ትዕግሥት በተፈታተነ የረዥም ሰዓት ጥበቃ አንዲት ሚኒ ባስ ታክሲ መጣች። እነሆ ከካዛንቺስ ፒያሳ ልንጓዝ መሆኑ ነው። ዛሬም እንደ ትናንቱ፣ እንደ ሳምንቱ፣ እንደ አምናው ለመጓዝ. . . የሕይወት ዋናው ቀመር በእንቅስቃሴ የተነደፈ መሆኑን ማንም ሳያስረዳን የተረዳነው የኑሮ ፊዚክስ ነው። ‹በእንቅስቃሴ ውስጥ ትግል፣ በትግል ውስጥ ለውጥ› በሚል ርዕስ መጽሐፍ ሳይጻፉ በፊት፣ ይህንን እውነት የሁሉም ሰው ነፍስ የደረሰበት ይመስላል። እናም ያላስገዳጅ እየተጓዘች፣ እየሮጠች፣ እየታገለች ነፍሳችን በሥጋ አድራ ትኖረዋለች። ኑሮ የዕለት ጉርስን ለማግኘት በመላወስ ውስጥ አቻና ተቀናቃኝ ዓላማ ሳይኖረው ዘልቋል። ነገር ግን ዘመኑ ከፍቶ በአቋራጭ ያላሰብነው ጠላት ተነስቶብናል፡፡ ይህ ጠላት ረቂቅና ሥውር ነው፡፡ ቀን አይል ጨለማ የትም ሥፍራ የመገኘት ብቃቱ ከባድ ነው፡፡ እኛም ጥንቃቄ በሚባለው መርህ ጉዞ ጀምረናል!
የሰው ልጅ ከእምነቱ፣ ከፍልስፍናው፣ ከፍላጎቱና ከምኞቱ ለአፍታ ገለል ሲል የሚፈተነው በእንዲህ ያለ ጊዜ ነው። ጊዜ ደግሞ ዋናው የለውጥ መካኒክ ነውና። ታክሲዋ በሚተራመሰውና በሚጋፋው ሰው እየተወዛወዘች የቻለችውን ያህል አስገብታን ስታበቃ ሞላች። ‹‹ጎበዝ! ጥንቃቄ እንድናደርግ እየተነገረን እኛ እዚህ እንደ ከብት እንተፋፈጋለን፡፡ ይኼ ቫይረስ ቻይና፣ ጣሊያን፣ ስፔን፣ ኢራን፣ አሜሪካ. . . ስንቶችን ወደ ሞት እንደሸኘ አልገባንም ማለት ነው. . .›› እያለ አጠገቡ ያብራራ ጀመር። በውስጡ ሌላ ስምና ቅጥያ እንደፈራ ንግግሩ ይመሰክራል። ወያላው ገብቶ በሩን እየዘጋ “ሳበው!” ይለዋል ሾፌሩን። ሁላችንም ሳይታወቀን ከቦታ ቦታ እንጎተታለን እንጂ፣ አደጋው የገባን አንመስልም!
ከጎልማሳው ፊት የተቀመጠው ወጣት፣ ‹‹አይዞህ ገብቶናል። ምን ይህን ያህል አጨናነቀህ?›› ሲለው፣ ‹‹ወዳጄ ዕውቀት ሳይሆን መላምት እንደ እውነት በሚታመንበት አገር እንዲያ ብዬ መናገር እንዴት አያደናብረኝ?›› አለው ቀስ ብሎ አሁንም ሌሎች እንዳይሰሙት። ‹‹አገራችን እኮ የዴሞክራሲ ባህል እንደ ልቡ የሚንሸራሸርበትን መስመር እየዘረጋች ነው፤›› ሲለው ወጣቱ ጎልማሳው ሳቅ እያለ ‹‹እ? . . . ምነው ግድቡን ረሳኸው?›› አለው። ተግባቡና ተሳሳቁ። ከሳቃቸው ኋላ የምሬት ወዮታ ስንሰማ ጆራችን እዚያ ተሰደደ። ‹‹በሞቀበት መሰደድ ግን በደም ነው እንዴ የወረስነው?›› ስትለኝ አጠገቤ የተቀመጠችው ልጅ ቁንጅናዋን አስተዋልኩ። ‹‹ቆንጆ አለማየት ከብዶን፣ ኑሮ ከብዶን፣ ኮሮና እያስፈራራን እንዴት ይሆን የምንዘልቀው?›› ይላል ሌላው እያንሾካሾከ። ‹‹ከሚያንሾካሽክ አይጠነቀቅም?›› ይለኛል በጥድፊያ ተሳፍሮ በታክሲዋ መጨናነቅ እየተበሳጨ ያለው አጠገቤ የተሳፈረ ጎልማሳ፡፡ መጥኔ ዘንድሮ!
‹‹ውይ! ውይ! ውይ! ኧረ ምን አባታችን ይሻለን ይሆን?›› ወደሚለው አውቆ አበድ መሳይ ወጣት እንደ ዞርን ነን። ለራሱ በፈጠረው ነፃነት ውስጥ ሌላ የሚያይም የሚሰማም አይመስልም። “ምነው?” አሉት ‹አንዳንድ› አጠገቡ የተቀመጡ ተሳፋሪዎች። ‹‹ታክሲ ነዋ። እዚህ ቆሜ ስጠብቅ ሰዓቱ አልፎብኛል። ብደርስም አልገባም እኮ፤›› አለ ጨንቆትና ከፍቶት። ‹‹የት ነው የማትገባው?›› አሉት አንድ አዛውንት በመገረም። ‹‹እዚያው ሥራ ነዋ። ከተጀመረ በቃ አያስገቡም፤›› ብሎ ሳይጨርስ፣ ‹‹አይዞህ ማርፈድ ራሱ አንዱ የኑሮ አካል ነው። ጎበዝ! ስም ጠሪ የለብንም እንጂ ለአንዳንዶቻችን እኮ ውሏችን ኑሮአችን ፈተና ሆኗል፤›› ብለው አዛውንቱ ፈገግ አሰኙን። ‘ተጨዋች ሽማግሌ አንቱ ሳይባል ያረጃል’ ማለት እሳቸው ይመስሉ ነበር፡፡ ነገር ግን በዚህ ዘመን መባል ያለበት ‹‹መካሪ አያሳጣ›› ስለሆነ ዕድሜ ይስጥልን ብንልስ!
ወያላው ሒሳቡን እየተቀበለ፣ “ሳንቲም ካላችሁ ተባበሩኝ!” ሲል ያስተጋባል። ሾፌሩ ‹‹ትርፍ ጭነሃል እንዴ?›› ብሎ ድንገት በርግጎ ጠየቀው። ‹‹አዎ! ሁለት ሰው አለኝ ምነው?›› ከማለቱ ሾፌሩ በብስጭት፣ ‹‹ስንቴ ትርፍ አትጫን ብዬ ላስጠንቅቅህ ግን? ያው ሁለት ናቸው፤›› ብሎ ትራፊኮቹን እየጠቆመ የታክሲዋን ፍጥነት አቀዘቀዘ። ወያላው በበኩሉ፣ ‹‹አንተ ደግሞ ሀቀኝነት ማንን ሲያነሳውና ሲያከብረው አይተህ ነው ትርፍ አልጭንም የምትለው? እየተበላንም ቢሆን መሥራት አለብን ፍሬንድ፤›› ብሎ ያደፋፍረው ጀመር። ትራፊኮቹ አፍ ለአፍ ገጥመው እያወሩ ሳያዩን አለፍናቸው እንጂ፣ እንዳያያዛችን ግን ኮሮና ካገኘን የሚምረን አይመስልም። ‹‹አቤት ሥራና ወሬ! በዚህ ዓይነት ስንቱ አገር አጥፊ ይሆን ተዝናንቶ የሚኖረው? ኧረ አቋራጩና ተቆራራጩ በዛ?›› አለች መጨረሻ የተቀመጠች ወጣት። ‹‹ምናልባት ይኼ መከረኛ ኮምፒዩተር ከ’ዴስክቶፕ’ በ’ሾርትከት’ ‘ፕሮግራም’ እየከፈተ ማቋረጥን ክፉኛ አለማምዶን ይሆን?›› ብሎ ፈገግ አለ አንዱ። እውነቱን እኮ ነው፣ ሰው ከአየውና ከሰማው ውጪ መች ይኖርና፡፡ ኑሮ ከተባለ ማለት ነው!
“አበስኩ ገበርኩ!” ይላሉ መጨረሻ ወንበር የተቀመጡ አዛውንት። ግርማ ሞገሳቸው ልዩ ነው። ፀገሩራቸው ሪዛቸውን ጨምሮ ቡፍ ብሎ ቆሟል። ‹‹ምነው አባት? ምን ሆኑ?›› አጠገባቸው የተቀመጠች አጭር ቀይ ኮረዳ ታጫውታቸዋለች። ‹‹ይኼ ኮሮና የሚሉት እየጨነቀኝ ነው!›› ሲሉ መለሱላት በእርጋታ። ‹‹አይዞዎት ማን የሚሆነውን ያውቃል ብለው ነው?›› ለማወጣጣት ነው ነገሩ። ‹‹ለዚህ እኮ ነው ልጄ ነጋ ጠባ አሟሟቴን አሳምረው የምለው። እሱስ ሳይሰለቸው ቀረ ብለሽ ነው?›› ፍስስ ይላሉ ደርሰው በተመስጦ። ‹‹ምነው ካልጠፋ ነገር አሟሟትዎ ያስጨንቀዎታል? ልጆች የሉዎትም? ባለቤትዎስ?›› የምትለቃቸው አትመስልም ወጣቷ። ጥያቄ እንጂ መልስ ጠፍቶ ነው ግራ የገባን!
‹‹ኧረ ሁሉም አሉ። የሁሉም አጠገቤ መኖር ነው አንድም የሚያሳስበኝ። በዚያ ላይ አንዳንዱ በአሟሟቱ ይበደልና በአቀባበሩ ይካሳል። ለምሳሌ ይኼው እንደምትሰሚው በዚህ እርኩስ ነገር በመላው ዓለም እየሞቱ ያሉ ሰዎች ድንገት አፈር ቢለብሱም፣ ይኼው ዓለም በየሰዓቱ በየደቂቃው እያሰባቸው ይውላል። ዓለም ይኼው በቫይረሱ ምክንያት አገር የለ ብሔር፣ ሀብት የለ ድህነት አንድ ሲሆን እያየ ነው። ይኼ ቫይረስ ይዞት የመጣው ነገር አዲስ ነው ልጄ። አየሽ ብዙ ብዙ አለ የሚያሳስበኝ፡፡ ወዲያ ደግሞ በረሃብና በቦምብ ተገደልሽ፣ ታመሽ ሞትሽ፣ የሮኬት ፍንጣሪ አግኝቶሽ ዓይንሽን አጠፋው ከአበቃልሽ አበቃልሽ ነው። በበኩሌ ታዲያ በሕይወት ስኖር ለመኖሬ ዕውቅና ባይሰጠኝም ስሞት ቀባሪ ካላሳጣኝ አሟሟቴ ‘ክላሲ’ ባይሆንም እንኳ፣ አስታዋሾቼ ‘ክላሲ’ በሆነ መንገድ ካሰቡኝ ምን እፈልጋለሁ?›› ብለው ፈገግ አሉ። ወይ ሰው! መፈለግም አለመፈለግም በማይችልበት ሁናቴ ውስጥ የሚገኝበት ቀን እንደሚመጣ እያሰበም፣ የሚፈልገውንና የማይፈልገውን ሲመርጥ ይኖራል? ‹‹ታዲያ ከሞት በኋላም ምርጫ አማረህ?›› ሲል የሰማነው ወያላ ስንት ቢያጆ ሸቅሎ ይሆን ከነጋ? የት እንደሚበላው እንጃ እንጂ እሱም ለሳንቲም ሲል ሕይወቱን የረሳ ይመስላል፡፡ እንዲያ በል ማለት አሁን ነው!
ጉዞ እየቆየ ነውና የሚያስተያየው አንድ እርጉዝ ተሳፋሪ በረዥሙ ስትተነፍስ አየናት፡፡ ብዙም ሳትቆይ፣ ‹‹እኔስ ምን አማረኝ መሰላችሁ?›› ብላ ዓይናችን አስፈጠጠችው። በዚህ የኑሮ ውድነት እርጉዝ እናቶች እንዳማራቸው ሳይበሉ እንደሚወልዱ ድንገት ብናስብ ዘመኑን ክፉኛ ረገምነው። “ምን የእኔ ልጅ?” አሉዋት አዛውንቱ በትዝታ ወደ ኋላ እያጠነጠኑ ያሉ መስለው። “ኮምፒዩተር . . .” ብላ ቀጣዩን ቃል ሳትናገር፣ ‹‹ጉድ ሆንን ሾፌር! የዘንድሮ እርግዝና ደግሞ ምነው ምግብና መጠጡን ትቶ ቴክኖሎጂ ላይ ሆነሳ? የእኔዋ ባለፈው ‘አይፎን’ አማረኝ ብላ ባለ በሌለ አቅሜ አስገዛችኝ፤›› ብሎ ወደ ጎልማሳነት ዕድሜ እየተጠጋ ያለ ወጣት አወራ። በሞት መሀል ሕይወት የሚዘራ እንዴት ደግ ነው እናንተ!
‹‹ኧረ እኔ አልጨረስኩም። እኔ ለማለት አስቤ የነበረው አገሬ ኮምፒዩተር፣ ስልክ፣ መኪና፣ ባቡርና ምንድነው ይኼ ኮሮና የሚባው ሰይጣን መድኃኒቱ የሚመረትባት ሆና ማየት አማረኝ ነበር፤›› ስትል ውጥረቱ ጋብ አለ። ‹‹ምናለበት የእኔዋም እንዳንቺ ወደ ኢንዱስትሪ አገርነት የመሸጋገራችን ዕቅዱ መሳካት ቢያምራት? ችግሩ ሁላችሁም ቢያምራችሁ ኮብልስቶኑ ተነጥፎ ሳያልቅ ምርምር የሚኖር አይመስለኝም፤›› አላት። ‹‹ውይ ሴቶች? ቆይ ግን እንዲህ ሁሉም ‘ብራንድ’ እየለበሱ፣ በብራንድ ሽቶ እየታጠቡ፣ ሽቅርቅር ብለው በከተማው የምናያቸው የኑሮ ውድነቱን በምን ቢቆጣጠሩት ነው?›› ብሎ ከኋላችን ካሉት ወጣት ተሳፋሪዎች አንደኛው አንደኛውን ቢጠይቀው፣ እንዳልሰማ ሆኖ ሌላ ወግ አስጀመረው። ‘ሰምተሃል!’ የሚሉት ደግሞ ፋሽን ሆነ ዘንድሮ፡፡ የማይረባ ወሬ እየደነጎሩ እኮ ነው!
‹‹ወይ ዘንድሮ! ለመሆኑ አሠሪዎቻችን፣ አሰማሪዎቻችን፣ ኢንቨስተሮቻችን በታክሲ ጥበቃ የምናጠፋውን ጊዜ እያሰቡ የአበልና የደመወዝ ጭማሪ ቢያደርጉልን ምናለበት?›› አለ የማይሰማ መስሎት አንድ ወጣት እየተንሾካሾከ። ‹‹ታክሲ የምንሠለፍበትንና የምንጠበቅበት ይታሰብልን ማለትህ ነው?›› ይለዋል ጓደኛው። ‹‹ታዲያስ! እንዲህ ተሰባብረን እንዳንሆን ሆነን እየፈጋን የማርፈድ ቅጣት ሰለቸን!›› እያለ ምሬቱን ከቀልድ ወደ ምር ሲያሸጋግረው፣ ‹‹እርፍ ይኼ ነበር የቀረን። መቼ ይሆን ሰበብ እየፈለግን ከዚህች ደሃ አገር ጉሮሮ ቀምተን ለመጉረስ ማሰብ የምናቆመው?›› ትላለች መሀል ወንበር የተቀመጠችው ቆንጆ። ‹‹አሄሄ አንቺ ጉርሻውን ትያለሽ የደላሽ። ምናለበት ግልምጫውና ሽኩቻው ባበቃ አትይም?›› አሉ አዛውንቱ። አሁንም ገላጋይ መጥቶ ሁሉም ጥጉን ይዞ ሕይወቱን ሊያድን አሸምቋል!
ሁሉም ከራሱ ሕመም እየተነሳ አስተያየቱን ሲዘነዝር ቆየና ድንገት፣ ‹‹ለመሆኑ አገራችን በየዓመቱ በስንት አኃዝ ነበር እያደገች ነው የተባለው?›› ብሎ ጎልማሳው ሲጠይቅ ‘በሁለት’ ብለው ሁለት ወጣቶች እኩል መለሱለት። ‹‹እሺ! እኛና ኑሯችን በስንት አኃዝ ነበር ቁልቁል የምንወርደው?›› ሲል ግን እንኳን የሚመልስ የሚተነፍስ ጠፋ። ‘ምርጥ ምርጡን ለእኛ አለ የደላው ባለጊዜ!’ የምትል ደፋር ጥቅስ ታክሲያችን ውስጥ ተለጥፋ ብናይ ያየነውን ማመን አቃተን። ቆይ የሚታመን እንዲህ ይጥፋ? እንዲህ እያውካካን ፒያሳ መድረሳችን ሳይታወቀን ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ሲለን ዱብ ዱብ እያልን ወረድን፡፡ ግን ነገር ግን ሁላችንም ፍርኃትን ልባችን ውስጥ ደብቀን በሰመመን ስንራመድ አንድ ድምፅ ከሩቅ ይሰማ ነበር፡፡ ‹ረቂቅ ጠላትን ለመዋጋት ዋነኛ ዘዴ ጥንቃቄ የተሞላበት ድፍረት ነው› የሚል፡፡ መልካም ጉዞ!