Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገር‹‹የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን…››

‹‹የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን…››

ቀን:

በአሰፋ አደፍርስ                

ሰው በተፈጥሮው ከእንስሳ የሚለየው ክብሩን፣ ወገኑንና አገሩን በማክበር ነው። እንዲያው ለሰው ሁሉንም ክብር እንስጥ እያልን የእንስሳትን የአስተሳሰብ፣ ፍቅርና ችሎታቸውን እየጣልንባቸው አቤት የሚሉበት የመናገር አንደበት የላቸውም ብለን እንጂ በፍቅር፣ የኖሩበትን ቦታ በማስታወስና ጌቶቻቸውን በመውደድ ከእንሰሳት የሚበልጥ ያለ አይመስለኝም። ለምሳሌ ውሻ ከነበረበት የደሃ ጎጆ ወደ ባለፀጋ ቤት ቢሄድ ያንን ቤት ሳይሆን፣ የኖረባትን የደሃ ጎጆ ፈልጎ ይመለሳል እንጂ የሀብታም ቤት ነው ብሎ አዲሱን መርጦ እዚያ የሙጥኝ ብሎ አይቀርም። በሬ፣ በቅሎና ፈረስም እንዲሁ ሲሆኑ አህያ ግን በደረሰችበት መጋደሟ የታወቀ ነው። ሆድ አደሮችም እንዲሁ ናቸው። አገርና ወገን ለእነርሱ ከመጤፍ ነውና፡፡

ይህንን የምልበት ምክንያት ሰዎች በተፈጥሮአቸው ለወገን፣ ለአገርና ለቤተሰብ እጅግ የሚያስቡና አገርን የሚወዱ ናቸው ለማለት ነው። ለምሳሌ አንድ ደሃ እንግሊዛዊ ምንም ጓደኛና ወዳጅ ቢሆን ከውጪ አገር ሰው ጋር የአገሩን ታላቅነት እንጂ ክፉውን አያወራም፣ ጓደኛውን ላለማስቀየም ለተጠየቀው ከመመልስ ይልቅ፣ እንግሊዛው በአገሩ የውስጥ ጉዳይ ብቻውን ከማንም ጋር ፈጽሞ አይነጋገርም (An Englishman never speak his country’s affair alone) ብሎ ታሪኩን ወደ ሌላ ይለውጣል እንጂ ምንም ቢያምነውና ጓደኛውም ቢሆን ስለአገሩ አያወራም። እኛ ግን የዋሆቹ እንኳን ተጠይቀን ሳንጠየቅም የጠላነውን የመንግሥት ወኪል የጎዳን እየመሰለን ሁሉንም እንዘከዝካለን።

- Advertisement -

ይኼውም የጥንቱ ኢትዮጵያዊ ሳይሆን የዛሬው ትውልድ ዘመን የተለመደ ሆኗል። ለካ መማር ባዶ ያደርግ ኑሯል። ይህንንም ያወቁ የጥንት አባቶችና እናቶች ልጆቻችን የዘመኑን ትምህርት ከተማሩ አገርን ይከዳሉ፣ ሃይማኖታቸውንም ይለውጣሉ ብለው ብዙ አስቸግረው ነበር፡፡ ግን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተምሮ አገርን ያሻሽላሉ እንጂ እንዴት አገርን ይጎዳሉ? ብለው ግማሹን በግድ ግማሹን በማባበል የትናንት ታላላቆቻችንና እኛን እንድንማር በር ከፍተው ጥሩ ሥራ የሠሩ መስሏቸው ነበር።    ለካስ እነኛ ያልተማሩ አባት እናቶቻችን የላቀ ዕውቀት ኑሯቸዋልና መጪውን ተገንዝበውት ነበር። አዎን ሃይማኖት ተለወጠ፣ አገር ሻጭ የሆኑ በጣት የሚቆጠሩም ተማሩ፣ አንድም ቀን እንደ እኩያ ለማያያቸው ዓረብ ግብፅም ሊሸጡን ተስማሙ፡፡ በግብፅ ብር ወገናቸውን መግደልም ተጀመረ፣ ንብረትም ይወድም ጀመር፣ ለዚህ መረጃ በተባለ የብዙሃን ልሳን ቴሌቪዥን ከምሽቱ አራት ሰዓት ጀምሮ ሐምሌ 12 ቀን 2012 ዓ.ም. በአንድ ዓረብ የተሰጠ መረጃ በኢትዮጵያዊ ኡስታዝ ጀማል በሽር በተባለ ሰው ተተርጉሞ የተላለፈውን ማየት ብቻ በቂ ይሆናል።

የሚገርም ነገር ግብፆች ለኢትዮጵያ ተንኮል ከማሰብ ተቆጥበው አያውቁም። በማስረጃነት፣ ኢትዮጵያን በበዓል ብዛት የድሮ የግብፅ ጳጳሳት አስረውን እነርሱም የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ሆነው እኛ ለሥራ እንዳንተጋና ሠርተን ውጤታማ እንዳንሆን ከ360 ቀናት ውስጥ ከሁለት መቶ ቀናት በላይ በሃይማኖት ስም  በዓል ነው እያሉ አስረውን ኖረን አሁንም እዚያው ላይ ነን፡፡ ቀጥለውም ግብጦ የተባለ ለአረቄ ማውጫ እንደ መልካም ነገር አምጥተው ለዚህ ለየዋህ ሕዝብ አንዴ ከወደደ ለማይጠራጠር ደግ ሕዝብ መልካም ነገር አስመስለው ሰጡት፡፡ ደጉ የኢትዮጵያዊ ሕዝብ ወዳጅ ካለ አይጠራጠርምና ያንን አስካሪ መርዝማውን ግብጦ ለጠጪነት የሚጋብዝ ጉድ አምጥተው እነሆ እስከ ዛሬ ሳንላቀቅ ተያይዘነዋል። ግብፅ ልታጠፋን ያልሞከረችውና ያልቆፈረችው ቀዳዳ የለም፣ አውቀንና ነቅተን ራሳችንን መጠበቅ የራሳችን እንጂ የማንም አይደለምና ሳናውቅ እንዳንጠፋ እንጠንቀቅ።

ዛሬ ዓረቦች በእኛ ስንፍና ለወጣቱ ሥራ መፍጠር አቅቶን የትም ሄጄ ሠርቼ ልኑር ብለው የሄዱትን የኢትዮጵያ ልጆች በዘመናዊ ባርነት በሚጠቀሙበትና ሲያመቻቸውም የሠራበትን-የሠራችበትን ነጥቀው አስቀርተው የሚያባርሩትን ዓረቦች ጋር በመመሳጠር የኢትዮጵያን ሕልውና ለመሸጥ ታችና ላይ የሚሉትን ከሃዲያን፣ መንግሥት ባለው የምርምራ ጥበብ ይዞ በማረፊያ ቤት ያቆያቸውን መልዕክተኞች አቶ ደብረ ጺዮን ይለቀቁ ሁሉም ተሰባስቦ ይደራደር ሲል፣ ለተገደሉትና ለጠፋው ንብረት እንደለመደው ዋጋ ያለመስጠቱን ነው የሚያሳየው። ለመሆኑ ከሌባና ነብሰ ገዳይ ጋር እንዴት ነው ቁጭ ተብሎ መወያየት የሚገባው? አወያዩስ ሰርቆና አሰርቆ ልምድ ካካበት ሽማግሌ መሆን አለበትና ታዲያ ለዚህ አስታራቂነት ደብረ ጺዮን ፈቃደኛ ይሆኑ? ይህ ልምድ የሚጠይቅ ጉዳይ ነውና ፈቃደኝነታቸውን በይፋ ቢገልፁ መልካም ሳይሆን አይቀርም።

በሌላ በኩል አገሪቱን ከእነርሱ በስተቀር የሚያስተዳድር የለም ማለታቸው ይሆን? ይህንንማ እኛ ዳር ተቀምጠን የበይ ተመልካች የነበርንና የምናውቀው ነውና ለእኛ ይተውት። አዎን! ለሺሕ ዓመታት የነበረን የክብር ሰንደቃችንን ለውጦ ወደፈለገው አድርጎት የሚሠራውን አሳጥቶት የኢትዮጵያ ጅምላ ፍርዱን ሰጥቶ፣ ራሱ የደብረ ጺዮን ጓዶች ራሳቸው በጠሩትና ባዘጋጁት የስብሰባ ጥሪ በቃችሁ ብሎ አሰናበታቸው፡፡ አሁንም አንድ ጥይት ሳንተኩስ አራት ኪሎ እንገባለን ብሎ ሕዝብን ከሕዝብ በማፈጀት የሚገባ መስሎት ተራወጠ፡፡ አሁንም ጀግኖች የኢትዮጵያ ልጆች እጅ ከፍንጅ ይዘው ለፍርድ እያቀረቡ ነው። ለመሆኑ ጭንቅላት ያለው ሰው የሠራውን መለስ ብሎ ማየት አይችልምን? ይህ የሚገርም ነገር ነው።

ወገኖቼ ያልሆነን መንገድ በመከተል አገራችሁን አትክዱ፣ ምንም እንኳ እምነት አልባ ብትሆኑም ዞሮ ዞሮ ኢትዮጵያ አምላክ አላትና አይጥላትም። አወዳደቃችሁ የከፋ እንዳይሆን ተጠንቀቁ። እኔ ቀደም ሲል ሰው በማይደፍራቸውና እንደ ሰይጣን በሚፈራቸው ጊዜ ነበር፡፡ ምክር መሳይ መልዕክት ለጓዳችው ለሥብሃት ነጋ የላኩለት። እንዲያው በአጭሩ እንዲህ በሚል መነሻ ነበር፡፡ መሪዎች እንድየ አመጣጣቸው እንድየ አስተዳደራቸውም ይገመገማሉ፣ ይፈረጃሉም፣ የሕዝብን ሮሮ አድምጡ፣ የራስን ብቻ ጥቅም አትከተሉ፣ ብዬ በ06/07/2007 የጻፍኩለትን ከጓዳችሁ ከሥብሃት ዘንድ ማየት ይቻላል። መቼም ይጥለዋል ብዬ አልገትምና።

ታላላቅ መንግሥታት ሕዝባቸውን ያዳምጣሉ፣ ያለያም ጊዜያቸው ሲደርስ ይተካሉ፡፡ እናንተ ግን ይህንን መመልከት አቅቷችኋልና አስቡበት ብዬ ከጻፍኩ በኋላ ደብዳቤውን ከማንበቡ በፊት ሒልተን ሆቴል ምሣ ጋብዞኝ በሚቀጠልው ቀን ስልክ ብደውል ከዚያን ጊዜ በኋላ ስልኩ ተዘጋብኝ። መዘግጋቱ መልካም ነው። ሁልጌዜ ከእኛ በላይ ላሣር ባዮች ሲዋረዱ እንጂ ተከብረው ሲዘልቁ አልታዩምና ይታሰብበት። ሕወሓት እንደማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ እንጂ ትግራይ ማለት አይደለምና በሰፊው ሕዝብ መገናኛ ሕዝቡን ለማወናበድ መቀባዠሩ ስለማያዋጣ ትክክለኛውን የፖለቲካ መስመር ይዞ መሄዱ ነው የሚበጀው።                                                                             

ታላቁን የትግራይ ኢትዮጵያዊነት ማንም ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ የሚኖር አይመስለኝም፣ ሊያስገባም አይችልም። የትግራይም ሕዝብ በዚህ የሚጠራጠር አይሆንም፡፡ የግንቦት 27 ፓርቲ ወይም የአማራ ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎች  እንጂ፣ ማንንም ከፓርቲው ውጪ የኔ ነው ብሎ አያስገድድም፡፡ ታዲያ ሕወሓት የትግራይን ሕዝብ የግሉ ያደረገው በትኛው ሕግ ነው? ወይ አለማወቅ! ትግራይ የሦስት ሺሕ ዘመናት ታሪክን የተጎናጸፈችና የታደለች አገር ስትሆን፣ ሕወሓት ግን ደርግ አስፀንሶ ያዋለዳት እንዲያው አብዝቼ ላጎናጽፋትና የ40 ዓመታት ጨቅላ የፖለቲካ ድርጅት መሆኗን ብትገነዘቡ የተሻለ ይሆናልና ብዙም የማይታወቅ መስሏችሁ አትዘባነኑ። እነ አቶ ደብረ ጺዮን ያስቡበት፣ ሁልጊዜ አፈሙዝ አያዋጣምና ይህንንም ከደርግ፣ ከጋዳፊ፣ ከሣዳም ኡሴንና ከሌሎች አምባ ገነን መሪዎች መማር ቀላል ይመስለኛል።                                                                                          

ሌሎች የዓረብ ፍርፋሪ ይደርሰናል ብለው የአገራቸውን ሚስጢር በማውጣትም ሆነ በሰርጎ ገብነት አገራችንን ለግብፅ ወገን በመሆን የሚራወጡት በመጨረሻ የሐዘን ማቅ ለብሰው የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ሆኖባቸው ከሁለት የወደቁ እንዳይሆኑ ቢያስቡበት እጅግ የተሻለ ይሆንላቸዋልና ረጋ ብለው እንዲያስቡበትና ወደየልቦናቸው እንዲመለሱ፤ ጊዜያዊ በድብቅብቆሽ የሚገባው ዶላር መጨረሻው ውርደትና አገር የለሽ እንዳያደርጋቸው ያስቡበት፣ ኢትዮጵያ እንኳንስ ይህንን ብዙውን አልፋለችና አይሞኙ።

ወደየልቦናቸው ተመልሰው ይቅርታን ጠይቀው ንሰሃ ይግቡ። ለኢትዮጵያ የተኙ ኃያላን አልነበሩም፡፡ ከጄኔራል ናፕይር ጀምሮ፣ የእንግሊዞችን የግፍ ምክርና የእነ ቱርኮችን፣ ግብፅን፣ ጣሊያንን አሁንም በዲጋሚ እንግሊዝንና ፈርንሳይን ጨምሮ የተደረገውን ደባ መመልከት ይቻላል፤ ያዳክሟታል እንጂ አያጠፏትም፡፡ እነኚህ ሁሉ የውጪ ኃይል ሲሆኑ ያሁኖቹ ከብብቷ ተነስተው ሊያጠቋት የተዘጋጁ አንጡራ ልጆቿ መሆናቸው ቢያሳዝንም የትም እንደማይደርሱ ተገንዝበው ወደ ልቦናቸው ቢመለሱ ይበጃቸዋል፡፡ ኢትዮጵያን እንደሆነ ፈጣሪዋ ይጠብቃታልና ለደቂቃ እንኳ አያስቡ። ቸሩ ፈጣሪ ከእርሷ ጋር ነውና።

ሰዎች አገራቸውን በቴክኖሎጂ፣ በኢንዱስትሪ፣ በእርሻና በእንሰሳት ሀብት አልምተው ከአገር ተርፈው ለሌላ እጃቸውን ሲዘረጉ፣ እኛ ሁሉ የሞላን፣ ውሀችን ለእነኝሁ ጉደኞች አጥፊዎቻችን ዳገቱን ወጥቶ ቁልቁለቱ ተወርውሮ አብልቶ፣ አጠጥቶና ሀብት በሀብት ሲያደርጋቸው፣ እኛ የበይ ተመልክካች መሆንን የምንመርጥበት ምክንያት እንዴት ቢታያችሁ ነው በዕለት ጉርሻ ተደልላችሁ አገራችሁን ለመሸጥ የምትራወጡት? ኧረ ልብ ግዙ፣ አናት አጥሸጥም፣ አትለወጥም፣ ነውር ነው! ገዢውም ለጊዜው የተደሰተ ይምሰል እንጂ ይታዘባችኋል። የወገንን ደም በከንቱ ለማፍሰስ የሚዳዳችሁም ያቺ ሞት ለማንም አትቀርምና የዘለዓለም ነዋሪዎች ያለመሆናችሁንም ተገንዘቡት። ሰዎች ለመሻሻል ይሽቀዳደማሉ እንጂ እንዴት ለጥፋት ትሽቀዳደማላችሁ? ለሟ አገራችን፣ መሬቱ ተንጣሎ ተኝቶ፣ ወራጅ ወንዞቻችን ተሽቆላሎ እየወረዱና ወጣቱ ኢትዮጵያዊ ምን ልሥራ እያለ የሥራ ያለህ ሲል፣ ወጣት ሴት ሕፃን አዝላ በየመንገዱ ለልጄ ወተት ሳይሆን ዳቦ መግዢያ የዕለት ጉርስ ስትለምን፣ ያንን ለሟሟላት ተባብረንና አብረን ከመነሳሳትና ሕዝባችንን ከረሀብ፣ ከቸነፈር አላቅቀን በሠራነው ሥራ ምረጡን፣ ለመመረጥ ይህንን ሠርተናል፣ የበለጠም ለመሥራት ዝግጁ ነን ብለን መወዳደር ሲገባን፣ ምነው ለቅሚያና ለዘረፋ ተሽቀዳደምን? ኧረ ልቦና ይስጠን!!

ወገኖቼ ማንም ሰው ያጠፋል ግን መታረም ደግሞ የበለጠውኑ ያስመሰግናልና አንዴ ከአጠፋን ጠፍተን እንቅር ከማለት ይልቅ፣ ከጥፋት መማርም ይቻላልና ወደ ልቦናችሁ ተመልሳችሁ ከኅብረተሰቡ መቀላቀልና ይቅርታን መጠየቅ የታላላቅ ሰዎች ሥራ ሊሆን ስለሚችል አትፈሩ ተመለሱ! ላጠፋችሁም ብትቀጡም፣ አባት ልጁን ይቀጣ የል? ቅጣት የመጨረሻ ጥፋት ማለት ሳይሆን ከስህተት መመለሽያና ከኅብረትሰብ ጋር የመቀላቀያ ዜይቤያችን፣ የነበር የመላው ኢትዮጵያዊ ባህል ነውና ቅጣታችሁን ተቀብላችሁ ልቦና ገዝታችሁ ከእኔ በላይ ላሣር ማለትን ትታችሁ ወደ ኅብረተሰቡ ተቀላቅላችሁ ያመለጣችሁን አገልግሎት አበርክቱ። ልቦና እንዲሰጣችሁ አምላኬን በፀሎት እማጠናለሁ። ስለ ግብፆች ብዙም አታስቡ፣ መሪዎቻችንም በርትተው ወደፊት ታሪክ እንዳይወቅሳቸው አንዲት ጠብታ ውኃ እንኳ ያላግባብ እንዳናፈስ ይታወቅ፣ ለመሆኑ የዛሬ ታዛቢ ትራምፕ አሜሪካ የሁበርን ግድብ ስትገድብ የታችኞቹን አገሮች አማክራ ነበርን? ወይስ በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት ነው? ይህም ይታይልን።ለሁላችንም ልቦና ይስጠን! አሜን!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ግለ ሕይወታቸውንና የጉዞ ታሪካቸውን የከተቡበት ‹‹ከባቹማ እስከ ቨርጂኒያ›› በሚል ርዕስ ለአንባብያን ያቀረቡት መጽሐፍ ደራሲ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...