Wednesday, September 27, 2023

የፌዴራል መንግሥቱን ልሳነ ብዙ የማድረግ ጅማሮና ፖለቲካዊ አንድምታው

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ቋንቋ ለመግባቢያ የማያገለግል መሣሪያ መሆኑ አንድ ሀቅ ቢሆንም ፋይዳው ግን ከዚህ በእጅጉ የዘለለ ነው። ቋንቋ የተናጋሪው ማኅበረሰብ የኩራት ምንጭ፣ በራስ የመተማመን ምንጭና የማንነት መገለጫ ነው። ይህ ፋይዳውም ቋንቋን ከተግባቦት መሣሪያነት በላይ ያጎላዋል። በኢትዮጵያ የተካሄዱ በርካታ የፖለቲካ ትግሎች መነሻ ምክንያቶችም ይህንን ዕውነታ የሚያስረዱ ናቸው። 

መጫና ቱለማ በሚል መጠሪያ በ1950ዎቹ የተመሠረተው የኦሮሞ መረዳጃ ማኅበር ከጥንስሱ ጉልበት አግኝቶ በወቅቱ ከነበረው የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት አስተዳደር ጋር ግጭት ውስጥ የገባበት ምክንያት፣ ማኅበሩ ሕዝባዊ ስብሰባዎቹን በኦሮሚኛ ቋንቋ ማካሄድ በመጀመሩ እንደነበር ይገለጻል። 

በመጫና ቱለማ እንቅስቃሴ ደስተኛ ያልነበረው የንጉሡ አስተዳደርም በ1958 ዓ.ም. ገደማ ማኅበሩ ኦሮሚኛ ቋንቋን በስብሰባዎቹ ከመጠቀም እንዲቆጠብ ትዕዛዝ ያስተላልፋል። 

መጫና ቱለማ ግን ይኼንን ትዕዛዝ ባለመቀበሉ በወቅቱ የነበረው መንግሥት የማኅበሩ አመራሮችንና አባላቱን በመያዝ በአገር ክህደት ወንጀል ጭምር በመክሰስ ከረዥም ዓመታት እሥር እስከ ሞት ፍርድ እንዳስፈረደባቸው፣ በማኅበሩ አንድ አባል ላይም የሞት ፍርድ ውሳኔው መፈጸሙን የሕገ መንግሥት ምሁርና ተመራማሪው ያሬድ ለገሰ (ዶ/ር) ከዓመታት በፊት ባሳተሙት የምርምር ጹሑፋቸው አስፍረዋል። 

‹‹የቋንቋ አስተዳደር በኅብረ ብሔራዊ ፌዴሬሽን›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት የጥናት ጽሑፋቸው የኢትዮጵያን ተሞክሮ በንፅፅር የተመለከቱት ያሬድ (ዶ/ር)፣ የንጉሡ አስተዳደር በመጫና ቱለማ ላይ በወሰደው ዕርምጃ የማኅበሩ እንቅስቃሴ ቢስተጓጎልም ዕርምጃው ግን የታመቀውን የቋንቋ ጥያቄ በኦሮሞ ልሂቃን እንዲሰርፅና ተቃውሞው እንዲቀጣጠል ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ። 

በትግራይ የቀዳማዊ ወያኔ አመፅን ለማዳከም የንጉሡ አስተዳደር ከወሰዳቸው ዕርምጃዎች በተጨማሪ፣ የትግርኛ ቋንቋ እንዳይነገር ማገዳቸው ለዳግማዊ ወያኔ (ሓወሓት) መፈጠር የሞራል ስንቅ ሆኖ እንዳገለገለና ትግሉም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምክንያት እንደነበር ያስረዳሉ።

የ1970ዎቹ የተማሪዎች የፖለቲካ ትግል ማጠንጠኛ ቋንቋን መሠረት ያደረገ የብሔረሰቦች ነፃነት ጥያቄ እንደነበር ይታወቃል።

በሕወሓት መሪነት በተካሄዴው የኢሕአዴግ ትግል ወታደራዊውን አስተዳደር የማስወገድ ዘመቻ በ1983 ዓ.ም. መጠናቀቁን ተከትሎ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ ቀዳሚ አጀንዳም በዚሁ ዙሪያ ያጠነጠነ ነበር። 

የሽግግር መንግሥቱ ቻርተር በ1983 ዓ.ም. በፀደቀበት ወቅት የወቅቱ የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ባደረጉት ንግግርም፣ ‹‹በመላ አገሪቱ የተካሄደው ጦርነት ቁልፍ ጥያቄ የብሔር ብሔረሰቦች ነፃነትን ለመመለስ ነው። ሕዝቦች የታገሉት በቋንቋቸው የመጠቀም መብታቸውን ለማረጋገጥ፣ በባህላቸው ለመጠቀምና ራሳቸውን ለማስተዳደር ነው። ይህንን መብቶቻቸውን ማረጋገጥ ባይቻል፣ ጦርነትን ማስቆምም ሆነ ሌላ ጦርነት እንዳይነሳ መከላከል አይቻልም፤›› ብለው ነበር። 

ይህንን ተከትሎ የተደነገገው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ኅብረ ብሔራዊ የፌዴራሊዝም ሥርዓትን በመዘርጋት የብሔር ብሔረሰቦች ነፃነትን፣ በቋንቋና ባህላቸው የመጠቀምና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት አረጋግጧል። 

ዘንድሮ 25 ዓመቱን የሚይዘው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ አምስት ሥር ስለቋንቋ የደነገገ ሲሆን፣ በዚህ አንቀጽ ሥር ከተቀመጡት መካከል ቀዳሚው ድንጋጌ፣ ‹‹ማናቸውም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በእኩልነት የመንግሥት ዕውቅና ይኖራቸዋል፤›› የሚል ነው። 

በቀጣዮቹ ድንጋጌዎች ደግሞ አማርኛ የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ስለመሆኑ፣ እንዲሁም የፌዴራል ሥርዓቱን የመሠረቱት አባል ክልሎች የየራሳቸውን የሥራ ቋንቋ በሕግ እንደሚወስኑ ተደንግጓል። 

በአንቀጽ 39 (2) ላይ ደግሞ ማናቸውም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብና ሕዝብ በቋንቋው የመናገር፣ የመጻፍ፣ ቋንቋውን የማሳደግና ባህሉን የመግለጽ፣ የማዳበርና የማስፋፋት፣ እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መብት እንዳለው ተደንግጓል። 

በዚህም መሠረት ባለፋት 25 ዓመታት ብሔር ብሔረሰቦች በቋንቋቸው የመጠቀም ምሉዕ ነፃነትን አግኝተው ቋንቋቸውን ሲያሳድጉና ማንነታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።  ይህ ዕድልም በኢትዮጵያ የቋንቋ ብዝኃነት እንዲጎለብት ያደረገ ሲሆን፣ እስከ 53 የሚደርሱ ቋንቋዎችም ለመጀመርያ ደረጃ ትምህርት መስጫነት መዋላቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ነገር ግን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የቋንቋ ጥያቄ አሁንም በተሟላ ሁኔታ ተመልሷል ማለት አይቻልም። 

ከሚነሱት ጥያቄዎች መካከል በቀዳሚነት ጎልቶ የወቅቱ ፖለቲካ ቁልፍ መከራከሪያ የሆነውም፣ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ የሆነውን የአማርኛ ቋንቋ የመገዳደር፣ በውስጡም የቋንቋ እኩልነት ጥያቄ ጎልቶ የሚነሳበት ነው። 

የቋንቋ እኩልነት ጥያቄው በኦሮሞ ብሔረሰብ የፖለቲካ ልሂቃን መካከል ጎልቶ የሚደመጥ፣ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ እየገነነ የመጣ የፖለቲካ አጀንዳ መሆኑ ይታወቃል። 

አማርኛ ቋንቋ በታሪክ ያገኘውን ዕድል ይዞ በአገሪቱ የመነገር አድማሱ ሰፊ በመሆኑ በፌዴራል የሥራ ቋንቋነት ቢመረጥም፣ የቀደሙት የኢትዮጵያ መንግሥታት አድልኦና በሌሎች ብሔሮች ላይ ያደረሱትን ጭቆናን አማርኛ ቋንቋ አስታዋሽ አድርጎ በመሳልና በማስተሳሰር የቋንቋ እኩልነት ፖለቲካው እንዲጎለብት ሆኗል።

ይህ ጥያቄ ፈጦ መምጣት መጀመሩ የፌዴራሉ መንግሥት ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ አንቱ በተባሉ የቋንቋ ባለሙያዎች ሲያስጠናው የነበረው፣ ነገር ግን ለረዥም ዓመታት ትኩረት ተነፍጎት ለተጓተተው የቋንቋ ፖሊሲ ትኩረት እንዲሰጥ አስገድዶታል።

ለፖሊሲ ዝግጅቱ በተሰጠው ልዩ ትኩረትም ሰነዱ ተጠናቆ የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ በየካቲት 2012 ዓ.ም. ላይ ሁሉን አቀፍ የሆነ የቋንቋ ፖሊሲ እንዲፀድቅ አድርጓል።

የፀደቀው የቋንቋ ፖሊሲም ላለፋት 25 ዓመታት የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ሆኖ እያገለገለ ከሚገኘው አማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ አራት ቋንቋዎች ተጨማሪ የሥራ ቋንቋ ሆነው እንዲያገለግሉ ወስኗል። በዚህም መሠረት ኦሮሚኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማሊኛና አፋርኛ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ሆነው እንዲያገለግሉ በፖለሲ ደረጃ ተመርጠዋል። 

  • ልሳነ ብዙ የፌዴራል መንግሥት ሥርዓት ጅማሮና አንድምታው

ኅብረ ብሔራዊ የፌዴራሊዝም ሥርዓትን የሚከተሉ አገሮች የሚከተሉት ቋንቋ ፖሊሲ በሁለት እንደሚከፈል የዘርፉ ተመራማሪዎች ያስረዳሉ።

አንደኛው የአስተዳደር ወሰንን መሠረት አድርጎ የሚዘጋጅና የሚተገበር (Territorial) የቋንቋ ፖሊሲ ሲሆን፣ ይህም ብሔር ብሔረሰቦች በአስተዳደር ወሰናቸው ውስጥ በራሳቸው ቋንቋ የመጠቀም መብትን ያጎናፅፋቸዋል። 

ሌላኛው ደግሞ የግለሰብ ምርጫን መሠረት ያደረገ (Individualistic) የቋንቋ ፖሊሲ ነው። ይህ የቋንቋ ፖሊሲ ሞዴል ደግሞ የግለሰቦች ምርጫን መሠረት የሚያደርግ ሆኖ፣ ሞዴሉን የሚተገብሩት አገሮች በአብዛኛው ጥቂት ብሔረሰቦች ብቻ አባል በሆኑባቸው የፌዴራል ሥርዓት መዋቅሮች የሚተገበሩ ናቸው። ለአብነትም ካናዳ ተጠቃሽ ስትሆን በፈረንሣይኛና በእንግሊዝኛ ተናጋሪ ማኅበረሰቦች የተዋቀረ የፌዴራል መንግሥት በመሆኑ፣ ሁለቱንም ቋንቋዎች የሥራ የፌዴራል መንግሥቱም ሆነ የክልል አስተዳደሮች የሥራ ቋንቋ በማድረግ፣ የአገሪቱ ዜጎች በመረጡት ቋንቋ የመንግሥት አገልግሎቶችን ማግኘት ይችላሉ።

በአሁኑ ወቅት በደቡብ አፍሪካ ዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ የሚገኙት የሕገ መንግሥትና ፌደራሊዝም ተመራማሪው ዮናታን ተስፋዬ (ዶ/ር) ከዓመታት በፊት፣ ‹‹የሁለት ፌዴሬሽኖች ወግ፣ የቋንቋ መብት አስተዳደር በደቡብ አፍሪካና በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት የጥናት ጽሑፋቸው በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ንፅፅራዊ ሀተታ አቅርበዋል። 

በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች በሚያቋቁሙት የፌዴራል ሥርዓት ውስጥ የአስተዳደር ወሰንን (Territorial) የቋንቋ ፖሊሲ አማራጭን መከተል የተለመደ መሆኑን የሚያስረዱት ዮናታን (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ የቋንቋ ፖሊሲም በዚሁ ሥር እንደሚወድቅ ያመለክታሉ። 

እንደ ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ ያሉ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች የሚወከሉበት ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ሥርዓት ውስጥ፣ የፌዴራል የሥራ ቋንቋን መምረጥ አስቸጋሪ መሆኑንም በጥናት ጽሑፋቸው አስረድተዋል።

እ.ኤ.አ. በ1996 ተሻሽሎ የፀደቀው የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥት በአገሪቱ ከሚነገሩ በርካታ ቋንቋዎች መካከል 11 ቋንቋዎችን የፌዴራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ ያደረገ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ደግሞ አማርኛን ብቻ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ አድርጎ መደንገጉን ያስታውሳሉ። 

በደቡብ አፍሪካ 11 ቋንቋዎች የፌዴራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ ሆነው ዕውቅና ቢያገኙም፣ በአብዛኛው የመንግሥት የሥራ ቋንቋ ሆኖ በጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው ከብሔር ተቃርኖ ውጪ የሆነውና በቅኝ ግዛት ተፅዕኖ ሰፊ የመነገር አድማስን የሸፈነው የእንግሊዝኛ ቋንቋ መሆኑን ያስረዳሉ። 

በዚህም ምክንያት ምንም እንኳ ሌሎቹ ቋንቋዎች የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ሆነው ዕውቅና ቢያገኙም፣ ካገኙት የመነገር ዕድል አንፃር የተሰጣቸው ዕውቅና ምልክታዊ እንደሆነ ያስረዳሉ። 

የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥት 11 ቋንቋዎች የሥራ ቋንቋ አድርጎ ሲመርጥ፣ የቋንቋዎቹ አጠቃቀምን በተመለከተ የመወሰን ድርሻን ለመንግሥት ተቋማት የአስተዳደር አካላት ሰጥቷል። 

በዚህም መሠረት የአስተዳደር አካላት ከአሥራ አንዱ የሥራ ቋንቋዎች ውስጥ ሁለት ቋንቋዎችን በሥራ ቋንቋነት እንዲመርጡ ሲወስን አመራረጡም በተናጋሪዎች ብዛት፣ በአጠቃቀምና በአስተዳደር ምቹነት፣ በወጪና በመሳሰሉት መሥፈርቶች ተመዝነው ጥቅም ላይ እንዲውሉ አድርጓል።

ኢትዮጵያ በየካቲት ወር 2012 ዓ.ም. ያፀደቀችው የቋንቋ ፖሊሲ አራት ተጨማሪ የሥራ ቋንቋዎችን በመምረጥ፣ በጥቅሉ አምስት የሥራ ቋንቋዎች የፌዴራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋዎች እንዲሆኑ ወስኗል። 

የቋንቋ ፖሊሲውን መፅደቅ ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹አማርኛ ቋንቋ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ በመሆኑ እርስ በርሳችን እንድንግባባ በማድረግ ረገድ ሚናው ትልቅ ነው። አማርኛ ቋንቋ በአገር ውስጥ ያለው የተናጋሪዎች ብዛትና የተደራሽነት ስፋት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ተጨማሪ የሥራ ቋንቋዎችን መጠቀም አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝና ተግባቦትን ለማሳለጥ አንዱ መንገድ ነው፤›› ብሏል። 

ተጨማሪ የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ የተመረጡት አራቱ ቋንቋዎች ከሚነገሩበት ክልል በዘለለ በጎረቤት አገሮች ጭምር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተናጋሪዎች ያሏቸው በመሆኑ፣ ከአማርኛ ቋንቋ ጎን ለጎን ጥቅም ላይ ቢውሉ ልሳነ ብዙ አገረ መንግሥት ከመገንባት ባሻገር ውሳጣዊና ቀጣናዊ ትስስርን እንደሚያፋጥን ገልጿል። 

ይሁን እንጂ በፀደቀው የቋንቋ ፖሊሲ ላይ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ሆነው የተመረጡት አራቱ ቋንቋዎች፣ የተመረጡበት ሕጋዊነት ጥያቄ ሳይነሳበት አልቀረም። 

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የፌዴራሊዝምና የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያ፣ ሕገ መንግሥቱ ሁሉም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እኩል እንደሆኑ ደንግጎ ሳለ ከላይ የተዘረዘሩት ቋንቋዎች የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ሆነው መመረጣቸው የሕጋዊነት ጥያቄ እንደሚያጭር ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ሕገ መንግሥቱ ቋንቋዎችን የማሳደግና የማበልፀግ ኃላፊነትን ለክልሎችና ለተናጋሪው ማኅበረሰብ ሰጥቶ ሳለ፣ የፌዴራል መንግሥት ይህንን ኃላፊነት መውሰዱ ሌላ የሕጋዊነት ጥያቄ እንደሚያስነሳ፣ በተጨማሪም ሒደቱ የቋንቋዎች እኩልነትን ሳይሆን መበላለጥን አመላካች እንዳያደርገው ያሳስባሉ። 

የቋንቋ ፖሊሲውን በማዘጋጀት ሒደት የተሳተፉ ምሁራን በበኩላቸው ፖሊሲው የፀደቀ ቢሆንም፣ አፈጻጸሙ ሕገ መንግሥት ማሻሻያ እንደሚጠይቅ በፖሊሲ ሰነዱ ላይ ጭምር ማመላከታቸውን ይናገራሉ። 

በፖሊሲ ዝግጅቱ ላይ ከተሳተፉት መካከል የቋንቋ ምሁሩ ሞገስ ይገዙ (ዶ/ር) ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያው እንዳለ ሆኖ፣ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ አራቱ ቋንቋዎች ቢመረጡም በቀጣይ ሌሎች ቋንቋዎችም በጥናት ላይ በመመሥረት የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ በፖሊሲው መመላከቱን ያስረዳሉ። 

ተጨማሪ የሥራ ቋንቋዎችን መምረጥ ቋንቋዎችን ማበላለጥ እንዳልሆነ የሚገልጹት ባለሙያው፣ ሁሉም ቋንቋዎች በተፈጥሮ እኩል መሆናቸውንና ይህንን መቀየር እንደማይቻል፣ ነገር ግን አንድ ቋንቋ ከሌላው ቋንቋ በመነገር አድማስ ደረጃው ከሌላው ሊበልጥ እንደሚችል ገልጸዋል። 

ከዚህ አኳያ አንድን ቋንቋ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ አድርጎ መምረጥ ከቋንቋ እኩልነት ጋር እንደማይጣረስ ይገልጻሉ። የቋንቋ ፖሊሲውን ለማዘጋጀት በዋናነት ተሞክሮ የተወሰደው ከደቡብ አፍሪካ መሆኑ ደግሞ፣ በደቡብ አፍሪካ እንደ ተከሰተው በርካታ ቋንቋዎችን የፌዴራል የሥራ ቋንቋ አድርጎ ዕውቅና በመስጠት ምልክታዊ ፋይዳ ላይኖረው ይችላል የሚል ሥጋትን የሚያንፀባርቁ ባለሙያዎች ይደመጣሉ።

በርካታ ቋንቋዎችን የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ማድረግ ክልሎች ከአንድ በላይ የሥራ ቋንቋን እንዲጠቀሙ የሚያደርግ በመሆኑ፣ ተጨማሪ የሥራ ቋንቋ ሆነው ከተመረጡት ይልቅ የአማርኛ ቋንቋን የአገልግሎት አድማስ የማስፋት ውጤቱ ከፍተኛ ስለሚሆን ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን እንደሚያጎለብት በአዎንታዊ ጎኑ ሲያነሱ፣ በሌላ በኩል ግን ቋንቋን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ትኩሳት እንዳይወለድ ሲሉም ሥጋታቸውን ያካፍላሉ።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -