Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትፍርድ ቤቶቻችን የመብቶቻችን አለኝታና መተማመኛ ለመሆን እየተዘጋጃችሁ ነው ወይ?

ፍርድ ቤቶቻችን የመብቶቻችን አለኝታና መተማመኛ ለመሆን እየተዘጋጃችሁ ነው ወይ?

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ከሚታወቁበት ዓይነተኛና ታላላቅ ጠባያት መካከል የአንደኛነቱን ቦታ የሚይዘው ፍርድ ነው ይባላል፡፡ ይታመንበታልም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለፍርድ፣ ለፍትሕ ጥልቅ የሆነ ስሜትና ዝንባሌ እንዳለው፣ ይህንንም ዘር በደም እንደሚተላለፍ ሁሉ እንደ ቅርስ ከአባቶች እንደሚወርሰው፣ የተጣላን ለማስታረቅ፣ የተበደለን ለማስካስም ሆነ ዳኝነት ለማየት በተቀመጠበት ሸንጎ ሁሉ ቃል ሲሰነዝር ከእውነታ እንዳይርቅ በጣም እንደሚጠነቀቅ፣ ፍርድ የተለየ የአምላክ/የፈጣሪ ቅዱስ ገንዘቡ ስለሆነ፣ ፊት ዓይቶና ወቀሳ ፈርቶ ቃል ማዛባት ክልክልና ነውር መሆኑን ታሪካችንና የታሪክ ጸሐፊዎቻችን ይነግሩናል፡፡

ዕውቁ ባላምባራስ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል በኢትዮጵያ ጥናት ሦስተኛው የኢንተርናሽናል ጉባዔ (ኮንፈረንስ) ላይ በ1958 ዓ.ም. ባቀረቡት ጽሑፍ ይህንን  አስረግጠው የገለጹት፣ 

- Advertisement -

‹‹ተረቶቹንና ምሳሌዎቹን ብንመረምራቸው፣ ጉልህ የሆነ የተጨበጠ ልማደ ሕግን ይዘው እናገኛቸዋለን፡፡ ወላጆች በተረት፣ በፈሊጥና በዘዴ እያደረጉ ዳኝነት ትክክለኛ ሚዛን መሆን እንዳለበት ለልጆቻቸው ያስተምራሉ፡፡ ከችሎት ላይ የተሰጠው ውሳኔ ምናልባት የሚያጠግበው ካልሆነና ህሊናው ተረታህ ካላለው ከአንዱ ዳኛ ወደ ሌላው በይግባኝ እየተራመደ ከመሄድ አይታገስም፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍትሕ ሲጓደል በብርቱ ያዝናል፡፡ ምንም የተወሰደው ሀብት ዋጋው ያነሰ ቢሆን በዳኝነት መዛባት እጅግ አድርጎ ይቆጫል፡፡ ይህንንም ‹በፍርድ ከሄደችው በቅሎዬ ያለ ፍርድ የሄደችው ጭብጦዬ ታሳዝነኛለች› የሚል ምሳሌው ሊያስረዳ ይችላል፤›› በማለት ጭምር ነው፡፡ ብዙ ነገሮችን መዘርዘርና መጨመር ይቻላል፡፡

‹‹ትንኝም ለሆዷ፣ ዝሆንም ለሆዱ/ውኃ ለመጠጣት ወደ ወንዝ ወረዱ›› ሲባል፣ ትልቅ፣ ትንሽ፣ ዓብይ፣ ንዑስ፣ ግዙፍ ሚጢጢ የሚባል ፍትሕ የለም ማለት ነው፡፡ ‹‹አሞኝ ውሎ አሞኝ ሊያድር ነወይ፣ ሠርቶ መብላት እንኳን ጤና ላይሆን ነወይ?›› ሲባል እናውቃለን፡፡ የ‹‹ጤና›› ጉዳይ የሆነው የመብት፣ የነፃነት፣ የፍትሕ ጥያቄ ነው፡፡ ‹‹ሰው በአገሩ ሰው በወንዙ ቢበላ ሳር ቢበላ መቅመቆ፣ ይከበር የለም ወይ ሰውነቱ ታውቆ›› ማለት ዓይነትም እንጉርጉሮና ሽለላ ገና አሁን በቅርቡ እ.ኤ.አ. በ1948 የፀደቀውና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች ዓለም አቀፋዊ ‹‹ትዕዛዛት›› የሆነው ‹‹ዩኒቨርሳል ዲክላሬሽን ኦፍ ሂውማን ራይትስ››ን የአንቀጽ አንድ ፍልስፍና ገና ዱሮ ዱሮ አውቃለሁ ብሎ የሚፎክርም ነው፡፡ የዲክለሬሽኑ አንቀጽ አንድ የሰው ልጆች ሁሉ በክብርና በመብቶች ነፃና እኩል ናቸው ብሎ ይጀምራልና፡፡

ድንገት አንተ የምታወራው ስለአንድ ሕዝብ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ሁሉ ነወይ ብሎ የሚጠራጠር ወይም የሚጠይቅ ካለ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ሁሉ በተረትና ምሳሌ የተንቆጠቆጡ ተመሳሳይ አጣማጅ አቻ ባላቸው የፍርድና የፍትሕ ምሳሌዎች ዕንቁነት ያጌጡ ናቸው፡፡ በአንድ የቸሀ ቋንቋ ተረትና ምሳሌ ለማስረዳትና በዚያውም ለመገላገል፣ ‹‹ወርቄን በፈቃዴ ከወሰደብኝ ይልቅ ቡቱቶዬን በጉልበት የቀማኝ ይቆረቁረኛል›› እንደሚባል ልጥቀስ፡፡ ይህ የቸሀ አባባል ከዚህ በላይ የጠቀስነው የአማርኛው የበቅሎና የጭብጦ ተረትና ምሳሌ አጣማጅ አቻ ምሳሌ ነው፡፡

ይህን የመሰለ የፍትሕ፣ የፍርድ፣ የዳኝነት ሕዋስ ያለው ሕዝብ ግን ዳኝነት እንደ እህል እንደ ውኃ ሊጠማው፣ ለእሱም ሲታገል ኖሯል፡፡ ሲታገለው የኖረው የፍትሕና የዳኝነት ሥርዓቱ ራሱ ጭምር ትግሉን ሲታገለው ቆይቷል፡፡ የሞት ባልንጀራ፣ እንደ ሞት የሚቆጥረውን ጥቃትን ኑሮው አድርጎ የሚቆጥረው ሕዝብ ዞሮ ዞሮ የአንዱን ባለአልጋ ግፍና የሥልጣን ዘመን በትግሉ ማሸነፉን ያውቀዋል፡፡ እርግጠኛም ነው፡፡ በአንድ ድንቅ የኦሮሞ ምሳሌ መሠረት ‹‹ቆርጦ የመጣን ትውከት ሰላሳ ጥሮሾዎች አይመክቱትም››ና፡፡ እንዲህ ያሉ ተደጋጋሚ ትግሎችና ድሎች ቢኖርም፣ በሕዝብ ትግል ፊት ግዙፍ የጭቆና መሣሪያዎች እምቧጮ ቢሆኑም፣ ካለፈው ታሪካችን ደግመን ደጋግመን እንደተረዳነው፣ በተለይም ከ1960ዎቹ ወዲህ ያለው ትግላችን እንዳረጋገጠው የዴሞክራሲ ትግላችን በገለልተኛ ተቋማት ምሥረታና ግንባታ ላይ ያተኮረ ባለመሆኑ ሁሉም ነገር መና እየሆነ በሰዎች፣ በመሪዎች ‹‹ቅን ልቦና››፣ መልካም ምኞት፣ በጎ ፈቃድ ቁርጠኝነት ላይ እየተመሠረተ ዴሞክራሲ፣ ከመብትና ነፃነት ከፍትሕና ከነፃ ዳኝነት ጋር የማይጨበጥ ነገር ሆኖ ቀረ፡፡

የደርግ መንግሥት ሥልጣን ላይ መውጣትና የአሥራ ሰባት ዓመቱ ታይቶ የማይታወቅ አድራጊ ፈጣሪነት፣ አሁንም ድረስ ገና ተከፍሎ ያላለቀ ዕዳና ጠንቅ ውስጥ ከቶን አለፈ፡፡ በተለይም የምንነጋገርበት የዳኝነትና የፍትሕ ሥርዓቱ ነገር በንጉሠ ነገሥት ዘመን ብቅ እያለ እየጎለበተ ዘመናዊነትን እያገኘ የመጣውን አሠራር ማረኝ የሚያሰኝ ሆኖ አረፈው፡፡ ባሰበትም፡፡ ፍርድ ቤቶች መደበኛ ሥራቸውን መሥራታቸውን ይቀጥላሉ ቢባልም ብዙ ነገር ከዚህ ‹‹የመደበኛ ፍርድ ቤቶች›› ክልል ውጪ ወጣ፡፡ ነፃና አብዮታዊ ዕርምጃ የፖለቲካ ጉዳይ ለሕግ የማይቀርብ ጉዳይ ሆነ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን የዳኞችና የዳኝነት ሥልጣን በ‹‹ደረቅ›› ወንጀልና የደቀቀው ኢኮኖሚ የሚያቀርብለትን የፍትሐ ብሔር ጉዳይ ማየት ብቻ ቢሆንም፣ በዚያ ቢወሰንም፣ የዳኝነትና የሕግ ተርጓሚው አካል የባሰ ዝቅጠት የመጣው ድኅረ ደርግ ነው፡፡

በጣም የማይመስል ነገር ይባል ይሆናል፡፡ የሽግግሩ ዘመን ቻርተር ፍርድ ቤቶችን እንደ ሦስተኛው የመንግሥት የሥልጣን አካል አክብሮ የሚያስተናግድ ቦታ እንኳን መሰጠት እንዳለበት በጭራሽ አያውቅም፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት ሥልጣንን በሚደነግግበት አንቀጽ ውስጥ ቻርተሩን መሠረት በማድረግ የፍትህ አስተዳደር ሥርዓት ይመሠረታል ብቻ አለ፡፡ የዴሞክራሲ መብቶች የሚለውን የቻርተሩን ድንጋጌ ጠቅሶ እነሱን በሚመለከት ‹‹ፍርድ ቤቶች ከመንግሥት ተፅዕኖ ነፃ ሆነው ይሠራሉ›› አለ፡፡ የቻርተሩን ትርጉም ለተወካዮች ምክር ቤት ሰጠ፡፡ ፍርድ ቤቶች ‹‹ነፃ›› ሆነው ይሠራሉ የተባለበት ዘርፍ ተለይቶ የወጣበት ምክንያት ፍርድ ቤቶች ነፃ የሆኑበት ዘርፍም (ማለትም የመቃወም፣ የመደራጀት ወዘተ) ገና በሽግግሩ ዘመን የተደቆሱና የጠፉ በመሆኑ ጨዋታው ሳይጀመር የኢሕአዴግን መላ የሠራ አካል ያጋለጠ ነበር፡፡

ኢሕአዴግ ገና ከግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. ጀምሮ እጅ ስጡ ብሎ ያሰራቸው የኢሠፓ የበላይ ባለሥልጣናት፣ የደኅንነትና የጦር ኃይሎች አባላት የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም የከተማ ነዋሪዎችና የገበሬ ማኅበራት ባለሥልጣናትና ግለሰቦች ክስ ጭምር ግዙፍ ዝግጅትና ግዙፍ የተቋም ግንባታ የሚጠይቅ ፈታኝ ጉዳይ ነበር፡፡ ይህን በተለምዶ የቀይ ሽብር ክስ እየተባለ የሚጠራውን ክስ የሚያቀርበው የልዩ ዓቃቤ ሕግ የተቋቋመው ከዓመት በኋላ ነሐሴ 1984 ዓ.ም. ቢሆንም፣ ከዚያም በኋላ እስከ ጥቅምት 1987 ዓ.ም. ክስ መመሥረት ባለመቻሉ ፕሬዚዳንት መለስ ዜናዊ በዚህ ጉዳይ ላይ መልስና ማብራሪያ መስጠት ራሱ ሰቀቀን እንደ ሆነባቸው በአደባባይ እስከ መግለጽና “ማፈር” ደርሰው ነበር፡፡ ይከላከሉ ለማለት እስከ ጥር 1995 ዓ.ም. ድረስ ጊዜ የወሰደበትና ከዚያም በኋላ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ የተሰጠው የሞት ፍርድ ውሳኔ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 28/2 መሠረት ወደ ዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ተለውጦ፣ ፍርደኞቹ የ20 ዓመታት የእስራት ዘመናቸውን ፈጽመው በአመክሮ ሲወጡ (መስከረም 23 ቀን 2001 ዓ.ም.) ጉዳዩ ገና አዲስ ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ወሬና አጀንዳ፣ የሽምግልና ርዕስ አልወጣም ነበር፡፡

በዚህ ላይ በዘር ማጥፋት ወንጀል የቀድሞ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጥፋተኛ አድርጎ የፈረደባቸው (ይህን ያለው ገና ይከላከሉ ብይን ላይ ነው) መዝገብና የክስ ሒደት፣ ያን ያህል ‹ጂኖሳይድ›ን ያህል የአገር ‹ጁሪስፕሩደንስ› ውስጥ ያስመዘገበው እዚህ ግባ የሚባል አንድም ነገር አልነበረም፡፡ ከዚያ ይልቅ አገራችን ውስጥ የመጣው ለውጥ ሒደትና ጅምር ‹‹የመፍትሔው አካል›› አድርጎ ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣናቸው በፈቃዳቸው እንዲለቁ የገፋቸው አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ዚምባቡዌ ሐራሬ መንግሥታዊ ላልሆነ ሥራ ጉዳይ ሄደው በዚያ አገር የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን ቢሮ በክብር ተቀብለው ያነጋገሯቸውና ፎቶግራፍም አብረዋቸው የተነሱት የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ዕጣ ፈንታ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ጣሊያን ኤምባሲ አሁንም ሙጥኝ ብለው የሚገኙና ሁለት ፍርደኛና ‹‹ተፈላጊ›› የቀድሞ የመንግሥት ባለሥልጣናት የወደፊት ዕድል ኢትዮጵያ ‹‹ፍርድ››፣ ‹‹ዳኝነት›› ውስጥ መፍትሔም ዕልባትም ያጣ እጅ እግር የሌለው ‹‹የእንዲያው ዝም ይሻላል›› ነገር ሆኗል (መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና ሁለቱ የጣሊያን ኢምባሲ ጥገኞች በሌሉበት የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው መሆኑን ያስታውሷል)፡፡

የአሁኑ ዴሞክራሲን በነፃ የመንግሥት አውታር፣ በነፃ ዳኝነት፣ በነፃ ፍርድ ቤት ላይ የማደላደል አዲስ ሥራ ይህን በመሰለ ጅምርና ውጤት ‹‹የተለከፈ›› እና የተሰናከለ ብቻ አልነበረም፡፡ ችግራችን ይህን ከመሰለው ‹‹አጋጣሚ›› የተለየ፣ ሆን ተብሎ የተሠራ ስህተት ብቻ ሳይሆን ጥፋትም ነበር፡፡ ይህንን ጥፋትም ፖለቲካዊ ‹‹ክፋትም›› ለማሳየት በምሳሌነት የምጠቅሰው የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ ነው ከሚል ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ጋር ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም የዳኝነት ሥራ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መሰጠቱ አይደለም፡፡ ያን ያህል ‹‹አጉል መሞላቀቅ›› የሚችል የዳኝነት አካል በጭራሽ የለንም፣ አልነበረንም፡፡

በፖለቲከኞቻችን ምክንያት ዳኝነት በሕግ የተከበረና ሊቀናበት የሚገባ ሥራ ነበር፡፡ ከ1948 ዓ.ም. የተሻሻለው ሕገ መንግሥት ጊዜ ጀምሮ የነበሩትና አሁንም ያለው ሕገ መንግሥት በዚህ ረገድ ብዙ ጉድለት የለባቸውም፡፡ በተለይም የ1948 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት የዳኝነት የመንግሥት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ ነው፣ ዳኞች የዳኝነት ተግባራቸውን በሙሉ ነፃነት ይሠራሉ፣ ከሕግ በቀር በሌላ ሥልጣን አይመሩም የሚለውን ጅምሩን የዳኞች አስተዳደር ጉባዔን በማቋቋም እንዲላወስ እንዲያንቀሳቅስና እንዲረማመድ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በዳኝነት አስተዳደር ባለሥልጣናቱ አማካይነት የልብ ልብ እንዲያገኝ አደረገ፡፡ መልካም ጅምር ታየ፡፡ ይህ በደርግ ዘመንም (በተወሰነ መልክ) መሻሻል አሳየ፡፡ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ሕግ የተፈጻሚነት ወሰን ዓቃቤ ሕጎችንና ሬጅስትራሮችንም ጭምር እንዲሸፍን ተደረገ፡፡

ኢሕአዴግ መጣ ስለፍትሕ ስለዳኝነት ብዙ ተነገረ፡፡ በተለይም ‹‹የፍትሕ አስተዳደርን ከማንኛውም ዓይነት ተፅዕኖ ነፃ ለማድረግ›› ባወጣው የመጀመርያው (የአሜን) አዋጁ (23/1984) የኢትዮጵያ ሕዝቦች የደረሰባቸውን ግፍ በሰፊው መግቢያው ላይ ሰፋፊ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔንም እንደ አዲስ አቋቋመ፡፡ በዚህ የአዲስ የ‹‹ሽግግር›› ዘመን አዲስ ተጨማሪ ነገር ባይመጣም ቢያንስ ቢያንስ የነበረው ቀጠለ፡፡ በ1987 ዓ.ም. የሁለተኛው የኢሕአዴግ ዘመን የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ማቋቋሚያ አዋጅ ሲወጣ ግን ከዳኛ ውጪ የሆነ የሌሎችን ሠራተኞችን አስተዳደር ከሲቪል ሰርቪስ የሠራተኛ አስተዳደር ነፃ ለማውጣት ሲታገል የቆየው ሦስተኛው የመንግሥት ዘርፍ፣ ከእነ ጭራሹ የሬጅስትራሮችን አስተዳደር ከዳኞች አስተዳደር ውጪ አደረገ፡፡ የዳኞች የክስ ጉዳይ (ኢሚዩኒቲ) ድንጋጌዎችም ተሰረዙ፡፡ በዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አባላት ጥንቅር ምክንያትም (በተለይም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሦስት አባላት) ጉባዔው፣ ከሕዝብ ተወካዮች ይልቅ የገዥው ፓርቲ ትዕዛዝ ማስተላለፊያ ሆኖ አረፈው፡፡ የጉባዔው ሌሎች አባላትም ከእነዚህ የተወካዮች ምክር ቤት ‹‹ውክልና›› ይልቅ የገዥውን ፓርቲ ትዕዛዝ ፈቃድና ፍላጎት የሚያስፈጽሙት አፓራቺኮ (ታማኝ አሽከሮች) ሆኑ፡፡

ዕድሜ ለመጋቢት 2010 ዓ.ም. ለውጥ፣ ለአዲሶችም የዳኝነት አካሉ የለውጥ አመራሮችና በዙሪያቸው ላሉ የለውጥ ኃይሎች ምሥጋና ይግባና ዛሬ አዲሱ የዳኞች አስተዳደር ረቂቅ ሕግ በእነ አቶ በረከትና በእነ አቶ አስመላሽ ጊዜ የማይዳፈሩ፣ ምናልባትም የማይታሰቡ ለውጦችን አስተዋውቋል፡፡ አንዱና ዋነኛው የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የገዥው ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የነበረበትን ሁኔታ የሚያቋርጠው የተወካዮች ምክር ቤት አባልነት ጨርሶ መቅረት ነወ፡፡ ረቂቁ ከ22 ዓመታት በፊት የነበረውን የዳኞች ያለ መከሰስ መብት ከተጨማሪ የዳኞች የመደራጀት መብት ጋር እንደገና አስተዋውቋል፡፡ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ግማሽ በድን የሆነበትንም ምክንያት ለማስወገድ የጉባዔው ሥልጣን፣ መላውን ሠራተኞች እንደያካትት የሚያስችል ደፋርና እስከ ዛሬ እዚህ ደረጃ ያልደረሰ ዕርምጃ ተራምዷል፡፡ 

የፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ጉዳይ ድሮም ቢሆን ኢሕአዴግ ለወጉና ለጌጥ ያህል ሕግ ሲያወጣለት የቆየ ጉዳይ ነው፡፡ ዳኛ፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ፖሊስ፣ የደኅንነት ሠራተኛ፣ የመከላከያ ባልደረባ፣ ወዘተ. የፓርቲ አባል መሆን አይችልም ማለት ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ ኢሠፓ ሲታገድ የነበረ ቢሆንም በአሠራር ግን ክልከላው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል መሆን እንጂ የእኔ ግን ምንም አይደለም ማለት ያህል ‹‹የተፈቀደ››ና ዋስትናም ያለው ስለነበረ ከዚህ በላይ የከበደ መከላከያ ሊበጅለት ይገባል፡፡ አገራችን ውስጥ ሙያዊ ኃላፊነት ፖለቲካዊ አመለካከትን፣ አዝማሚያንም ዝንባሌንም በልጦ መፅናቱንና አሸንፎ መውጣቱን እስክናረጋግጥ ድረስ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ያሉ መንግሥታዊ ዓምዶች (ዳኝነት፣ ምርጫ ቦርድ፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ደኅንነት፣ መከላከያ፣ ፖሊስ፣ ወዘተ.) ኢአድሏዊነትን ለመመሰል ዓይነት በጨርቅ እንደተጋረደችው ሴት ለፓርቲያዊም ሆነ ለብሔርተኛ አድልኦ ዓይናቸው የተጋረደ ሆኖ፣ የሁላችንም የጋራ አለኝታ ተደርገው ለመታየት የበቁበት ታሪክ እንዲጀምር ከፖለቲካ መነካካት (በተለይ ዳኝነት ውስጥ) ሊጠብቅና ሊሸሽ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡

የዓብይ አህመድ መንግሥት በዚህ ተጠነዋችና ተቃዋሚ በበዛበት ሽግግር ውስጥ የጀመራቸው ዴሞክራሲን በገለልተኛ ዓውደ መንግሥት ‹የመንግሥት አውታራት› ላይ የማደላደል ሥራ፣ በተለይ በዳኝነት ዘርፍ ውስጥ ብዙ አደገኛ ፈንጂ የበዛበት የለውጥ መንገድ ላይ መሄድና መረማመድን የሚጠይቅ ነው፡፡

በዚህ ጽሑፍ ሁሉንም ገጽታዎችን አገላብጠን ያላየናቸው አዲሱ የዳኞች/የዳኝነት አስተዳደር አዋጅ ረቂቅ ገና ፓርላማ ውስጥ (የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያጋጠመውን ዓይነት) በርካታ አሰናካይ ነገር ሊያጋጥመው እንደሚችል ከአሁኑ መዘጋጀት አለበት፡፡ በሕጉ ረቂቅ ውስጥ የተካተቱት ድንጋጌዎች እንዳለ ሕግ ሆነው መፅደቃቸውም፣ በኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ ውስብስብ ትስስር አኳያ የዚህ ጉዞ መዳረሻ አይደለም፡፡ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የዳኞችን ደመወዝ የመወሰን ሥልጣን በሕግ ከተጎናፀፈ በኋላ የገንዘብ ሚኒስቴር አዲሱን የዳኞች ደመወዝ የጉባዔውን ‹‹ሕግ›› ሕግ አልመስለው ብሎ፣ የአስፈጻሚው አካል (የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት) ትዕዛዝ ካልመጣልኝ መፈጸም አቸገራለሁ ብሎ፣ ይህም ዜና ሆኖ እናውቃለን፡፡

የፍርድ ቤቶችን የሰው ኃይል ሁሉ በአንድ አስተዳደር ውስጥ የማምጣት ሥራ አዋጁ ከፀደቀ በኋላም ብዙ ግትልትል ጣጣዎችን አስቀድሞ አይቶ መጋፈጥ ያስፈልጋል፡፡ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከፐብሊክ ሰርቪስ ኮሚሽን፣ ከመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ጋር የተተበተበው ዕትበት አዋጅ ሰምቶ ብቻ እሺና አቤት አይልም፡፡ ለዳኝነት ተቋሙ በነፃና በቀጥታ ይመደባል የሚባለው በጀት ራሱ ከነፃነቱ ጋር መተናነቅ የሚችል ብዙ ውስብስብ ትስስር አለው፡፡ በነፃና በቀጥታ ለፍርድ ቤቶች የተደበው ገንዘብ የሚገዛውን የአገልግሎት፣ የዕቃ ዓይነት፣ ዋጋ የዋጋ ገደብ የሚወሰነው ሌላ ከሆነ በየመንገዱ የሚያጋጥመው መንተፋተፍ ‹‹መኪናውን›› እስከ መቆም ሊያደርሰው ይችላል፡፡

ዛሬ ከመደበኛው የዘወትር ሥራ ውጪ እጅግ በጣም ብዙ የፍርድ ቤት ውሎዎችን፣ የችሎት ዜናዎችን፣ የቅድመ ክስ ቀጠሮዎችን የዘረገፉ ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ ባለጉዳዮችና ቤተ ዘመዶቻቸው፣ ደጋፊዎቻቸው፣ መርማሪ ፖሊሶች፣ የታወቀና የተለመዱ የሚዲያ ተቋማት ሁሉ ራሳቸው ሕዝብ ዕይታ ውስጥ ናቸው፡፡

ፍርድ ቤቶች እዚህ ውስጥ አዲስና ያልተለመደ ከግዳጅ ያላነሰ ብርቱ ተግባር አለባቸው፡፡ አዲሱ ነገር ሕጉ አይደለም፡፡ ሕጉ 25 ዓመታት ሙሉ ሲያየንና ሲስቅብን ኖሯል፡፡ ለውጡንም ያመጣው፣ ወደ ሐዘንና ተቃውሞ ወደ የሕዝብ ብሶትና ምሬት የተለወጠ አፀፋዊ ምላሽ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የሰብዓዊ መብት ምዕራፍ ውስጥ የተደነገጉት የመጀርያዎቹ አንቀጾች ሕገ መንግሥታዊ መተማመኛና ዋስትና የተሰጠባቸው፣ መንግሥትንና ፖሊስን ለመከልከል ነው፡፡ የሕግ አስከባሪዎችን ቀፍድዶ ለመያዝ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች ይህን ሕግ ከጥንቱ ከጠዋቱ ሙሸት ወጥተው በአዲስ መልክና በሕገ መንግሥቱ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችና በዓለም አቀፋዊ ስታንዳርድ መሠረት ማስተዳደር አለባቸው፡፡ ዳኞችም የፍትሕ ሥርዓቱ በአጠቃላይ ሊመልሳቸው የሚገባ ጥያቄዎችም ብዙና ውስብስብ ናቸው፡፡

ለምሳሌ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 17 በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጪ ማንም ሰው ነፃነቱን አያጣም፣ በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጪ አይያዝም … ይላል፡፡ እንዴት ነው አንድ ሰው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚያዘው? በፍርድ ቤት ትዕዛዝም ሆነ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የተያዘ ሰው የነፃነት መብት ለምን ‹‹ጊዜ ቀጠሮ›› የሚባል ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ይሰወርብናል? ለምን ዛሬም ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ሆነን ‹‹በአፈሳ ይታፈሳል፣ በንጥር ይመለሳል››፣ ‹‹ሌባ ተይዞ ዱላ ይጠየቃል›› ውስጥ እንዳክራለን? በምን ምክንያት ሁልጊዜም አጣርተን ከማሰር ፈንታ፣ አስረን እናጣራለን? ኧረ እንዴት ሆነና ነው በሌሎች የኢሕአዴግ ‹‹ጠላቶች›› ላይ ሲፈጸም የኖረው ያልሆነ ስም ሰጥቶ የመጥለፍ፣ የመፈንገል፣ የመወንጀል፣ የማሰርና በቀጠሮ የማሰቃየት ተግባር፣ እነ አቶ ስዬ አብረሃን ሳይቀር አልምር ያለው በምን ምክንያት ነው? የሕግ አወጣጡ፣ ዳኝነት መቀመጡ ለራሱ ለ‹‹ውድቡ›› እስኪገለማ ድረስ ለምን በሰበሰ? የዳኝነት አስተዳደር ረቂቅ ሕጉን በማሻሻል  ላይ ያሉት ባለሙያዎችና ዘርፉ ሊመልሳቸው ሊጨነቅና ሊጠበብባቸው የሚገቡ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ዜጎች ከግለሰብና ከሌላ ቡድን አድራጊ ፈጣሪነት ብቻ ሳይሆን ከመንግሥት ከራሱ አድራጊ ፈጣሪነት የምንጠበቀው የመንግሥትና የተቋማቱ ሕግ አስከባሪነት፣ የመንግሥት የወንጀል ምርመራ ሥራ፣ ከሳሽነትና የዓቃቤ ሕግ ለሕግ ተከራካሪነት ወደ ዜጎች መብት ድፍጠጣ እንይንሸራተት አድርገን ሥርዓት መገንባት ስንችል ብቻ ነው፡፡ ይህን ማድረግ የምንችለው ደግሞ ተደጋግሞ እንደተባለው ኢወገናዊ በሆኑ ተቋማት ላይ ዴሞክራሲን ስናደላድል ነው፡፡ ያጎደለን ይኸው ነው፡፡

ዴሞክራሲን ከማደላደል፣ በዳኝነት አካሉ ላይ (ሕገ መንግሥቱ በምዕራፍ ዘጠኝ ‹‹ነፃ የዳኝነት አካል›› ይለዋል) ሥር ነቀል ለውጥ ከማካሄድ ትግል ጋር ፍርድ ቤቶች ሽግግሩ ውስጥ የተዘረገፉ አዳዲስ ጉዳዮች ያቀረቡላቸውን ዳኝነት ማየት/መስማትና ማስተናገድ አለባቸው፡፡ ከባድና ብርቱ ሥራ ነው፡፡ ሥራውን ከባድና ብርቱ ሸክም የሚያደርገው በመደበኛው የዘወትር ሥራ ላይ የተዘረጋው፣ አዳዲስ ጉዳዮች የፍርድ ቤቱን ዳኝነትና የዳኝነት ቁጥጥር ጠይቀው በመቅረባቸው ብቻ አይደለም፡፡ ተቋሙ እንዳለ፣ ፍርድ ቤቶች በየደረጃቸውና በየፊናቸው ከሌሎች የመንግሥት ዘርፎች፣ የሥልጣን አካላት፣ ሕግ አስከባሪዎችና አስፈጻሚዎች፣ እንዲሁም ከሌሎች አካላት ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንደገና የሚመረምሩበት፣ እንደገና የሚያቀናጁበትና የሚያጣምዱበት ጊዜም መሆኑ ነው፡፡ ከፖሊስ፣ ከፖሊስና ከዓቃቤ ሕግ፣ ከተጠረጠሩ፣ ከተያዙና ከተከሰሱ ሰዎች፣ ከማረፊያ ቤትና ከወህኒ ቤት፣ ከሚዲያ ጋር ያለው የዱሮው ግንኙነት ሁሉ አዲስ ‹‹ግብግብ›› ያመጣል፡፡ ለምሳሌ ‹‹ከጥላቻ የሚወርድብኝ ስድብና ውግዘት ብቻ ማስረጃ ሆኖ ጥፋተኛ ተብዬ እንዲበየንብኝ አልሻም›› ወይም ተቀዳሚ የስሜት ፍርድ ያልተጫነው እውነተኛ ፍትሕ›› እየተለከልኩ ነው የሚል አቤቱታ ዝም ብሎ በዱሮው መንገድ እንዳሻው የሚተው/ባፈተተ የሚሄድ አይደለም፡፡ ሐሳብን የመግለጽና የፕሬስ ነፃነትን ከተከሳሽ ትክክለኛ ፍትሕ ከማግኘት መብትና ከፍርድ ቤቱ ነፃነት ጋር ያገናዘበ አዲስ ዕይታን ውለዱ ይላል፡፡ በትንሹም በትልቁም ብርክ የማይዘው ራሱን ከሕዝብ አስተያየት የመከተ አዲስ አሠራር ከፍርድ ቤቶች ይጠይቃል፡፡

የሕዝብን ተስፋና እምነት መርታት የሚችል፣ አለኝታ ለመሆን የሚበቃ፣ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ መብቶችና ነፃነቶቻችን  የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር/የብረት መዝጊያ ሆኖ የሚያገለግል የዳኝነት አካል ከባድና ረዥሙን መንገድ መያያዝና መዝለቅ የሚቻለው፣ ይህን በመሰለ ፈታኝ ጊዜ ፖሊስና ዓቃቤ ሕግን በሥልጣኑ ውስጥ ለሕግ እንዲገዙ ከሕግ በታች ሆነው እንዲረማመዱ ማድረግ፣ ሕጎችን፣ የመብት ድንጋጌዎችን፣ በተለይም በፖሊስ የወንጀል ምርመራ ሥራ መመርያ ወይም ተራ ደንብ ላይ ሳይሆን፣ ሕገ መንግሥቱ የተደነገጉትን (ከአንቀጽ 17 ጀምሮ ያሉትን) የነፃነት መብት፣ ከኢሰብዓዊ አያያዝ የመመከት መብት፣ የተከሰሱ ሰዎች መብት፣ በጥበቃ ሥር… ያሉ ሰዎች መብት፣ ወዘተ. መኗኗሪያችን መሆናቸውን ሊያረጋግጡና ለዚያም ሲተጉ ሲታዩ ነው፡፡

ይህንን ለማድረግና መሆኑንም ለማረጋገጥ ለሕጎች ተፈጻሚነትና ለመብቶች ተጨባጭነት መተማመኛ በሆነው በገለልተኛ የተቋም፣ በተለይም የነፃ ዳኝነት አካል ተግባር ላይ በጭራሽ መዘናጋት የለብንም፡፡ ለፍርድ ቤቶች ነፃነትና ገለልተኝነት፣ ለዳኞች ባለሙያነት (ፕሮፌሽናሊዝም) መታገል አለብን፡፡ የሥርዓት ግንባታ ትግሉ ደግሞ ይህንን ለውጥና ሽግግር ከክሽፈት ለማዳን ከመረባረብ ይነሳል፡፡

 ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...