Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገር‹‹እኔንስ ማን ይቆንጥጠኝ?››

‹‹እኔንስ ማን ይቆንጥጠኝ?››

ቀን:

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

ወ/ሮ ወርቅ ያንጥፉ የሚባሉ ሴት ነበሩ ይባላል፡፡ ሴትዮዋ ከሃምሳም ከመቶም ዓመት በፊት የነበሩ እመቤት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከሺሕ ዓመት በፊትም የኖሩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ጊዜው እንደ መንፈሳቸው አይታቅም፡፡ ብቻ ግን ‹‹እኔንስ ማን ይቆንጥጠኝ አሉ ወ/ሮ ወርቅ ያንጥፉ›› እየተባለ ስማቸውና ድርጊታቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ እኛ ዘመን ደርሷል፡፡ ታዲያ ወ/ሮ ወርቅ ያንጥፉ ማን ነበሩ? ‹‹እኔንስ ማን ይቆንጥጠኝ?›› ያሉት እርሳቸው ናቸው? በዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እምነት ከሁሉም የሚወለዱባላባት ዘርና ባላባት ናቸው፡፡

ስማቸውም ወርቅ አንጥፈው ይቀበሉሽ፣ ወርቅ ይሸልሙሽ፣ ወርቅ በወርቅ ያድርጉሽ፣ በአጭሩ ደግሞ የምትሄጅበት መንገድ እንዳይጎረብጥሽ፣ የምትቀመጭበትና የምትንተራሽው መከዳ እንዲመችሽ፣ የምትተኝበት አልጋ እንዳይቆረቁርሽ ወርቅ ያንጥፉልሽ እንደማለት ነው፡፡ ከዚህ ሲያጥር ወርቅ ያንጥፉ ይሆናል፡፡

ወ/ሮ ወርቅ ያንጥፉ ከባላባትነቱ በተጨማሪ የንጉሠ ነገሥታት ዝርያ አላቸው ይባላል፡፡ ትንቢቱ ‹‹እኔንስ ማን ይቆንጥጠኝ?›› እስካሉበት ጊዜ አልተፈጸመም እንጂ ንጉሠ ነገሥት አግብተሸ ንግሥተ ነገሥታት ትሆኛለሽ ተብሎ ተነግሮላቸዋል፡፡ ትንቢቱ ግን በሕይወት ዘመናቸው ይነገር፣ እናታቸው ወይም አያት ቅድመ አያታቸው ይናገሩት የተረጋገጠ ነገር የለም፡፡

ትንቢቱ ይፈጸምም አይፈጸምም በትውልድ ሥፍራቸው ግን ከንግሥተ ነገሥታት በላይ ተፈርተውና ተከብረው የሚኖሩ ባለ ብዙ ጋሻ መሬት ናቸው፡፡ ተራው ሰው የሚያየው አጥር ግቢያቸው ከቤተ ክርስቲያን ግቢ አይተናነስም ነበር ይባላል፡፡ ከዚያ በላይ ማስፋት ከፈለጉም ‹‹ድራሸ ቢሱን›› ሁሉ አባረው፣ ዘመድም ከሆነ ራቅ ወዳለ ሥፍራ ቤት እንዲቆረቁር አድርገው በዙሪያቸው ያለው መሬት መውሰድ  ይችላሉ፡፡ ለነገሩ ነው እንጂ የያዙት ግቢ የሰፊዎች ሰፊ ነው፡፡ አንዳንዱም ግቢያቸውን ‹‹ንጉሥ አጥር›› ይሉታል፡፡ ታዲያ በግቢያቸው ውስጥ ትልቅ ቤት ስላለና ዙሪያ ምላሹን በዛፍ የተሞላ ስለነበረ አንዳንድ ከሌላ አካባቢ የሚመጡ እንግዶች ቤተ ክርስቲያን እየመሰላቸው ይሳለሙት ነበር አሉ፡፡

ወይዘሮዋ ወደ ቤተክርስቲያን ሲሄዱና ሲመለሱ፣ ወደ እርሻቸው ሲሄዱና ሲመለሱ የሚያይ አንዳንዱ ግንባሩ መሬት አስነክቶ፣ አንዳንዱ ደግሞ ከወገቡ ለጥ ብሎ እጅ ይነሳቸዋል፡፡ ሲያልፉ ሲያገድሙ ‹‹እልልል!›› የሚሉ እጃቸውን እያዩ የሚኖሩ ሴቶችም አሉ፡፡ ታዲያ ቅድስት ለመሆን እርሳቸውስ ቢሆን ምን ጎደላቸው? ከቤታቸው የማይጠፋው ደብተራ ምትኩ ስለቅድስናቸው፣ ስለ ብጽዕናቸው፣ ስለውበታቸው ተቀኝቶላቸዋል፡፡ እርሱ ቅኝት በሚቀኝበት ድግሥ የሚገኙ ሊቃውንት ‹‹ይበል! ድንቅ ነው! ወይ ጉድ አንተኮ እንዲያው!›› እያሉ አሞግሰዋቸዋል፡፡ ከቁመናቸው ግዝፈትቅላታቸው፣ ከቅላታቸው የጸጉራቸው መርዘም፣ ከጸጉራቸው መርዘም የግንባራቸው ጸዳል፣ በዚያ ላይ ደርባባነታቸው ተጨምሮ ‹‹አንዳንዱ የመልአክ ዝርያ አላቸው›› ብሎ እርስ በርስ ሲነጋገር፣ አንዳንዱ ደግሞ ‹‹ሰይጣንምኮ ቆንጆ ነው ይባላል›› ብሎ ወደዚያ ያዛምዳቸዋል፡፡ ይህ እንግዲህ ከርስቱ ያፈናቀሉት፣ ወይም ከፍተኛ ግብር የጣሉበት የተማረረ ገባር ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ወ/ሮ ወርቅ ያንጥፉ በስማቸው ታቦት ቢሠራላቸው ባልከፋቸው! እንዲያውምኮ ‹‹እሜቴ ወርቅ ያንጥፉ›› በማለት ፈንታ ‹‹እሜቴ ታቦቷ›› የሚሏቸውም ነበሩ፡፡

አዎን፣ ስማቸው ‹‹ወርቅ ያንጥፉ›› ስለሆነ ብቻ አይደለም፡፡ በነበራቸው ማኅበራዊ ልዕልና መተያያቸው ወርቅ ነው፡፡ እና ወርቅ በወርቅ ናቸው፡፡ ንግሥቶችን ወይም ንግሥተ ነገሥታትን ሲጎበኙ ‹‹አሁን እርሷ ከማን በልጣ ነው ለንግሥትነት የተመረጠችው›› እያሉ  እያጉተመተሙ ከቤታቸው ወርቅ ካባ ለብሰው፣ የወርቅ ጫማ ተጫምተው፣ በባለወርቅ ርካብ፣ ባለወርቅ ልጓም፣ ባለ ወርቅ መርገፍ በተሸለመ ሰጋር በቅሎ በወርቅ ኮርቻ ተቀምጠው በትንሿ የወርቅ ሙዳያቸው መቶም ሁለት መቶም መሐለቅ የሚመዝን ወርቅ ይዘው ነው ይባላል፡፡ ‹‹ዕድሌ ነው እንጂ እኔ ሰው አላማ፣ የአህያ ልጅ በቅሎ ወርቅ ተሸልማ›› እየተባለ ቆዛሚ እንጉርጉሮ የተንጎረጎረው ለወይዘሮ ወርቅ ያንጥፉ በቅሎ እንደሆነ የሚናገሩ አይጠፉም፡፡

እንዲያው አሉባልታ እንዳይሆን እንጂ በድብቅም ቢሆን ‹‹ያልቀመሳቸው ንጉሥ የለም›› ተብለው ይታማሉ፡፡ ሐሜቱን እንኳን ‹‹ሰላም ለዓይንች፣ ሰላም ለጥርስች፣ ሰለም ለጉንጭች፣ ሰላም ለከናፍርች፣ ሰላም ለወርቅ አሎሎ ጡትች፣ ሰላም ለእምብርትች፣ እያለ እስከ እግር ጥፍራቸው የሚወርደው ደብተራ ምትኩም ይታማል አሉ፡፡ ይህ ሐሜት የመጣው ከደብተራ ምትኩ ነው ይባላል፡፡ እርሳቸው ከሚኖሩበት የሁለትና የሦስት ቀን መንገድ ተጉዞ ከሚገኝ መንደር እንደሚባለው ከሆነ በዚያ ነገር የተነሳ ‹‹ነብር ናት፣ ኧረ ነብር ሳትሻል አትቀርም›› ይባልላቸዋል፡፡ ይህን ስም በልቡ ያሰበ ግን ደብተራ ምትኩ ስለሆነ ከሱ ሌላ ሊያወጣላቸው የሚችል አይኖርም፡፡ ቢኖርም አይታወቅም፡፡

ወ/ሮ ወርቅ ያንጥፉ ቤታቸው ከዕለት ጉርስና ካመት ልብስ በስተቀር በማይከፍሉት አገልጋይ የተሞላ ነው፡፡ እህል የሚፈጩት፣ ጠጅና ጠላ የሚጠምቁት፣ አረቂ የሚያወጡት፣ የሚጋግሩት፣ የሚያርሱት የማገዶ እንጨት አምጥተው የሚፈልጡት፣ የጦር መሣሪያ የሚያነግቡት ሲቆጠሩ በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ያን ሁሉ አገልጋይ ተጠሪነቱ ብቻ ሳይሆንይወቱ ለራሳቸው፣ ለወ/ሮ ወርቅ ያንጥፉ፣ ስለሆነ እንደፈለጉ ማድረግ ይችላሉ፡፡ የግላቸው የሆነ እስር ቤት ሳይቀር እቤታቸው አለ፡፡ ከፈለጉም ከእነዚያ ‹‹ማንዘራሾች›› መካከል ‹‹የጠገበውን›› መግደልና እዚያው ግቢያቸው መቅበር ይችላሉ፡፡ ወይም መገረፍ ካለበት አንዱን ጎረደማን አዘው ሊያስገርፉ ይችላሉ፡፡ ጎረደማኑንም ቢሆን በሌላ ጎረደማን ማስወገር ይችላሉ፡፡ የወ/ሮ ወርቅ አንጥፉ የመጨረሻ ቅጣት፣ ለወጣት ሴትም  ሆነ ለአሮጊት ብሽሽት አጠገብ ገብቶ መመዝለግ ነው፡፡ መቆንጠጥ ነው፡፡ የእሜቴ ምዝለጋና ቁንጥጫ ባሳማሚነቱ የታወቀ ነው፡፡ እርሳቸው እያዩ ከወንድ ጋር የምትዳራ ከተገኘች ለዚህ ያነሳሳት አካሏን በሚጥሚጣ ማቃጠል ነው፡፡ ይህ ታዲያ ‹‹የምሷን አገኘች›› የሚያስብል ተራ ቅጣት ነው ለወ/ሮ ወርቅ ያንጥፉና ለአገልጋዮቻቸው፡፡

በወ/ሮ ወርቅ ይንጥፉ ቤት የሚገኙ አገልጋዮች ፍቅረኛ፣ ጓደኛ፣ ወዳጅ፣ ወንድም፣ እህት፣ አባት፣ እናት የሚባል አያውቁም፡፡ እርሳቸው ካዘዙ አንዱ በሌላው ላይ አስከፊ የቅጣት ዕርምጃ ሊወስድ ይችላል፡፡ አድርግ ያሉትን ሁሉ በጸጋ ያደርጋል፡፡ ማድረግ ብቻ አይደለም ትክክል ነው ብለው ያምናል፡፡ ለምሳሌ የገብሬ ምስጢረኛ  የሆነው ምርኩዜ፣ ‹‹ይህንን ቅንዳሻም ምንትስ አቅምስልኝማ›› ካሉ አጅና አግሩን አሥሮ በፍልጥ ሊደበድበው ወይም እንደ ሁኔታው በጅራፍ፣ ወይም በከዘራ ውኃ እስኪል ሊገርፈው ይችላል፡፡ እሜቴም ብትሆን ፍቅረኛዋ ተጋድሞ ሲገረፍ ጎበዝ ከሆነች ምራቋን ውጣ ዝም፣ የማትችል ከሆነ ‹‹እልል›› ልትል ትችላለች፡፡ ማታ አብረው ሲያድሩ ግን ያባበጠ ገላውን በስብም፣ በቅቤም እያሸች ልታጠፋለት መሞከሯ አይቀርም፡፡ ቢሆንም ‹‹እረፍ ብዬ አልመርኩህም›› ብላ ለእሜቴ ያላትን ወገንተኝነትና ታማኝነት ልትገልጽ ትችላለች፡፡ ባትገልጥና መጥፎ፣ አረመኔ መሆናቸውን ጠቅሳ ብታማቸው ገብሬ ራሱ ይነግራቸውና ዋጋዋን ታገኛለች፡፡

በወ/ሮ ወርቅ ያንጥፉ ቤት እርስ በርስ መተማመን የሚባል ነገር የለም፡፡ ጓደኛ ጓደኛውን አያምንም፡፡ ፍቅረኛ ፍቅረኛውን አያምንም፣ የበላይ የበታቹን አያምንም፡፡ ኧረ ዘመድ ዘመዱን አያምንም፡፡ በጭራሽ መተማመን የሚባል ነገር የለም፡፡ ስለሆነም የእያንዳንዱ ሰው ነፍስ ለወ/ሮ ወርቅ ያንጥፉ ያደረች ናት፡፡ ‹‹የፎገራ ሜዳ የበየዳ ላም ነሽ፤ አጥፊየም አልሚየም ሕይወቴም አንች ነሽ፡፡›› ተብሎ የተዘፈነላቸው ናቸውኮ፡፡  ኦዎን ፎገራ ሰፊ ነው፡፡ ለምለም ነው፡፡ ብዙ አዝመራ ይታፈስበታል፡፡ የፎገራንስ ምርት ማን ችሎ ይሰበስበዋል? የበየዳ ላምስ ብትሆን ብዙ ወተት በመስጠት ትታወቃለች፡፡ ጡቶቿ አይነጥፉም፡፡ ቀኑን ሙሉ እንዳጋቱ ይውሉና ማታ ጥጃዎቻቸው ይጎድሉላቸዋል፡፡ ለመሆኑ ቢፈለግስ ማን የበየዳን ጉራንጉርና ውጣ ውረድ አልፎ  ያልባል? ዘፈኑም የእረኛ ነው፡፡ ተጠቃሚውም እረኛ ነው፡፡ እረኛ ደግሞ ስንቱን ይጠባል?

ወ/ሮ ወርቅ ያንጥፉን በሚመለከት ምሁራን የሚባሉ የእምነት አባቶች በድሆችና ከፍ ብሎም በመካከለኛው መደብ ላይ እንደሚያደርጉት ‹‹ተው እንጂ፣ ተይ እንጂ፣ ይተው እንጂ፣ በሰማይ ቤትኮ ቅጣት አለ፡፡ ለንጉሠ ነገሥቱም፣ ለባንዲራውም ጥሩ አይደለም›› ብለው አይቆጡም፡፡ ‹‹ኧረ ሰው ጉድ አለ እሜቴ፣ ኧረ ለርሰዎም ቢሆን በምድርም በሰማይም ጥሩ አይደለም! ወዘተ›› ብለው አይመክሩም፡፡ ዕውቀታቸውን ብቻ ሳይሆንልጣናቸውን ለሆዳቸውና ለህልውናቸው አሳልፈው ሸጠዋልና ለብቻ እንኳን ሲሆኑ ስለእርሳቸው ጥፋት አይነጋገሩም፡፡ የሚገስጹበት ስልት አያወጡም፡፡ እንዲያውም ዋና ዋናዎቹ ምሁራን እሜቴ ቢያጠፉም ያጠፉ አይመስላቸውም፡፡ እንዲያውም የሚፈጽሙትና የሚያስፈጽሙት ግፍ ቅድስና ሆኖ ሊታያቸው ይችላል፡፡ ግንሳ ምን ያድርጉ? እነርሱምኮ ነፍስ አላቸው፡፡ ከሰማይ ወርዶም ሆነ ከምድር ወጥቶ የሚያድናቸው እስከሌለ ድረስ አድርባይ ከመሆን የተለየ አማራጭ የላቸውም፡፡ ‹‹ኧኸኸኸ እያዩ ነው ማደር፣ ኋላ ከመቸገር›› ይባል የለ? አዎን ኋላ ከመቸገር፣ እያዩ ነው ማደር፡፡ ጊዜውን መሻገር፡፡

ለነገሩማ ጠዋት ከእንቅልፋቸው ሲነሱና ማታ ሲተኙ እንዲሁም ቤተክሲያን ሲሄዱና ‹‹እየጸለዩ ነው›› እንዲባልላቸው ሲፈልጉ ትርጉሟ ሳትገባቸው የሚያነቧት፣ ከማንበብም አልፈው የሸመደዷት የጸሎት መጽሐፍ አለቻቸው፡፡ ያችን መጽሐፍ፣ በጣም ከመሸመደዳቸው ብዛት አንድም ድንገት የጥዋፍ መብራት ቢጠፋ ወይም ሰው ብርሃን ቢከልላቸው፣ በደንብ አቋርጠው የማያነጋግሩት ሰው ሲመጣ ገጾችን እየገለጹ በቃላት ሊያንበለብሏት ይችላሉ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፣ እንደ መምሬ ተክሌ እርሳቸውምረፍተ ነገር፣ ወይም አንቀጽ ሊጠቅሱ ይችላሉ፡፡ ትርጉሙ ምን እንደሆነ ራሱ ይወቅ፡፡ ደግሞስ ለማወቅ ምን አስጨነቃቸው? ከማሃይማን ፊት ሁልጊዜ ሊቅና ሊቀ ሊቃውንት ናቸው፡፡ እንዲያውም ከነመምሬ እንትና ይበልጣሉ፡፡ ከምሁራን ፊትም ብዙ ጊዜ በአቦ ሰጡኝ ትክክል  ይሆናሉ፡፡ ባይሆኑም እንዳልሆኑ ሳይሆን እንደሆኑ ይቆጠርላቸዋል፡፡ 

‹‹ኧረ ባዛኝቱ!›› ሲሉም ለእርሳቸው ብቻ የምታዝን ይመስላቸዋል እንጂ በሥራቸው የምትቆጣ፣ ለልጇ የምትናገርባቸው አይመስላቸውም፡፡ ኧረ በትልቁ ፈጣሪንም የእርሳቸው ቲፎዞ አድርገው የሚመለከቱበት ጊዜ አለ፡፡ ይኸው ለእርሱ ስል አርዳለሁ፣ እጋግራለሁ፣ እጠምቃለሁ፣ አበላለሁ፣ አጠጣለሁ፣ አለብሳለሁ፣ እመጸውታለሁ፡፡ ከዚህ የበለጠ ከእኔ ምን ይፈልጋል?›› የሚሉበት ጊዜ አለ፡፡ ‹‹እንዳች ያለ ታማኝና አማኝ የትም ይትም አይገኝም›› ያላቸው የሚመስላቸው ጊዜም አለ፡፡

አየ እሜቴ ወርቅ ያንጥፉ! በእምነቱ ብቻ ሳይሆን ጎበዝ ገበሬን ሲያዩ የጎበዝ ጎበዝ ገበሬ አድርገው የሚያቀርቡበት ጊዜ አለ፡፡ ‹‹አየህ ሲታረስ እንዳለንጋ እጥፍ ዘርጋ፣ እንደዛፍ ወዲህ ዘመም ወዲያ ዘመም እያሉ ነው እንጂ እንጨት እንደዋጡ ተገትሮ በማፏጨትና በሬን በመግረፍ ብቻ አይደለም፡፡ በግራም በቀኝም ስታይ፣ ወደፊትም ወደኋላም ስትመለከትደንብ የታረሰውንና ያልታረሰውን ታያለህ፡፡ ሞፈርህን ጠበቅ፣ ጫን ስትል የታቹ አፈር ይወጣል›› ብለው መካሪ ይሆናሉ፡፡ ለአረሚውም፣ ለአጫጁም፣ ለከማሪውም ለወቂውም የሚሆን ምክር አያጡም፡፡ በዚህም የተነሳ እሜቴ ወርቅ ያንጥፉ ‹‹ምሁርም ብትሆኚ፣ ገበሬም ብትሆኚ ሁሉም ያምርብሻል፣ እንዳንች ያለ ፍጡር ከወዴት ይገኛል›› እየተባለ ይዘፈንላቸዋል፡፡   

ሴትነትማ ጭራሹን ‹‹የሴትነት አምላክ እጇን ታጥባ የሠራችኝ ናት›› ብለውም ይናገራሉ፡፡ ያን ቢሉ በግዛታቸው ማን ይቆጣጠራቸዋል፡፡ ደግሞ ለማለት! በመሠረቱ፣ ያች የሴትነት አምላክ ትኑር አትኑር ጉዳያቸው አይደለም፡፡ ‹‹ኧረ የለም›› ብሎ የሚያሳምናቸው ከሌለ በስተቀር ‹‹እርሷ ራሷ የሴትነት አምላክ ሠርታኛለች›› ብለው ቢናገሩ ማናባቱ ማንደፍሮ ‹‹የሴት አምላክ አለች እንዴ?›› ብሎ ይጠይቃቸዋል፡፡ የጠጅ አጣጣል፣ የጠላ አጠማመቅ የአረቄ አወጣጥ፣ የጥጥ አነዳደፍና አፈታለል፣ የእንጀራ አገጋገርና የወጥ አሠራርማ ማን ችሏቸው፡፡ እኔ ነኝ ያለች ባለሙያ ‹‹እኔ ምናውቃለሁ፣ እርሰዎ ይውቃሉ እንጂ›› ካላለች ሥራዋ ጥንብ እርኩሱ ነው የሚወጣው፡፡ የሚጣፍጠው ይመርባታል፡፡ የጠራው ይደፈርስባታል፡፡ መልካም መዓዛው ይቀረናባታል፡፡ በወ/ሮ ወር ቅያንጥፉ ካልወደዱ፡፡

ወ/ሮ ወርቅ ያንጥፉ ገበሬና የቤት ባለሙያ ብቻ ሳይሆኑ ስለብረት አቅልጦ ማረሻ፣ መጥረቢያ ፋስ፣ ቆንጨራ መሥራት ያላቸው ዕወቀት ባህር እንደሆነ ይገምታሉ፡፡ የሚያህላቸው የለም እየተባለም ይተረክላቸዋል፡፡ ከየት መጥቶ፡፡ ለምሳሌ አንድ ማረሻ ቢሰበርባቸው ደንበኛቸው ራሱ ወይም ሌላ ይሥራውም አይሥራውም ማወቅ አይጠበቅባቸውም፡፡ ብቻ በአካባቢያቸው የሚኖር ብረት ሠሪ ያስጠሩና ‹‹አየኸው የሠራኸው ማረሻ!›› ብለው የመምታት ያህል እፊቱ ይወረውሩበታል፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ይቅር በሉኝ›› ከማለት በስተቀር ሌላ አማራጭ አይኖርም፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ‹‹እሜቴ ይህ ከዓረብ ብረት የተሠራ ማረሻ ነው፡፡ ቢያንስ ሃምሳና ስልሳ ዓመት አገልግሎ ሊሆን ይችላል›› ብሎ የተናገረው ባለሙያ እንዳይሆን ሆኖ ከተደበደበ በኋላ በምሕረታቸው ወደ ቤቱ ተመልሷል፡፡

ለወ/ሮ ወርቅ ያንጥፉ ልብስ የሚሸምን ሸማኔ፣ የቀሚሳቸው ጥልፍ የሚጠልፍና ጫማ የሚሠራ ባለሙያ አስቀድሞ የቁስም የአፍም ጉቦ በመስጠት በአካባቢው ሰው እንዲደነቅ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ‹‹አቤት እሜቴ፣ የለበሱት ቀሚስ፣ የተቀነቱት መቀነት፣ የተጫሙት ጫማ በመልአክ እንጂ በሰው የተሠራ አይመስልም፡፡ እከሌ ከባህር አስመጥቶ እኔ ሠርቸዋለሁ ብሎ ብዙ ገንዘብ ለመውሰድ ካልሆነ እርሱ ሊሠራው አይችልም›› ብለው ማዳነቅ አለባቸው፡፡ ይህን ጊዜ ከፈለጉ ዝም ለማለት፣ ከፈለጉ ለማድነቅ፣ ከፈለጉ ደግሞ ለማጣጣል ይችላሉ፡፡ ወይም ትልቅነታቸው እንዳይቀነስባቸው ‹‹ምን ይደረግ የናቴ አጥንት እንዳይወቅሰኝ ብዬ ይኸው በእርሷ ሸማኔና ጠላፊ አሠራለሁ፡፡ አሁን ከባህር ማምጣት ተስኖኝ ወይም በንግሥቲቱ ሸማኔ ማሸመን ሳልችል ቀርቼ ነው?  ግን የናቴ ታዛዥ አሽከሯ ስለሆነ፣ አደራም ስላለችኝ አደራዋን እንዳልበላ ያመጣልኝና የጠለፈልኝን እለብሳለሁ›› ብለው ሊያልፉት ይችላሉ፡፡

አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ‹‹ሰውዬው ከቤተ እስራኤሎች በኩል በመሆኑ ልብሱን ብቻ አይደለም ሸምኖና ጠልፎ የሚያመጣላቸው፡፡ ከልብሱና ከጥልፉ ጋር የሚጨምረው ሌላ ድግምት አለበት›› ብለው ይናገራሉ፡፡ ቤተ እስራኤሎች ጥበበኞች ስለሆኑ በመጀመሪያ ድርና ፈትሉ ላይ ይደግሙበታል፡፡ ያኔ በድርና በማጉ መንፈስ ያድርና ሥራው ይሰልጣል፡፡ ቀጥሎ ሲሸምነው ይደግምበትና ልዩ ይሆናል፡፡ በመጨረሻም ሲጠልፈው ዘልዓለማዊነትን ያገኛል፡፡ እስቲ ከእኛ መካከል እሜቴ ልብስ አልቆባቸው አይቶ የሚያውቅ አለ?›› እያሉ ይንሾካሶካሉ፡፡  አንዳንድ ምስጢር እናውቃለን የሚሉ ደግሞ ‹‹ሌሊት በጠፍ ጨረቃ ላሎ የተባለውን ጅኒ ተሳፍሮ ይመጣና ማንም ሳያየው በመስኮት ይገባል፡፡ ከዚያም እሜቴን ሰውሮ በመዝጊያው ቀዳዳ ይዟቸው ይወጣና ዓለምን ሲያዞራቸው ያድራል፤›› ይላሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ ተናጋሪ መካከል አየሁ ያለ ቢኖር አንድ ሰው ሲሆን እርሱም ‹‹ሌሊት ደጃቸው ተኝቼ ሳለ እግሬን ረገጠኝ፡፡ ብንን ብል ከወገባቸው በታች የማይታዩ፣ ከወገባቸው በላይ ሸማኔውና እሜቴ ናቸው፡፡›› ብሎ ለራሱ የተናገረ ሰው ብቻ ነው፡፡

ለነገሩ እንኳን ወ/ሮ ወርቅ ያንጥፉም አዋቂ በጓዳ በር በኩል ደብቀው ማስገባት ይወዳሉ፡፡ ታዲያ የሚያስገቡት እያንዳንዱ አዋቂ የራሱ የሆነ የሥራ ድርሻ አለው፡፡ አንዳንዱ የቡና ደካ አንባቢ ነው፡፡ አንዳንዱ ኮከብ ቆጣሪ ነው፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ከፊት ለፊቱ ሞራ ዘርግቶ የሚያነብ ነው፡፡ ሌላም አለ መጣፍ ገላጭ፡፡ እንደሚባለው ከሆነ በባህር የሚኖሩ አዋቂዎች እየመጡ አሸንክታብ የሚጽፉላቸው አሉ፡፡ አሸንክታቡ በግዕዝ፣ በእብራይስጥ፣ በዓረብኛ፣ በሕንድኛ፣ በአርማንኛ የተጻፈ ስለሆነ የሚያስመጡት አዋቂ ከብዙ አገሮች መሆኑን ያመለክታል፡፡ መጠራጠር ጥሩ ነውና በእንግሊዘኛ የተጻፈም አሸን ክታብም ይኖራቸው ይሆናል፡፡ ያንን ሁሉ አሸንክታብ በጅማት በተሠራ ሁለት ክንድ ገመድ ይሰኩና ከቀኝ ትከሻቸው፣ በአንገታቸው በኩል፣ ወደ ግራ ጎናቸው ይወርዳል፡፡ በአካባቢው አሳሳቢ ሁኔታ ከተከሰተ እናታቸው ያወረሷቸውን አሸንክታብ ሊጨምሩበት ይችላሉ፡፡ አይታይም እንጂ ቢታይ ኖሮ ዝናር የታጠቁ ይመስላሉ፡፡  ከእነዚህ ሁሉ ዋናው አዋቂ ግን አንድ ሁለት ክንድ ከስንዝር ርዝመት ከእርሳስ ትንሽ ወፈር የምትል አርጩሜ እየለካ ‹‹እንዲህ ይሆናል፡፡ እንዲህ ይፈጠራል›› እያለ የሚነግራቸው አዋቂ ነው፡፡ ይህ አዋቂ የንጉሠ ነገሥቱ ጭምር ስለሆነ በዓመት አንድ ጊዜ ወይም ሁለት ጊዜ ቢሆን ነው፡፡ እርሱ የሚናገራት መሬት ጠብ አትልም ይባላል፡፡ በእርግጥም ከቤተ መንግሥቱ ከሚያገኘው መረጃ እያመጣ ‹‹እንዲህ ይሆናል፣ እንዲህ ይፈጸማል›› ስለሚላቸው ለዚህ ሁሉ ባዕድ ለሆኑት ወ/ሮ ወርቅ ያንጥፉ እውነት ነው፡፡ እርሱ የነገራቸውን ለሚያምኗቸው ሰዎች በተራቸው በህልሜ አየሁ ብለው ስለሚናገሩ ሲፈጸም ‹‹አላልኩም፣ ይኸው ሆነ›› ይላሉ፡፡

ታዲያ ዝም ተብሎ የሚጎተት አዋቂ የለም፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ አዋቂ የራሱ የሆነ ምስ አለው፡፡ አንዳንዱ የሚጠይቀው ምስ የዶሮ ጫጩት ደም፣ ወይም የኮከበ ድርብ ነጭ፣ ጥቁር፣ ቀይ፣ ገብስማ፣ ጠጠርማ ዶሮ ደም፣ ወይም የአራት እግር አሻል ግንባረ ቦቃ በግ፣ ወይም የጅብማ በግ ደም፣ እንዲያ እያለ የሰው ደም ሊጠይቅ  ይችላል፡፡ ወ/ሮ ወርቅ ያንጥፉ ምንም ይጠየቁ ሥራቸው ለጤንነታቸው፣ ለክብራቸው፣ ለመንፈሳዊ ኃይላቸው፣ ለተፈሪነታቸው፣ ለግርማ ሞገሳቸው፣ ለሀብታቸው፣  የተጠየቁትን ማቅረብና ደሙን አብረው መቋደስ ነው፡፡  እናታቸው ‹‹አዋቂ ያልጠየቀና በአዋቂ ያልተመራ፣ ስሙ የማይጣፍጥ ዕጣውም መራራ›› የሚል አስተሳሰብ  ነበራቸው፡፡

ይህስ ባይሆን? መተቱ ባይዝ፣ አዋቂዎቹ እንዳሉት ሆኖ ባይገኝስ? ለዚህም መፍትሔ አላቸው፡፡ ሲጀመር  በአባትና በእናታቸው ተወልደው ያደጉና እንደ ዕቃ በውርስ የተላለፉ ጎረደማኖች፣ የጎረደማን ልጆችና የልጅ ልጆች አሉ፡፡ በቤታቸውም የተወለዱትም ቢሆን በልጅነታቸው አዋቂዎች ላይ በማፍጠጥ፣ ወይም በማሳበቅ፣ በወጣትነታቸው ነገር ፈልገው አካባቢውን የሚያምሱ፣ ካደጉ በኋላም አዋቂዎቹ የማይሰጧቸውን ኃይል፣ ተፈሪነት፣ ግርማ ሞገስ ያጎናጽፏቸዋል፡፡ ሀብታቸውንና ንብረታቸውን ቢፈልጉ ሶሎግ ውሻ፣ ሲፈልጉ ነብር፣ ሲፈልጉ፣ ግሥላ፣ ሲፈልጉ አንበሳ፣ ሲፈልጉ ተኩላ ሆነው ይጠብቁላቸዋል፡፡ ዕድሜ ለእነሱ የወ/ሮ ወርቅ ያንጥፉ ስም ዝም ተብሎ እንደ ተራ ነገር አይነሳም፡፡ በዚህ ረገድ፣ እንኳንስ ለራሳቸው ለሌሎች ባለውለታዎቻቸውም ይተርፋሉ፡፡

ከዚህ ሰፋ ያለ ሲሆንና ሚስጥር ሲኖረው ሰው ገድለው፣ ቋንጃ ቆርጠው፣ ቤት አቃጥለው የሸፈቱ ታዋቂ ሰዎችን መጠቀም ይችላሉ፡፡ ከእርሳቸው ጋር የተቀያየመ በማግሥቱ ሀብት ንብረቱ ብቻ ሳይሆን ሕይወቱም በእነዚህ ሰዎች ሊጠፋ ይችላል፡፡ ከአጥፊዎቹና ከአስጠፊዋ ወ/ሮ ወርቅ ያንጥፉ በስተቀር ማን እንዳጠፋው እንኳን ከቶ ማወቅ አይቻልም፡፡ ምናልባት፣ ምናልባት ፍንጭ ከተሰማ አጥፊው ራሱ ይጠፋል፡፡ በአጥፊው ላይ ትንሽ ጥርጣሬ ካላቸው እርሱ ራሱ በሌላ አጥፊ ይጠፋል፡፡ እንዲያ እያለ ይቀጥላል፡፡ ታዲያ ለዚህ ሁሉ የሚያስፈልጋቸው ትንሽ ለጥይት መግዣ፣ የዓመት ልብስ፣ ወደ አካባቢ ሲመጡ መደበቂያ ቦታ መስጠት፣ ጥፋት ሲያጠፉ ‹‹እነሱ አያጠፉም፣ አጥፊዎቹ ሌሎች ናቸው›› ብለው በነገሩ ባልዋሉበት ሰዎች ላይ ማላከክ ነው፡፡  ከተመቻቸውም ከመንግሥት ምሕረት ጠይቀው፣ ከጠላቶቻቸው ጋር አስታርቀው እንደ ለማዳ እንስሳ በሄዱበት የሚከተሏቸው አንጋቾች ማድረግ ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ዘዴያቸው ብዙ ጊዜ ተጠቅመዋል፡፡ ተውሎ የሚታደርበት ረዥም ጉዞ ሲጓዙ ከቦታ ቦታ እየተቀባበሉ ይሸኟቸዋል፡፡ አዋቂዎች የማይሰጧቸውን ኃይል፣ ተፈሪነት፣ ግርማ ሞገስ ይሰጧቸዋል፡፡ ያጎናጽፏቸዋል፡፡

ታዲያ ምን ያደርጋል? መሳሳት አይቀርምና ከዕለታት አንድ ቀን አይሳሳቱት ስህተት ተሳሳቱ፡፡ በዚያ ዕለት ንጉሠ ነገሥቱ በዚያ አድርገው ሊያልፉ መፈለጋቸውን ባለ አርጩሜው አዋቂያቸው ስለነገራቸው ከአያት ቅድመ አያት በውርስ ሲተላለፉ የመጡ ጋኖች፣ ርኮቶች፣ ደንበኛዎች ሁሉ ጠጅ እንዲጣልባቸው፣ ጠላ እንዲጠመቅባቸው፣ ወይን እንዲጨመቅባቸው፣ ቡኮ እንዲቦካባቸው ከዕቃ ቤት ወጡ፡፡ ውኃ ከወንዝ በአህያ እየመጣ በእንጨት በርሚል ውስጥ ሲሞላ ተዋለ፡፡ ከዚያ ሁሉ ዕቃ አንዱ ጋን እንደ ሌሎች ጋኖች ከሸክላ የተሠራ ቢሆንም ከሰባት ትውልድ በፊት ወደ አገራችን መጥተው የነበሩ ፈረንጆች የሠሩት ነበር፡፡ ጋኑ በእጅ ጭብጥ ኳኳ ሲደረግ እንደ ብረት ይጮህ ነበር፡፡ ውኃ ቢያስቀምጡበት ከሰማየ ሰማያት የወረደ አስመስሎ ያቀዘቅዘዋል፡፡ ‹‹ከዚያ ጋን የሚጠጣ ውኃ የልብ መድኃኒት ነው›› ተብሎ ይነገርለት ነበር፡፡ በዚያ ጋን የሚጣል ጠጅ፣ የሚጨመቅ ወይን፣ የሚጠመቅ ጠላ ‹‹ማየ ሕይወት ነው›› ይባልለት ነበር፡፡ መልኩም ከሌሎች የበለጠ ውብ ነበር፡፡ ‹‹የጋኖች ሁሉ ንጉሥ›› ቢባል ያንሰው እንደሆን እንጂ አይበዛበትም፡፡ ታዲያ እርሳቸውም ያንን ጋን ለልጅ ልጅ ለማስተላለፍ ምኞቱ ነበራቸው፡፡ ቢሆንም በዕለቱ አንዲት በዕድሜ የገፉ አገልጋይ ጋኑን እርሳቸው እንደሚፈልጉት አድርገው ለማጠብ ሳይችሉ መቅረታቸውን አይተው ‹‹ተይ አንች ቅንዳሻም፡፡ ተራ ጋን መሰለሽ እንዴ?›› በማለት እርሳቸው ራሳቸው እስከ ክንዳቸው በሰፊው የወረደው እጅጌያቸውን ሰብስበው ማጠብ ጀመሩ፡፡ ወፍራምና ረዥም ክንዳቸውን አስገብተው በግራዋ ቅርንጫፍ ማጠብ እንደ ጀመሩ ያ ጥንታዊ ጋን ዓይን እንደበላው ሁሉ ለሁለት ክፍል አለ፡፡

ምን ይሁኑ! አሮጊቷ አገልጋይ ናቸው እንዳይሉ ራሳቸው ከውስጥ አጥባለሁ ብለው ሲፈገፍጉ መትተውታል፣ ራሳቸውን እንዳይወቅሱ ወቀሳ አልለመዱም፡፡ እርር ድብን ብለው በነበሩበት ጊዜ አጠገባቸው የነበሩትንና ራሳቸው የሰበሩት ያህል ፈርተው እየተንቀጠቀጡ የነበሩትን አገልጋይ አዩዋቸው፡፡ ‹‹ወግጅልኝ ቡዳ! እስካሁን በዓይንሽ ቀርጥፈሽው ይሆናል›› ብለው ተቀመጡ፡፡ ያኔ እሜቴ ወርቅ ያንጥፉን ማነጋገርም፣ ማጽናናትም፣ ማስተዛዘንም አይቻልም፡፡ ለዘመናት ተክብሮ የኖረውን ጋንም መጠገን አይቻልም፡፡ ብቻ ግን ለራሳቸው በሚመስል ቃል ‹‹ወየው ጉድ! እኔንስ ማን ይቆንጥጠኝ? ከቶ ማን ይቆንጥጠኝ?›› አሉ፡፡ አዎን እርሳቸው እንደሚያደርጉት በጭኖቻቸው መካከል ገብቶ መመዝለግ እንኳን አይመልሰውም፡፡

ለማንኛውም ተረታቸው ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ መጥቶ ወደ እኛ ደርሷል፡፡ እኛም እነሆ እንደዚህ አስተላለፈናል፡፡ የደራሲው መብት በሕግ የተጠበቀ  ነው፡፡ ማባዛትም ሆነ በመጽሐፍ መልክ ማሳተም ፈጽሞ ክልክል ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...