ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለስፖርትና ለኦሊምፒክ እንቅስቃሴ ላሳዩት ምሳሌነት ከአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር (አኖካ)፣ ‹‹አኖካ ኦርደር ኦፍ ሜሪት›› (ANOCA ORDER OF MERIT) የተሰኘ ዕውቅና አገኙ፡፡
የዕውቅና ሽልማቱን ወደፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚያመቻቸው ቀንና ቦታ ለመስጠት እየጠበቁ መሆኑን የአኖካ ፕሬዚዳንት መግለጻቸውን መቀመጫው ናይሮቢ ያደረገው ካፒታል ኤፍኤም በድረ ገጹ ዘግቧል፡፡
ይህ ሽልማት እንዲሰጥ የተወሰነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የኢትዮጵያን ስፖርት ለማዘመን፣ ከአገሪቱ የልማት ዘርፎች እኩል እንዲታይና እንዲራመድ ማስቻላቸውን ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና ስፖርት ኮሚሽን በጋራ ለአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ባሳወቁት መሠረት መሆኑን የአኖካ ፕሬዚዳንትና የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል ሙስጠፋ ቤራፊ የላኩት ደብዳቤ ያሳያል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ ቶኪዮ ኦሊምፒክ ቡድንና ለኦሊምፒክ አካዴሚ ግንባታ ሦስት ቢሊዮን ብር ለመስጠት ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡