በሔለን ተስፋዬ
የትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ በየጊዜው ከሚነሱ ችግሮች መካከል ሕገወጥ የትምህርት ማስረጃ ተጠቃሽ ነው፡፡ በተለያዩ ቦታዎች የሚማሩ አንዳንድ ተማሪዎች ሳይለፉና ሳይጥሩ እንዲሁም በሚገባው ደረጃ ላይማሩና ዕውቀት ሳይሸምቱ የመጀመርያ ዲግሪ፣ የሁለተኛ ዲግሪ ባለቤት ሲሆኑ መቆየታቸውም አይዘነጋም፡፡
ተሹማምንት ሳይቀሩ በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ እስከ መታማት የደረሱበት ጊዜም እንደነበር ይነገራል፡፡ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ ሰርተፍኬት ሲሸምቱ ቆይቷል፡፡
በኢትዮጵያ ሐሰተኛ ትምህርት ማስረጃን የያዙ ሰዎች በማይገባቸው ሥራና የሥራ እርከን ላይ ተቀምጠው ሲሠሩ እንደነበር መንግሥት መግለጹ ይታወሳል፡፡
ይህ እንደ አገር የአሠራር ሒደትን ወደ ኋላ ከማስቀረት፣ የትምህርት ዘርፍ እንዳያድግ ወደ ኋላ ከመጎተቱ በበለጠ ትውልድ የሚያበላሽ ተግባር በመሆኑ ምሁራን ሲኮንኑም ነበር፡፡
መንግሥት ይህንን አስመልክቶ በተለያዩ ጊዜያት መረጃዎችን በማግኘቱም የብዙዎችን ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ከማገድ ጀምሮ ቅጣትም አስተላልፏል፡፡
ይሁንና አሠራሩ ዘመናዊና ቀልጣፋ ባለመሆኑ በመንግሥት ደረጃ የትምህርት ሥርዓቱን ለመቆጣጠር እጅግ አዳጋች ሆኖ ቆይቷል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ አሠራሩ ተቋማቱን ለመመዘንና በየጊዜው ለመቆጣጠር አመቺ ባለመሆኑ የመመርያ ጥሰቶች፣ ኋላ ቀር አሠራሮችን ተያያዥ ጉዳዩን ለመቅረፍ ሠርቷል፡፡ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያሰችል አውቶሜትድ ሶፍትዌር ሐምሌ 28 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡
ላለፉት ዓመታት ከፍተኛ የሕግ ጥሰቶች፣ የትምህርት ጥራት መጓደል ስለታየ የኢኖቬሽንና ቴከኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በጋራ ከሃያ በላይ የሶፍትዌር ባለሙያዎችን በማሰማራት ለ18 ወራት የሠሩትን ሥራ በማጠናቀቅ የመረጃ አስተዳደር ዘርግተዋል፡፡
የመረጃ አስተዳደር ሥርዓቱን ሁሉም በጉጉት ሲጠብቀው የነበረ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ሒሩት ወልደ ማርያም (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል፡፡
ፕሮፌሰር ሒሩት፣ በርከት ያሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመፍታት አጋዥ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተስፋ መሆናቸውን ገልጸው፣ ‹‹ወቅታዊ፣ የተሟላ ይዘት ያለው፣ ግልጽነትን የተላበሰ፣ ከትክክለኛ ምንጭ የተገኘና ጥራት ያለው ውሳኔ ለመስጠት አውቶማሽኑ ከማገዙ ባሻገር ተቋማዊ ተልዕኮን በውጤታማነት ለመሥራት ያስችላል፤›› ብለዋል፡፡
አውቶሜሽኑ ተፈላጊ መረጃዎችን በማደራጀት ለሚመለከተው አካል በወቅቱ ግብረ መልስ ለመስጠት የሚያስችል የመረጃ እስተዳደር ሥርዓት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የትምህርት ተቋማት የት እንዳሉ፣ ስንት ካምፓስና ምን ያህል ተማሪዎች እንዳሏቸው፣ የመምህራን ቁጥር፣ የሚይዙት የትምህርት ዓይነት ሁሉ በመረጃ አልነበረም የሚሉት ፕሮፌሰር ሒሩት፣ ይህም በትምህርት ጥራትና አግባብነት ላይ ጫና ማሳደሩን ተናግረዋል፡፡
ክፍተቶቹ ሕገወጥነትን ሲያስከትሉ መቆየታቸውን በመጠቆም፣ ወቅታዊና የተደራጀ መረጃ ለዜጎች ማቅረብ ከሁሉም አካል የሚጠበቅ ተግባር ብቻ ሳይሆን ግዴታ በመሆኑ አሁን የተሠራው ሥራ ኃላፊነትን ከመወጣት ጋር የተያያዘ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የሚመለከቱ ወቅታዊ መረጃዎች ተደራሽ ማድረግ የተጠቃሚዎችንና የባለ ድርሻ አካላትን ተሳትፎ የበለጠ ለማጎልበት እንደሚረዳ፣ የመረጃ አስተዳደር ሥርዓቱ ሕገወጥ የሆኑ አሠራሮችን ለማጋለጥ የሚያግዝ ከመሆኑ ባሻገር የተቋማትን አሠራር በቴክኖሎጂ የመደገፍና የማዘመን ጅማሮ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
የመረጃ አያያዝ ሥርዓቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባሉበት ሆነው በአጭር ጊዜና በቀላሉ የዕውቅና ፈቃድ የሚያገኙበት፣ የሚያወጡበትና ሌሎችም አገልግሎቶች የሚገኙበትን ምቹ ሁኔታ አካትቶ የያዘ ነው፡፡
ተገቢውን መሥፈርት ያሟሉ ተቋማት ያላቸውን ፕሮግራሞች፣ ካምፓሶቻቸውን፣ የተማሪዎች ቁጥር ሲጨምሩም ሲቀንሱም በመረጃው አስተዳደሩ የሚመዘገብ ይሆኗል፡፡
በዚህ መልኩ ለሚመለከተው አካል ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል አገልግሎት ሲሆን፣ በዘርፉ የሚታየውን ሕገወጥነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ቴክኖሎጂ ነው፡፡
የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አንዱዓለም አድማሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ላለፉት ዓመታት በትምህርት ሥርዓቱ የሕግ ጥሰቶችና ከፍተኛ የሆነ የትምህርት ጥራት መጓደል መታየቱን አስታውሰው፣ እስከ ዛሬ በማንዋል ሲሠራ የነበረው አሁን ሙሉ ለሙሉ አውቶሜት በመደረጉን በኢትዮጵያ ያሉ ተመራቂዎች በሙሉ በመረጃ አስተዳደሩ ስለሚያዙ ቀጣሪ መሥሪያ ቤቶች ከመረጃ አስተዳደሩ በቀጥታ ማግኘትና ማረጋገጥ እንዲችሉ ያግዛል ብለዋል፡፡
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የመረጃ አስተዳደር ሥርዓት የከፍተኛ ትምህርትን ለማዘመንና ከቴክኖሎጂ ጋር ለማስተሳሰር አበረታች ጅማሮ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
አያይዘውም እንደገለጹት፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በኢንስቲትዩቱ በኩል የተለያዩ ተቋማት ደረጃውን የጠበቀ የመረጃ አስተዳደር ሥርዓት በመዘርጋትና ሶፍትዌር በማሳደግ የጀመረውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
የኢንፎርሜሸን ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ለመሥራት ከከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ጋር እየሠራን ነውም ብለዋል፡፡
ከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተሰጣቸው ፈቃድ መሠረት እየሠሩ እንደሆነና እንዳልሆነ ቁጥጥር ለማድረግ የመረጃ ሥርዓት አስተዳደሩን አጋዥነት ያስረዱት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ቀሬ ናቸው፡፡
በዚህም በተቋማቱ የተመዘገቡ ተማሪዎችን ከመቅጠር ጀምሮ ተማሪዎች ስለሚማሩባቸው ተቋማት መሠረታዊ መረጃ ይዘው እንዲገቡ ያግዛል፡፡ በመረጃ አስተዳደር ሥርዓቱ ማንኛውም ተቋሙን ማስመዝገብ የሚፈልግና ለማኅበረሰቡ የትምህርት አገልግሎት የሚሰጥ መጠቀም ይችላል፡፡ የመረጃ ሥርዓት ደኅንነትን ለመጠቀም፣ አግባብነት ያላቸው ወይም የተፈቀደላቸው ተጠቃሚዎች ብቻ በድረ ገጹ እንዲጠቀሙ ይደረጋል፡፡ በመረጃ ሥርዓት አማካይነት ተቋማት የሚያደርጉትን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ የመከታተልና የማረጋገጥ ሥራ ይሠራል፡፡
ቴክኖሎጂው የትምህርት ተቋማት የሚፈልጉትን አገልግሎትን ለማግኘት የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ድረስ መምጣት ያስቀረም ነው፡፡
በሌላ በኩል የከፍተኛ ትምህርት ተዳራሽ እንዲሆን በኦንላይን ትምህርት ማቅረቢያ ሥርዓት ተዘርግቷል ያሉት ሚኒስትሯ፣ ከቅበላ እስከ ምረቃ የሚደርስ አዲስ መመርያ በከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ በኩል ተዘጋጅቶ በቦርዱ መፅደቁን ገልጸዋል፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ የፈጠረው የገጽ ለገጽ የትምህርት አካሄድ በመቋረጡ፣ በትምህርት ፍኖተ ካርታው የተቀመጠው የኦንላይን ትምህርት መተግበር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች ዕድሜያቸው ከ19 እስከ 25 ዓመት ክልል ውስጥ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 13 በመቶ ብቻ ዕድሉን እያገኙ ይገኛል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ፍላጎትን ለማሟላትም የኦንላይን ትምህርት ያግዛል ተብሏል፡፡