Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የድርቅ መነሻ የሆኑትን ችግሮች ለመቅረፍ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ጀምረናል›› አቶ ተሾመ ታከለ፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የደቡብ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ደቡብ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤትን ከፍቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ቅርንጫፉ በአካባቢው የሚታዩ የሰብዓዊ ቀውስ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሠራ ነው፡፡ ካለፉት ዘጠኝ ወራት ወዲህ ደግሞ ከመደበኛ ሥራው ጎን ለጎን የኮቪድ – 19 ወረርሽኝ እያስከተለ ያለውን ተፅዕኖ ለመቋቋም በጎ ፈቃደኞችን ጭምር በማሰማራት እየሠራ ይገኛል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ የሳኒታይዘር ማምረቻ አዘጋጅቶ ለጥቅም አውሏል፡፡ ከ300,000 በላይ በጎ ፈቃደኞችን እንዳሰማራ የሚገልጸው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ፣ በክልሉ በሚገኙ 25 ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በሚገኙ የመንግሥት ጤና ተቋማት የሙቀት መለኪያ ማከፋፈሉን ይገልጻል፡፡  የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ተሾመ ታከለን ታምራት ጌታቸው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የቀይ መስቀል ደቡብ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት መቼ ተቋቋመ? በምን ያህል ወረዳዎችና ዞኖች ውስጥ አገልግሎት ይሰጣል?

አቶ ተሾመ፡- የደቡብ ቀይ መስቀል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የተቋቋመው በ1973 ዓ.ም. ነው፡፡ በደቡብ ክልል በሚገኙ 25 ወረዳዎች፣ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ይንቀሳቀሳል፡፡ በ16ት ወረዳዎች ውስጥ ደግሞ መዋቅር ዘርግቶ ሙሉ የአምቡላንስና የፋርማሲ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፡፡ ቅርንጫፉ ከድንገተኛ አደጋ፣ ከጎርፍ፣ ከሰብዓዊ ድጋፍ ባሻገር በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ በሆኑ ችግሮች ላይ አቅዶ እየሠራ ነው፡፡ የድርቅ መነሻ የሆኑትን ችግሮች ለመቅረፍ የተቀናጀ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ጀምረናል፡፡ ከስምንት ዞኖች የተውጣጡ 20 ሞዴል አርሶ አደሮች የሥራው ተሳታፊ ናቸው፡፡ እነዚህን አርሶ አደሮች በማሠልጠን ወደየአካባቢያቸው ተመልሰው የተራቆቱ መሬቶችን በማልማታቸው ዘንድሮ ከጎርፍ ነጻ ከመሆናቸውም በተጨማሪ በቅርቡም በካርቦን ሽያጭ ላይ ለመሰማራት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ እነዚህንና ሌሎች ሥራዎችን በመሥራት ችግር ሲደርስ እህልና ዕርዳታ ይዞ ከመቅረብ በላይ በተለይ በደቡብ ቅርንጫፍ በርካታ ሥራዎችን እየሠራን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- የደቡብ ቀይ መስቀል ቅርንጫፍ ባለፉት ሁለት ዓመታት ራሱን እንደ አዲስ በማደራጀት ሥራዎችን እየሠራ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ምን ምን ሥራዎችን በዚህ ጊዜ ውስጥ አከናውኗል?

አቶ ተሾመ፡- ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ ለሕዝባችን ያስተማርነው ጠባቂነትን ነው፡፡ ይህንን አስተሳሰብ ለመለወጥ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ራሱን ከማደራጀትና ከመለወጥ ጀምሮ መዋቅሩን በማሻሻል ለቀይ መስቀል የጀርባ አጥንት የሆኑትን በጎ ፈቃደኞችን እንዲሁም ሀብት የመሰብሰብ ሥራ ሠርቷል፡፡ በ47 ጤና ጣቢያዎች 50 አምቡላንሶች የነበሩ ሲሆን፣ አሁን በ77 ጤና ጣቢያዎች 171 አምቡላንሶች አሉን፡፡ የበጎ ፈቃደኞችንም 300,000 ያደረስን ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት ከ16,000,000 ብር ላይ ቁሳቁሶችን ጨምሮ የተለያዩ አቅም ፈጥረናል፡፡ ከ800 በላይ የጌዲዮ ተፈናቃዮችን ለአንድ አባወራ በአራት ዙር በዓመት 20 ሺሕ ብር እያገዝን እንገኛለን፡፡ ተፈናቃዮችንና ሥራ አጦችን በማደራጀት በዘላቂ ልማት ሥራ መፍጠር የተቻለው በዚህ ሁለት ዓመት ነው፡፡ ቀይ መስቀል ከራሱ በተጨማሪ ኅብረተሰቡ በራሱ የሚረዳዳበት ባህልን ለመፍጠር ሠርቷል፡፡ በጉራጌ ዞን ቦዲ ወረዳ ላይ ‹‹የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ፕሮጀክት›› በሚል እዚያው በኅብረተሰቡ በተውጣጡ ሽማግሌዎች አማካይነት የሚመራ ፕሮጀክት በመቅረጽ ኅብረተሰቡ ከአሥር ሳንቲም ጀምሮ እስከሚችለው ወይም፣ ከአንድ ኩባያ በቆሎ ጀምሮ እስከ ኩንታል በማምጣት ብሮቹን በኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ገቢ በማድረግ እህሎቹን ደግሞ መጋዘን በማድረግ በችግር ጊዜ ሁሉም ኅብረተሰብ እኩል የሚካፈሉበት፣ በሰላሙ ጊዜ ደግሞ ሥራ ላጡ ሥራ የሚፈጥሩበትና አቅመ ደካሞችን የሚያግዙበትን መንገድ ፈጥረናል፡፡ ይህ ተሞክሮ ከኮሮና በኋላ በ60 ወረዳዎች የሚቀጥል ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- በቀይ መስቀል መድኃኒት ቤቶች እንደ ትልቅ ክፍተት የሚታየው የተፈለገው መድኃኒት አለመኖር ነው፡፡ እንዴት ያዩታል?

አቶ ተሾመ፡- ይህ እንደ ሕዝብ እንደ መንግሥት ከፍተኛ ችግር ነው፡፡ ችግሩን ባገኘነው መድረክ ሁሉ እንናገራለን፡፡ በቅርቡ ደም ማቅጠኛ መድኃኒት ፈልገን በአካባቢያችን በሚገኙ ሁለት መድኃኒት ቤቶች ጠየቅን፡፡ አንዱ ቦታ 640 ብር ሌላው ስፍራ 700 ብር አሉን፡፡ ከከተማዋ ራቅ ያለ የቀይ መስቀል ፋርማሲ በአጠጋጣሚ ስንጠይቅ በ48 ብር አገኘን፡፡ ኅብረተሰቡና መንግሥት ለቀይ መስቀል መድኃኒት ቤቶች ትኩረት ሊሰጡ ይገባል የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ለትርፍ ያልተቋቋመ በመሆኑ መጪውም በጣም ቀላል ነው፡፡ አንድ ባለሙያና አምስት በአምስት የሆነ አንድ ክፍል ብቻ ነው የሚፈልገው፡፡ ሀብቱን ማሰባሰብ እጅጉን ቀላል ነው፡፡ በሚቀጥሉት ጊዜያትም ትኩረት አድርገን በዚህ ችግር ላይ የምንሠራ ይሆናል፡፡ ሌላው በዚህ ችግር ከባድ ተጠቂ እየሆነ ያለው ደሃው ገበሬ ነው፡፡ ማስታገሻ ለማግኘት እንኳን ዋጋውን መቋቋም እያቃተው ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በአገራችን የተከሰተውን ኮሮና ለመከላከል ምን እያደረጋችሁ ትገኛላችሁ?

አቶ ተሾመ፡- ኮቪድ – 19 በተመለከተ በርካታ ሥራዎችን እየሠራን እንገኛለን፡፡ ከ300 ሺሕ በላይ በጎ ፈቃኞችን በማሰማራት የትምህርት፣ የሥልጠናና የመንከባከብ አገልግሎት እየሰጠን ሲሆን፣ በክልሉም የመጀመርያ የሆነውን በቀን ስድስት ሺሕ ሊትር ሳኒታይዘር የሚያመርት ፋብሪካ በግቢያችን ገንብተን በቅናሽ ዋጋ ለመንግሥትና መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች እያቀረብን ነው፡፡ በ25ቱም ዞኖችና ወረዳዎች ማረሚያ ቤቶች የኮቪድ – 19 የመጀመርያ መለያ የሆነውን የሙቀት መለኪያ በነፃ አከፋፍለናል፡፡ የሳኒታይዘር ርጭትም እያካሄድን ነው፡፡ በቅርቡም ለክልሉ የሚበቃ ሳኒታይዘር ማምረቻ ለመገንባት ዝግጅት እየደረግን እንገኛለን፡፡ ኮቪድ በጎና ክፉም ነገር አምቶብናል፡፡ ደጉ ነገር በክልሉ የሚገኙ ከ116 ሺሕ በላይ መምህራን፣ የመንገሥት ሠራተኞችና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ለበጎ ፈቃደኝነት ሥራ ለመመልመል ረድቶናል፡፡ መጥፎ ጎኑ ደግሞ የዘመቻ ሥራ የሆነው የእርከን ሥራ አጓቶብናል፡፡ በገቢም ደረጃ የመቀዛቀዝ ሁኔታ አምቶብናል፡፡

ሪፖርተር፡- ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ወደፊት ምን ለመሥራት አቅዷል?

አቶ ተሾመ፡- በ2013 ዓ.ም. ለመተግበር የታሰበው ፕሮጀክት  ከኦስትሪያ ቀይ መስቀል ጋር በመተባበር በ48 ሚሊዮን ብር ወጪ የመረጃ ቋት (ዳታ ሴንተር) ለመገንባት ነው፡፡ ይህ የደቡብ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱን ሙሉ በሙሉ በዘመናዊ አሠራር የሚቀይረው ይሆናል፡፡ ጠቅላላ ያሉትን ከ500 በላይ አምቡላንሶች በቋቱ የሚገቡ በመሆኑ የት ናቸው፣ ምን ሠሩ የሚለውን ይከታተላል፡፡ በክልሉ አደጋ ሲከሰት ከማዕከል ሆኖ ለመቆጣጠር ያስችላል፡፡ የራሱን ገቢ ለማሳደግ ከክልሉ መንግሥት ጋር በመተባበር እስከ 18 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ሥራ የተጀመረ ሲሆን፣ በዞኖች ሕንፃዎችን ለመገንባት እየተነጋገርን እንገኛለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች