃንን ከመግደልና ከማውደም በተጨማሪ፣ የግል ቂም ያላቸው ታዋቂ ግለሰቦች ጭምር ያቄሙባቸውን ሰዎች ንብረት ሲያስወድሙ እንደነበር ሰምተሃል? ካልሰማህ እኔ ልንገርህ፣ ይህ ሰይጣናዊ ድርጊት በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ተፈጽሟል…” እያለ ደም ሥሩ ሲገታተር ወባ የያዘው ይመስል ነበር፡፡ “እነ ማን ናቸው ሰዎቹ?” የሚል ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ “ተወኝ እባክህ እዚህ አገር ስንት ጉድ አለ መሰለህ…” እያለ ሳግ ሲተናነቀው ጉዳዩ ገባኝ፡፡

ይኼ የሥራ ባልደረባዬ ከዘመዶቹ ንብረት ውድመት በተጨማሪ በጎረቤቶቻቸው ላይ የተፈጸመውን ዘግናኝ ግድያ ሲነግረኝ፣ እንዲህ ያለ አረመኔነት እዚህ አገር ውስጥ መቼ እንደ ተለመደ ግራ ገባኝ፡፡ ሰሞኑን ሚስቱ ጎራዴ ታጥቀው በመጡ አረመኔዎች ሕፃናት ልጆቹ ፊት የተገደለችበት አባወራ፣ በሰቀቀን ውስጥ ሆኖ የደረሰባቸውን ነውረኛ ድርጊት ሲናገር በቪዲዮ አይቼ ስለነበር ውስጤ ታሞ ነው የሰነበተው፡፡ የሥራ ባልደረባዬ ዘመዶቹ ሥራ ሳይመርጡ ለበርካታ ዓመታት የለፉበት ንብረታቸው መውደሙ ብቻ ሳይሆን ያስቆጨው፣ በገዛ አገራቸው እንደ ባዕድ ታይተው መኖሪያ ጭምር ማጣታቸው ነው፡፡ በተጨማሪም በዚህ በሠለጠነ ዘመን ሰብዓዊ ፍጡርን እንደ አውሬ እያደኑ የገደሉና ያስገደሉ ግለሰቦች፣ አሁንም በተለያዩ መንገዶች ዘመዶቹን እንደሚያስፈራሩዋቸው መስማቱ አንገብግቦታል፡፡

“ሕግ ባለበት አገር ውስጥ በወገኖቻችን ላይ ግድያና ውድመት ተፈጽሞባቸው የሚታደጋቸው መጥፋቱን ስረዳ ሕይወቴን ማጥፋት እመኛለሁ፤” ሲለኝ ደነገጥኩ፡፡ እሱን እያባበልኩና እያረጋጋሁ ሳለሁ ድንገት አንዲት የሥራ ባልደረባችን መጣች፡፡ ሁኔታችንን ስታይ ተደናግጣ፣ “ምን ሆናችኋል?” በማለት ጠየቀችን፡፡ ቁጭ እንድትል ካደረግኳት በኋላ ጓደኛዬ የነገረኝን ዘርዝሬ አስረዳኋት፡፡ “አይ ወንድሜ! አይ ወንድሜ!” እያለች ደረቷን ከደቃች በኋላ የሌሎች ሰዎችን ገጠመኞች ነገረችን፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ተመሳሳይ ድርጊቶች መፈጸማቸውንና በርካታ ወገኖችም መጎዳታቸውን ገልጻ፣ ይህ አልበቃ ብሎ በየአካባቢው ያሉ ሹሞች አሁንም እያስፈራሩዋቸው እህህ እያሉ በሥጋት ስለሚኖሩ በርካታ ምስኪኖች ዘረዘረችልን፡፡

ይህች የሥራ ባልደረባችን፣ “ቆይ ይህ ሁሉ ድርጊት ሲፈጸም መንግሥት በአገሩ የለም? የተለያዩ የሰላም ኮንፈረንሶች ተካሂደው ዕርቅ ወርዶ በሰላም ለመኖር አልተቻለም፡፡ የታለ የተጀመረው ሥራ ሲባል ውጤቱ ዜሮ፡፡ እዚህ አገር በኃይለኛ መንግሥት እየተረገጡ ካልሆነ በስተቀር ለጥ ሰጥ ብሎ በሥርዓት መኖር አይቻልም እንዴ? ኃይለኞችና ጉልበተኞች እንደፈለጉ ሆነው ሕዝቡን ሲያጠቁ ከጥቃት የሚከላከል ተቆጣጣሪ መንግሥታዊ ተቋም ወይም የፀጥታ አካል ከሌለ እንዴት በሰላም ይኖራል? የማንም ሥርዓተ አልበኛ እየተነሳ ከመንግሥት በላይ ሲሆን እንዴት ዝም ይባላል?” እያለች በኃይለ ቃል ተናገረች፡፡ “ከሰብዓዊነት ተርቆ አረመኔነት በተስፋፋበት አገር የሕግ የበላይነት ከተጣሰ የማፍያዎች ሰለባ መሆናችን አይቀርም…” ስትል የስንቶቻችን ዕጣ ፈንታ አሳሰበኝ፡፡ ሕግን ተማምነው ሕይወታቸውንና ንብረታቸውን የሚያጡ ንፁኃን ዜጎች ሲበረክቱ፣ የአገር ህልውናም ያሳስባል፡፡ ሕገወጥነት ሲሰፍን ደግሞ ምን ሊከተል እንደሚችል ሁላችንም እናውቀዋለን፡፡ እኔ የምለው መንግሥት ሕግ አክብሮ ያስከብር ነው፡፡ ሕግ የማይከበርበት አገር እንኳንስ የእኛ ቢጤ ተራ ዜጎች መንግሥትን የሚመሩ ሰዎች ሳይቀሩ የሕገወጦች ሰለባ ይሆናሉ፡፡ ልብ ቢባል መልካም ነው፡፡

(ንብረት አድነው፣ ከኮልፌ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...