ድርድሩ ለሦስተኛ ጊዜ ዳግም መራዘሙ ተገለጸ
ታላቁ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል ያለው አለመግባባት ሊፈታ የሚችለው በድርድር ብቻ መሆኑን ኢትዮጵያ በድጋሚ አስታወቀች።
ኢትዮጵያ ይህንን ያለችው ሦስቱ አገሮች ለመደራደር የያዙት ቀጠሮ ለሦስተኛ ጊዜ ከተራዘመ በኋላ ባወጣችው መግለጫ ነው።
የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ሦስቱ አገሮች በልዩነቶቻቸው ላይ ለመደራደር ለሰኞ ነሐሴ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ይዘው የነበረ ቢሆንም፣ በሱዳን ጥያቄ ድርድሩ በድጋሚ እንዲራዘም ተወስኗል፡፡ ድርድሩ የተራዘመው ለሦስተኛ ጊዜ ሲሆን፣ ለመራዘሙ ምክንያት የሆኑት ግብፅና ሱዳን በተናጥል ባቀረቧቸው ጥያቄዎች መሆኑ ተገልጿል።
ሦስቱ አገሮችን እያወዛገበ የሚገኘው የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌትና አስተዳደርን በተመለከተ ኢትዮጵያ የራሷን ሰነድ ከሁለት ሳምንት በፊት ያቀረበች ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ይህንን ማድረጓን ተከትሎ ግብፅና ሱዳን ሰነዱን ለመመርመር ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጽ ድርድሩ እንዲራዘም በማድረግ ላይ ናቸው።
የአፍሪካ ኅብረት ሦስቱም አገሮች በአፍሪካዊ ስሜት እንዲደራደሩ ባለፈው ሳምንት ጥሪ ቢያቀርብም፣ ግብፅና ሱዳን ዳግም ድርድሩ ያለ በቂ ምክንያት እንዲራዘም እያደረጉ መሆኑ ታውቋል።
አገሮቹ ድርድሩን በመቀጠል የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ቢሮ ስብሰባ በተካሄደ ሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ የመካከለኛና የመጨረሻ ሪፖርት ለኅብረቱ ሊቀመንበር ሪፖርት እንዲያቀርቡ ይጠበቅ እንደነበር ኢትዮጵያ በመግለጫዋ አስታውሳለች።
ድርድሩ በመጪው ሰኞ ነሐሴ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚቀጥል ያመለከተው መግለጫው፣ በድርድር የሚደረስበት ስምምነት ብቸኛ አማራጭ በመሆኑ ኢትዮጵያ ለድርድሩ ውጤታማነት አበክራ ትሠራለች ብሏል፡፡