Saturday, July 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮ ሊዝ ኩባንያ ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣባቸውን 16 ኮምባይነሮች ለገበሬዎች በኪራይ አስረከበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮ ሊዝ ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ እያንዳንዳቸው በአማካይ ከ250 ሺሕ ዶላር ያላነሰ ወጪ የጠየቁና በጠቅላላው ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸውን 16 ኮምባይነሮች፣ በሻሸመኔ ከተማ ለሚገኙ ገበሬዎችና ማኅበራት በኪራይ አስረከበ፡፡

ኩባንያው ሐምሌ 28 ቀን 2012 ዓ.ም. ኮምባይነሮቹን ለሻሸመኔ ገሬዎችና ማኅበራት ባስከበበት ሥነ ሥርዓት ወቅት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀጋዬ ግሩም እንደተናገሩት፣ ኢትዮ ሊዝ በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ኢንቨስትመንቱን ወደ 200 ሚሊዮን ዶላር በማሳደግ በእርሻ ሜካናይዜሽንና በተለያዩ አገልግሎቶች ላይ ለመሰማራት አቅዷል፡፡ እያደገ የመጣውን ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎች ፍላጎት በመጠኑም ለማስተናገድ የሚቻልበትን ስልት በመንደፍ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አቶ ፀጋዬ አስታውቀዋል፡፡

በሻሸመኔ የተካሄደው ርክክብን ጨምሮ እስካሁን ለተጠቃሚዎች ያቀረባቸው የግብርና መሣሪያዎች ቁጥር ወደ 100 እንዳደረሰ ያስታወቀው ኢትዮ ሊዝ፣  የመሣሪያዎቹ አጠቃላይ ወጪም ሰባት ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ አስታውቋል። ከእነዚህ በተጨማሪ ኩባንያው በመጪው ዓመት መስከረምና ጥቅምት ወራት ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ተጨማሪ መሣሪያዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የሚያስፈልጉትን ሥራዎችን እያጠናቀቀ እንደሚገኝ ገልጿል። 

ነዋሪነቱ በባሌ ሮቤ ጨፌ ዶንሳ ገበሬ ማኅበር ውስጥ የሆነው ወጣት ድሪባ አሰፋ፣ በኢትዮ ሊዝ ከቀረቡ ኮምባይነሮች የመጀመርያውን የአንድ ሚሊዮን ብር ክፍያ በመፈጸም ለሦስት ዓመታት በሚቆይ የኪራይ ስምምነት ተረክቧል፡፡ ጠቅላላ ክፍያው 5.5 ሚሊዮን ብር የሆነውን ይህን ኮምባይነር ከሦስት ዓመታት በኋላ የራሱ ለማድረግ ማቀዱን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

ወጣት ድሪባ የራሱን ጨምሮ ከቤተሰቡ አሥር ሔክታር መሬት በማረስ ገብስና ስንዴ ያመርታል፡፡ ከዚህ በፊት የመጀመርያ የሆነውን ኮምባይነር ከኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ተበድሮ በገዛው ኮምባይነር የራሱን ጨምሮ በአካባቢው ለሚገኙ ገበሬዎች በኩንታል ከ50 እስከ 70 በማስከፈል እህል ያጭድ ስለነበር፣ የዚያን ልምድ በመውሰድ አዲሱን ኮምባይነር ለመግዛት እንደወሰነ ተናግሯል፡፡

እየተለዋወጠ በመጣው የአየር ንብረት ምክንያት ምርት ሳይበላሽ በቶሎ ከማሳ ለመሰብሰብ እንደሚቻል፣ አጭዶና ሰብስቦ ወደ ጎተራ ለማስገባት ይወስድ የነበረውን የአንድ ሳምንት ጊዜ፣ በ30 ደቂቃ ውስጥ አጭዶ መውቃት መቻል ትልቅ ዕፎይታን ከመስጠት ባሻገር ብክነትን እንደሚያስቀር አምራቹ አብራርቷል፡፡

ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ኮምባይነሮች፣ ክላስ ከተሰኘው የጀርመን የግብርና ማሽነሪዎች አምራች ኩባንያ የተገዙ ናቸው፡፡ ለእርሻ መሣሪያዎቹ የጥገና አገልግሎት በመስጠት የቴክኒክ ሥራዎችን የሚቆጣጠረው የሚከታተለው ካሌብ የእርሻ መሣሪያዎች ጥገናና ሥልጠና ማዕከል የተሰኘው አገር በቀል ኩባንያ ነው፡፡

የካሌብ ኩባንያ የንግድ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሚካኤል ተስፋዬ ለሪፖርተር ስለ ሥራው ሲገልጹ፣ ‹‹ሰብል በመሰብሰብ ወቅት እስከ 30 በመቶ ምርት ይባክናል፡፡  የገበሬው ምርት በብዛት ባክኖ የሚቀርበትን አሠራር እነዚህ መሣሪያዎች በመቀየር ትልቅ ጥቅም ይሰጣሉ፤›› ብለዋል፡፡

ወደ ሥራ በመግባት ሁለተኛ ዓመቱን ያስቆጠረው ኢትዮ ሊዝ፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ በማግኘት በ400 ሚሊዮን ብር የተመዘገበ ካፒታል የተቋቋመ፣ በኒው ዮርክ ከተማ የሚገኘውና አፍሪካን አሴት ፋይናንስ ለተሰኘ እህት ኩባንያ በመሆን የሚንቀሳቀስ ተቋም ነው፡፡ ኢትዮ ሊዝ ከእርሻ መሣሪያዎች በተጨማሪ የሕክምናና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ላይ የሚታዩ ዕጥሮችን ለማሟላት በኪራይ የሚያቀርብ ኩባንያ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመርያው የግል የሊዝ ፋይናንስ አቅራቢ ኩባንያ በመሆን ፈቃድ ያገኘው ከሦስት ዓመታት በፊት ነበር፡፡

በዚህ ዓመት የካቲት ወር ከግብርና ሚኒስቴርና ከግርብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ጋር የግብርናውን ዘርፍ በሜካናይዝድ እርሻ ለማገዝ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል፡፡ በዚህ ስምምነት መሠረት በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት የ150 ሚሊዮን ዶላር ግምት ያላቸው ዘመናዊ የግብርና መሣሪያዎችና ማሽነሪዎች፣ ለግብርና ሜካናይዜሽን ማዕከላት እንደሚያቀርብ መገለጹን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች