Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየተጨቆኑ የመስኖ ግድቦችና ሰፋፊ እርሻዎቻችን የተፈጸመባቸው ሴራ (ክፍል ሁለት)

የተጨቆኑ የመስኖ ግድቦችና ሰፋፊ እርሻዎቻችን የተፈጸመባቸው ሴራ (ክፍል ሁለት)

ቀን:

በፉፉ ሞጆ

የቻይና፣ የህንድ፣ የአሜሪካ፣ የብራዚል፣ የአውስትራሊያ፣ ወዘተ አገሮች ልምድ አስረግጦ እንደሚነግረን አንድ አገር በምግብ ራሷን ለመቻል ብቻ ሳይሆን፣ ለኢንዱስትሪ አስተማማኝና በቂ ጥሬ ዕቃ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ በማምጣት ረገድ በዝናብ ላይ ከተመሠረተ እርሻ ይልቅ የመስኖ እርሻ ልማት ወሳኝ ናቸው፡፡ እንዲሁም ጥናቶች እንደሚያሳዩት ፈጣንና ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ ከመንገድ ወይም ከስልክ መሠረተ ልማቶች በበለጠ ለመስኖ ልማት ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ ነው፡፡ በተለይ ግድብን ተመርኩዞ የሚካሄድ ሰፋፊ የመስኖ እርሻ፣ አገራዊ ዕድገትና ብልዕግና የማቀጣጠል ተፈጥሯዊ ባህሪያትን ይዟል፡፡ ሰፊ መሬትን፣ ሁሉንም ዜጎችን፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን፣ ወቅታዊ እውቀቶችን፣ በርካታ ማኅበረሰቦችን፣ የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎችንና የፋይናንስ ተቋማትን፣ የሙያ ስብጥሮችን፣ ግዙፍ የገንዘብ ዝውውርና ምንጮችን፣ ወዘተ የሚጠይቁና የሚጠቀሙ በመሆናቸው በአጭር ጊዜ የአንድ አገር ፖለቲካዊ ማኅበራዊ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ላይ ተፅዕኖ በማሳደርም ሆነ በመፍጠር የሚስተካከለው ዘርፍ የለም፡፡ ለወጣቶች ሥራ ዕድል በመፍጠር የኃይል አማራጮች በማቅረብ፣ የማኅበረሰብ ግንኙነትና ትስስር በማቀላጠፍ፣ የቱሪዝምና የትራንስፖርት ሥርዓቱን በመቅረፅ፣ የመረጃ ልውውጥ፣ የፍትሕ ሥርዓት፣ የዕውቀት ሽግግር፣ ወዘተ በመክፈት የኮንስትራክሽን የንድፍ የጥናት የምርምር፣ የከፍተኛ ትምህርት ሥርዓትን በመቅረፅ፣ የተመጣጠነ ምግብ በማቅረብ፣ ወዘተ ህልቆ መሳፍርት ፋይዳቸው አምራችና በፈጠራ የተካኑ ወጣቶች በማፍለቅ አገር የተረጋጋ ዘላቂ ልማት እንዲሁም በዓለም ተሰሚና ተፅዕኖ ፈጣሪ እንድትሆን ያደርጋሉ፡፡

የተዘረዘሩ የመስኖ ግድብና እርሻዎቻችንን አገራዊ ፋይዳ በቁጥር ለማሳየት እንሞክርና በእርሻዎቹ ለማልማት የታቀደው ማሳ 550 ሺሕ ሔክታር ቢሆንም፣ ለማልማት የተሞከረው ግን 44 ሺሕ ሔክታር ወይም ስምንት በመቶ ብቻ ነው (በጊዜ ካልተስካከሉ በመገንባት ላይ ያሉትም ተመሳሳይ ዕጣ ይጠብቃቸዋል በሚል ታሳቢ)፡፡ ከ90 በመቶ በላይ ውኃና መሬት ጥቅም እየሰጠ አይደለም፡፡ ሁሉም 550 ሺሔ ሔክታር ላይ የተለያየ ሰብል በድግግሞሽ ማምረት ቢቻል ቢያንስ እስከ 20 ቢሊዮን ብር የሚገመት የተጣራ ትርፍ ወይም እስከ 25 ሚሊዮን ኩንታል (የአገሪቱን የምግብ ሰብል ወደ 10 በመቶ አካባቢ) የሚደርስ የሰብል ምርት በየዓመቱ በማቅረብ በምግብ ራሳችንን ለመቻል፣ ለአግሮ ኢንዱስትሪና ለሌሎች ፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃ አቅርቦት፣ የውጭ ምንዛሪ ለማስገባት ወይም ለማዳን፣ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ወጣቶች ሥራ ለመፍጠር፣ ወዘተ ያግዛሉ፡፡ ተዘርዝሮ የማይዘለቀው ፋይዳቸው የማኅበረሰባችን መድኅን፣ ለአገራዊ ሰላም ደኅንነትና የታለመውን የብልፅግና መንገድ ለማሳለጥ ያበቃሉ፡፡ የመስኖ ውኃ ሽያጭ ከተተገበረ ደግሞ እንዲሁ በቢሊዮኖች የሚገመት ብር ገቢ ያስገኛሉ፡፡ የእርሻ መሣሪያዎች፣ የተረፈ ምርት፣ ወዘተ ላይ ተመሥርቶ የሚፈጠረው አዲስ የኢኮኖሚ ዘርፍና ሌሎችም ያብባሉ፡፡ የተጀመሩት የመስኖ ግድቦቻችን በሁሉም ክልሎችና ድንበሮቻቸው አካባቢ መገኘታቸው በራሱ ፍትሐዊና ተመጣጣኝ ዕድገትን ለማረጋገጥ ከውስጥና ከጎረቤት አገሮች የሚገኙ ሕዝቦች ተስማምተው እንዲኖሩ የማድረግ ዕድሎችን ያዘሉ ናቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ወንጂና መርቲ ከተማ የተመሠረቱት በ7000 ሔክታርና በ10000 ሔክታር የመስኖ እርሻ በያዙ አንድ አንድ ፋብሪካዎች ላይ ብቻ መሆኑን ለተገነዘበ፣ ግማሽ ሚሊዮን ሔክታር የመስኖ እርሻ ሊያንቀሳቅስ የሚችለውን ሕዝብና ኢኮኖሚ መገመት አያዳግትም፡፡ ለአገሪቱ የወደፊት ዕድገት እጅግ ትልቅ ተስፋ ብቻ ሳይሆን ወሳኝም ናቸው የተባለው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ፋብሪካ፣ መንገድ፣ ባቡር፣ ስልክ፣ ንግድ፣ ወዘተ የቱንም ያህል ቢስፋፋ በዘላቂና በቂ የግብርና ምርቶች ካልታገዘ ተገኘ የሚባለው አገራዊ ዕድገት የእንቧይ ካብ ከመሆን አይድንም፣ መሠረት አይኖረውም፡፡ ልምዳች የሚነግረን ይህንኑ ነው፡፡

ዘላቂ ዕድገትን ለማረጋገጥ ደግሞ በሥርዓት ተጠንተውና ተገንብተው አገልግሎት መስጠት በቻሉ የመስኖ እርሻዎች እንጂ፣ ለጊዜያዊ አጀንዳ ማስፈጸሚያነት በሚገነቡ፣ በቅንጅት በማይመሩ፣ በካድሬ ጣልቃ ገብነት በሚዘወሩ፣ ለምዝበራ በተጋለጡ፣ ተጀምረው በሚቋረጡ፣ ወዘተ መስኖ እርሻዎች ከሆነ የማኅበረሰብን ሰላምና ኑሮ በማናጋት የአገር ህልውናን ቀውስ ውስጥ የመክተት አቅም እንዳላቸው አሁን አገራችን የምትገኝበት ሁኔታ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ትልቅ ወንዝ ገድቦ ጥቅም ላይ አለማዋል አገር የሚያፈርስ ሃይለኛ ቦምብ እንደ ማጥመድ ይቆጠራል፡፡ ቶሎ ካልደረስን አይቀርልንም፡፡ በደለል ክምችት ዕድሜያቸው እያጠረ ያለው አልዌሮና ተንዳሆ ግድብ አገልግሎት ሳይሰጡ ቢፈርሱና አደጋ ቢያደርሱ ምን ሊባል ነው? በነገራችን ላይ በመነሻ ጥናታቸው መሠረት አልዌሮና ጎዴ የቀራቸው የአገልግሎት ዕድሜ ከ 30 ዓመት በታች ነው፣ ግማሽ ዕድሜያቸው አብቅቷል፡፡ ሌሎቹም አብረው እያዘገሙ ናቸው፡፡ እነዚህ ትልልቅ ግድቦችና ሌሎች የመስኖ እርሻዎቻችን ከመንገድ እንዲቀሩ፣ ነባሮቹም እንዲሽመደመዱ የተደረገው እንዴት ባለ ሁኔታ ነው? ወያኔ ከተከተላቸው የአጭርና የረዥም ጊዜ ሥልቶች መካከል የተወሰኑትን እነሆ፡፡

በሰበብ የተጀመሩትን ማስቆምና ነባሮችን ማውደም

ቀደም ሲል ያነሳናቸው ጣና በለስ፣ አልዌሮና ጎዴ በአግባቡ ተጠንተውና ከፊል አካሎቻቸው በአግባቡ ከተገነባ በኋላ፣ ቀጣይ ሥራዎቻቸውን ሙሉ በሙሉ አቋርጦ እንደ አሮጌ ዕቃ የተጣሉ የመስኖ ልማቶቻችን ሁነኛ ምሳሌ ናቸው፡፡ በደርግ የተጀመረ ልማት ለአገር አይጠቅምም ብሎ ነገር አለ እንዴ? አገር የማውደም ድብቅ አጀንዳ ካልሆነ በስተቀር ሚዛን የሚደፋ ምክንያት ደፍሮ የሚያቀርብላቸው ያለ አይመስለኝም፡፡ ከሰምና ተንዳሆ ግድብና መስኖ ልማቶችም እንዲሁ በስኳር ልማት በዓለም ተወዳዳሪ ለመሆን በሚል ሥውር ሽፋን ሊገነቡ ከታሰቡ አሥር ፋብሪካዎች መካከል ናቸው፡፡ ግድቦቹና የሸንኮራ አገዳ ለማልማት የተመረጠው መሬት ደግሞ ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ ከፍተኛ መጠን ያለው ጥራቱን የጠበቀ የጥጥ ምርት ይገኝበት የነበረና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ጉልህ ሚና የነበረው የመካከለኛው አዋሽ መስኖ እርሻን በማጥፋት ነበር፡፡ በዚህ ብቻ ሳያበቃ ወንጂን የመሰለ ነባር እርሻን ለማስፋፋት በሚል እንደ ወለንጪቲ ቦፋ ያሉ በርካታ አዳዲስ እርሻዎችን በመጨመር፣ ውጤታማ የነበረውን ፋብሪካ ይዘው ለመጥፋት እያንገዳገዱት ይገኛል፡፡

ባለሙያዎች ብቁ ጠያቂና ተረጋግተው የሚሠሩ እንዳይሆኑ ማድረግ

ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ያሰበ መንግሥ፤ ዕቅዱን ለማሳካት በዋናነት ከሚያስፈልጉት የማስፈጸሚያ መሣሪያዎች መካከል በዘርፉ የሠለጠኑ ብቃት ያላቸው ባለሙያዎች መሆናቸው ዕሙን ነው፡፡ ለዚያውም የአገር ውስጥ ባለሙያ፡፡ ከያሉበት በማሰባሰብ፣ አቅማቸውን በማሳደግ፣ ከለላ በመስጠት፣ ወዘተ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ድጋፍ ያደርጋል፣ ይንከባከባል፣ ወዘተ ተብሎ የሚጠበቀው የወያኔ መንግሥት ግን በተቃራኒው ይሠራ እንደነበር ሁሉም የሚያወቀው ነው፡፡ ብዙ ምጣድ ጥዶ ጋጋሪን ማባረር፤ በእንጀራ ጋገራ ሽፋን ሥውር ዓላማ ለመፈጸም የሚደረግ አሻጥር ካልሆነ ታድያ ምን ሊባል ነው?

ባለሙያዎች ዞር ሲደረጉ ከነበረባቸው ግልጽና ሥውር ተግባራት መካከል ጥቂቶቹን እንይ፡፡ ሙያዊ አቅም አለው ወይም ፍፁም ታዛዥ ላይሆን ይችላል ብለው የገመቱትን ትልቅ ፕሮጀክት እየመራ የሚገኝ የመስኖ ባለሙያን ሰብብና አጋጣሚ ጠብቆ በቀጭን ትዕዛዝ ዞር በማድረግና በማጥፋት ተወዳዳሪ የሌላቸው አቶ ሽፈራው ጃርሶ ናቸው፡፡ ብቁውን ዞር አድርገው ታዛዥ ካድሬ ባለሙያ ሰይመው ያሻቸውን ሲያደርጉ ኖረዋል፡፡ በሥራ አስኪያጅነትና በቦርድ አመራርነት በቆዩባቸውም ሆነ ተፅዕኖ ማሳደር ከሚችሉባቸው ተቋማት ለምሳሌ የኦሮሚያ መስኖ ጥናትና ግንባታ ቢሮዎች፣ የፌዴራል ጥናትና ዲዛይን ኢንተርፕራይዝ፣ የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ቢሮና የፋብሪካ እርሻ፣ ወዘተ ከኃላፊነት ያስነሱትና ያነሱት፣ ወደ ሌላ አካባቢ በምደባ የወረወሩት፣ ከሥራ ያሳገዱት፣ ከደረጃ ዝቅ ያደረጉትና ያስደረጉት የመስኖ ባለሙያ ተቆጥሮ አይዘለቅም፡፡ አንድ ምሳሌ ብናነሳ አለማያ ዩኒቨርሲቲ በግብርና ምህንድስና ዘርፍ (Agricultural Engineering) አብረው ተምረው አንድ ላይ ተመርቀው፣ በተለያዩ የአገሪቱ ተቋማት ተቀጥረው በመስኖ ሙያ ላይ ይሠሩ የነበሩ አራት ብቁ ባለሙያዎች (አንደኛው የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ነው) የአቶ ሽፈራው ሰለባ ሆነዋል፡፡ ከኦሮሚያ ቢሮዎች በአንድ ጊዜ ወደ ስምንት የሚደርሱ የመስኖ ባለሙያዎች ላይ ዕርምጃ መውሰዳቸውን ሰምተናል፡፡ የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ቢሮ ተቀጣሪ የተወሰኑ ባለሙያዎችን ከአካባቢው ዞር እንዲሉ ያለ በቂ ምክንያት ወደ ተለያዩ የፋብሪካ እርሻዎች ለመመደብ ያደረጉት ሙከራ በክስ ከሽፎባቸዋል፡፡ ሰውየው በየሄዱበት መሥሪያ ቤት ባለሙያውን የልማት ፀር የሚል ታርጋ ለጥፈውለት ማባረርና ማሸማቀቅ ተቀዳሚ ተግባራቸው መሆኑ፣ የመስኖ ልማቶቹን ለማሰናከል ሆነ ተብሎ የሚደረግ ስለመሆኑ አሁን እርሻዎቻችን የሚገኙበት ሁኔታ ምስክር ነው፡፡ ባለሙያዎቹ የተባረሩባቸው ድርጅቶች ደግሞ የመስኖ ግድቦችንና እርሻዎችን በማጥናት፣ በመንደፍ፣ በመገንባት፣ በማስተዳደር ሥራ ላይ ቀንደኛ ተዋናይ ሲሆኑ ቀደም ሲል ከተጠቀሱ የመስኖ ተቋማት መካከል በእሳቸው ኃላፊነትና ጣልቃ ገብነት ምክንያት የተሰናከሉት ከሰም፣ ተንዳሆ፣ ፈንታሌ ቦሰት ጥቂቶቹ ሲሆኑ አደጋ ካንዣበበባቸው ደግሞ ኩራዝና ወልቃይትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ውኃና መስኖ ሙያ ውስጥ ሲሠራ የቆየ በመንግሥት ተቋማት ለበርካታ ዓመታት ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎች ወደ ሌላ አገር ወይም ድርጅት ያለ ተወዳዳሪ በከፍተኛ ክፍያ ተቀጥረው መወሰዳቸውን መታዘቡ አይቀርም፡፡ ውኃ ሀብት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ውስጥ የሠሩና የሚሠሩ ባለሙያዎች ዓይነተኛ ምሳሌ ይሁኑ እንጂ ዩኒቨርሲቲዎቻችን፣ የምርምር ተቋሞቻችን፣ የዲዛይንና የኮንስትራክሽን ድርጅቶቻችን፣ ወዘተ ሁሉ ሰለባ ናቸው፡፡ ታላላቅ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ውስጥ መቀጠር የግል ስኬት አድርገን ብዙዎቻችን ብንደሰትበትም፣ እንደ አገር ካሰብነው ግን አውዳሚና በረዥሙ የታቀደልን ሥውር ተንኮል መሆኑን ልንገነዘብ ግድ ይለናል፡፡ የዚህ ሰለባ የሆኑና ወደፊትም የሚሆኑ ባለሙያዎችን ቤቱ ይቁጠረውና ሁላችንም የምናወቃቸውን ለማሳያነት ላንሳ፡፡ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ድርድር የፊት መሪና የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር (ዶ/ር/ኢንጂነር ስለሺ በቀለ)፤ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በሌሎችም ተቋማት በመምህርነትና በተመራማሪነት ለረጅም ዓመታት ሲሠሩ ቆይተው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቢሮን ተቀላቅለው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አገራቸውን ለማገልገል ባላቸው ጠንካራ ፍላጎት ምክንያት ባይመለሱ ኖሮ፣ የግድቡን ግንባታ ድርድር በአሸናፊነት በመወጣትና አሁን ያለውን ቁመና ይኖረው ነበር ወይ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ እሳቸው አምልጠው ለትልቅ ስኬት ቢያበቁንም፣ ከዚህ ቀደም ያጣናቸው ባለሙያዎች ስንት ይሆኑ? ከመጋረጃው ጀርባ ያለው ማን ይሆን?

ደካማ፣ ያልተረጋጉና ያልተቀናጁ ተቋማትን መፍጠርና ጠንካራዎችን ማድከም

በአንድ ወቅት ስመ ጥር የነበሩና ሥራዎቻቸው አሁን ድረስ በየገጠር ቀበሌው ውስጥ የሚታይላቸው የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የትግራይ፣ የደቡብ ክልሎች መስኖ ጥናትና ግንባታ ተቋማት ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ድንገት ከመድረክ ጠፍተው አቅመ ቢስ በሆኑ ተመሳሳይ የክልል ተቋማት እንዲተኩ ተደርገዋል፡፡ የትልልቅ መስኖዎች ባለቤት የሆኑት የፌዴራልና የክልል ውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ቢሮዎች ፍፁም የማይተዋወቁና የሥራ ግንኙነታቸው የላላ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም የመስኖ ልማቱን ለሁለት ከፍሎ በግብርና ሚኒስቴርና በውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሥር በማዋቀር የሥራ ወሰንና ኃላፊነት መምታታትና መዘበራረቅ እንዲፈጠር ተደርጓል፡፡ የትልልቅ መስኖዎች ጥናትን፣ ግንባታንና አስተዳደርን እንዲሁ ለበርካታ ተቋማት በማከፋፈል ከግብ እንዳይደርሱ ታስረዋል፡፡ እነዚህ ተቋማት በየጊዜው ራሳቸውን እንደ አዲስ እያዋቀሩ ውጤታማ እንዳይሆኑ ተደርገዋል፡፡ ለማሳያ ያህል እንኳን አንድ እኔ የተሳተፍኩበት የዳሰሳ ጥናት ሰላሳ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ዘጠና ቀበሌዎችን ለመዞር ዕድል ሰጥቶኝ ነበር፡፡ ከዳሰሳው የተገኘው ውጤት እንደሚያሳየው የሁሉም ቀበሌዎች ቀዳሚ የልማት ችግር ሆኖ የተገኘው የመጠጥ ውኃ፣ ሁለተኛው መብራት ሲሆን፣ ሦስተኛው ደግሞ የመስኖ ልማት ነው፡፡ ኢንተርኔትና ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ እንዲሁም የገጠር መንገድ ለሁሉም ቀበሌዎች መዳረሱ ቢያስደንቀኝም ቅሉ፣ ሲበዛ የከነከነኝ ግን ሦስቱም ሕዝቡ የጠየቃቸው የመሠረተ ልማት ዘርፎች ካለፉት ሃያ ምናምን ዓመታት ጀምሮ አሁንም ድረስ በአንድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሥር ተወሽቀው መዝለቃቸው ነው፡፡ ‹‹አቅም ሲገኝ ራሳቸውን ችለው ለየብቻ ይዋቀራሉ፤›› ነበር ያሉት ዶ/ር ካሱ ኢላላ፡፡

የመስኖ ግድቦቻችን ወቅታዊ ጉዳይም ቢሆን ያው ነው

መነሻ ሰበብና ጥሩ ምሳሌ በመሆናቸው እናብራራው፡፡ እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ የትልልቅ መስኖ ግድቦችን ጥናትና ግንባታ የሚከታተለውና ግንባታቸው ከተጠናቀቀ በኋላም በባለቤትነት የሚያስተዳደረው ውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ቢሆንም ቅሉ በአቅም ውስንነት ምክንያት እዚህ ግባ የሚባል ሥራ ማከናወን አልቻለም ነበር፡፡ የመስኖ ግድቦች ሁኔታ ያሳሰበው መንግሥት (አለመልማታቸው ይሆን ወይም ሌላ እንጃ) ከአራትና ከአምስት ዓመታት በፊት፣ በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የተገነቡና በመገንባት ላይ ያሉ በዚህ ሰነድ ውስጥ የተዘረዘሩ አሥራ አንድ የሚደርሱ የመስኖ ግድቦችን ተረክቦ እንዲያስተዳድር፣ ሌሎች የመስኖ ግድብ ግንባታዎችን እንዲያካሂድ በሚልና የመስኖ ውኃ ሸጦ የሚመልሰው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ብር ከንግድ ባንክ በብድር ተሰጥቶት በአዋጅ ተቋቋመ፡፡ ምንም እንኳን ግድቦቹን በባለቤትነት የወሰደው ኮንስትራክን ኮርፖሬሽን ራሱ የብዙዎቹ ግድቦች ተቋራጭ መሆኑና በግንባታ ሥራ ላይ የተሰማራ በመሆን አወቃቀሩን በተመለከተ ጥያቄ ቢያስነሳና በቀጣይም ችግር መፍጠሩ ቢረጋገጥም (አላቻ ጋብቻ እንዲሉ)፣ በወቅቱ የተረሱ የመስኖ ግድቦቻችን ባለቤት አገኙ ቀን ወጣላቸው ተብሎለታል፡፡ በሌላም በኩል ግድቦቹ እርሻ አልባ በመሆናቸው ውኃ የሚገዛ ደንበኛ በሌለበት ብድር መመለሱን አጠያያቂ ቢያደርገውም፣ እንደ ጅምር ይበል የሚያሰኝ ተግባር ተብሎ ነበር፡፡ ኮርፖሬሽኑም የግድብ አስተዳደር ዘርፍን አቋቁሞ በበርካታ መዋቅራዊ ችግሮች የተተበተበና ለአገራችን ፍፁም አዲስ የሆነ ዘርፍን በማንቀሳቀስ መሠረት የሚጥሉ ሥራዎችን ማከናወን ችሎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ዘርፉን ከጥንስሱ ያቋቋመውና በእግሩ ለማቆም ሲንቀሳቀስ የነበረውን ጠንካራና ልምድ ያለው ብቁ ባለሙያና የዘርፍ ኃላፊን ኬንያ የሚገኝ ዓለም ዓቀፍ ተቋም በከፍተኛ ደመወዝ ወሰደው (ገለል አደረገው እንበል)፡፡ የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ በውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሥር ከግድብ አስተዳደር ዘርፍ ጋር ተወራራሽ ኃላፊነት የተሰጠው የመስኖ ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቋመ፡፡ የባንክ ብድር ያሳሰበው የግድብ አስተዳደር ዘርፍ ግድቦቹን ወደ ልማት አስገብቶ የውኃ ተጠቃሚ በማድረግ፣ አንድም ከውኃ ሽያጭ ገቢ ሰብስቦ ብድር ለመመለስ፣ በሌላም በኩል አገሪቱን በሰብል ምርት ለማገዝ በሚል ዓላማ ሥራ ፈትተው የተቀመጡ ግድቦቻችን ላይ በሰብል ልማት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለመሳተፍ የሚረዳ የአዋጭነት ጥናት አዘጋጅቶ ለመንግሥት አካላት ቢያቀርብም (በርካታ መረጃ የተወሰደው ከዚህ ሰነድ ነው)፣ የሥራ ወሰናችሁ አይደለም በሚል ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል (መተብተብ ከዚህ በላይ የት ይገኛል?)፡፡ በዚህ ሳያበቃ እግሩ ያልጠናው የግድብ አስተዳደር ዘርፍ የተረከባቸውና ችግሮች የተጫኑት የመስኖ ግድቦቻችን ሸክምና የመስኖ ውኃ ተጠቃሚ ደንበኛ አለመኖር ሳያንሱ የኃላፊነት መደራረብ፣ የአወቃቀር ችግር፣ የውስጣዊ ድጋፍ ዕጦት፣ አመራር ብቃት ማነስ፣ የውስጥ መጠላለፍ፣ ወዘተ ተደርበውበት እየተንደፋደፈ መሆኑ እየታወቀ ውጤት አላስመዘገበም የሚል ወቀሳ ከውስጥ (የመስኖ ግድቦቹ ግንባታ ላይ እጃቸው በነበረበት ግለሰቦች ፊት መሪነት፣ አዲሱን አመራር በማሳሳት) ይዘንብበት ጀመር፡፡ በሦስትና በአራት ዓመታት ውስጥ ፍሬያማ አልሆነም በሚል የተዛባና የተቻኮለ ምክንያት፣ በግዙፍነታቸው ዝቅ ከሚሉ ዘርፎች ለምሳሌ ሕንፃ ግንባታ አንሶ (ግድብና ሕንፃን አወዳድሩ) በማዕከል ደረጃ እንዲዋቀር ተፈረደበት፡፡

ለአገሪቱ ዕድገት ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት ዘርፍ መሆኑ በሚያስተዳድረው በቢሊዮን የሚገመት ገንዘብና ቀደም ሲል የጠቃቀስናቸው ፋይዳዎች የሚናገሩ ቢሆንም፣ ካለማወቅ ይሁን ወይም በተተበተብንበት ረዥም ሥውር ሴራ ምክንያት ብልጭ ብሎ የነበረው ትልቅ ራዕይ ዳግም ለመጨለም ተቃርቧል፡፡ ሴራው አስተሳሰባችንን ጭምር ሳያዛባው አልቀረም እላለሁ፡፡ ለነገሩ ከጥንስሱ ተጠቃሚ በሌለበት ውኃ ሸጠህ መልስ ብሎ በከፍተኛ ወለድ ገንዘብ ማበደር፣ የግድቦቹን ግንባታን በአግባቡ አጠናቆ ካላስረከበ መሥሪያ ቤት ጋር ማዋቀር፣ ተመሳሳይ ኃላፊነት ለሁለት መሥሪያ ቤቶች በአዋጅ መስጠት፣ ወዘተ በእርግጥ ግድቦቹ ወደ ልማት እንዲገቡ ታስቦ የተሠሩ ናቸውን የሚል ጥያቄ መጫሩ አይቀርም፡፡ መፈተሽ ግድ ይላል፡፡

ፀረ መስኖ ልማት የትምህርት ሥርዓት

ግብርናን ማዕከል ያደረገ የመንግሥትን ፖሊሲ፣ የግብርና ትምህርትን ማጠንከር ግድ ይለዋል፡፡ ከክረምቱ እርሻ ጋር የነበረውን ለጊዜው እንለፈውና የመስኖ እርሻን በተመለከተ የነበረው የትምህርት ሥርዓትን (አሁንም የተሻሻለ አይመስለኝም) ስንፈትሽ  ግን፣ በእርግጥ ወያኔ ግብርናን ማዕከል ያደረገ ፖሊሲ ይከተል ነበር ወይ ያስብላል፡፡ ዓለማያ ዩኒቨርሲቲ ይሰጥ የነበረው በዘርፉ በርካታ ብቁ ባለሙያዎችን ያፈራው የግብርና ምህንድስና (Agricultural Engineering) የትምህር ዘርፍ ያለ በቂ ምክንያት (በወቅቱ የትምህርት ሚኒስቴር ገነት ዘውዴ ፊታውራሪነት) በማስፈራራት መዝጋትና ቀስ በቀስ የመስኖ ሙያ ትምህርት ከካሪኩለሞች ውስጥ መወገዳቸውን ትኩረት አይስጠው እንጂ ሁሉም ያስታውሰዋል፡፡ በአርባ ምንጭ፣ በሐዋሳ፣ በወሎ፣ በመዳ ወላቡ፣ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች በውኃ ሀብትና መስኖ ምህንድስና (Water and Irrigation Engineering) የሙያ ዘርፍ በመጀመሪያ ድግሪ ለማስመረቅ የተቀረፀው የትምህርት ፕሮግራም አለ ለማለት ካልሆነ በስተቀር፣ ከመስኖ ይልቅ ውኃና ሲቪል ምህንድስና ላይ ያተኮረ ነው፡፡ መስኖ ላይ ያተኮሩ ትምህርቶች ሽፋን ስምንት በመቶ ሲሆን፣ ሲቪል ምህንድስናን የሚመለከቱ ትምህርቶች ሽፋን ግን 24 በመቶ ይደርሳል፡፡ ታዲያ ውኃና ሲቪል ምህንድስና ማለት ይቀል ነበር እኮ፡፡ ለመስኖ ቅርብ የሆኑ ሙያዎች ትምህርትቶችም ቢሆኑ እንኳን፣ በውስን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ብቻ እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡

በዲላ፣ በጎንደር፣ በመቀሌ፣ በወለጋ፣ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች በውኃ ሀብትና መስኖ አስተዳደር የሙያ ዘርፍ በመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችን ማስመረቅ ተጀምሮ የነበረ ሲሆን፣ የሙያ ዘርፉ በሲቪል ሰርቪስ ዝርዝር ውስጥ ባለመካተቱ ተመራቂ ተማሪዎች ሥራ ማግኘት አልቻሉም በሚል ምክንያት ትምህርቱ የተቋረጠ ከመሆኑም በላይ፣ ተመራቂ ተማሪዎችን ወደ ሥራ የሚያስገባ ድርጅት (የመንግሥትም ሆነ የግል) ባለመገኘቱ እንደገና ተጠርተው የተመረቁበት ሙያ ስያሜ በሌላ እንዲቀየር መደረጉ የቅርብ ትዝታ ነው፡፡  አርሶ አደሩ የመስኖ ተጠቃሚ ለመሆን ተደጋጋሚ ጥያቄ እያነሳና የመስኖ መሠረተ ልማቶች በተገቢው መንገድ እያገለገሉ አለመሆናቸውን እየወተወቱ፣ ብዛትና ጥራት ያለው የመስኖ ባለሙያ እንደሚያስፈልግ ቢታውቅም ትምህርቱ መቋረጡ የመስኖ ልማትን ለማኮላሸት የተደረገ መሆኑን ይነግረናል፡፡

በዚህ ብቻ ሳያበቃ የመስኖ ሰብል አመራረት፣ የመስኖ ውኃ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሙያዎች ባለመኖራቸው የመስኖ ልማቱ ኃላፊነት ለሲቪል መሐንዲስና ለውኃ ሀብት መሐንዲስ እንዲወድቅ ሆኗል፡፡ የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች፣ የሚኒስትሮቻችን አማካሪዎች (የህዳሴ ግድብ አማካሪ ኮሚቴን ጨምሮ) የወረዳና የዞን ባለሙያዎች፣ ወዘተ ውስጥ የመስኖ ባለሙያዎች ተሳትፎ እዚህ ግባ የሚባል አይደለ፣፤ ሲሳተፉም አይታይም፡፡ ከላይ እስከ ታች መዋቅር ውስጥ የሉበትም ማለት ይቻላል፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ ያሉ ባለሙያዎች በሌላ ሥራ ላይ ተጠምደው ከሙያቸው ርቀዋል፡፡ በየወረዳ በሚገኙ የግብርና ቢሮዎች ውስጥ የመስኖ አካላት ንድፍ በሲቪል ምህንድስና ምሩቃን ሲሠሩ ማየትም የተለመደ ነው፡፡ የሚገርመው ሌላው ነገር በየገጠር ቀበሌው የእንስሳ፣ የሰብል፣ የአፈር ጥበቃ፣ ወዘተ ኤክስቴንሽን ተመራቂ ባለሙያዎች ተመድበው ሲሠሩ መስኖን በተመለከተ ግን የመጀመሪያ ተመራቂ ባለሙያዎች የተገኙት ከአንድና ከሁለት ዓመት በፊት መሆኑ ነው፡፡ ለዚያውም በስንት ውትወታ፡፡ ላለፉት ሃያ ዓመታት በየትኛውም የቴክኒክ ተቋም አይሰጥም ነበር፡፡ የአለማያ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ምህንድስና ዘርፍ ከተዘጋ 15 ዓመታት በኋላ፣ በአገሪቱ የመስኖ ልማት ተሳትፎ ላይ ብቁ ባለሙያ አለመኖር እንደ አንድ ምክንያት በመቅረቡ የተነሳ ትምህርቱ የመዘጋቱን አመክንዮ የተየቁት ዶ/ር ካሱ ኢላላ፣ ‹‹በወቅቱ አስፈላጊ አልመሰለንም ነበር፤›› የሚል አጭርና ድፍን መልስ ሰጥተውናል፡፡ በአልመሰለንም ለአንድ አገር ልማት ወሳኝ የሆነ የትምህርት ዘርፍ እንደ ዘበት ሲዘጋ ተመልከቱ፡፡ በውጤቱ አገራችን ምን አገኘች ምን አተረፈች ቢባል፣ መልሱ በአግባቡ የማይሠሩ የመስኖ እርሻዎችን ይሆናል፡፡ በአገራችን ከሚገኙ አነስተኛ የመስኖ እርሻዎች ውስጥ 45 በመቶው ፍፁም አገልግሎት የማይሰጡ ሲሆን፣ የተቀሩትም በችግር የተተበተቡ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ በአገራዊ የሰብል ምርትና ኢኮኖሚው ውስጥ የመስኖ እርሻዎች ድርሻ ከአምስት በመቶ ያልዘለለ መሆኑን የምናውቅ ስንቶቻችን ነን?

የሸውራራ ሙያዊ አመለካከት መረጃና ጠንጋራ ፖሊሲዎች

ውሀና ለም መሬት በተትረፈረፈባት አገር ግድቦች ጦማቸውን እየዋሉ፣ አገር ራሷን በምግብ ራሷ እንድትችል በሚል የውኃ ማቆር ፖሊሲ ማውጣት ምን ይሉታል? አለማወቅ ነው ወይስ ተንኮል? በ1994 ዓ.ም. የወጣ የስትራቴጂ ሰነድ የዘርንፉ አስቸጋሪነት ዘርዝሮ በቀጣይ አሥር ዓመታት ውስጥ የስኳር ኢንዱስትሪ የመገንባት እቅድ እንደሌለ በግልጽ ካስቀመጠበት ተቀልብሶ፣ ከ1997 ዓ.ም. የምርጫ ጥፊ ማግሥት አሥር ትልልቅ ፋብሪካዎች መገንባት መጀመር የጤና ነው ይባላል? ምንም የውኃ አማራጭና የሚቀምሰው ለሌለው አርሶ አደር ማኅበረሰብ የመስኖ አዋጭነት ጥናትን እንደ ምክንያት አድርጎ መስኖ አለመገንባት (እንደ ወልቃይት ዓይነቱ ላይ ደግሞ ገንዘብ መርጨት)፣ በእውነት የሰው ልጅ ረሃብና ሞት ለመስኖ ከሚወጣው ገንዘብ ረክሶ ነውን? ውይይት ላይ ብታነሱት እንኳን ካድሬ ባለሙያ ጭምር መልስ ሳይሰጣችሁ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎት ያልፋል፡፡ የወረዳና የገጠር ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን እያስፈራሩና ባለሙያ እያስገደዱ የተጋነነ የመስኖ ልማት መረጃ መሰብሰብ ደግሞ ሌላው ነው፡፡ የአገሪቱ የአነስተኛ መስኖ ሽፋን ከ2.7 ሚሊዮን ሔክታር በላይ ነው እየተባለ ሲዘገብ ኖሮ ኖሮ በቅርብ የተደረገ ቆጠራ ከ0.9 ሚሊዮን ሔክታር በታች መሆኑን ሲያጋልጥ ምን ያህል ያስደነግጥ? ምን ያህል ያሳፍር?

አንዳንድ ካድሬዎች በየስብሰባው እንደሚሰብኩን ወይም ዶ/ር ካሱ እንዳሉት አልመሰለንም ነበር ዓይነት አመክንዮዎችን መርሳት አለብን፡፡ አንድ ወይም ሁለት ግድቦች ብቻ ቢሰናከሉ፣ በጥናት ወይም በንድፍ ወይም በግንባታ ችግር ነው ልንል እንችል ይሆናል፡፡ ሁሉም የመስኖ ግድብ ሽባና ሥራ ፈት ሆኖ ሲገኝ ግን አጋጣሚ ነው ተብሎ የሚታለፍ አይደለም፡፡ እንዴት ሊሆን ይችላል ብሎ መጠየቅ የአባት ነው፡፡ ከላይ በጥቂቱ ለማሳየት የተሞከሩ የማፍረስ ሥልቶች በአንድነት ሲተገበሩ ውጤታቸውን፣ የመስኖ ግድቦቻችንና እርሻዎቻችን ያሉበት ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ ማሳያ መነጽሮቻችን ናቸው፡፡ የአገሪቱን ልማት የማይፈልግ ከሆነ እኮ ከጅምሩ ግድቦቹን አለመገንባት ወይም እየዘረፈም ቢሆን ማጠናቀቅ ይችል ነበር የሚል ጥያቄ ሊቀርብ ይችላል፡፡ መልሱ በአጭሩ ወያኔ እኮ ነው  የሚል ይሆናል፡፡ አገር በብሔር ከፋፍሎ ለማፍረስና ለዘረፋ የፖለቲካ ፍጆታ ሲል የማይፈነቅለው ድንጋይ የሌለው ይህን አያደርግም አይባልም፡፡ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በተቻለ መጠን እንዳይጠናቀቁ ማክሸፍ የሚፈልግበት ምክንያቶች አንደኛ የአገር ውስጥ ተቋራጭ ወይም ድርጅቶችን ለማበረታታት በሚል ለሚሰገስጋቸው አባሎቹ የሚያከፋፍለው ቢሊዮን ብሮች ተመራጭ ምንጭ ትልልቅ ፕሮጀክቶች በመሆናቸው፣ ሁለተኛ የሚዘረፍ ብር ከዓለም ዓቀፍና ከአገር ውስጥ የገንዘብ ተቋማት በብድር ስም ለመሰብሰብ እንዲረዳው፣ ሦስተኛ ሕዝቡን ልማት እያመጣሁልህ ነው በማለት ለማሞኘትና እስከ ቻለ ጊዜ ለመግዛት፣ አራተኛ በሚያከፋፍለው ብር ደጋፊ ለመሰብሰብ፣ አምስተኛ በሕዝቡ መካከል የታቀደ ከፍተኛ የገቢ ልዩነት በመፍጠር መቃቃርን ለመኮትኮት፣ ስድስተኛ የአካባቢ ማኅበረሰብ የተፈጥሮ ሀብቶቹን ተጠቅሞ ራሱን እንዳይችልና አቅመ ቢስ ሆኖ እንዲኖር፣ ሰባተኛ በሚፈጠር የኑሮ ውድነት ወደ ታቀደ ቀውስ እንዲገባ ለማመቻቸት፣ ወዘተ የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በመጨረሻ እንደ መንደር ወንበዴ ብቻውን እየተንጎማለለ መኖር ትልቁ ሕልሙ ነበር፡፡ ሕዝብን በብሔር ከፋፍሎ ከለያዩ በኋላ የኢኮኖሚ ልዩነት በመፍጠር ለማቃቃር ይረዳ ዘንድ፣ ግዙፍ የመስኖ ግድቦችን ጀምሮ አለመጨረስን የመሰለ ወደ ውጤት የሚያደርስ መንገድ ከየትም አይገኝም፡፡ አገራችን ደግሞ ለዚህ ምቹ ነበረች (ነበረች ልበል እንጂ)፡፡

ባይሆን ዕውቀቱን ከየት አገኘ የሚለው ጥያቄ ሚዛን ይደፋል፡፡ አሻጥሩም (Conspiracy) እዚህ ላይ ነው፡፡ መነሻ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ ወያኔ አገሪቱን ለማፈራረስ ሲሠራ እንደነበር የሚያጠያይቅ አይመስለኝም፡፡ እንደ ቀዳሚ መሣሪያ የመስኖ ልማቶችን ማውደም መምረጡ ላይ ትንሽ ልበል፡፡ የሚመለከታቸውን ተቋማትን ማሽመድመድ፣ ባለሙያን ማኮላሸት፣ የትምህርት ሥርዓቱን ማበላሸት፣ ወዘተ የሚፈለገውን ውጤት እንደሚያስገኝ ለየትኛውም ዘርፍ የሚሠራ ሥልት ቢሆንም፣ አንድ ሰው የመስኖ ልማት ያለውን አገራዊ ፋይዳም ሆነ አገር የሚያወድም ዕምቅ ኃይል መሸከሙን በቅጡ ጠንቅቆ ተረድቶ ለመተግበር፣ ከወረቀት ባለፈ በረዥም ዓመታት ልምድ የተፈተነ ዕውቀት ሊኖረው ግድ ይላል፡፡ ከወያኔ ጋር ከነበራት የትግል ጊዜ ጉድኝት፣ ለአገራችን ካላት ዘመን የተሻገረ ጥላቻና የማፈራረስ ሕልም፣ ተደጋጋሚ የመበታተን ሙከራና በመስኖ ልማት ላይ ካሳለፈችው ታሪካዊ ልምድ አኳያ  እንደ ግብፅ ያለ አገር በቅርብ አይገኝም፡፡ ወያኔና ግብፅ አገራችን እንዳታድግ ከተቻለም እስከ መጨረሻው እንድትበታተን ያላቸው ፅኑ ፍላጎት አንድ ያደርጋቸዋል፡፡ አሁንስ ወዳጅ አይደሉ፡፡ ልዩነታቸው በመስኖ ልማት ላይ ያላቸው የግንዛቤ ልዩነት ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ወያኔ በትግል ላይ በነበረበት ጊዜያት ግብፅ የመስኖ ልማታችን ላይ እንዲያተኩር በሚገባ ሳታጠምቀው አልቀረም፡፡ መንግሥት ከሆነ በኋላ ግን በተላላኪነት ብቻ ሳይሆን፣ የራሱ ፅኑ ፍላጎትና ምኞት በመሆኑ እንደ ጎበዝ ተማሪ የተመከረውን አገር የማፍረስ ሥልት ያለ ግብፅ ድጋፍ በሚገባ ተግባር ላይ ሲያውል ኖሯል፡፡ ግብፆች የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጀመር ጀምሮ ለዓመታት እንቅልፋቸውን ሲለጠጡ ከርመው፣ የአሜሪካ ያለህ የሚል እሪታቸው በዶ/ር ዓብይ ዘመን መበርከቱ የሚነግረን ይህንኑ ሀቅ ነው፡፡ በአጭሩ ለግብፅ የተመቸ መንግሥት ወይም ቡድን ነበር ማለቱ ይቀላል፡፡ ይህ የእኔ ምልከታ ሲሆን፣ የተለየ ያለው ከተገኘ እሰየው፡፡

ታዲያ ምን ይደረግ?

የመስኖ ልማታችን ትንሳዔን ለማብሰር ዝርዝር የልማት ስትራተጂ ከመቀየስ በፊት፣ የተነከርንበትን ሥውር ሴራ ምንነትና ጥልቀት መረዳት የመጀመሪያው ዕርምጃና የመፍትሔው ቁልፍ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ መነሻም እሱ እንጂ ሌላ የሚጠበስ ዓሳ በዘይት የለም፡፡ በቅድሚያ አሻጥር እንደ ተሠራብን፣ ድሩ እንደ ተበተበን፣ አተያይና አመክንዮአችንን እንደ ሰወረ፣ ወረቀት ያለው ካድሬና ባለሙያ እንደ ተቀላቀሉብን፣ ወዘተ መገንዘብ ለምናቀርበው የመፍትሔ ዕርምጃ ወሳኝነቱ የላቀ መሆኑን መቀበል ያስፈልጋል፡፡ የመስኖ ልማትን ራሱን ችሎ በሚኒስቴር መስሪያ ቤት ደረጃ ማዋቀር ወይም ገንዘብ አፈላልጎ መጠነ ሰፊ የመስኖ ግንባታዎችን ማጧጧፍ፣ የትምህርት ሥርዓቱ እንዲህ ይሁን፣ ወዘተ ዓይነት ስትራቴጂዎችን መቅረፅ ብቻቸውን ለግብ የማያበቁበት ምክንያት ችግሩን ለመፍጠር ያላቸው አስተዋፅኦ ኢምንት በመሆኑ ነው፡፡ የዘርፉ አከርካሪ መመታት የተጀመረውና የተሰበረው ብቁ ባለሙያዎችን በማስወገድ እንደ መሆኑ፣ ፅኑ አቋም ያላቸው ባለሙያዎችን ከካድሬ (የተተበተበ ወይም የተወጋ ወይም የተሰለበ ወይም ወይም ማለት ነው) ባለሙያዎች መለየት ላይ ሊሠራ ግድ ይላል፡፡ ይሁንና በአሮጌ አመራር የተሾሙ ካድሬዎችን ቀይሮ ችግሮችን እንደ ማስተንፈስ ቀላል አይደለም፡፡ በየተቋማቱ የተሰገሰጉ ካድሬ ባለሙያዎችን ማለት (እንደ አቶ ሽፈራው ጃርሶ እና አሁንም ታች የመንግሥት አመራር ድረስ የሚገኙ ካድሬ ባለሙያዎች) ፀጉር ውስጥ እንደተሰገሰገ ማስቲካ ካልተላጩ የማይለቁ ናቸውና፡፡ መላጨቱ ደግሞ አይሆንም፡፡ ጉዳት ሳያደርስ ማስለቀቅ ዕውቀት፣ ብልኃት፣ ጥንቃቄና ጊዜ ይፈልጋል፡፡ የዶ/ር ዓብይ መንግሥት ትልቁ ፈተናም ይህ ነው፡፡ ያለፈው አልፏል፡፡ የዞረ ድምራችንን በማራገፍ ቀጣይነታችንን ግን መሬት ማስረገጥ ይጠበቅብናል፡፡

ብዙ ከመጓዛችን በፊት ለማጠቃለል ህዳሴ ግድብ ካልጠፋ ቦታ ድንበር ላይ እንዲገነባ የተፈለገው ሱዳንን ለማስፈራራት ነው ብላችሁ እንደ እኔ አሁንም እንደ ተሞኛችሁ ነው ወይ? የመስኖ ግድቦቻችን ለምን እርሻ አይኖራቸውም ብለን ተቆርቁረናል ወይ (ድንጋይ ወርውረናል ወይ)? ግብፅ ከራሷ አልፋ ሌላ አገር ግድብ ላይ የምታደርገውን ጣልቃ ገብነት እያየን፣ እኛ የራሳችንን ግድቦች ስለማሽመደመዳችን ታዝበናል ወይ? በሥውር ሴራ ስለመተብተባችን ተስማምተናል ወይ? ከቀልባችን ለመመለስ ተዘጋጅተናል ወይ? የቀረውን እናንተ ጨምሩበት፡፡

መውጫ

ተስፋ ማስቆረጥ እንዳይሆንብኝ ህዳሴ ግድብን ከመስኖ ግድቦቻችን አጣምሬ የመፍትሔ ምክረ ሐሳብ ልሰንዝርና እንደ አገባቤ ልውጣ፡፡ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ፡፡ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ውኃ ሙሌት ምድሪቱ ከዓባይ ያደረገችው የልማት ተራክቦና የቃል ኪዳን ማተብ ነው ቢባል  ማጋነን አይደለም፡፡ የተረገዘው ልማትን ለወግ  ማዕረግ ለማብቃት ምጥ፣ ጡት ማጥባት፣ ማሳደግ፣ ወዘተ ይጠብቁታል፡፡ የልማት መንገድ ከተጀመረ ጊዜ ይወስዳል፣ ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ አለበለዚያ በቀላሉ የመጨንገፍ ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ግድቡ አለቀ ብሎ መፎከርና መዘናጋት አያስፈልግም፡፡ የመጀመሪያው የውኃ ሙሌት የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ የሚዘልቁ ጠንካራና መጠነ ሰፊ ጥቃቶችን የሚጋብዝብን ሲሆን፣ የአንድ ለእናቱ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን ብቻ ከጠበቅን ተሸናፊ መሆናችን አይቀርም፣ እንሆናለንም፣ ለግብፅ እንመቻለን፣ ፅንሱም ይጨናገፋል፡፡ የሱዳን ግድቦችን አስታውሱ፡፡ ግድቡ ከተጠናቀቀ ደግሞ ራሳችን የዓባይ ወንዝ ልማት ጠላቶችና የግብፅ አጋር እንዳንሆን ከአሁኑ እንዘጋጅ፡፡ ግብፅ አሻጥር ስትሠራብን ነበር እያልን ማላዘናችን አብቅቶ፣ ከውስጥ ጭምር የሚፈጠረውን ትግል ለማሸነፍ አቅም እንገንባ፡፡ ሺሕ ዓመታት ጠብቀን ያገኘነውን ከእጃችን አስጥለው ሌላ ሺሕ ዓመታት እንዳያስጠብቁን የቆለፍነውን ሳጥናችንን ሰብረንም ቢሆን እንውጣ፣ በሰፊው እንመልከት፣ የተተበተብንበትን እንበጣጥስ፡፡

በዓባይ ተፋሰስ በርካታ ግድቦች ተለይተዋል፣ ተጀምረዋል፣ መንገድ ቀርተዋል፣ ተገንብተዋል፡፡ ግብፅ ህዳሴ ግድብ እንደማይጎዳት እያወቀች ወከባ መፍጠር የፈለገችው እነዚህ እንዳይለሙ ስለመሆኑ ተገንዝበን ወደ ተግባር መቀየር አለብን፡፡ ሁለተኛው የውኃ ሙሌትን ለማጨናገፍ የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡ ስለዚህ በሚቀጥሉት ሁለትና ሦስት ዓመታት (እስከ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ) ወደ ሥራ የሚገቡ የመስኖ ግድቦችን ለይቶ ውጤታማ ማድረግ ቀላል፣ ርካሽ፣ ፈጣንና እጅግ የሚያዋጣ የአጭር ጊዜ ሥልት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ቢያንስ አርጆ ደዴሳ፣ ርብ መገጭ (ሁለቱ ለግብፅ ውኃእያጠራቀሙ በበጋ ይለቃሉ) እና በለስ ያሉ ጅምር ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ምርጥ ብልኃትነው፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች በድምሩ 165 ሺሕ ሔክታር (ከሦስት የአዲስ አበባ መስተዳድር ስፋት ይበልጣሉ) ያለማሉ፡፡ ለምን ከተባለ አንደኛ የግብፅን ሐሳብ በመበታተን የመደራደርና ተፅዕኖ የማሳደር አቅም ያዳክማሉ፣ ሁለተኛ የህዳሴ ግድብ መገንባት ወደፊት ለምንገነባቸው የመስኖ ግድቦች ተግዳሮት ይዞ መምጣቱ ስለማይቀር በትንሹም ቢሆን እነዚህና ሌሎች የመስኖ ግድቦች ህዳሴ ላይ የሚኖራቸውን ተፅዕኖ በቶሎ ለመለየት ያስችላል፣ ሦስተኛ ሕዝባዊ ተሳትፎውን እንደ ጥሩ አጋጣሚ የገንዘብ ምንጭና እንዲሁም ለእነዚህና ለሌሎች የመስኖ ግድቦች ፍፃሜ ፈር ቀዳጅ ይሆናል፣ አራተኛ የክልሎቹን ልማት ወደ ላቀ ደረጃ ያስገባሉ፣ በክልሎቹ ውስጥም ሆነ መካከል መግባባትና ሰላምን ያሰፍናሉ፣ አገሪቱም ሰላም ትሆናለች፡፡

ሰላም! ቸር እንሰንብት!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የመስኖ መሐንዲስ ሲሆኑ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]  ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ (ክፍል አንድ)

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...