Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምርት ገበያ ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያወጡ የግብርና ምርቶችን በማገበያየት ዓመቱን አጠናቀቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲሱ ዓመት ጥጥ በምርት ገበያ ይስተናገዳል ተብሏል  

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ2012 ዓ.ም. ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያወጡ 762 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የግብርና ምርቶችን በማገበያየት የበጀት ዓመቱን አጠናቀቀ፡፡ ምርት ገበያው እንዳስታወቀው፣ በምርት መጠን 99 በመቶ፣ በዋጋ 113 በመቶ በማከናወን ዕቅዱን አሳክቷል፡፡ በአዲሱ ዓመት አዳዲስ አሠራሮችን ለመተግበር ስለመዘጋጀቱም ገልጿል፡፡

ምርት ገበያው የ2012 ዓ.ም. ሥራ አፈጻጸሙን እንዲሁም የ2013 ዕቅዶቹን በማስመልከት ዓርብ ነሐሴ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. መገለጫ ሰጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድምአገኝ ነገራ እንደገለጹት፣ የተሸኘው በጀት ዓመት አፈጻጸም ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር፣ በግብይት መጠን የ12 በመቶ በዋጋ ረገድ የ18 በመቶ ጭማሪ አስመዝግቧል፡፡

የ2012 ዓ.ም. የግብይትና የዋጋ መጠን እስከ ዛሬ በምርት ገበያው ከተከወናወነው ግብይት ሁሉ ብልጫ እንዳለው የጠቀሱት አቶ ወንድምአገኝ፣ በበጀት ዓመቱ ከተገበያየው ምርት ውስጥ ቡና 40.5 በመቶ፣ ሰሊጥ 34.4 በመቶ ድርሻ ነበራቸው ብለዋል፡፡ ለአገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኘው ቡና ግብይት ከዕቅድ በላይ በመጠን የ10 በመቶ፣ በዋጋ 19 በመቶ ብልጫ ያለው ግብይት እንደተፈጸመበት ያስታወቁት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ይህም በ2012 ዓ.ም. የተመዘገበው የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እንዲጨምር ወሳኝ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አብራርተዋል፡፡ የሰሊጥ ግብይትን በተመለከተ ከአቶ ወንድምአገኝ መረዳት እንደተቻለው፣ ከምርት መጠን የዕቅዱን 98 በመቶ ሲያሳካ፣ በዋጋ በኩል የአንድ በመቶ ብቻ ጭማሪ ነበረው ተብሏል፡፡ ግብይታቸው በምርት ገበያው በኩል ብቻ እንዲከናወን በአስገዳጅነት ከተደነገጉት ምርቶች መካከል አረንጓዴ ማሾ በከፍተኛ መጠን ለግብይት በመቅረቡ፣ ከዕቅድ በላይ 64 በመቶ ለማገበያየት እንዳስቻለ ገልጸዋል፡፡

36,000 ቶን አረንጓዴ ማሾ ለማገበያየት ቢታቀድም፣ በከፍተኛ መጠን ያስመዘገበ ምርት በመቅረቡ 59,210 ቶን ወይም ከዕቅዴ የ64 በመቶ ብልጫ የተመዘገበበት ምርት ወደ ግብይት ማዕከላት መምጣቱ ተመልክቷል፡፡

ምርት ገበያው ዋነኛ ግቡ ትርፉ ማካበት እንዳልሆነ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ቢያስታውቁም፣ በእያንዳንዱ ግብይት ወቅት ከሚያገኘው የአገልግሎት ክፍያና ሌሎች ገቢዎች 190 ሚሊዮን ብር እንዳተረፈ አስታውቀዋል፡፡ ተቋሙ በራሱ ገቢ የሚተዳደርና ከመንግሥት በጀት በማይበጀትለት በመሆኑ፣ ከሚያገኘው ገቢ ወጪዎቹን በመሸፈን ከወጪ ቀሪ 190 ሚሊዮን ትርፍ ማስመዝገብ እንደቻለ ተጠቅሷል፡፡

ምርት ገበያው ባለፉት 12 ዓመታት ውስጥ 6.6 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ምርት በ275 ቢሊዮን ብር ማገበያቱን ያስታወሱት አቶ ወንድምአገኝ፣ የክፍያና የርክክብ ሥርዓቱ ያለ ምንም መስተጓጎል ለገዥና ሻጭ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ለግብይት የሚቀርቡ ምርቶች የላቦራቶሪ ፍተሻ ተደርጎባቸው በሚሰጣቸው የጥራት ደረጃ ላይ ተገበያዮች የሚያቀርቡትን የቅሬታ መጠን ወደ አንድ በመቶ ለመቀነስ የተሠራው ሥራም ወደ 0.59 በመቶ ሊቀንስ እንደቻለ አስታውቀዋል፡፡

ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚቀርበውን ቡና የጥራት ደረጃ የሚያሳዩ ናሙናዎችን በመመልከት ገበያተኞች ግብይት እንዲፈጽሙ ማድረግም በ2012 ዓ.ም. ከተከናወኑ ሥራዎች ውስጥ ተካቶ ቀርቧል፡፡

የእያንዳንዱን ምርት አፈጻጸም በማስመልከት የተሰጠው መግለጫ እንደሚያሳየው፣ 308,303 ቶን ቡና በ24.8 ቢሊዮን ብር መገበያየቱን ነው፡፡ 262,099 ቶን ሰሊጥ በ11.4 ቢሊዮን ብር፣ 78,208 ቶን አኩሪ አተር በ1.1 ቢሊዮን ብር፣ 59.210 ቶን አንጓዴ ማሾ በ1.6 ቢሊዮን ብር፣ 47.925 ቶን ነጭ ቦሎቄ በ1.04 ቢሊዮን ብር፣ 6.259 ቶን ቀይ ቦሎቄ በ103 ሚሊዮን ብር ያስመዘገቡ ግብይቶች ተፈጽመዋል፡፡

ባለፉት 12 ዓመታት ውስጥ የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት፣ የሚያገበያየቸውን ምርቶች መጠን በመጨመር፣ የቴክኖሎጂ አቅሙን በማሳደግ፣ ወደ አርሶ አደሩ የቀረበ አገልግሎት በመስጠት፣ አዳዲስ አሠራሮችን በማስረጽና ተቋማዊ አቅሙን በማሳደግ ሥራዎች ላይ ውጤታማ ጉዞ ማከናወኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አውስተዋል፡፡

በተሸኘው በጀት ዓመት ከተከናወኑ አንኳር ጉዳዮች ውስጥ በነቀምቴ ከተማ አዲስ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከል ሥራ መጀመር በኤሌክትሮኒክ ዘዴ ለሚካሄደው የጨረታ ግብይት (ኢ-ኦክሽን)  545 ተገበያዮች ሥልጠና ወስደው ዕውቅና ማግኘታቸው ወደ ግብይት ሥራው መቀላቀላቸው፣ የግብይት መረጃ ለማሠራጨት የሚረዱ 77 የግብይትና የገበያ መረጃ ሰጭ ኪዮስኮች በተለያዩ አካባቢዎች መተከላቸው ከግብይቱ ጎን ለጎን የጠቀሱ የምርት ገበያው ተግባራት ናቸው፡፡ የመጋዘን አገልግሎት ደኅንነቱ የተጠበቀና ተዓማኒነቱ የተጠበቀ መሆኑን ለማረጋገጥ በተለያዩ ቅርንጫፎች የደኅንነት ካሜራዎች መተከላቸውም ተጠቅሷል፡፡ የምርት ቅበላና ርክክብ ሥርዓቱን ደኅንነት የበለጠ ለማረጋገጥም ሒደቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በታገዘ መንገድ ክትትል ለማድረግ የሚረዱ 36 የደኅንነት ካሜራዎች በሳሪስ፣ በቦንጋና ጊምቢ ቅርንጫፎች መተከላቸው ተገልጿል፡፡

 ምርት ገበያ የኮሮና ወረርሽኝ ተፅዕኖ እንብዛም ሳይጎበኘው ዓመቱን ለማጠናቀቅ እንደቻለ የጠቀሱት አቶ ወንድምአገኝ፣ ሌሎች ተግዳሮቶች ግን ተፈታትነውት ነበር ብለዋል፡፡ ካጋጠሙት ችግሮች መካከል በዓለም ገበያ የቡና፣ የቅባትና የጥራ ጥሬ ምርቶች ዋጋ መቀነስ፣ የቀይ ቦሎቄ ግብይት በምርት ገበያው ብቻ እንዲካሄድ ቢወሰንም በኮንትሮባንድ ንግድ ጫና ምክንያት በሚፈለገው መጠን ለግብይት መቅረብ አለመቻሉ ተጠቅሰዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ ለመጋዘንና ለግብይት ማዕከላት ግንባታ የሚፈለግ ቦታ አለማግኘትም ከዓመቱ ችግሮች መካከል ተመድቧል፡፡

ምርት ገበያው ከ2012 ዓ.ም. አፈጻጸሙ በተጨማሪ የ2013 ዓ.ም. ዕቅዱንም አስታውቋል፡፡ የአዲሱ ዓመት ዓበይት ዕቅዶቹ ከሆኑት ውስጥ በምርት ቅበላና ግብይት ሒደቱ ላይ አዲስ የሚካተቱ ምርቶችን ጨምሮ 784 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ምርት ለመቀበል መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡ አኩሪ አተርን በግብዓትነት ተጠቅመው ዘይት ለሚያመርቱ ፋብሪካዎች አዲስ የግብይት መስኮት በመክፈት አገልግሎት መስጠት፣ የእርግብ አተር፣ የዥንጉጉር ቦሎቄና የጥጥ ግብይቶችን ማስጀመር ምርት ገበያው ያቀዳቸው ተግባራት ናቸው፡፡

በዚህ በጀመት ዓመት ካጋጠሙን ችግሮች መካከል ተብለው በሥራ አስፈጻሚው ከተጠቀሱት ውስጥ ከዓለም ገበያ ዋጋ መዋዤቅ ጋር የተያያዙ ይገኙባቸዋል፡፡ በተለይ በዓለም ገበያ ላይ የቡና፣ የቅባትና ጥራጥሬ ምርቶች ዋጋ መቀነስ፣ ቀይ ቦሎቄ ግብይቱ በምርት ገበያው ብቻ እንዲካሄድ ቢወስንም በኮንትሮባንድ ንግድ የተነሳ በበቂ መጠን አለመቅረቡ በዋናነት ተጠቅሰዋል፡፡

በ2013 ዓ.ም. ሊሠሩ ከታቀዱት ውስጥ ሰሊጥና አኩሪ አተርን በግብዓትነት ተጠቅመው ዘይት ለሚያመርቱ ፋብሪካዎች አዲስ የግብይት መስኮት ተከፍቶላቸው በየቅርንጫፎቹ ምርቶች ገቢ እንደሚደረጉና እንደሚገበዩ ይጠበቃል፡፡

ከዚህ ባሻገር ተደራሽነቱን ለማሳደግ የምርት ቅበላ አቅሙን ለማሳደግ በቡሌ ሆራ፣ መቱና ቴፒ ከተሞች ያስገነባቸው አዳዲስ መጋዘኖችን ሥራ ለማስጀመር አቅዷል፡፡ በቅርንጫፎች የሚሰጠው የመጋዘን አገልግሎት ማዘመን፣ በዘመናዊ የግብይት ሥርዓቱ ሊካተቱ የሚችሉ የቅመማ ቅመምና የማዕድን ዓይነቶችን በመለየት ጥናት ለማካሄድ፣ የላቦራቶሪ አገልግሎትን በዲጂታል የመምራትና የፍተሻ ማረጋገጫ ሥርዓትን መጨመር፣ ሦስተኛ ትውልድ የግብይት ሶፍትዌር ማልማት፣ የፊውቸርና ፎርዋርድ ግብይት ሥርዓትን ሥራ ላይ ለማዋል የሚካሄደውን ጥናት ማጠናቀቅ፣ በጎንደር፣ አዳማና ጅማ ከተሞች አዲስ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከላት መክፈት፣ የዋናው መሥሪያ ቤት ግንባታ ዲዛይን ሥራ ማሠራት ከአዲሱ ዕቅዶቹ ውስጥ ተካተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገነባው የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ፣ ለገሐር አካባቢ ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት ጀርባ በሚገኝ ቦታ ላይ እንደሚታነጽ ተጠቅሷል፡፡ አጠቃላይ ግንባታው 1.7 ቢሊዮን ብር ገደማ እንደሚጠይቅ የተገለጸው ሕንፃ፣ ከ20 ወለሎች በላይ እንደሚኖሩት ተጠቅሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች