አንዱ ከሳሽ ሌላው ተከሳሽ የሆኑበት የአገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲያከትም፣ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር፣ የመጠላለፍ ፖለቲካ እንዲወገድና አዲስ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር ትግል እንደሚያደርግ ምክክር ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (ምክክር) አስታወቀ፡፡
ፓርቲው ይህን አቋሙን ይፋ ያደረገው ለሦስት ቀናት በፓርቲው ማኒፌስቶ ላይ ሲያካሂድ የነበረውን ውይይትና ማሻሻያ መጠናቀቅን ተከትሎ ሰኞ ነሐሴ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ነው፡፡
ፓርቲው የዜጎችን ነፃነት ለማስከበር የሶሻል ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም የሚከተል መሆኑን ያስታወቀ ሲሆን፣ በዚህ ርዕዮተ ዓለም እየተመራ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታና እሴቶችን በመውሰድና በማጣመር በሚቀርፃቸው ፖሊሲዎች የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች እንደሚያደርግም የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ሳሳሁልህ ከበደ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ግለሰብ የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ሙሉ በሙሉ የሚከበርበት ኅብረ ብሔራዊ ኅብረተሰብ እንዲያብብ እንደሚታገል ያስታወቀው ፓርቲው፣ በዚህም መሠረት ‹‹እጅግ ውድ የሆነው የሰው ልጅ እሴት ነፃነት እንደመሆኑ በሁሉም መስክ የግለብ ነፃነት ቀዳሚ ሥፍራ ይይዛል፤›› በማለት ፓርቲው ከቡድን መብት ይልቅ ለግለሰብ መብት ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ሁሉም ሰዎች በተፈጥሯቸው እኩል በመሆናቸው ኢትዮጵያውያን በዘር፣ በቀለም፣ በትምህርት፣ በሀብት፣ በፆታ፣ በሃይማኖት እንዲሁም በአመለካከት ላይ የተመሠረተ አድሎ ሊደረግባቸው አይገባም የሚል አቋም የሚያራምድ ፓርቲ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
አሁን ካለው ፓርላሜንታዊ የፖለቲካ ሥርዓት ይልቅ በሕዝብ ቀጥታ የሚመረጥ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት ለመገንባት እንደሚታገል ያስታወቀው ፓርቲው፣ ‹‹ለአንድ ጊዜ የተመረጠ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አገሪቱን ለአምስት ዓመታት ይመራል፣ ይህ ፕሬዚዳንት ከሁለት ጊዜ በላይ በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አይወዳደርም (አይመረጥም)፤›› የሚል የፖለቲካ ፕሮግራም እንዳለውም አስታውቋል፡፡
ከጥምር ጎሳ የተወለዱ ከ43 ሚሊዮን በላይ ዜጎች እንዳሉ የሚገልጸው ፓርቲው፣ በአዲስ አበባና ሌሎች ትልልቅ ከተሞች የሚኖሩ ሕዝቦች በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውክልና የሌላቸው በመሆኑ ውክልና እንዲኖራቸው ፓርቲው እንደሚታገልም አስታውቋል፡፡
ምክክር ፓርቲ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ2011 ዓ.ም. እውቅና ካገኙ ፓርቲዎች አንዱ ሲሆን፣ ፓርቲው በአገር አቀፍ ፓርቲነት የሚወዳደር እንደሆነም አስታውቋል፡፡