በሊባኖስ ቤሩይት ብቸኛ በሆነው ወደብ ሐምሌ 28 ቀን 2012 ዓ.ም. የደረሰው የአሞኒየም ናይትሬት ክምችት ፍንዳታ ሊባኖስ የነበረባትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ይበልጥ ያጎላ ሆኗል፡፡ 200ዎች የሞቱበት፣ ከ100 በላይ የገቡበት ያልታወቀበት፣ ከ6,000 በላይ የተጎዱበትና ከ300,000 ሰው በላይ የተፈናቀለበት ፍንዳታ፣ መንግሥት እንዲፈናቀልም ምክንያት አድርጓል፡፡
ሊባኖሳውያን በፍንዳታው ምክንያት የመጨረሻ ብሶታቸውን የገለጹበትና መንግሥት እንዲጠየቅ ተቃውሞ ሠልፍ የወጡበትም ነው፡፡ ኢኮኖሚው ወድቋል፣ ሙስና ተንሰራፍቷልና መንግሥትም እየሠራ አይደለም በሚል መንግሥትን የሚኮንኑት ሊባኖሳውያን፣ በቤይሩት እ.ኤ.አ. ከ2013 ጀምሮ የተከማቸው 3,000 ቶን ያህል አሞኒየም ናይትሬት የመንግሥትን ችላ ባይነት ያሳያል ብለዋል፡፡
በሊባኖስ ወደብ አካባቢ የተከሰተው ፍንዳታ ድምፅ ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ ድረስ ተሰምቷል፡፡ በአካባቢውና በርቀት የሚገኙ ንብረቶችንና ሕንፃዎችን ያወደመው ፍንዳታ፣ ቤይሩትን በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ንብረትና በዋጋ የማይተመን የሰው ሕይወት አስገብሯታል፡፡
የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐሰን ዲያብ በቤይሩት የሁለት ሳምንት አስቸኳይ ጊዜ ያወጁ ሲሆን፣ ለመከላያውም ሙሉ ሥልጣን ሰጥተዋል፡፡ የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ሚሼል ኦውንና ሌሎች የደኅንነት አካላትን ያቀፈው የሊባኖስ ከፍተኛ የመከላከያ ምክር ቤትም ቤይሩት የአደጋ ሰለባ መሆኗን አውጇል፡፡
ሊባኖሳውያን ደግሞ ለፍንዳታው መከሰት ምክንያት የሆኑ ሰዎች እንዲጠየቁ ሲሉ ተቃውሞ ወጥተዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ የሊባኖስ መከላከያ ፍርድ ቤት 16 የወደብ ሠራተኞች እንዲታሰሩ ማድረጉን አሳውቋል፡፡ ከ700 በላይ ተቃውሞ ሠልፈኞች መጎዳታቸውም ተነግሯል፡፡
ቀድሞውንም በሙስና ተዳክሟል የተባለው የሊባኖስ ኢኮኖሚ በፍንዳታው ይበልጥ በመንኮታኮቱ ሕዝቡን ለሰብዓዊ ዕርዳታ ዳርጎታል፡፡ የፍንዳታውን መከሰት ተከትሎ ቤይሩትን የጎበኙት የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካና የቀጣናው አገሮችን አስተባብረው ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲያደርጉ አስችለዋል፡፡ አጽንኦት የሰጡት ለሙስና ሥር ነቀል መፍትሔ ካልተደረገ በሊባኖስ በወር ጊዜ ውስጥ የነዳጅና የምግብ እጥረት እንደሚከሰት ነው፡፡
የአውሮፓ ኅብረት 33 ሚሊዮን ዩሮ (38 ሚሊዮን ዶላር) ለአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ መልቀቁንም አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ ፕሬዚዳንት ማክሮን ባዘጋጁት ኮንፍረንስ የ300 ሚሊዮን ዶላር ሰብዓዊ ዕርዳታ ቀጥታ ለሕዝቡ ለማድረስ ቃል ተገብቷል፡፡
በቤይሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት አካባቢ በመሄድ የተደረገው ተቃውሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዲያብ ምርጫ ቀድሞ እንዲደረግ እንዲወስኑ አድርጓቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫውን ከታቀደው ጊዜ ቀድሞ ለማካሄድ የሚያስችል ረቂቅ እንደሚያዘጋጁ፣ ይህም አገሪቷ ከገባችበት ቀውስ ለማውጣት ብቸኛው መፍትሔ እንደሆነ ገልጸው ነበር፡፡
ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወንበር የመልቀቃቸውን ደብዳቤ ለአገሪቱ ፕሬዚዳንት አቅርበዋል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀደም ብሎ የሊባኖስ የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ማናል አብዲል ‹‹ሊባኖስ ወደማትወጣው አዘቅት ገብታለች›› ብለው መልቀቂያ አስገብተዋል፡፡ የኢንቫይሮመንት ሚኒስትሩ ዳሚኖስ ካታርም ሥልጣን ከለቀቁት ውስጥ ይሰለፋሉ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትርን ዲያብ የመልቀቂያ ደብዳቤ የተቀበሉት ፕሬዚዳንት ኦውን፣ ሚስተር ደያብ አዲስ መንግሥት እስኪመሠረት እንደ ባለአደራ እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሪፎርም በሊባኖስ
በሊባኖስ ባለፈው ሳምንት የፈነዳው የአሞኒየም ናይትሬት ክምችት በአገሪቱ ሕዝቦች ዘንድ ቁጣንና የፖለቲካ ተቃውሞውን አስከትሏል፡፡ ይህ ቀድሞውንም ለነበረው የኢኮኖሚ ቀውስ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኗል፡፡
አብዛኞቹ የሊባኖስ ዜጎች መንግሥታቸው በሙስና መዘፈቁን በመግለጽ ኮንነዋል፡፡ ፍንዳታው የተከሰተውም በመንግሥት ቸልተኝነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሕዝቡ ከመስከረም 2019 ዓ.ም. ጀምሮ ሃይማኖትን መሠረት አድርጎ የተመሠረተው መንግሥት ለሙስና የተጋለጠ፣ አቅም የሌለውና ብልሹ አስተዳደር ነው ሲል በተደጋጋሚ ተቃውሞ ወጥቷል፡፡
ፍንዳታውን ተከትሎ በተቀሰቀሰ ቁጣ ከጠቅላይ ሚኒስትርነት የመልቀቂያ ደብዳቤ ያስገቡት ሚስተር ዲያብ፣ ሥልጣን የመልቀቅ ፍላጎት ባይኖራቸውም በአገሪቱ ያለው ችግር እንዳስገደዳቸው አልጀዚራ አስፍሯል፡፡
እሳቸው ለሁለት ወራት በሥልጣን ቆይተው በአገሪቷ በሚደረገው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሪፎርም የተለያዩ አካላትን አሰባስበው ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት ፈልገው ነበር፡፡ ሆኖም በካቢኔያቸው በኩል ያለው ውጥረት ሥልጣን እንዲለቁ አስገድዷቸዋል፡፡
የሚስተር ዲያብ መንግሥት በሂዝቦላህ የሚደገፍ በመሆኑ ወደ አንድ ወገን ያደላ ነውም ይባላል፡፡ በመሆኑም በአገሪቱ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሪፎርም ለማድረግ ቃል የገቡትን ያህል አልቻሉም፡፡ አሁን ግን የሪፎርሙ ሥራ መጀመር አለበት፡፡ የአልጀዚራው በርናርድ ስሚዝ ከቤይሩት እንደዘገበው፣ በሊባኖስ ለውጥ ለማምጣት የታለመውን ሪፎርም ማድረግ ግን ቀላል አይሆንም፡፡ ምክንያቱም የሊባኖስ የምርጫ ሥርዓት የተዘረጋው በአገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ሰዎችን ለመጠበቅ ነው፡፡ በአገሪቱ ያለውን ችግር ለመቅረፍም ፖለቲከኞችን ማግባባት ያስፈልጋል፡፡
በአንድ በኩል በሂዝቦላህ የሚደገፈው መንግሥት በሌላ በኩል ይህንን ተቃውሞ በየጊዜው ሠልፍ የሚመጣውን አስታርቆ መሄድም ግድ ይላል፡፡ ሁሉንም ያሳተፈ መንግሥት መመሥረትም ወሳኝ ነው፡፡ ይህ የአገሪቱን ፖለቲካና ኢኮኖሚ መልሶ ለማዋቀር ያስችላል ተብሎ ታምኖበታል፡፡ ሆኖም ሚስተር ዲያብ ሪፎርሙን ሳያካሂዱ ሥልጣን ለቀው ከሄዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችንና ሌሎች ተቋማትን ይቆጣጠራሉ፡፡ ይህ ደግሞ በሊባኖስ የተረጋጋ ኢኮኖሚና ፖለቲካ እንዳይኖር ያደርጋል፡፡