በመስፍን ሀብቱ
የአንድን አገር የፖለቲካ ‘ዳይናሚክስ’ ለመረዳት የፖለቲካ ክስተቶቹን ብቻ ነጥሎ መረዳት ብቻ አይበቃም። በተለይም የፖለቲካ ትንተና የሚያደርጉ ተንታኞችና የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች/አክቲቪስቶች የኅብረተሰባዊ ዳይናሚክሱን (ሶሻል ዳይናሚክስ) ካልተረዱ ትክክለኛ ትንተና ወይም ፖሊሲ ለማውጣት ሊቸግራቸው ይችላል። በኢትዮጵያ በሁሉም ኅብረተሰቦች ውስጥ አዎንታዊ ሊባሉ የሚችሉ አያሌ ኅብረተሰባዊ ወጎች (Values) እንደ መኖራቸው አሉታዊ የሆኑ አያሌ ወጎችም አሏቸው። የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ መሳ በመሳ ልማዳዊ (Traditional) በመሆኑ ዘመናዊ መንግሥት ለማቋቋም ከተደረገው ሙከራ ጋር ተያይዞ ቅንጣት በምታክለዋ የኢንዱስትሪ ዘርፍ፣ በዘመናዊ ንግድና በተለይም በዘመናዊ ትምህርት ምክንያት እነዚህ ልማዳዊ ወጎች መቀየር ጀምረው ነበር። በዚህ ረገድ ወደ ዘመናዊነት ለሚደረገው ሽግግር ትልቁ እንቅፋት የራሱ የገዥው መደብ አባላት መሳ በመሳ ልማዳዊ በመሆናቸው የኑሮ ዘይቤያቸውም ልማዳዊ ነበር።
ምንም ሚኒስትር ወይም ዳኛ ቢሆን፣ መምህር ወይም የጦር መኮንን ቢሆን፣ በግል ኑሮው ልማዳዊ ከመሆኑ የተነሳ እንኳን ለወጣቱ ትውልድ አርዓያ ሊሆን ከልጆቹ አንዳንዴም ከባለቤቱ ጋር በሚገባው ቅራኔ (ወጎች ላይ የተመሠረቱ ቅራኔዎች) ምክንያት፣ የራሱንም ቤተሰብ በሚገባው መምራት ያልቻለውም ነበር። ከዚህ የተነሳ የገዥው መደብ አንድ እግሩ ዘመናዊነት ላይ ያረፈ ቢመስልም እንዳለ ልማዳዊ ነበር ማለት ይቻላል። ለዚህ ነው አገሪቱንም በሙሉ ልብ ወደ ዘመናዊነት ሊመራት ያልቻለው። ራስ ካሳ ንጉሡን፣ ‹‹ይኼን ሁሉ የደሃ ልጅ አስተምረህ ኋላ ራስህ ላይ እባብ ይጠመጥምብሃል›› ያሉትን ልብ ይሏል። ያኔ ገንነው የነበሩት ወጎች የልማዳዊው ወጎች ነበሩ። ከእነዚህም ወጎች በርካታ አሉታዊ ገጽታዎች ያላቸው ቢሆኑም ተገቢና ምን ጊዜም ጠቃሚ የሆኑ ወጎችም ነበሩ። በዚህ ረገድ አንዳንድ ሰዎች የነበሩትን ልማዳዊ ወጎችን ያለ ምንም ሂስ እንዳለ ልንኮራባቸው የሚገቡ ወጎች ናቸው ማለታቸውና አንዳንድ የምዕራባዊው ዘመናዊነት ላይ ጫና የሚያደርጉ ደግሞ፣ ልማዳዊ ወጎችን መሳ በመሳ “ኋላቀር” ብለው መደፍጠጣቸው ተገቢ አይደለም።
ይህ ሁኔታ የሚያሳየው አገሪቱ የሽግግር ጅማሮ ላይ አንደ መሆኗ በባህልም ረገድ ሽግግር ላይ እንደነበረች ነው። የዓለም ሁኔታ በተለይም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በማያወላዳ መንገድ መላው ዓለም ወደ ዘመናዊነት ዓለም ለመግባት ሽግግር ላይ ነበር ማለት ይቻላል። እዚህ ላይ እንደ ሶሻል ሲስተም ካፒታሊዝምም ሶሻሊዝምም የዘመናዊ መንግሥት ፕሮጀክቶች መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። በሁለቱ ሶሻል ሲስተሞች መሀል በነበረው እሽቅድድም፣ በተለይም የካፒታሊስቱ ወገን ተሰሚነቱን ከሚያስፋፋበት ዘዴ አንደኛው ምዕራባዊነትን በባህላዊ ዘዴ ማራገብ ነበር። በዚህ ረገድ የምዕራቡ ዓለም መሪ የሆነው ዩናይትድ ስቴትስ በሆሊውድ ፊልሞች፣ በሮክ ዘፈኖች፣ በሚዲያ፣ በመጽሔቶች፣ በፋሽን ዲዛይኖች፣ እንዲሁም በዘመናዊ ትምህርትና በሌሎችም ባህል ነክ ዘዴዎች በአንድ በኩል እንደ አሜሪካ ዴሞክራሲና ነፃነት የሰፈነበት፣ የሠለጠነ፣ ሁሉም በሽ በሽ የሆነበት፣ እንዲያውም ወርቅ የሚታፈስበት እስኪመስል ድረስ እጅግ መጠነ ሰፊ ባህላዊ ዘመቻ ሲያደርግ በሌላ በኩል ደግሞ ሶሻሊስት ነን በሚሉ አገሮች (በጊዜው ሶቭየት ኅብረት፣ ቻይና፣ ወዘተ.) ውስጥ ያለውን ሥርዓት “የኮሙዩኒስት ሥርዓት” እያለ የማጥላላትና የማበሻቀጥ ዘመቻ አካሂዷል። ይህንን ሲያደርግ በራሱ አገር ውስጥ ለሰብዓዊ መብት የሚታገሉትን ቀደም ሲል በባርነት ተሸማቅቀው የነበሩትን አፍሮ አሜሪካኖች፣ የሶሻሊስት ሥርዓት የፈለጉትን ሁሉ እያሳደደ እያሰረና እየገደለ ነበር። ይኼኛውን ድርጊቱን ግን በምንም ዓይነት አይጠቅሰውም።
ሶሻሊስት ነን የሚሉትም በዚያው ልክ የድሮ ሥርዓት ናፋቂ፣ የአሜሪካ ቡችላ እያሉ በርካታ ሰው አሠቃይተዋል፣ ገድለዋልም። አሁን እንደ ኢትዮጵያ ያሉት አገሮች ደግሞ የእነዚህ ሁለት ኃያላን ወጎች መፋለሚያ ሆኑ። የንጉሡ መንግሥት የዩናይትድ ስቴትስ ተከታይ ስለነበር በአገሪቱ ገንኖ የነበረው የውጭ ወግ፣ የአሜሪካኖቹ በተለይም የሆሊውድ ወግ ነበር። ልማዳዊ ወጎችን ይፈታተኑ ከነበሩት አንደኛው ይኼው የአሜሪካው ወግ ሆነ። የእዚህ ወግ ነፀብራቁ በብዙ መንገድ ይገለጽ ነበር። ምሁሩ የአሜሪካውን አመለካከት ይዞ ይኼ ነው መንገዱ ይላል፣ ሚዲያው የዜናና የትንተና ምንጩ የምዕራቡ ሆነ፣ አንዳንድ ከሆሊውድ ፊልሞች ቲፎዞነት ወደ ሙዚቃ የገቡትም ዘፋኞች ኤልቪስ ፕሪስሊ ነን አሉ። በአጭሩ ምዕራባዊነት እንደ ባህል እንዲህ በመሰለ ጥራዝ ነጠቅነት ይገለጽ ነበር። ይህ ሁሉ ሲሆን ከአገሪቱ ሕዝቦች 90 በመቶ የሚሆነው ይኼ የምዕራቡ ባህላዊ ወረርሽኝ ያልነካው ወይ ገበሬ ወይ አርብቶ አደር ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው የደርግ አገዛዝ የመጣው።
የ17 ዓመታቱ የደርግ አገዛዝ ይኼን የምዕራቡን ባህላዊ ወረራ ከላይ በፖሊሲና በፕሮፓጋንዳ ደረጃ ሊቀይረው ቢሞክርም፣ ራሱ በሕዝቡ ዘንድ እጅግ የተጠላ ስለነበር እንዲያውም “የማያውቁት አገር ይናፍቃል” በመሰለ በርካታ ሰው ጭራሽ የምዕራቡ በተለይም የአሜሪካ ናፋቂ ሆነ። በወያኔ ጊዜ ደግሞ አገዛዙ የምዕራቡ ደጋፊ ነኝ በማለቱና “የሶሻሊስቱ” ዓለምም ስላበቃለት ለምዕራቡ ልማድ ማጎብደዱ በአንድ ጊዜ ተመነደገ። በእዚያ ላይ ዩናይትድ ስቴትስ ዲቪ የሚባል ፕሮግራም ጀምሮ ሰዎችን እያወዳደረ በነፃ ወደ አሜሪካ ያግዝ ጀመር። አሜሪካ ከመቅፅበት ወርቅ “የሚታፈስበት” ሆነ። እዚያ የሄዱትም በአብላጫው ስለዓለም ታሪክና የፖለቲካ ሁኔታ፣ እንዲሁም ስለአሜሪካ ታሪክና ፖለቲካ ራሱ በቂ ግንዛቤው ያልነበራቸው ስለነበሩ አዕምሯቸው በአሜሪካ የአመለካከት ሳሙና የታጠበ ሆነ። ገንዘብ እያጠራቀሙ ወደ አገር ለዕረፍት ሲመጡ በዚህ ደሃ ሕዝብ ላይ ጉራቸውን ነፉበት፣ የወላጆቻቸው ቤት እያለ ትናንት የኖሩበትን ቤት ረሳነው በመሰለ ያለ ሆቴል አያርፉም። በተለይም ወጣቱ ይኼን እያየ ዓላማውም ህልሙም አሜሪካ መግባት ሆነ።
ይኼ ሁሉ ሲሆን ማኅበራዊ ዳይናሚክሱ ደግሞ ምን እንደ ደረሰ ማየት ያስፈልጋል። በደርግ እጅግ ግፈኛ አገዛዝ ምክንያት በተለይም የቀይ ሽብር ብሎ አገሪቱን በሽብር ሲገዛ ያደረገው እጅግ ዘግናኝ ግድያና ድብደባ በሰው መሀል መተማመን እንዳይኖር አደረገ። አለመተማመኑ ከፖለቲካ ነፃ ስላደረገ በሰላም ለመኖር ዓይነተኛ ባህላዊ ወግ ሆነ። ከጣሊያን ጦርነት ጀምሮ የተገነባው በባልንጀራ መሀል የነበረው መተማመን ተነነ። ተማምነው ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ነፃነትና ዴሞክራሲ የታገሉት የተረፋቸው መረሸንና መገረፍ ሲሆን፣ በሰላም የመኖር አማራጩ እንዲያም ሲል ኑሮን ለመግፋት የሚያዋጣው ማጎብደዱ ሆነ። ሳያምኑበት ለደርግና ለባለሥልጣኑ ለቀበሌ ሊቀመንበር ሳይቀር ማጎብደዱ “የሚያዋጣ” ሆነ።
በደርግ ጭፍጨፋ አያሌ ምሁራን ስላለቁ ወይም ወደ ስደት ስለሄዱ በአገሪቱ የዕውቀት ክፍተት ተፈጠረ። ምሁር ነኝ የሚለው ራሱ አጎብዳጅ ሆነ። በወያኔም ጊዜ ይኼው አጎብዳጅነት ቀጠለ። ወያኔም የሚያጎበድዱለትን እንጂ ሐሳባቸውን የገለጹትን ስለማይፈልግ የአጎብዳጅነት ባህሉ ቀጠለ። ያጎበደደ ይወጣለት ጀመር። በቂ ትምህርትና ሥልጠና የሌላቸው የወያኔ ባለሥልጣናትና ካድሬዎች ኢትዮጵያን የምታህል አገር ሲገዙና ሲፈልጡ ከተጠቀሙበት መንገድ አንደኛው፣ ለአገዛዛቸው እንዲመቻቸው ካረቀቁት ሕገመንግሥት በላይ ያልታወጀ ‘ሕግ’ ነበራቸው፣ የጫካ ሕግ (Law of the Jungle)። ሙስና ለመፈጸም ሕጉ ሳያመች ሲቀር በጫካው ሕግ ብዙ ነገር ተሠርቷል፣ በቂ ትምህርት እንደሌለው እየታወቀ ካድሬው አጭበርብሮም፣ ገዝቶትም ዲግሪ በዲግሪ ሆነ። በተለይም ቢሮክራሲ ውስጥ የተሰገሰገው ንዑስ ከበርቴ ይህችም አለች ለካ በመሰለ በተራው ዲግሪ በዲግሪ ሆነና የቢሮክራሲው በር እንዲከፈትለት አደረገ። ይህ እንደሠራ ሲታወቅ በማጭበርበር አርት የተካኑ ሰዎች ብቅ እያሉ ያልሆኑትን ነን እያሉ ሥልጣንም ሀብትም አካበቱ። ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ በዚህ የማጭበርበር ዘዴ የተካነ የባለጌ ሊቅ ‹‹ፕሮፌሰር ነኝ፣ አለቃዬም ኦባማ ነው›› ብሎ ስንት ጉድ እንደሠራ ይታወቃል።
እንዲህ ያለው ሌብነት እየሠራ ሲታይ በርካታ ሰው ተጨመረበት። ዲግሪ፣ ሰርቲፊኬት፣ የመንጃ ፈቃድ፣ እንዲሁም ሌላውም ማመሳከሪያ ሁሉ በጉቦ ማውጣት ልማድ ሆነ። እንደ ነውርም መቆጠሩ እየቀረ ሄደ፣ ሁሉም እያረገው ነዋ! ይህ አመለካከት ሰው የተለየ ባህሪ እንዲኖር አደረገው። በቀደም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ሰው የማይታመን ሆነ፣ ቅሌታሙ በዛ፣ የመንግሥት ሠራተኛው ሥራውን እንዳያጣ እንጂ ለአገሩ መሥራት የሚለው በአዕምሮው እንዳይኖር ሆነ፣ አስመሳይነት፣ ያልሆነውን ሆንኩ ባይነት፣ አጭባርባሪነት ነገሠ። ባህላዊ፣ ልማዳዊና የወጎቻችን እሴቶች እየተቀየሩ ሄዱ። አሜሪካ ልጆቻቸውን ሊጎበኙ የሄዱ አዛውንት እንኳ ሳይቀሩ ሰዎች ለዘመዶቻቸው እንዲያደርሱላቸው የሰጧቸውን ገንዘብ ስንቶቹ ሳይሰጡ እንደቀሩ ‹‹ሽማግሌው ሳይቀር ቅሌታም ሆኗል›› እስኪባል ራሳቸው እንደበሉት የታወቀ ነው። በአገራችን የነበሩ (አሁንም ትንሽ የቀሩ) የሚያስመሠግኑ የልማድና የወጎ እሴቶቻችን በእንደዚህ ዓይነት መንገድ ተቀያየሩ።
እንዲህ ያለው የእሴቶች መለወጥ በአገር ወዳድ ስሜታችን ላይም ተፅዕኖውን አሳረፈ። አሜሪካን ከማምለክ የተነሳ ምንም ነገር ይሁን ከአሜሪካ ከሆነ ይወደሳል። አሜሪካ የሚኖረውም ኢትዮጵያዊ “ዳያስፖራ” በሚል በተሳሳተ ቅፅል ተጠምቆ ይወደስና ይመለክ ጀመር። ትናንት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያልጨረሰው አሜሪካም ሄዶ ሳይማር የጉልበት ሥራ የሚሠራው ሁሉ እንደ አዋቂ ይታይ ጀመር። ይህንን የሚያውቀው በየሆቴሉና በየሐኪም ቤቱ ሥራው ሽንት ቤት መጥረግ ወይም በየራንቹ የፈረስ ጥርስ መቦረሽ የሆነው አሜሪካ/ካናዳ ነዋሪ ለዕረፍት አዲስ አበባ ይመጣና ያቺን ያጠራቀማትን ዶላር በርካሽ እየመነዘረ እንደ ሚሊየነር ይታይ ጀመር። አሜሪካ እግሬ ይግባ እንጂ እገሌ እንዲህ ከሆነ እኔማ ብዙ ነገር መሥራት እችላለሁ የሚለውም ወጣት በዛ። ስለዚህም በየትም ይሁን በየት አሜሪካ ግባ እንጂ እያሉ ወላጆች ሁሉ ሳይቀሩ ልጆቻቸው በደንበር አሻጋሪ ወንጀለኞች አሜሪካ እንዲገቡ ገፋፉና ብዙ ወጣት በየበረሃውና (ሳሃራ) በየባህሩ (ሜዲትራኒያን) ቀረ።
እጅግ አድርጎ በሚያስቅ ወይም በሚያበግን (እንደ ተመልካቹ ስለሆነ) መንገድ ከአሜሪካ ስለመጣ እንደ አዋቂ እንዲያስቆጥር ሙከራ በዚያ ሰሞን የተደረገ ነበር። “በአስቂኝነቱ” በሚታወቀው በሰይፉ ፋንታሁን ሾው አንድ ጊዜ ኤሊያስ ተባበል የተባለ ዘፋኝ እንግዳ ሆኖ ቀረበ። ዘፋኙ አሜሪካ ከሰላሳ ዓመት በላይ ቆይቶ መምጣቱ ነው። እና እስኪ ገጠመኝህን ተናገር ተብሎ ዘፋኙ ተጠየቀ። ኤሊያስ ሆዬ በአንድ ወቅት ሱፐርማርኬት (ዲፓርትመንት ስቶር ነው የሚባለው እዚያ) የሆነ ነገር ገዝቶ ለመክፈል ወረፋ ሲጠብቅ ከአንድ አፍሮ አሜሪካዊ ጋር ይላከፋል። አሜሪካኑ ‹‹ጮኸ ጮኸና አላቆም ሲለኝ መንኪ (ዝንጀሮ) አልኩትና አሳበድኩት›› ብሎ በድል አድራጊነት ያንን ጥፍር ውስጥ የሚያስገባ እጅግ አሳፋሪ ገጠመኝ አወራና አረፈው። ኤልያስ ‹‹አገሬ ከተመለስኩ ደርግ ሊበላኝ ሊሰለቅጠኝ ይችላል›› ብሎ ለምኖ ግሪን ካርድ ያገኘ ነው። እንዲህ ያለ ሰው አሜሪካኖችን አመሥግኖና አክብሮ እንደመኖር እጅግ አፀያፊ በሆነ መንገድ አንደኛ አፍሮ አሜሪካኖችን መሳደብ በራሱ የቅሌት ቅሌት፣ የበላበትን ወጪት ሰባሪነት ነው። ሁለተኛ አንድ አፍሪካዊ አንድ አፍሮ አሜሪካንን ልክ አንደ ኬኬኬ ፋሺስት ዘረኞች “ዝንጀሮ” ብሎ መሳደቡ፣ የእሱን የዓለም ድንቁርና ከማሳየት ያለፈ ሌላ ነገር የለውም። ኤሊያስ ነጭ የሆነ ዘረኛ ቢያጋጥመው እሱንም “ሄይ ኒገር ቦይ” ሊለው እንደሚችል አለማወቁ ራሱ ያሳዝናል። ‘ዳያስፖራው’ ኤልያስ ከአሜሪካ ስለመጣ ብቻ ራሱን አዋቂ አድርጎ ስለቆጠረ አላውቂነቱን አውጆ አረፈው። ኤልያስ እንኳ አላዋቂ ሆኖ ነው እንበል፣ የሚገርመው ደግሞ ‘አስቂኙ’ የሰይፉ ሥራ ነው። ያ ፕሮግራም የቀጥታ ሥርጭት (ላይቭ) እንዳልነበረ ሁሉ ኤዲት መደረጉ አልቀረም። ግን ሰይፉም የኤልያስን አላዋቂነት ተጋርቶ ይህንን አሳፋሪ ገጠመኝ ተመልካቹን “እንዲያስቅ” እንዳለ ለቀቀው።
ስለዘረኝነት ካወራን አይቀር በብዙ አፍሪካ አገሮች፣ ‹‹እናንት ኢትዮጵያውያን ዘረኞች ናችሁ›› የሚሉን መብዛታቸውን ማስተዋል ተገቢ ነው። አፍሪካውያን ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃ የጣሊያን ፋሺስቶችን ድል ያደረገች መሆኗን ስለሚያውቁ፣ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ክብር አላቸው። ይህንን ክብር ግን እኛው ራሳችን እየሸረሸርነው ነው። ደርግ ሊበላኝ ነው ወይም ወያኔ ሊገለኝ ነው ብሎ የፖለቲካ ጥገኝነት አግኝቶ ተከብሮ በሚኖርበት አገር አመሥግኖ እንደ መኖር፣ የእዚያን አገር ሰው “ባሪያ” የሚለው ኢትዮጵያዊ በርካታ ነው። ለምሳሌ ኡጋንዳ ውስጥ በተለይም ካምፓላ በርካታ ኡጋንዳውያን ከኢትዮጵያውያን የሚሰነዘርባቸውን የዘር ጥቃት እያስተዋሉ፣ የህንዶቹ ዘረኛነት ሳያንስ ኢትዮጵያውያንን ያመጣብን ሙሴቬኒ (ፕሬዚዳንቱ) በመሆኑ ‹‹ቆይ ያ ጊዜ ሲመጣ እናሳያችኋለን›› የሚሉ በርክተዋል።
እንዲህ ያለው አመለካከት በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ብቻ ሳይሆን እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥም የሰፈነ ነው። ይኼን አሌ ማለት አይቻልም። እንዲያውም ሐምሌ 27 ቀን 2012 ዓ.ም. በፋና ቴሌቪዥን በሚተላለፈው ተወዳጁና አስቂኙ “ዘጠነኛው ሺሕ” በተባለው ድራማ ላይ አቡሽን ሆኖ የሚሠራው ወጣት ፍቅረኛው ስላኮረፈችው፣ በተለምዶ “ለምቦጭሽን አትጣይ” የሚለውን ትቶ ጥፍር ውስጥ በሚያስገባ ዘረኛ መግለጫ “እንደ ናይጄሪያ ከንፈር አደረግሽው” ዓይነት ብሎ አረፈው። ይኼን ሳይ ‹‹የዚህ አገር ቴሌቪዥኖች ኤዲተሮች የሏቸውም እንዴ?›› እንድል አድርጎኛል።
ውይይት ላይማ ማነው ደፍሮ ‘ከአዋቂው’ (በስህተት ዳያስፖራ የሚባለው) ጋር የሚከራከረው? በእርግጥም ትንሽ ትምህርት ያገኘው የተማረውን አካብዶ አካብዶ እንደ ከፍተኛ ስኮላር እየተቆጠረ በየሚዲያው የሚጠየቀው፣ ቃለ ምልልስ የሚደረግለትም ከእሱ ጋር ነው። ስሙን ሰምተን የማናውቀው አሜሪካ አለ የተባለ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተመራማሪ ነው እየተባለ ይደመጣል። ሚዲያውና ሌላውም ማመሳከር የሚባል በአዕምሯቸውም ሽው አይል። በእርግጥ ሰውየው/ሴትየዋ እንደምትለው ‘ኤክስፐርቲዙ’ አለው/አላት ወይ ተብሎ መጠየቅ ነውር ይመስል ሚዲያውም፣ የመንግሥት ቢሮዎችም አይጠይቁም። ለምሳሌ እስካሁን ድረስ እንደ ታላቅ ኢኮኖሚስት የሚታይና በሚዲያው ቃለ ምልልስ የሚደረግለት አንድ ግለሰብ፣ እሱ አንደሚለው ካሊፎርኒያ ካለ አንድ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪ እንደሌለውና ዩኒቨርሲቲው ይኼንን ግለሰብ እንደማያውቀው አሜሪካ ያለው ጋዜጠኛ አበበ ገላው ደርሶበታል። ሌላ ጊዜ ደግሞ አንድ የከባድ ሚዛን ቦክሰኛ ነኝ፣ አሜሪካም በዚህ በዚህ አሸንፌያለሁ ብሎ እንደ ተለመደው አሜሪካ አምላኩ የሆነው ሚዲያ አሞካሽቶ አሞካሽቶ በኋላ ሰውየው የወጣለት ቀጣፊ፣ ቦክሰኛም እንዳልሆነ ታወቀ። ካምፓላ (ኡጋንዳ) ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ ሌባ ከካናዳ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ ካናዳ እንዲሄዱ ለመርዳት ነው የመጣሁት ብሎ ስደተኛውን የማመልከቻ ፎርም እያስሞላ ጠቀም ያለ ገንዘብም እያስከፈለ በደንብ ከነደፋቸው በኋላ፣ አንድ ጠዋት ተሰወረና ያ ሁሉ ስደተኛ ገንዘቡን ተበልቶ ቀረ። እንዲህ የመሳሰሉ የቅጥፈት ሥራዎች ከላይ ከጠቀስነው የባህላዊ እሴቶች መቀየር የመጣ ነው። አንድ ፈረንጅ ከሰሞኑ፣ ‹‹እናንት ኢትዮጵያውያን ጥሩ ሰዎች ነበራችሁ፣ አሁን ግን. . .›› እንዳለው ነው።
የጣሊያን ፋሺስቶች አገራችንን ወርረው በሕዝባችን ላይ ባካሄዱት ጭፍጨፋና ያደረሱት ግፍ፣ በድኅረ ጣሊያን ወረራ የነበረው ትውልድ በአገር ወዳድነት ተኮትኩቶ ያደገ ነበር። አገር ወዳድነት አገር ስትወረር ብቻ የሚገለጽ እሴት አይደለም። አገር ወዳድነት ሁልጊዜ ለአገር ጥሩ ነገር ማሰብና መሥራት ማለት ነው። በዚህ ረገድ አገር ሲባል ተራራውና ሸንተረሩ አይደለም፣ ሕዝቡ ነው። ስለዚህ በሰላምም ጊዜ አገር ወዳድነት ለሕዝብ ጥሩ ነገሮችን መሥራትን ይመለከታል። ወጣቶችም በዚህ አቅጣጫ መኮትኮት አለባቸው። ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ማንነት መኩራት አለባቸው። በተለያየ የብሔር ማንነታቸውም መኩራት አለባቸው። አንደ ቀስተ ደመና የተዥጎረጎረው ባህላዊ እሴቶቻቸው ማንነታቸውን ይገልጻል። የወላይታውን ባህላዊ ልብስና ጭፈራ የሌላው ብሔረሰብ አባላት እንደ ራሳቸው አድርገው መውሰድ፣ የእነሱም የሌላው እንደሆነ መቁጠር ይኖርባቸዋል። ሠለጠኑ የተባሉት ፈረንጆች እኮ እንዲህ ያለው አንደ ቀስተ ዳመና የተዥጎረጎረው ባህልና ማንነት ያስደንቃቸዋል። እኛ ደግሞ በዚህ መኩራት አለብን። የአንዳችን ባህል ከሌላው ይበልጣል ሳንል ሁሉንም በእኩልነት ማየት አለብን።
ሁለተኛው አገር ወዳድነት የሚገለጸው ለፈረንጁ ባህልና እሴቶች አለማጎብደድን ይመለከታል። በራሳችን ባህል፣ ልማድ፣ ወጎችና እሴቶች መኩራት አለብን እንጂ የእኛ እሴቶች ከፈረንጅ ‘ዝቅ ያሉ’ ወይም ‘ያልሠለጠኑ’ ናቸው ብለን በፍፁም ማመን የለብንም። እንዲህ ስንል በእርግጥ ከፈረንጁ እሴቶች ደግሞ ጠቃሚ ጎኖች የሉም ማለት አይደለም። ለነገሩ በዓለም ያሉ ሕዝቦች በሙሉ የራሳቸው ባህላዊ እሴቶች አሏቸው። የእኛ ባህላዊ እሴቶች በሙሉ አዎንታዊ እንዳልሆኑት ሁሉ፣ በሌሎችም ባህሎች የፈረንጅን ጨምሮ ጎጂ እሴቶች አሉ። የማንኛውም ሕዝብ እሴቶች አዎንታዊ ጎኖች እንዳሉት ሁሉ ለእኛ የሚጠቅሙ ከሆነ እነዚህን እሴቶች መጋራት እንችላለን። የምንጋራው የፈረንጁን ብቻ አይደለም።
ከላይ እንደጠቀስነው በሁለቱ ኃያላን መንግሥታት የሽኩቻ ዘመን የአሜሪካው ኃያል ተሰሚነቱን ለማስፋፋት ባህላዊ ዘመቻም እንዳደረገ ገልጸናል። በዚህም በመላው ዓለም “አሜሪካ አምላኩ” የሆኑ ግለሰቦችን ማፍራት ዓላማው ነበር። ዘዴው የተለያየ እንደሆነም ጠቅሰናል። ከእነዚህ አንደኛው በሥነ ጽሑፍና (ፊልሞች፣ ጋዜጣና መጽሔት፣ ሙዚቃ፣ ወዘተ.) በሚዲያ በኩል የሚደረገውን ነው። በእነዚህ አውታሮች ከሚነዛው ፕሮፓጋንዳ አንደኛው ውበትን የሚመለከት ነው። ቆንጆ የሚባለው ቆዳው ያልጠቆረ እንዲያውም ነጣ ያለ፣ አፍንጫው ቀጥ ሰልከክ ያለ፣ ፀጉሩም ሉጫ የሆነ እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች (ምናልባት ኒጄር ውስጥ እንዳለው አንድ የፉላኒ ኅብረተሰብ በስተቀር) ባለው ባህላዊ ወግ ደግሞ ቆንጆ መሆን የሚጠበቅባቸው ሴቶች ናቸው። ሴቶቹም ቆዳቸው የነጣ፣ አፍንጫቸው ሰልካካ፣ ፀጉራቸው ሉጫ እንዲሆን መከራቸውን ያያሉ። የቆዳ መንጣቱና የአፍንጫው ሰልካካነት እስካሁን በሰው ሠራሽ መንገድ ሊቀየር ተሞክሮ ብዙ ጉዳት አስከትሏል። ፀጉር ግን ተፈጥሮ ቢሆንም ሰው ሠራሽ ወይም ደግሞ የታከመ ሂውማን ሄር ተሠርቶለታል። ቁንጅናን ፈረንጅ አዕምሯችን ውስጥ እንደ ቀረቀረው በሉጫ ፀጉር ተርጉመን ሴቶቻችን ይኼው ለሰው ሠራሽ ወይም ሂውማን ሄር ሲጋደሉ እናያለን። አፍሪካዊ ማንነታችን አሳፍሯቸው ነው? ወይስ ያ ዊግ ወይም ሂውማን ሄር የእሷ እንዳልሆነ መንገደኛው ሁሉ እያወቀ “የእሷ ያልሆነውን የእሷ ነው” እንዲባል ነው? በጣም የሚያሳስበው ግን በባህልና በባህሪ ተምሳሌት መሆን የሚገባቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት የሆኑ ሴቶች ሚኒስትሮችም ጭምር ይህንኑ ሂውማን ሄር መጠቀማቸው ነው። ከጥቂት ዓመታት ጀምሮ በአገራችን ገንኖ ያለ ዋነኛ የጉራማይሌ ተምሳሌት ይኼ ሴቶቻችን የሚራኮቱበት ሰው ሠራሽ ፀጉር ነው። ሌላው በቅርብ የተጀመረው ጉራማይሌ ደግሞ ሴቶች ቆዳቸው እንዲነጣ የሚጠቀሙበት ክሬም ተፈላጊነቱ እየተስፋፋ መምጣቱ ነው። ይህ ተግባር በሴቶች ላይ ጉዳት በማስከተሉ እንደ ጋና ያሉ አገሮች ከልክለዋል። በኢትዮጵያም በዚህ ጉዳይ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ብዙ ጉዳት ሳይደርስ ማስቆም መቻል አለበት።
ጉራማይሌው በሴቶች ብቻ የሚገለጽ አይደለም። ወጣት ወንዶችም የፋሽን ሰለባዎች ናቸው። ከፀጉር ይጀምራል። የአፍሮ አሜሪካን ራፕ ዘፋኞችን ተከትለው ፀጉር ማንጨብረር፣ በጣም አስቂኝ በሆነ ስታይል መቆረጥ፣ አስቂኝ በሆነ ስታይል ሰላም መባባል፣ ወዘተ. ሌላው አስቂኝ ስታይል ደግሞ ከጉልበት በታች ሹጥጥ ያለ ሱሪ መልበስ ነው። አንዳንድ በመነሳት ላይ ያሉ ዘፋኞች እንዲህ ያለ ሱሪ ለብሰው በቴሌቪዥን ይታያሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ የአለባበስ ሥነ ምግባር በቴሌቪዥንም መኖር አለበት።
ሌላው የጉራማይሌ አባዜ ደግሞ ብዙም ያልተነገረለት ስምን አሜሪካዊ የማድረግ አባዜ ነው። በተለይ ታዋቂ የሆኑ ግለሰቦች ስማቸውን አሜሪካዊ አድርገው ምንም ሂስ ሳይቀርብባቸው ሲቀር፣ ወጣቱ ሁላ ተነስቶ ስሙን በተቻለ መጠን አሜሪካዊ ሊያደርግ ቆረጠ። የታወቁ ሰዎች ኅብረተሰባዊ ኃላፊነት (Social Responsibility) ስላለባቸው ከእንዲህ ያለ ከንቱ ሥራ በመቆጠብ በራሳቸው ማንነትና በባህላቸው መኩራታቸውን በማሳየት ተምሳሌት መሆን አለባቸው።
ስለኢትዮጵያ እየዘፈኑ ስማቸው እንኳ ኢትዮጵያዊ እንዳይሆን ማድረግ እርስ በሩስ የሚቃረን ነው። በዚህ ምክንያት የቴዎድሮስ ካሳሁን አባት አቶ ካሳሁን መሆናቸው እስከዚህ አይታወቅ ይሆናል፣ ሰውየው “ቴዲ አፍሮ” ነኝ ስላለ። ጎሳዬ የሚባለው ደግሞ “ጎሲ ነኝ” አለ። ዮሴፍም “ጆሲ” ሆነ፣ አንዱ ደግሞ ትንሳዔን የመሰለ ቆንጆ ስም ይዞ “የለም. . . ቲኑ ነኝ” አለ (እውነትም “ቲኑ”!) ሌሎችም በርካቶች አሉ። ከሁሉ የሚገርመው ሚዲያው ራሱ እነዚህን ቅፅል ስሞች እንደ ደንበኛ ስም ተቀብሎ በተለይ በቴሌቪዥን ያስተዋውቃቸዋል። አንዱን ተዋናይ “ቤቢ” ይለዋል። ሌሎችም በርካቶች አሉ።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡