Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባንኮች ከከተማው አስተዳደር ጋር የአክሲዮን ኩባንያ ለመመሥረት ተስማሙ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቦሌ መንገድ ስምንት ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ግዙፍ ሕንጻ ሊገነቡ ነው

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ባንኮች አትራፊ የአክሲዮን ኩባንያ በማቋቋም አብረው ለመሥራት መስማማታቸው ተሰማ፡፡ መነሻቸውን ዘመናዊ የንግድና የግብይት ማዕከል በመግንባት ለማስጀመር ባደረጉት ስምምነት መሠረት አስተዳደሩ የግንባታ ቦታ መስጠቱ ታውቋል፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ ባንኮቹ ከከተማው አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጋር በመነጋገር በጋራ ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉበት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ በዚህ መሠረት በከተማው ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጥ የንግድና የግብይት አገልግሎት መስጫ ማዕከል እንደሚገነቡ ይጠበቃል፡፡

ለታሰበው የሕንጻ ግንባታ የሚውል፣ በቦሌ መንገድ ከፍሬንድሽፕ ሕንፃ ጎን የሚገኝ ስምንት ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ የከተማ አስተዳደሩ መስጠቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

 በከተማው አስተዳደርና በባንኮች የጋራ ኢንቨስትመንት የሚገነባው ፕሮጀክት ከፍተኛ ወጪን እንደሚጠይቅ ሲገለጽ፣ ፕሮጀክቱን ዕውን ለማድረግ ሁሉም ባንኮችና የከተማው አስተዳደር ባለአክሲዮን የሚሆኑበት ኩባንያ እንደሚቋቋም ተገልጿል፡፡ ይህንኑ ኩባንያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥራ ለማስጀመር ዝግጅት እንደተደረገ የሪፖርተር ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ ኩባንያ የማቋቋሙን ሐሳብ ባንኮች ለቦርድ በማቅረብ ምን ያህል ድርሻ እንደሚገዙ ቦርድ እንዲወስን ለማድረግ መስማማታቸውም ተጠቅሷል፡፡

እንደ ምንጮች ከሆነ፣ በከተማ አስተዳደሩ በኩል የቀረበው ቦታ ላይ ደረጃውን የጠበቀና ለተለያዩ የንግድ ሥራዎች የሚውል ሕንፃ፣ በቦሌ አፍሪካ ጎዳና መንገድ ዳር በሚገኝ ቦታ ላይ እንደሚገነባ ይጠበቃል፡፡  

ባንኮች የአክሲዮን ድርሻቸውን ከማስወሰን በተጓዳኝ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበርም ግዙፍ ኢንቨስትመንት እንደሚጠይቅ የሚነገርለትን የሕንጻ ግንባታ ሥራ እንደሚያስተባብር ተነግሯል፡፡

ከተማ አስተዳደሩና ባንኮች በጋራ ለመሥራት ከወሰኑባቸው ምክንያቶች አንዱ በየዓመቱ ለተማሪዎች ምገባ፣ ለትምህርት መሣሪዎችና ለመሰል ማኅበራዊ ድጋፎች የሚያስፈልገውን ሀብት ከማቅረብ ባሻገር፣ የከተማ አስተዳደሩ እነዚህን ሥራዎች የሚደጉምበት ቋሚ የገቢ ምንጭ እንዲኖረው በማሰብ ጭምር ጥምረት መፍጠራቸው ተገልጿል፡፡ በመሆኑም አስተዳደሩ በአክሲዮን ኩባንያው ላይ በሚኖረው ድርሻ መሠረት የሚያገኘውን ትርፍ ለተማሪዎች የሚያስፈልጉ የትምህርት ቁሳቁሶች አቅርቦቶችና አገልግሎቶች የሚውሉ ወጪዎችን መሸፈን የሚችልበት ዕድል ይፈጠርለታል፡፡

በዚህ ዕቅድ መሠረት ባንኮች ለሕንጻ ግንባታ የሚውለውን የኢንቨስትመንት  ወጪ በየአክሲዮን ድርሻቸው ልክ ያዋጣሉ፡፡ የከተማ አስተዳደሩም መሬት በማቅረብ  የአክሲዮን መዋጮውን በዓይነት በማድረግ ይሳተፋል፡፡ የተሻለ አማራጭ ከተገኘ ሌሎች መንገዶች ሊታዩ ይችላሉ ተብሏል፡፡

ይህንን ፕሮጀክት ዳር ለማድረስ እየተንቀሳቀሱ ከሚገኙ ምንጮች የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ በዚህ ቁልፍ ቦታ ላይ የሚታነፀው ሕንፃ ዘመናዊ አገልግሎቶች ሊሰጡ የሚችሉ የሕንፃው ክፍሎች ባሻገር በዚያ መስመር ያለውን የፓርኪንግ ችግር ለማቃለል ያስችላል የተባለ ግንባታ ይኖረዋል፡፡ በርካታ ተሽከርካሪዎችን የሚይዝ ፓርኪንግ እንዲገነባበት ጭምር ፕሮጀክቶችን በተመለከተ ከተካተቱ ዕቅዶች መካከል አንዱ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ በተለየ የከተማዋን ገጽታ ከመለወጥ ባለፈ በከተማ ውስጥ በዘመናዊ መንገድ አገልግሎት የሚሰጡ የገበያ ማዕከሎች መዝናኛና ከሌሎች ቢዝነሶች አገልግሎቶች ሊውል በሚችል ደረጃ እንዲታነፅ የታሰበ ነው፡፡ በተለይ አንድ ዘመናዊ ሞል ሊያካትታቸው የሚገቡ ይዘቶች ይኖሩታል፡፡

ይህ ዓይነቱ የመንግሥትና የግል ዘርፉ አጋርነት ለባንኮችም መልካም አጋጣሚ በመሆኑ፣ ተጨማሪ የጋራ የኢንቨስትመንት ሐሳቦች እንዲካተቱበት ተደርጎ ዲዛይኑ እንዲሠራ በሁለቱም ወገን ፍላጎት እንዳለ ታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት 18 ባንኮች በሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡ በመጪው ዓመትም ተጨማሪ ባንኮች ገበያውን እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል፡፡ ይህ ፕሮጀክት አዳዲስ ባንኮችንም እንደሚያካትት ተጠቅሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች