Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርያሳስባል እንጂ ምነው አያሳስብ?

ያሳስባል እንጂ ምነው አያሳስብ?

ቀን:

በመርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ

እውነቱን ለመናገር ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንን በአሁኑ ወቅት ብዙ፣ በጣም ብዙ የሚወዘውዟቸውና አብዝተው የሚያስጨንቋቸው አገራዊ ጉዳዮች እንዳሉ ጨርሶ ሊስተባበል አይችልም፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፍፃሜና የውኃው ሙሊት፣ ይህንኑ ተከትሎ የተደቀነባቸው የውጭ ኃይሎች ተፅዕኖና የውስጥ መሰሪ ባንዳዎቻቸው የሽብር እንቅስቃሴ፣ መያዣ መጨበጫው የጠፋበት የኦሮሞ ጽንፈኞች ፖለቲካ፣ ድኅረ ሲዳማ ሪፈረንደም ትኩሳቱና እየናረ የመጣው የደቡብ ክልል አደረጃጀት፣ የብሔር ፖለቲካው ጡዘት፣ እዚህም እዚያም እያደረሰ ያለው የሕዝብ ለሕዝብ ግጭትና ከኖረበት ቀዬ መፈናቀልና ለተለያዩ ሰብዓዊ ችግሮች መጋለጥ፣ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት እያሽቆለቆለ የመጣው ኢኮኖሚና እርሱ በተራው የፈጠረው ማኅበራዊ ምስቅልቅል፣ የአገሪቱ ሁለንተናዊ መዳከምና በተለይም ወደብ አልባነቷን በመንተራስ ሰላምና ደኅንነቷን ለመፈታተን ከሁሉም ማዕዘናት በቀጥታም ሆነ በእጅ አዙር የሚቀነባበረው ሴራና የሚካሄደው ዘመቻ. . . ከብዙዎቹ ማሳያዎች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው፡፡

በእርግጥ ከእነዚህና ከመሳሰሉት አንገብጋቢ አጀንዳዎች ጋር ሲነፃፀር ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በትግራይ ክፍለ ግዛት በተናጠል አካሂደዋለሁ የሚለውና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው ከሠፈር ዕድርተኞች ወይም ዕቁብተኞች አወካከል ጋር የሚያወዳድሩት ምርጫ መሳይ ሽርጉድ ያን ያህል አያስጨንቃቸውም፡፡ ይህንኑ ሀቅ ሰሞኑን ለሰበሰቧቸው ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ሳይቀር በአደባባይ ሲነግሯቸው ሰምተናል፡፡

ሆኖም በራያ፣ በጠለምትና በወልቃይት ጠገዴ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎቻችን ይህንን የምንተዳዬ አነጋገር ሲሰሙ ምን እንደሚሏቸው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትንሽ አስበውበት ይሆን? ሕወሓት ራሱ የተወከለበት የአገሪቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን ተርጉሞ ስድስተኛው ዙር ምርጫ እንዲራዘም ቀደም ሲል ካሳለፈው ውሳኔ ባፈነገጠ አኳኋን፣ በቆረጣ እየተዘጋጀ ነው በሚባልለት በዚህ የሆያ ሆዬ ምርጫ ወጥቶ እንዲሳተፍ በመቀስቀስ ላይ የሚገኘው ሰፊው የትግራይ ሕዝብስ ቢሆን አባባላቸውን በቀላሉ ይቀበለው ይሆን? ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕወሓት ሕገ መንግሥቱን በጠራራ ፀሐይ ረግጦና በኃይል ደፍጥጦ በአሁኑ ወቅት እያደረገ ያለውን የወሮበላ እንቅስቃሴ ከመጤፍ የቆጠሩት አይመስልም፡፡

እንደ እሳቸው ሥር የለሽ ትንታኔ ከሆነ ረብ የለሹ የትግራይ ምርጫ በመሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ስለማይለውጠው ‹‹ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት በከንቱ ከማባከን የዘለለ ሊሆን አይችልም፡፡ የክልሉ መንግሥት ሥልጣን አካላት ዕድሜ እንደሆነ እንደፌዴራሉ መንግሥት አቻዎቻቸው ሁሉ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስቀድሞ ባሳለፈው ውሳኔ እኩል ተራዝሟልና ሕወሓት በዚህኛው ምርጫ ተመልሶ ቢያሸንፍ እንኳ የተለየ ትርፍ አያገኝም፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹ችግር የሚሆነው ሌላ ተቃዋሚ ድርጅት በክልሉ ተወዳድሮ የፖለቲካ ሥልጣኑን የጨበጠ እንደሆነ ብቻ ነው፤›› ሲሉ አዲስ ዕውቀት ሊያስጨብጡን ሞክረዋል፡፡

በዚህ ጉራማይሌ አነጋገራቸው ታዲያ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ አውቀውትም ይሁን ሳያውቁት አስቀድመው ያጣጣሉትን ምርጫ ሕጋዊነት በይፋ መቀበላቸውንና ለተፈጻሚነቱ በፅናት መቆማቸውን የዘነጉት መስለው ታይተዋል፡፡ በመሠረቱ መወገዝ ያለበት ውጤቱ ብቻ ሳይሆን ሒደቱም ጭምር እንደሆነ ተገቢው ግንዛቤ እንዲወሰድበት ያስፈልጋል፡፡ ፈረንጆቹ እንደሚሉት ‹‹የመርዛማ ዛፍ ፍሬ መርዛማ›› በመሆኑ አንኳሩ ነጥብ በምርጫው ማን ያሸንፋል የሚለው ሳይሆን፣ ምርጫው ራሱ ሕገ መንግሥታዊ ድጋፍ አለውን? የሚለው እንደሆነ ከወዲሁ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ተለዋጩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አቋም

እንደ ኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ስምንትና አንቀጽ 61 ድንጋጌዎች የተጣመረ ንባብ ከሆነ፣ የሕገ መንግሥቱ ባለአደራ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ስብስብ የሆነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ እንደ አንድ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ተቆጥሮ ይህንኑ የበላይ ሕግ የሚተረጉመው የመጨረሻ የሥልጣን አካልም እሱ እንደሆነ በአንቀጽ 62 ንዑስ አንቀጽ ዘጠኝ (1) ድንጋጌ ሥር በጉልህ ተጠቅሷል፡፡

ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ይመስላል፣ ዕመት ኬሪያ ኢብራሂም እርሳቸው ደጋግመው እንደሚለፍፉት በራሳቸው ውሳኔ ይሁን በድርጅታቸው አስገዳጅ ትዕዛዝ ወደ መቀሌ ኮብልለው አስደማሚ የክህደት መግለጫ በሰጡ ማግሥት፣ አዲስ የተመረጡትና ቃለ መሃላ ፈጽመው ሥራ የጀመሩት የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ የትግራይ ክልል ሕገ መንግሥቱን በመጣስ የጀመረውን የተናጠል እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲያቆምና ወደ ጤናው እንዲመለስ ሰሞኑን ይፋዊ ማስጠንቀቂያ እንደ ጻፉለት ሰምተናል፣ አንብበናልም፡፡

ይህ ጸሐፊ ግብዞቹ የሕወሓት መሪዎች ለዚህ ማስጠንቀቂያ አዎንታዊ ምላሽ ይሰጣሉ ብሎ ቅንጣት ያህል ባያምንም፣ አፈ ጉባዔ አደም ፋራህ በልበ ሙሉነት የተነሱበትን መንደርደሪያ ሕገ መንግሥታዊነት ያጠይቃል፣ ያደንቃልም፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 62 ንዑስ አንቀጽ (ዘጠኝ) ድንጋጌ ሥር ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሰጣቸው ዓበይት ሥልጣንና ተግባራት መካከል፣ ‹‹የትኛውም ክልል በራሱ ጊዜ ሕገ መንግሥቱን በአመፅ ወይም በፍፁም ደንታ ቢስነት ጥሶ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ በሚጥልበት ጊዜ የፌዴራሉ መንግሥት አስፈጻሚ አካል ጣልቃ ገብቶ ኃይል በመጠቀም ጭምር የተባለውን ጥሰት እንዲያስቆም›› የሚያዘው ይገኝበታል፡፡

የላይኛው ምክር ቤት በሕገ መንግሥት ደረጃ የተጎናፀፈው ይህ ወፍራም ሥልጣን ዘግይቶ በአዋጅ ቁጥር 359/1995 ዓ.ም. አማካይነት ይበልጥ ተጠናክሮ የተደነገገ ሲሆን፣ ዝርዝር አሠራርም ተበጅቶለታል፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት በክልሎች ጣልቃ እንዲገባ ሲታዘዝ ሊፈጽም የሚገባውን ሥነ ሥርዓት ለመወሰን በወጣውና ቅርጫት ላይ ተጥሎ በከራረመው በዚህ አዋጅ አንቀጽ 13 ንዑስ አንቀጽ (አንድ) ድንጋጌ መሠረት፣ ‹‹የትኛውም ክልል ሕገ መንግሥቱን በመጣስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ ስለመሆኑ በራሱ አነሳሽነት ሲያውቅም ሆነ፣ ከሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ወይም ከሌላ ከማናቸውም መንግሥታዊ አካል በኩል መረጃ ሲደርሰው ተፈላጊውን ቅድመ ምርመራ ካካሄደ በኋላ የተባለው አደጋ መኖር/አለመኖሩን ለመወሰን እንዲያመቸው፣ ጉዳዩን በዝርዝር አጣርቶ ውጤቱን ያቀርብለት ዘንድ ለአገሪቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም አግባብ ላለው ለሌላ የመንግሥት አካል›› መመርያ ሊሰጥ ይችላል፡፡

‹‹የደረሰውን ሪፖርት ወዲያውኑ ተቀብሎ ከመረመረ በኋላም ከሚያገኘው መረጃ በመነሳት አስፈላጊ ሆኖ ያገኘው እንደሆነ ምርመራው እንዲካሄድ በተወሰነበት ክልል ውስጥ የፌዴራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባና የእርምት ዕርምጃዎችን እንዲወስድ ያደርግ ዘንድ›› ከፍ ብሎ የተጠቀሰው አንቀጽ 13 ንዑስ አንቀጽ (አራት) ድንጋጌ ለዚሁ ምክር ቤት በማያሻማ ኃይለ ቃል ሥልጣን ይሰጠዋል፡፡ የአዋጁ አንቀጽ 14 ንዑስ አንቀጽ (ሁለት) ፊደል ተራ ቁጥሮች ሀና ለ ድንጋጌዎች ደግሞ በክልሎች ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚታዘዘው አስፈጻሚ የመንግሥት አካል የሚወስዳቸውን ዕርምጃዎች ምንነት የሚያብራሩ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ በዚህም መሠረት ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሁኔታውን አሳሳቢነት ተመልክቶ የተደቀነውን አደጋ ሊቀለብስ ወይም በቁጥጥር ሥር ሊያውል የሚችል የፌዴራል ፖሊስ ኃይል ወይም የአገር መከላከያ ሠራዊት (ካስፈለገም ሁለቱን) በክልሉ ውስጥ በጊዜያዊነት ሊያሠማራ›› ይችላል፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ጥሰቱ ቀጥሎ የአመፁ ደረጃ የሚስፋፋ መስሎ ከታየማየዚያ ክልል ሕግ አውጪ ምክር ቤትም ሆነ ከፍተኛው አስፈጻሚና አስተዳደራዊ አካል ሳይቀሩ ከሥራ እንዲታገዱና ለፌዴራሉ መንግሥት በቀጥታ ተጠሪ የሆነ ጊዜያዊ አስተዳደር እስከ ማቋቋም›› የሚደርስ መሬት አንቀጥቅጥ ውሳኔ ሊሰጥ እንደሚችልም ከወዲሁ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጧል?

መቼም ጠቅላይ ሚኒስትራችን የብዝኃ ልሳን ጌታ መሆናቸው በእጅጉ ደስ ያሰኛል፡፡ ሰሞኑን ሌላው በሕዝብ ዘንድ ዓብይ መከራከሪያ ሆኖ የሰነበተው ታዲያ ይህንኑ ማለፊያ ተሰጥአ አልቀው በመጠቀም ከፋና ቴሌቪዥን ጋር በትግርኛ ቋንቋ ያደረጉት ቃለ ምልልስ ነው፡፡ ያንኑ ቃለ ምልልስ መነሻ አድርገው፣ ‹‹ሰፊው የትግራይ ሕዝብ በዚህ ቀውጢ ወቅት ከዶ/ር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል ጎን እንዲቆምና እርሳቸውን በተናጠል እንዲደግፍ›› ሲሉ ያስተላለፉት የተማፅዕኖ ጥሪ፣ በተለይ እየተመዘዘ በሰፊው ሲያጨቃጭቅ ቆይቷል፡፡

አንዳንድ ወገኖች ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ ዋዛ የወረወሩትን ያንን አባባል ሕወሓትን ለመከፋፈል እንደ ተቀየሰ አዲስ ብልኃት ቆጥረውታል፡፡ ሌሎች ደግሞ ‘ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጡ’ በማለት አቃለው እንደ ተመለከቱባቸው ታዝበናል፡፡ እንደ አንድ የአገር መሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለዶ/ር ደብረ ፅዮን ወቅታዊ አቋም ያላቸው መረጃ ከሁላችንም የተሻለ እንደሚሆን በማመን፣ እኔ በበኩሌ ከሁለቱም ተቃራኒ ጎራዎች የሚሰነዘሩትን እነዚህን ሽሙጦች ከመጋራት መቆጠቡን መርጫለሁ፡፡ በእርግጥ ይህ ያልተጠበቀ ጥሪ ከሁሉም በላይ የፈንቅል አስተባባሪዎችን ክፉኛ እንዳስቀየመባቸው ሰምቻለሁ፡፡

የትናንት አንጋቾች ለከት የለሽ እንጉርጉሮ

ሕወሓት ራሱን በራሱ ያቀለለና ከማዕከላዊው መንበረ ሥልጣን እስከ ወዲያኛው የተገለለ ቡድን ነው፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ክርስቶስ ዳግም ከክብርና ሞገሥ ጋር ይመለሳል ብለው ዛሬም ቢሆን በተስፋ የሚጠብቁት የመሀል አገር ቅሪቶቹ በቁጥር ቀላል አይደሉም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ‘ጅብ ከሄደ የሚያለቃቅስ ውሻ’ ይመስል እነሆ ጨለማው ተገፎ በብርሃን ሲተካ በሐሰት ባላንጣዎቹ መስለው ለመታየት እርስ በርስ የሚሽቀዳደሙት የቀድሞ ባልንጀሮቹ፣ ነባር የኦሕዴድና የደኢሕዴን አባላት ወደ መንግሥትና መንግሥት አደር ወደሆኑ ፓርቲ መራሽ መገናኛ ብዙኃን ተቋማት ብቅ እያሉ፣ ‹‹ድሮም ቢሆን አዛዥና አዛዣችን እርሱ ነበር››፣ “እኛ እኮ ከምኑም የለንበት”፣ በማለት ዓይናቸውን በጨው አጥበው የሚያሰሙን ለከት የለሽ ኑዛዜ ፍፁም አታካች ሆኖብናል፡፡ ይህ ዓይነቱ የ’እኔ የለሁበትም’ የተኩላ ጩኸታቸው በተሸናፊነት ሥነ ልቦና ታጅቦ በብሔራዊው ቴሌቪዥን አማካይነት እየተቀነባበረ በየምሽቱ ዓብይ ዜና ሆኖ ሲቀርብልን፣ እንደተለመደው ሕወሓትን ረግመን እነርሱን ብቻ እንድንመርቅ ታስቦ የሚሰናዳ ይመስላል፡፡ እንዲህ ያለው የአላጋጮች ሙሾ በፍፁም መቆም ይኖርበታል፡፡

የፌዴራሉ መንግሥትም ቢሆን በሕወሓት ላይ ሊወስድ ያቀደው ዕርምጃ ካለ ‘ሙያ በልብ ነው’ ብሎ ያለ ማወላወል መውሰድ እንጂ፣ የዛሬዎቹ የእርሱ አባላት ትናንትና ከትናንት ወዲያ የታሪኩ ክፍልና አካል ያልነበሩ ይመስል፣ ሕወሓት/ኢሕአዴግ በዘመነ አገዛዙ ዴሞክራሲያዊና የእውነተኛ ፌዴራላዊ ሥርዓት ጠበቃ እንዳልነበር አሁን ገና ገባኝ እያለ በየመድረኩ ልባችንን ሲበዛ ባያቆስለው መልካም ነው፡፡

አበቃሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በሕግ ሙያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በ1981 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው የሕግ ፋኩልቲ ያገኙ ሲሆን፣ በሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተመድ የሰላም ዩኒቨርሲቲ ጣምራ ትብብር ይካሄድ ከነበረው የአፍሪካ ፕሮግራም በሰላምና በደኅንነት ጥናት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ ዋና የሕግ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...